ቦርከና
ጥር 30 2010 ዓ.ም
የፌደራሉ አቃቤ ህግ ትላንት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም አራጌ ከሌሎች ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑ ፌደራል እና ክልል እስር ቤቶች ካሉ አስረኞች ጋር እንደሚለቀቁ ቢገልጹም ፤ ማንነታቸው ባይታወቅም መንግስቱን ከሚመሩ ባለስልጣናት ውስጥ ባልሰሩት ወንጀል ተከሰው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ የተፈረደባቸውን ሁለቱን እስረኞች ያለመፍታት አዝማሚያ አሳይተዋል::
አንዱዓለምን እና እስክንድርን ለመፍታት የተደረሰው ውሳኔ እንደተቀለበሰ የታወቀው ዛሬ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች አንዱዓለምን እና እስክንድርን ወደ ቢሮ በማስጠራት “የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል ነን” ብላችሁ ፈርሙ ተብለው ለመፈታታቸው እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጠ በኋላ ነው:: ሆኖም አንዱዓለም እና እስክንድር “የግንቦት ሰባት ዓባል ስላልሆንን ዓባል ነን ብለን አንፈርምም” በማለት መንግስት ለዳግም ውንጀላ ለማመቻቸት ያመጣው ነው የተባለውን ወጥመድ ሰብረውታል::
የአንድነት ለፍትሕ እና ለዲሞክራሲ ጸሃፊ የነበረው አንዱዓለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር በሽብርተኝነት እና አመጽ በማነሳሳት ወንጀል ተከሰው የአስራ ስምንት አመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስካሁን ለስድስት ዓመታት ያህል በእስር ቆይተዋል:: ሆኖም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ሆነ ኢትዮጵያውያን እንደ ፖለቲካ እና የህሊና እስረኛ እንደሚያዩአቸው ይታወቃል::