ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት – አኦትይፕ
ጥር 6 2010 ዓ ም
የህወሃት የቅርብና የሩቅ ዓላማ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበላይነትና በሰፊው በመቆጣጠር ለትግራይ ያደላ የካፒታሊስት ሥርዓት በመፍጠር እስከተቻለ ድረስ በበላይነት አብሮ ለመኖር ካልሆነም ኢትዮጵያን አደህይቶ፣ አዳክሞ ወይንም አድቅቆ ለመለየት ነው። ለዚህም ዓላማው ማስፈፀሚ አንደኛው ዋና መንገድ መንግስታዊ ካፒታሊዝም በትግራይ እና ክሮኒ ካፒታሊዝም ወይም ብልሹ ካፒታሊዝም በተቀረው በኢትዮጵያ መመስረት ነው። በትግራይ ክልል ላይ እየተገበረ ያለው የመንግስታዊ ካፒታሊዝም አካሄድ የቻይናን አካሄድ የሚመስል ሲሆን፤ ዓላማው አብዛኛው የክልሉን ሕዝብ የልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ ክልሉን የመሀከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የታለመ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ እየተገበረ ያለው የክሮኒ ወይም ብልሹ ካፒታሊዝም አካሄድ ዓላማው ለዘረፋና ለምዝበራ አመቺ የሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት በተቀረው ኢትዮጵያ በመዘርጋት የወያኔ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሕገ ወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበላይነት በመቆጣጠር የትግራይ ክልልን የልማት ጉዞ የሚያግዝ ካፒታል እንደ ድርጅትም፤ እንደ ቡድንም፣ እንደ ግለሰብም ማግበስበስ ነው። ይህ እንግዲ ወያኔዎች የሚያመልኩት የመለስ ዜናዊ እኩይ አእምሮ የነደፈው የዘረፋ ራዕይና ዕቅድ ነው።
የመለስ ዜናዊ ቡድንና አንዳንድ የትግራይ የፓለቲካ ልዒቃን አለመግባባት የተፈጠረው የዚህ ዕቅድና ራዕይ የአተገባበር ዘዴና ይህ ፕላን ኤርትራዊያንን ይጨምር ወይስ አይጨምር በሚለው ነው። የመለስ ዜናዊ ቡድን ፍላጎትና ድሮም እንደሚያምኑበት የትግራይ የረዥም ጊዜ ግብ ከኤርትራ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነበር። እንደ መለስ ቡድን አስተሳሰብ ትግራይ በኤርትራ ተቀባይነት ሊኖራት የሚችለው የትግራይ ኢኮኖሚ ወደ መሀከለኛ ገቢ ደረጃ ሲደርስ ብቻ ነው። ደሀ ትግራይ ኤርትራን አታጓጓም። እንደ መለስ ዜናዊ ትንታኔ የትግራይ ዋናው ችግር ድህነት ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ ያለው ዋናው ችግር ግን የድህነት ሳይሆን የአስተዳደር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ትግራይን ከድህነት አውጥቶ ወደ መሀከለኛ ገቢ ለማድረግ በኢትዮጵያ የተበላሸ አስተዳደር በማስፋፋት ያለውን ሀብት በሰፊውና በፍጥነት መበዝበዝ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ ያለው ብልሹ አስተዳደር በህወሃት ሆን ተብሎ የሚተገበርና የሚፈለግ ነው። በስፋትና በጥልቀት ለመዝረፍ በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘረፋ አመቺ ሆኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል። በህወሃት ትንታኔ በትግራይ ያለው ልማት በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደረገው