spot_img
Sunday, September 24, 2023
Homeአበይት ዜናዛሬም በቀጠለው የወልድያ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች ሞቱ (ዶቬ)

ዛሬም በቀጠለው የወልድያ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች ሞቱ (ዶቬ)

advertisement
ወልዲያ - Woldia
የህወሓት መንግስት ታጣቂ ናቸው የተባሉ በንጹሃን ላይ ዘግኝ እልቂት ያደረሱባት የወልደያ ከተማ
ፎቶ ፤ ከማህበራዊ ድረ ገጽ

ዶቬ
ጥር 13 2010 ዓ ም

በአማራ ክልል በወልድያ ከተማ ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ዛሬም በቀጠለው ግጭት በርካቶች መጎዳታቸውን፣ ሆቴሎች እና ህንጻዎች መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በወልድያ ግጭት የተቀሰቀሰው የጥምቀት በዓል በዋለ በማግስቱ የሚከበረውን የቃና ዘገሊላን በዓል በጭፈራ እያከበሩ የነበሩ ምዕመናን በጸጥታ ኃይሎች እንዳይጨፍሩ ከተከለከሉ በኋላ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በዓል አክባሪዎቹ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ነበር ብለዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ በትላንትናው ዕለት በነበረው ግጭት አምስት ሰዎች እንደተገደሉ መስማታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው በትላንቱ ግጭት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ ያደርጉታል፡፡ ቆስለው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት ውስጥ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ትላንት ከተገደሉት የከተማይቱ ነዋሪዎች ውስጥ ዕድሜው ከ14 ዓመት ያልበለጠ ታዳጊ እንደሚገኝበት ሁለቱም ነዋሪዎች አረጋግጠዋል፡፡ ታዳጊው በጥይቶ ተመትቶ ከቆሰለ በኋላ ቆይቶ መሞቱን አንደኛው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ እኚሁ ነዋሪ ዕድሜው ከ20 እስከ 26 ዓመት የሚገመት እና ነዋሪነቱ ሚጠ ጊዮርጊስ በሚባለው የከተማይቱ ክፍል የሆነ ወጣት መሞቱን ሰምቼያለሁ ብለዋል፡፡ ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው በፒያሳ ያለ የባለብረታ ብረት ድርጅት ባለቤት ከሞቱት ውስጥ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በወልድያ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ተኩስ ይሰማ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች እስከ ቀኑ ስምንት ድረስ መቀጠሉን ለዶይቼ ቬለ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ከስድስት ሰዓት በኋላ ትንሽ የመረጋጋት ነገር አለ ግን ጠዋት ላይ የነበረው የከፋ ነበር ብለዋል” በጎንደር በር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪ፡፡ የዛሬው “ጸብ” የተቀሰቀሰው ትላንት የሞቱ ሰዎችን የቀብር ስነ ስርዓት ለመፈጸም በወጡ ሰዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት እንደነበር የከተማይቱ ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በግጭቱ ሰዎች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ቢነገርም ትክክለኛውን ቁጥር ማረጋጋጥ አልተቻለም፡፡

በጸጥታ ኃይሎች የኃይል እርምጃ የተቆጡ የወልድያ ነዋሪዎች በከተማይቱ ያሉ ሆቴሎች እና ህንጻዎችን ማቃጠላቸውን ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ እንደነዋሪዎቹ ገለጻ በዛሬው ግጭት በፒያሳ የሚገኙት አርሴማ እና መቻሬ ሆቴሎች እንደዚሁም ኃይላይ ህንጻ ተቃጥለዋል፡፡ የአቢሲኒያ ባንክ የፒያሳ ቅርንጫፍም ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል፡፡

በዛሬው ግጭት ይበልጥ የተጠቁት ፒያሳ፣ አዳጎ እና ጎንደር በር የተባሉት የከተማይቱ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረዋል። በከተማይቱ አሁንም ከፍተኛ አለመረጋጋት እና ውጥረት አለ ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ራሳቸውን ከጉዳት ለመደበቅ በየቦታው ተሸሽገው እንዳሉም አስረድተዋል፡፡

በወልድያ ስላለው ግጭት መረጃ ለማግኘት ወደ አማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ ትላንት ያነጋርናቸው የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ በቀለን ጉዳዩን ገና በማጣራት ላይ እንደሆኑ ገልጸውልን ነበር፡፡ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ትላንት ምሽት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ በወልዲያ በወጣቶች እና በጸጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡ የሟቾቹን ቁጥር ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡ “ግጭቱን በመቀስቀስ ለንጹሀን ህይወት መጥፋት የሆኑ አካላትን ከበቂ ማጣሪያ በኋላ ለህግ የማቅረብ ስራ ይሰራል” ሲሉም ጽፈዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,682FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here