ከወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ
ጥር 23 ቀን 2010 (January 31, 2018)
ሕዝብ ቻይ ነው፤ሕዝብ ታጋሽ ነው።ትግስቱ ግን ገደብና መጨረሻ አለው።ትእግስቱን እንደፍርሃት የሚቆጥሩ ጭፍኖችና እብሪተኞች ብቻ ናቸው።የወሎ ሕዝብ እንደተቀረው ወገኑ ላለፉት 27 ዓመታት የወያኔን የግፍ ቀንበር እያንገሸገሸውም ቢሆን ከዛሬ ነገ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊያመራ ይችል ይሆናል በሚል ግምት ተሸክሞ ኖሯል።
አሁን ግን ከድጡ ወደማጡ እየሆነ በመሄዱና የግፍ ጽዋው ሞልቶ በመፍሰሱ ብሎም የጭካኔው እርምጃ እቤቱ ድረስ መጥቶ ለብዙ ወጣት ልጆቹና አዛውን ወገኖቹ ሞት ምክንያት በመሆኑ ትዕግስቱን ወደ እምቢባይነት አመጽ ቀይሮ በመፋለም ላይ ይገኛል።ወያኔም ከምድር ጦሩ በተጨማሪ የአየር ሃይሉን በማሰለፍ ደርግ ፈጸመው ከሚለው ከሃውዜኑ እልቂት ባላነሰ ደረጃ ሕዝብ በመደብደብ ላይ ተሰማርቷል።
መንግሥት ተብዬው የወያኔ አጋዚ ጦር በወሎ ምድር በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ሲዘረዘር በጥቂቱ ይህንን ይመስላል።
1) ቀደም ሲል በቆቦ ከተማ የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች በእምነት ተቋማቸው ላይ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት በመቃወማቸው በአፋር ሚሊሽያ ጦር ጥቃት ሲደርስባቸው ፣ለዘመናት በአንድ ክ/ሃገር፣በወሎዬነት ተስማምተው በኖሩት ማህበረሰቦች መካከል በቋንቋ ተዋረድ የልዩነት ግንብ ገንብቶና ለያይቶ እርስ በርሳቸው እየተጋጩ በጠላትነት እንዲኖሩና በመካከላቸው ቂምና ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል።
2) በወልድያ ከተማ የጥምቀትን በዓል በሚያከብሩ ምዕመናን ላይ ተኩስ በመክፈት 13 ሰዎች ሲገደሉ 7 ሰዎች ቆስለዋል። በአልሞ ተኳሽ ከሞቱት መካከል በሰላም የበዓሉን አከባበር ይመለከት የነበረ የ13 ዓመት እምቡጥ ልጅ ነው።በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች በአጋዚ ጦር ታፍሰው ወደ ትግራይ ተወስደው የደረሱበት አይታወቅም።ይህ ሁሉ ግፍ የተፈጸመው የእምነት አባቶች የሰጡትን ምክርና ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመስማት ሲሆን ለዕምነቱና ለምዕመናኑ ካላቸው ንቀትና ጥላቻ የተነሳ ነው።
3) በወልድያ የደረሰውንና የተፈጸመውን ግፍ ተመልክቶ በቆቦ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ 7 ወጣቶች ተገለዋል፣ ቁጥራቸው ያልታወቀም ቆስለዋል፣ታፍነው ተወስደዋል።
4) ተመሳሳይ የድጋፍና ተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደበት የመርሳ ከተማ ከ20 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ብዙዎች ቆስለዋል፣አያሌዎችም የደረሱበት አይታወቅም።
5) ሶስት ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት በደሴ-አላማጣ መስመር የሚጎርፈውን የጦር ሃይል ሲያዩት በአካባቢውና በጠቅላላ በአገሪቱ የሚፈነዳ ሁኔታ እንዳለ ያመላክታል።
የተቀሰቀሰው የወጣቱ እምቢባይነት እንደቋያ እሳት እየተቀጣጠለ ወደ ሌሎቹ ወረዳዎች፣አውራጃዎችና ክፍለሃገሮች በመዛመት ላይ ነው።ቆቦና መርሳ ላይ የሚካሄደው ግብግብ አሁንም ቀጥሏል።በሌሎቹም ቦታዎች እንዲሁ ሕዝቡ አሻፈረኛ ብሏል። ከእንግዲህ ምንም ሃይል ቢመጣ የሚያቆመው አይኖርም፤የሚያቆመው ቢኖር የወያኔና የግብረአበሮቹ የጎሳ ስርዓት መወገድና ያገራችንን አንድነትና ልዑላዊነት የሚያረጋግጥ በሕዝባዊ ስርዓት መተካት ብቻ ነው። እስከዚያ ድረስ ወሎ እጁን ላይሰጥ ምሎና ቆርጦ ተነስቷል።
የወሎ ክፍለሃገር በተለይም ወልድያ ከተማ ለወያኔ ክልል ካለው ቅርበት ለጥቃት የተመቼ ነው።ከዚያም በላይ የዘረፋው መግቢያ መንገድና በሩ፣ የእህል ምንጩ ስለሆነ ወያኔ ያንን ማጣት አይፈልግም።የሞትና የሽረት ጥያቄ ስለሆነ ብሎም ለሌላው መቀጣጫ ለማድረግ ያለ የሌለ ሃይሉን አፍሶ በቁጥጥሩ ውስጥ ለማድረግ የማያደርገው ሙከራ፣የማይፈጽመው ግፍ አይኖርም። ይህንን ሊቀንስ የሚችለው አንዱና ዋናው ዘዴ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በያለበት በአንድ ላይ ትግሉን ሲያስተጋባ ነው።
ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር እንደ ከዚህ ቀደሙ የሰሜን፣የደቡብ፣የምስራቅና የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ የጀመረውን አገርና ወገን አድን ትግሉን እንዲቀጥልበት ወገናዊ ጥሪ ያደርጋል። የክፍላተሃገራቱ ከተማዎች ነዋሪ በተለይም የደሴ፣የአዲስ አበባ፣የሃረር፣የድሬዳዋ፣አዋሳ፣ጅማ፣ዲላ፣አሶሳ፣ነቀምት፣ጅጅጋ፣አሰላ….ወዘተ የዚህ ሕዝባዊ ትግል አካል በመሆን የየድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በወሎ ሕዝብ ስም ጥሪ ያስተላልፋል።የተነጣጠለ ትግል ለውድቀትና ለሽንፈት ስለሚዳርግ በሁሉም ቦታ በአንድ ላይ መነሳት የግድ ይላል። በባዶ ተስፋና ፍርሃት ወይም ልመና የወያኔ ስርዓት አይለወጥም። ወያኔ አገር ለማፈራረስ ታጥቆ የተነሳ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ሃይል መሆኑን መጠራጠር አይገባም።በእርቅና ድርድር ወይም በሰላም እለውጠዋለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነትና የተፈጥሮ ጸባዩን አለማወቅ ነው።
የወያኔ ስርዓት አራማጅ በሆኑት የየክፈለሃገሩ ተወላጆች ላይ የማይመለሱ ከሆነ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ተገቢ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።ስለሆነም የሚመለከታቸው ግለሰቦች ከሚወድቀው ስርዓት ጋር አብረው ከመውደቅ አሁኑኑ ሰልፋቸውን እንዲያስተካክሉ ይመከራሉ።
በቢሮክራሲው የምትሰሩት፣በጦር ሃይሉ የተመደባችሁ ወገኖቻችን ቅድሚያ የምትሰጡት ላገራቸሁ አንድነትና ለወገናችሁ ደህንነት ይሁን።ሕዝብ የሚታገልለት የስርዓት ለውጥ እናንተንም ከባርነትና ከጭንቀት ነጻ ለማውጣት እንደሆነ ተረዱ። የሕዝቡን ትግል ትቀላቀሉ ዘንድ የወሎ ማህበር ጥሪውን ያስተላልፍላችዃል።የፍርድ ቀን ሲመጣ ከሚያፍሩበትና ከሚሸማቀቁበት የወያኔ አገልጋይነት ይልቅ ሊኮሩበት በሚያስችለው በሕዝባዊነት ቦታ መዋሉ ይመረጣል።
በተጨማሪም በውጭ አገር መንግሥታት መተማመን የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር መገንዘብ ያስፈልጋል።በራስ መተማመን ትልቁ መሣሪያ ነው።የውጭ መንግሥታቱ ግፋ ቢል የሚያመጡት ነገር ቢኖር በጥገና ለውጥ የወያኔ ስርዓት እንዲቀጥል ማድረግ ብቻ ይሆናል።እስከአሁንም ድረስ ተንከባክበው ያቆዩት እነሱ ናቸው።
በውጭ አገር የሚኖረው አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ሕዝባዊ ትግሉን በሞራልና በቁሳቁስ እንዲሁም በገንዘብ መርዳት አለበት። በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ መገደብ የለበትም።እርዳታውን የሚያስተባብር ከአንድ ነጠላ ድርጅት ጋር ያልተሳሰረ አንድ አገር አቀፍ የድጋፍ አካል መፍጠር ዛሬ ነገ ሳይል ሥራውን መጀመር ይኖርበታል።ለዚያ ብሔራዊ ግዳጅ ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ ነው።
ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር ሰሞኑን በወሎና በሌሎቹ ያገራችን ክፍሎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ መንግሥት ተብዬው የወያኔ አጋዚ ጦር የፈጸመውን ጭፍጨፋ ፣ግድያና ማቁሰል እንዲሁም አፈና እያወገዘ፤ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ልባዊ ሃዘኑን እየገለጸ መጽናናትን ይመኛል።
በደልና ግፍ የፈጸሙት የመንግሥት ባለስልጣኖች፣ የጦርና የደህንነት ባልደረቦች በሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። ሕዝባዊው ትግል በድል ይጠናቀቃል እንጂ አይቀለበስም!
ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኖራለች!!