ዝርፍያ ጋር መርእ ያለው ቁርኝት አለው። ትግራይን ለማልማት ካስፈለገ የተቀረው ኢትዮጵያን መዝረፍ ያስፈልጋል። ህወሃት የሚሰራው ለትግራይ ነው በዚህ ላይ ብዥታ ያለበት ሰው ካለ እውነታውን ለማየት ያልቻለ፣ የማይፈልግ ወይም አውቆ የሚክድ ሰው ነው። በግለሰብ ደረጃም ቢሆን የትግራይ ተወላጆችን በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ በአድሎና በዘረፋ ሀብታም እንዲሆኑ ማድረግ ህወሃት ትግራይን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ሀብት ለመዝረፍ የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ ነው። ዘረፋው የሚካሄደው እንደ መንግስትም፣ እነድ ድርጅትም፣ እንደ ቡድንም፣ እንደ ግለሰብም ነው። እንደ መለስ ዜናዊ እምነት ከድህነት ለመውጣት ከዚህም ከዛም የሚገኘውን ጥቅም በማንኛውም መልኩ በፍጥነት መለቃቀም ያስፈልጋል። የመለስ ዜናዊ ራእይ ትግራይን በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ አቅም እንደ እስራኤል ማድረግ ነው ለዚህም የትግራይ ምሁራኖችን ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ በግልፅ ይማፀን ነበር። ለዚህም ይመስላል አብዛኛው የትግራይ ምሁራኖች የህወሃት ደጋፊ የሆኑት።
በተቀረው ኢትዮጵያ ብልሹ አስተዳደር ማስፋፋት ዋንኛው የህወሃትን የበላይነት ማስጠበቂያ መሣሪያ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ከተመሰረተ፤ የክልሎች አስተዳደር ከህዝብ ጋር ይቀራረባል ይደጋገፋል። ይህ ደግም ለህወሃት አደጋ ነው። ምክንያቱም የክልል አመራሮች የህዝብ ድጋፍና የህዝብ ፍቅር ካላቸው የህወሃት ታዛዥና ሎሌ ሊሆኑ አይፈልጉም። ስለዚህ ህወሃት መልካም አስተዳደር እንዲመሰረት የሚፈልግ ድርጅት አይደልም። ይህ ሆን ተብሎ በህወሃት የተነደፈ ዘዴ ነው። በየክልሎቹ መልካም አስተዳደር ከሰፈነ የህወሃት የበላይነት ያከትማል ማለት ነው። ይህ ከህወሃት መርእና የቅርብም ሆነ የሩቅ ጊዜ ግብ ጋር ይፋለሳል። ስለዚህ ህወሃት የሚፈልገው በብልሹ አስተዳደር የሚጨማለቁና የህዝብ ፍቅርና አመኔታ የሌላቸው ከህወሃት ማፍንገጥ የማይችሉና በሚፈልገው ጊዜ በሌላ መሰል ግለሰቦች የሚተካቸው የክልል አመራሮች ነው። የክልል አመራር ሆነው በሥራቸው ምክንያት በህዝብ የሚወደዱ አመራሮች ዋንኛ የህወሃት ጠላቶች ስለሆኑ በአመራር ቦታቸው ብዙም አይቆዩም ነበር። በተቀረው ኢትዮጵያ የህወሃት ዋና ዓላማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ሳይሆን፤ ብልሹ አስተዳደር እንዲሰፍን በማበረታት በህዝብና በአመራሮች መሀከል ጥላቻን በማጠናከር አመራሮቹ ከህዝብ ይልቅ በህወሃት እንዲመኩ በማድረግና አመራሮቹን መቆጣጠርና የህወሃት የብዝበዛ መሣሪያ ማድረግ ነው። በማይፈልጋቸው ጊዜም ያለ ችግር በሌሎች አዳዲስ አገልጋዮች መተካት ነው። ስለዚህ ህወሃት እና መልካም አስተዳደር በተቀረው ኢትዮጵያ አብረው ሊኖሩ ወይም ሊሄድ አይችሉም። ህወሃት እና መልካም አስተዳደር በተቀረው ኢትዮጵያ መሠረታዊ የሆነ ተቃርኖ አላቸው። ይህም ማለት ህወሃት የበላይ እስከሆነ ድረስ መልካም አስተዳደር በተቀረው ኢትዮጵያ ሊፈጠር አይችልም። በተቀርው ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ለመመስረት ካስፈለገ የህወሃት የበላይ አገዛዝ ከኢትዮጵያ መወገድ አለበት። መልካም አስተዳደር የህወሃት ጠላት ሲሆን፤ ህወሃትም የመልካም አስተዳደር ጠላት ነው። ህወሃት በበላይነት እየገዛ መልካም አስተዳደር በተቀረው ኢትዮጵያ ይገኛል ብሎ መድከም ከንቱ ልፋት ነው። መልካም አስተዳደር ከተመሠረተ ዘረፋ በጣም ይቀንሳል ወይም ይቆማል። ህወሃት ደግሞ ካልዘረፈ ሊኖር አይችልም። ህወሃት መዝረፍ ካልቻለ መርእ አልባ ይሆናል። ምክንያቱም የህወሃት ዋናው መርእ መዝረፍ ስለሆነ።
