ጥር 7 ፣ 2010

አፍቃሪ መንግስት የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ የፌደራሉን ጠቅላይ አቃቢ ህግ ጠቅሰው እንደዘገቡት የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ክስ ተቋርጧል። ዶ/ር መረራ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ በታወጀ ማግስት ለስራ ጉዳይ ከሄዱበት ከአውሮፖ ሲመለሱ ተይዘው ከአንድ አመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በእስር ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።
በፌደራል ደረጃ የአንድ መቶ አስራ አምስት ሰዎች ክስ ተቋርጧል የተባለ ሲሆን ፤ በደቡብ ክልል እስከ አራት መቶ አስራ ሶስት የሚደርሱ “ተጠርጣሪዎች”ም እንዲሁ ክሳቸው ተቋርጧል ተብሏል።
ኢህአዴግን የመሰረቱት አራት ዘውጌ ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በማድረግ ከሁለት ሳምንት በላይ የወሰደ ግምገማ በማድረግ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና ለብሄራዊ መግባባት “በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ” ያላቸውን እስረኞች እንደሚፈታ ማሳወቁ ይታወሳል።
ሆኖም በፌደራል ደረጃ ይለቀቃሉ ከተባሉት ከዶ/ር መረራ ጉዲና ውጭ በተቃዋሚ መሪነት የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ስም አልተጠቀሰም። በደቡብ ክልል ክሳቸው ተቋርጧል የተባሉት ለእስር የተዳረጉት በጌዲዮ ዞን ተነስቶ ከነበረ ግጭት ጋር በተያያዘ እንደነበረም የፋና ዘገባ ይጠቁማል ።
እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ዘገባ እስረኞቹ እስከ ረቡዕ ባለው ጊዜ “የተሃድሶ ስልጠና” ወስደው ይፈታሉ።
———
ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።