(ጥር 13፣ 2010) “የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለእርቅ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ” ሲል የሰነበተው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይህ የማዘናግያና የማጭበርበሪያ ፕሮፓጋንዳው በአየር ላይ እንዳለ ወትሮም ወደ ተካነበት የጅምላ ግድያና የጅምላ እስር ተመልሷል። የጥምቀትን በአል በሰላም ለማክበር በወጡ ንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያም የሚያመላክተው የስርአቱን ፍጹማዊ አውሬነትና ሁሌም ደም የተጠማ መሆኑን ነው። የተለያዩ የሃይማኖት በአላት በአገራችን ከሁሉም ቀናት በላይ ሰላም መቀራረብና ፍቅር የሚገለጥባቸው፣ የተጣላ ይቅር የሚባባልባቸው የተራራቀ የሚቀራረብበትና ሁሉም እንደ እንደእምነቱ በመንፈሳዊ ስነምግባር እለቱን የሚያስብበት ከጸብ ይልቅ ፍቅርና መተሳሰብ የሚጉላባቸው ናቸው። ይህ የአገራችን የተለያዩ ማህበረሰቦች ባህልና ወግ ሁኖ ሳለ ከባህላችንና ከስርአታችን የተፋታው ስርአት አመታዊውን የጥምቀት በአል ለማክበር በወጡ ንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የፈጸመው የጅምላ ግድያ በ2009 የኢሪቻን በአል ለማክበር ቢሾፍቱ ላይ በወጡ ወገኖቻን ላይ የተፈጸመውን ሰቆቃና ግድያ ያስታውሰናል።
ይህ የግፍ ጽልመትን በአገራችን ላይ በመጫን ለሃያ ሰባት አመታት የገፋው ስርአት እንደ ተቀዳሚ ሙያው አድርጎ የያዘው ወገኖቻችንን በጅምላ የመግደል የማሰርና የማሰቃየት አባዜ እንደ ክፉ አመል የተጸናወተው በመሆኑ ራሱ በቅርቡ እንዳመነው የመግደል የመዝረፍና የመዋሸት አዙሪት ውስጥ የገባ ስርአት ነው። በመሆኑም ይህ ስርአት በራሱ ይለወጣል ወይንም ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ብቻ ሳይሆን የስርአቱን መሰረታዊ ባህርይና የስርአቱን ቁንጮዎች ስነ ልቦናዊ ማንነት በሚገባ ካለመገንዘብ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው።
የአንድ ሐገር መንግስት ስራና ሃላፊነት ህዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ማድረግ እንጂ ህዝብን መግደልና ማሰቃየት አይደለም። በአገራችን ለሃያ ሰባት አመታት የተፈጸመው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ህዝቡ ሰላም አስከባሪ መንግስት ግን ሰላም አዋኪ። ህዝቡ አብሮ መኖርንና መቀራረብን ሲተገብር መንግስት ግን መለያየትንና መራራቅን እየሰበከ በህዝቡ መካከል ደም መቃባትና መቃቃር እንዲሰፍን መዶለቱን ሙያዬ ብሎ ተያይዞታል። አገራችን እስከዛሬ በሌሎች አገሮች እንደታየው ወደ ከፍተኛ ደም መፋሳሰና እልቂት ያላመራቸውም በኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋነትና ስር የሰደደ የአብሮ መኖር ባህል እንጂ እንደ ስርአቱ እኩይነትና እንደ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ደም ጥማት ቢሆን በአገራችን ሊደርስ የሚችለውን አስከፊ አደጋ መገመት አያስቸግርም።
ሕወሓት/ ኢሕአዴግ ያለማሰለስ በወገኖቻችን ላይ በየጊዜው የሚፈጸመው የጅምላ ግድያና ሰቆቃ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለነጻነት ለፍትህና ለእኩልነት የምናደረገውን ትግል ይበልጥ በተጠናከርና በተባበረ መልኩ እንድንገፋበት ያነሳሳናል እንጂ ለአንድ አፍታም አያሰናክለንም። በወገኖቻችን ላይ በወልዲያ ከተማ የተፈጸመው የጅምላ ግድያም በተመለከተ የኢትዮጵያ ሐገራዊ ንቅናቄ ከልብ የተሰማውን ሃዘን ሲገልጽ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ወዳጅ ዘመዶች መጽናናቱን ስንመኝላቸው በስርአቱ ነፍሰ ገዳዮች ቆስለው በመታከም ላይ ላሉት ደግሞ በቶሎ ያገግሙ ዘንድ እናስባቸዋለን።
ይህ አስከፊ ስርአት አብቅቶ በአገራችን የዲሞክራሲና የፍትህ ስርአት ሊገነባ የሚችለው ላፍታም በስርአቱ የማጭበርበር ስልት ሳንዘናጋ ተባብረን በከፍተኛ የተጠናከረ መንፈስ እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከታለመለት ግብ ስናደርስ ነው። ለዚህም አላማ መሳካት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ያለመታከት ይሰራል። በመጨረሻም ይህ ቅጥ ያጣ የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዊ በደልና አፈና አብቅቶ አገራችን በዲሞክራሲያዊ ስርአት ስር ወደ ዘላቂ ሰላም እንድታመራ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ለሚያደረገው ትግል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያላችሁ ወገኖቻችን ከጎናችን እንድትሰለፉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ጥር 13፣ 2010 enmpr@protonmail.com