በአጠቃላይ የህወሃቶች ዓላማና ተልዕኮ የተቀረው ኢትዮጵያን በመዝረፍ ትግራይን ወደ መሀከለኛ ገቢ ክልል ማሸጋገር ነው። ነገር ግን ይህ የወያኔዎች ዓላማ የተቀረው ኢትዮጵያ ላይ ቀጣይ ያለው ልማት እየፈፀሙ ቢሆን ኖር በጄ ሊባል ይችል ነበር። ነገር ግን የአገሪቱን ድንግል መሬት ለውጭ ባለሀብት ለረዥም ዓመታት አግባብ ላልሆነ ልማት በማከራየት፤ የአገሪቱን ትልልቅና አትራፊ ኢንደስትሪዎችን ከህወሃት ጋር ሽርካና ለፈጠሩ የውጭ ባለሀብቶች በመቸብቸብ፤ የአገር ውስጥ ባለሀብትን ለአገራዊ ብልፅግና ብዙም ምርታም ባልሆነው ነገር ግን ለግል ብዙ ትርፍ በሚያስገኘው የሕንፃና የቤት ግንባታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲርመሰመስ በማድረግ የአገሪቱን የልማት አቅጣጫ እየተጨናገፈ ነው። ይህ በተቀረው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ብልሹ አካሄድ በትግራይ ግን የለም። በትግራይ የተገነቡና ያሉ ኢንደስትሪዎች በሙሉ የትግራይ ክልል ሀብቶች ሲሆኑ፤ በትግራይ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶችም ቢሆኑ ከወያኔዎች ጋር በሽርክና የተያያዙ ናቸው። በተቀረው ኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስቲሪዎች ግን ከትግራይ ባለሀብቶች ጋር ሽርክና ባላቸው የውጭ ባለሀብቶች እየተዋጡ ናቸው። በተቀረው ኢትዮጵያ የሚገነባው ብልሹ ካፒታሊዝም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ደሀና ሎሌ የሚያደርግ ሲሆን በትግራይ የሚገነባው መንግስታው ካፒታሊዝም ግን አብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ወደ መሀከለኛ ገቢ ደረጃ ለማድረስ የታለመ ነው። ወያኔዎች ኢትዮጵያን የመካከለኛ ገቢ አገር ደረጃ እናደርሳለን ሲሉ በራዕያቸው ያለው ትግራይን የመካከለኛ ገቢ ደረጃ ማድረስ ሲሆን፤ ለምን የተቀረው ኢትዮጵያም መድረስ አልቻለም ተብለው ቢጠየቁም፤ እኛም ምን እናውቃለን የክልሎቹን አስተዳዳሪዎች ጠይቁ እንደሚሉ መታወቅ ይገባውል። ለዚህም የቅርብ ማረጋገጫ የአማራ ተወካይ ነኝ የሚለው ብልጡ በረከት ስማዖን ትግራይ ላለው የትግራይ የኢኮኖሚ መነሳሳት ምክንያት የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥንካሬ ሲሆን፤ በኦሮሚያና በአማራ ያለው ድክመት ምክንያቶችቹ ደግሞ የክልሎቹ አመራሮች ድክመት ነው በማለት ሲተች እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን በቅርቡ በተደረገው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ መግለጫ በህወሃት ውስጥ ያለው የዘረፋ ቡድን በየክልሎቹ ለሚገኘው ብልሹ አስተዳደር ዋና ተጠያቂ እንደሆነ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ነው። ይህን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፋት ሃያ ሰባት ዓመታት የሚያውቀው ጉዳይ የሆነና፤ ነገር ግን ይህ ዘራፊ የተባለው ቡድን በህወሃት ሆን ተብሎ ዘረፋን እንዲያስፋፋ ዲዛይን የተደረገ ቡድን ነው።
