ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
ጥር 12 2010 ዓ ም
“እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?
አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?” የጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 2 ከቁጥር 21 እስከ 23።
ቅዱስ ጳውሎስ፤ ለሮሜ፤ ለቆሮንቶስ ሰዎችና ለሌሎች፤ ከሚሰሩት ሃጥያት ይልቅ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው እግዚአብሄርን እንዲከተሉ፤ ማስተማሩን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ለሮሜ ሰዎች ካስተላለፍው አንዱ መልእክት፤ ከላይ የተጠቀሰው ነው። ልክ እንደ ሮሜ ሰዎች፤ ላለፉት 27 ዓመታት፤ “ለሕወሓት/ኢሕአዲግ ሰዎች” ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ፤ ከድርጅት ይልቅ ሃገርን እንዲያስቀድሙ፤ በተለያየ መልኩ፤ ባለን አቅም ሁሉ መለዕክት አስተላልፈናል። ይህ መልዕክታችን ግን ሰሚ ያላገኘ ጩኸት ብቻ በመሆኑም፤ ዛሬም ተጨማሪ መልዕክት ማስተላለፉ ግድ ይላል። በተለይም በአሁኑ ወቅት፤ የሕወሓት/ኢሕአዲግ መሪዎች፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በመቆጣጠር ላለፉት 27 ዓመታት በሕዝብና በሃገር ላይ የፈፀሙትን ግፍና በደል በአደባባይ ሲናዘዙ፤ አባላቶቹና ደጋፊዎች፤ በባለሥልጣናቱ ላይ ግፊት ከማድረግ ይልቅ፤ “የፀጥታ ተቃውሞን”፤ ወይም የውስጥ ለውስጥ ሹክቻን መርጠው፤ ገዥው ፓርቲ፤ በተለይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በአጠቃላይ ለዓለም ሕዝብ የገባውን ቃል ከመተግበር ይልቅ፤ ግማሽ መንገድ ላይ እግሩን አንጠልጥሎ እንዲቆም ግፊት እያደረጉብተ ነው።
ዛሬ የምናየው የለውጥ ማዕበል፤ በተለይም በኦሮሞና በአማራ ክልል ወጣቶች ከፍተኛ ትግልና መስዋዕትነት እየጎረፈ በመጣ አደገኛ ጎርፍ እየተገፋ የሚገኝ የህዳሴ ለውጥ፤ በብአዴንና ኦሕዴድ መሪዎች ግፊት፤ ነገር ግን የኢሕአዲግ ቁንጮ የሆነው ሕውሓት ያልተዘጋጀበት ለመሆኑ፤ ከገዥው ፓርቲ የሚወጡት እርስ በእርስ የተጣረዙት መግለጫዎች በግልጽ ያሳብቃሉ። በእኔ እምነት፤ የመጣውን ይህን የለውጥ ማእበል ለማብረድ በሚመስል መልኩ፤ ገዥው ፓርቲ፤ ያለሕግና ፖለቲካዊ በሆነ ፍርድ ቤቱ በግፍ ያሰራቸውን በሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች “በቁጥ ቁጥ” እየፈታ የሚገኘው በግል ጥቅም በሰከሩ፤ የሥልጣን ጥም ባናወዛቸው፤ በሙስና በተዘፈቁ፤ እጃቸው በንፁሃን ዜጎች ደም የተነከሩ አባላትና ደጋፊዎቹ በሚያደርጉበት ግፊት ነው። የሕውሓት/ኢሕአዲግ አባላት በግልጥ ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር፤ የለውጥ ማዕበሉ ወደ ኋላ የሚመለስበት ምንም ዓይነት መንገድ አለመኖሩን ነው። ዛሬ እየተንደረደረ የሚመጣው የለውጥ ማዕበል፤ ላለፉት 27 ዓመታት ሞልቶ ከፈሰሰው የግፍ ውቅያኖስ የመነጨ መሆኑን ለአንድ አፍታ እንኳን ሊዘነጉት አይገባም። ይህ ግፍ ያንገሸገሸው ሕዝብ፤ በላዩ ላይ የተጠመደውን የግፍ ቀንበር ነቅሎ ለመጣል፤ የጀመረውን ግስጋሴ አያቆምም። ይህ በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ መሆን አለበት።