ምናልባት አንዳንድ የዋህ ሰዎች ወያኔ በተቀረው ኢትዮጵያ ትልልቅ ልማት እየሠራ ነው በማለት እንደ ዓባይ ግድብና እንድ የባቡር አግልግሎት የመሣሰሉትን በማየት ሊታለሉ ይችላሉ። የወያኔ እኩይ ዓላማም ይህው ነው። ሕዝቡን ሊያዘናጉና ሊያታልሉ የሚችሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እዚም እዚያም በማሳየት የወያኔን ዘራፊነት በሰፊው ለመቀጠል ነው። ወያኔ ለቆመለት ዓላማ ሀብት መዝረፍ የሚችለው እኮ ኢትዮጵያው ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው። ነገር ግን ይህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የወያኔን ዓላማ እንዲያሳካ በብልሹ ካፒታሊዝም ዘዴ የሚተገበር ነው። የጣሊያን ኮሎኒያኒዝም በኤርትራ የገነባው ኢንደስትሪዎችና የመሠርተ ልማት በጣም ብዙ ነበረ፤ ነገር ግን ዓላማው ለኤርትራ ሕዝብ ታስቦ አልነበረም። ለኢጣሊያን ኮሎኒያሊስቶቹ ታስቦ ነበር። ከላሚቷ የሚገኘውን ወተት ለማብዛት እኮ ላሚቷ እስክታርጅና እስክትደክም ድረስ ብዙ ወተት የምትሰጥበትን ዘዴ ማመቻቸት ያስፈልጋል። የወያኔዎችም ዓላማ እንደዚሁ ነው የተቀረው ኢትዮጵያ እስኪደክም ድረስ በፕላንና በዘዴ መመዝመዝና መመዝበር ነው። ወያኔ የሚሰራው፣ የሚገለው፣ የሚያስረው፣ የሚዋሸው ለመዝረፍ ብሎ ነው። ወያኔ ያለዝርፍያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊቆጣጠር አይችልም። ወያኔ ያለ ዝርፍያ ሊኖር አይችልም። ያለዝርፍያ ወያኔ ይከስማል። ዝርፍያ የወያኔ መርእ ነው። ወያኔ ካልዘረፈ መርእ አልባ ይሆናል።
የወያኔ የኢንዱስትሪ ፓሊስ ዕቅድም የሚያንፀባርቀው የተቀረውን ኢትዮጵያ የሚያራቁት ፓሊሲ ነው። የፓሊሲው ዋና አቅጣጫ እንደሚያመለክተው ከትግራይ በስተቀር በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሌቤት እንዲሆኑ የታለመው ከወያኔ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጋር ሽርክና የሚገቡ ታላላቅ የውጪ ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ የሚከፋፈለው ለወያኔዎቹና ለውጭ ኩባንያዎች ይሆናል ማለት ነው። የተቀረው ኢትዮጵያዊ ከኢንዱስትሪ ልማቱ የሚያገኘው ጉልበቱን በመሸጥ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ መግፋት ነው። ባለሙ አገሮች የኢንዱስትሪ ልማት ዋናው ተፈላጊነትና ዓላማ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን እንደውም ትልቁ ዓላማው ከፍተኛ ካፒታል በማመንጨት አገሮቹ ቀጣይ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲያደርጉና የሕዝቡን ህይወት የሚለውጡ የማህበራው አግልግሎቶችን ለማስፋፋት የሚውል የካፒታል አቅም ማመንጨት ነው። ነገር ግን በተቀረው ኢትዮጵያ የታለምወ የወያኔዎቹ የኢንዱስትሪ ፓሊስ ዓላማ የሚያበልፅገው በአብዛኛው የወያኔዎቹ ሽርክ የሆኑትን የውጭ ኩባንያዎችና ወያኔዎችን ሲሆን። ይህን በመጠቀም ወያኔዎቹ ክልላቸውን ወደ መሀከለኛ ገቢ ሊያደርስ የሚችል ካፒታል ከውጭ ኩባንያዎቹ ጋር ይከፋፈላሉ ማለት ነው። ስለዚህ በጠቅላላው በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ ይተገበራል የሚባለው የኢንዱስትሪ ፓሊሲ የአንበሳ ድርሻ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወያኔዎችና የወያኔ ሸርካ የውጭ ኩባንያዎች ይሆናሉ ማለት ነው።
ይህ ዘዴ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ይጠቀሙበት የነበረው ዓይነት ዘዴ ነው። የቅኝ ተገዢ አገሮች ለቅኝ ገዢዎቹ አገሮች ብልፅግና የሚውል ከፍተኛ ካፒታል ያመነጩ ነበረ። ይህንንም ለማድርግ ቅኝ ገዢዎቹ በቅኝ ተገዢ አግሮች ውስጥ የካፒታል ማመንጨቱን ሥራ የሚያቀላጥፉ በርካታ መሠረተ ልማቶችንና ኢንዱስትሪዎችን ገንብተው ነበር። ሩቅ ሳንሄድ በኤርትራ የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ያደረጉትን ማየት ይቻላል፡፡ በተለይ የእንግሊዙ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በየኮሎኒዎቹ የእንግሊዝን የብዝበዛ መዋቅር የሚያስጠብቁና የሚያስፈፅሙ አቀባባይ ሎሌዎችና ተባባሪዎችን ከየአካባቢው ህዝብ ገዢዎች በመሰየምና ጥቂቶችን የአገር ተወላጆች የብዝበዛው ተጠቃሚ በማድረግ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ላይ ከፍተኛ ብዝበዛና በቀላሉ የማይሽር ከፍተኛ ጉዳት አስከትለዋል። የአውሮፓን የብዝበዛ አገዛዝ በመላው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያመቻቹና ተገባራዊ ያደረጉት “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በሚሉ በየአካባቢው የሚገኙ የአፍሪካ ገዢ መደቦች ነበሩ። ለግል ጥቅም ብለው ህዝባቸውንና አገራቸውን በጣም ያስመዘብሩ ነበር። እንግዲህ ከወያኔ መገላገል ማለት ለ27 ዓመታት በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ከፍተኛ ግፍና ዘረፋና መገላገል ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ቀጣይ እድልና የህዝቡንም የዘመናት የልማትና የፍትህ ጥያቄዎች ለመመለስ ነው። የኢትዮጵያ ዋናው ችግር ድህነት ሳይሆን የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ነው። የህወሃት አገዛዝ ከተቀረው ኢትዮጵያ ካልተወገድ በስተቀር በተቀረው ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርና ፍትህ ሊመጣ አይችልም።
የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማ በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በኦሮሞና በአማራ የፖለቲካ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው ያለፈ ታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድና በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን የትብብር ጉዳዮች ላይ ጥረት ማድረግ ነው።
የአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com
——
በዚህ ድረ ገጽ ነጻ አስተያየትም ሆነ ሌሎች መጣጥፎች ለማውጣት ፤ እና ሌሎች መረጃዎች ለማቀበል በሚከተለው አድራሻ ይላኩ editor@borkena.com
ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ማድረግ አይርሱ።