ገዥው ፓርቲና አባላቱ፤ አትሰረቁ እያሉ የሚሰርቁ፤ ስለሕግ እየሰበኩ፤ ሕግ የሚጥሱ፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንገነባለን እያሉ፤ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞችን የሚያፈርሱ ለመሆናቸው፤ ገዥው ፓርቲ ከሰጠው መግለጫ ውጪ ተጨማሪ ምስክር የሚያሻ አይመስለኝም። በተለይም ተራ አባላቱና ደጋፊዎቹ፤ የገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍ እያዩና፤ አንዳንዶቹም የግፉ ቀጥተኛ ተሳትፊ ሆነው፤ ከሃገር ጥቅም ይልቅ ለድርጅት ጥቅም በመቆም፤ ከሃገር ፍቅር ይልቅ፤ የድርጅት ፍቅር በማሳየት፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሃገራችን ለደረስችበት አዝቅት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬም ቢሆን የድርጅታቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲውተረተሩ እናያለን። የገዥው ፓርቲ ስህተቱን በማመን መግለጫ ባወጣበት ወቅት፤ የትግራይ ኦንላይን (Tigray online) እና የአይጋ ፎረምን ድህረ ገጽ ለጎበኘ፤ እነዚህ የገዠው ፓርቲ ፕሮፖጋንዲስቶች፤ ልክ የቅርብ ዘመድ እንደሞተበት ሰው፤ ሃዘን ላይ እንደነበሩ ለማውቀ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም። ምንም እንኳን Tigray online በድንጋጤ ድባብ ተውጦ ዝምታን ቢመርጥም። አይጋ ፎረም ግን፤ የገዥው ፓርቲ ፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ሲያበስር፤ ይህንን ዜና ከ1999 የቅንጅት መሪዎች አፈታት ጋር በማመሳሰል፤ ሲወራጭ ተስተውሏል።
ምንም እንኳን፤ ገዥው ፓርቲ ባልጠበቀው ሁኔታ፤ ከድርጅቱ ውጭና ውስጥ በመጣበት ከፍተኛ ማዕበል ተወጥሮ፤ ማእበሉን ለማዛል መግለጫ ቢያዋጣም፤ የገዥው ፓርቲ አንኳር ተጠቃሚዎችና የሙስና ነገስታቶቹ፤ ብርክ ይዟቸው፤ ገዥው ፓርቲ ለሕዝብ የገባው ቃል ከሞላ ጎደል ተገባራዊ እንዳይሆን፤ እየታገሉና አፍራሽ ሚና እየተጫወቱ ለመሆኑ በርካታ ምልክቶች አሉ። በቅርቡ “ከፍትሕ ሚኒስትሩ” የተሰጠው አሳዛኝና አሣፋሪ መግለጫ፤ ገዥው ፓርቲ ሊቆም ያሰበበትን ግማሽ መንገድና በውስጡ ያለውን ሽኩቻ የሚጠቁም ነው። ገዥው ፓርቲ በትረ መንግስቱን በጠመንጃ አፈሙዝ ከጨበጠበት ከግንቦት 20፣ 1983 ጀምሮ የኖረበት የሽፍጥና የግፍ አገዛዝ ከጅምሩ ገሃድ የወጣ ቢሆንም፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ፤ ግፉንና ሽፍጡን ለመከላከል በየአደባባዩ ሽንጣቸውን ይዘው ተከራክረዋል፤ የግፉም ተካፋይ ሆነዋል። ሃገራችን፤ ከፍተኛ የደም መፋሰስን አስተናግዳለች፤ ዜጎች እርስ በእርስ እንዲጠላሉ፤ እርስ በእርስ እንዲጋደሉ፤ በሕወሓት/ኢሕአዲግ ሰዎች ከፍተኛ ቅስቀሳ ተደርጓል፤ የብዙ ውድና ብርቅዬ ዜጎች ሕይወት፤ ሊጠብቃቸው ሃላፊነት ባለበት የገዛ መንግስታቸው አረመኔያዊ ጥቃት ያለአግባብ ጠፍቷል። ዛሬም ያለምንም ሃፍረት በየአደባባዩ ስለፍትህ፤ የሕግ የበላይነት፤ ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት መከበር የሚከራከሩት የሕወሓት/ኢሕአዲግ ሰዎች ቆም ብለው ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ እገደዳለሁ። ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንዳስተላለፈው መልዕክት የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርጉ፤ ታግለንልንለታል የሚሉት ፍትሕ፤ የሕግ የበላይነትና፤ የዲሞክራሲ ስልተ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እውን እንዲሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መልዕክቴን ለማስተላለፍ እገደዳለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደም መፋሰሱ መቆም አለበት፤ ከቂም ወደ እርቅ መምጣት አለብን፤ የጦርነት አዙሪት መሰበር አለበት፤ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ግን፤ የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው። ገዥው ፓርቲ የፈጸመውን ግፍና በደል መገንዘብና መቀበል ይኖርባቸዋል፤ ወደራሳቸው ማየትና፤ በእውነተኛ ግለ ሂስ እራሳቸውን መገምገም አለባቸው፤ ከድርጅት ይልቅ ሃገርን ማስቀደምም ይጠበቅባቸዋል። የሌለውን ነገር እንዳለ አድርጎ ከመከራከር ይልቅ፤ የሕግ የበላይነት ያለባትን፤ ለሁሉም ዜጎችዋ እኩል የሆነች፤ ጥቂቶች የበኩር ልጆች፤ ብዙሃኑ ደግሞ የእንጀራ ልጆች ያልሆኑባት፤ ዘላቂ ሰላምና ቀጣይ እድገት የምታሳይ፤ ለሕዝቧ ተገንና ኩራት የሆነች ዲምክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጎን መቆምና መታገል ይኖርባቸዋል። ጊዜም ሳይፈጁና ሳያንገራግሩ፤ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታ ግፊት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያቆጠቆጠው ተስፋ ጨልሞ ወደ ሌላ ነውጥ ከመሄዳችን በፊት፤ ተጨማሪ ብርቅዬ ዜጎች ሕይወታቸውን ከማጣታቸው በፊት፤ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ ብለን አብረን እንጩኽ። እንጸየፈዋለን እያላችሁ የምትሰብኩትን ስርዓተ አልበኝነት፤ እራሳችሁ አታድርጉት፤ መልእክቴ ይህ ነው። የፖለቲካ እስረኞች ከተፈቱም በኋላ፤ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ኮምሽን ተቋቁሞ በአስቸኳይ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ እንሂድ። ልክ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንዳለው፤ ለእናንተ ያለኝ መልዕክት፤ ከመዘግየቱ በፊት ልብ ግዙ፤ ሃገርን አስቀድሙ፤ ለሕዝባችን ቁሙ።
ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንዳሉት፤ “ሁላችንም በተለያየ መርከብ መጥተን ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን ያለነው አንድ ጀልባ ውስጥ ነው”። አዎ ሁላችንም ያለነው አንድ ጀልባ ውስጥ ነው፤ ጀልባው ከተቀደደ፤ ጎርፉ ሁላችንንም ይዞ እንደሚሄድ እንገንዘብ።
ከአክብሮት ጋር።
ጸሃፊውን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል : tibebesamuel@yahoo.com
___
ማስታወሻ : በዚህ ጽሁፍ ላይ የተነጸባረቁ ሃሳቦች የጸሃፊውን ሃሳብ ያንጸባርቃሉ። በዚህ ድረ ገጽ ነጻ አስተያየት ወይ ሃሳብ ለማካፈል ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com