spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትወልዲያ፣ ቆቦ እና መርሳ የነበረው የሕዝብ ቁጣ (ክፍል አንድ) - ከብሩክ አበጋዝ

ወልዲያ፣ ቆቦ እና መርሳ የነበረው የሕዝብ ቁጣ (ክፍል አንድ) – ከብሩክ አበጋዝ

ከብሩክ አበጋዝ

ብሩክ አበጋዝ -
ጸሃፊው ብሩክ አበጋዝ
በሰሜኑ የወሎ ክፍል ህዝባዊ ተቃውሞ እና ቁጣ የተካሄደባቸውን ሁሉንም ከተሞች በሚገባ የማውቃቸው ናቸው፤ ባለፈው ክረምት በሥራ ጉዳይ በእነዚህ አካባቢወች በከተማው በገጠሩም በተዘዋወርኩበት ወቅት እግረ መንገዴን የማህበረሰቡን ፖለቲካዊ እሳቤ እና የወጣቱን የፖለቲካ ንቃት በቀጥታም ባይሆን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ታዝቤ ነበር። አሁንም ከአራት ወራት በኋላ የሼኹ አባ ጌትዬን በዓል ለማክበር መርሳ ከተማ ተገኝቼ ነበር፤ ቆቦ፣ አላማጣም ሄጄ ወልዲያ ላይ ከርሚያለሁ። አሁን ተመልሼ በሄድኩበት አጋጣሚ የነበረውን የማህበረሰቡን የፖለቲካ ሳስተውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆነው የፖለቲካው ግለት እና መንግስታዊ ተቃውሞው ማደጉ አስገራሚ ሆኖብኛል። እንደ እኔ ትዝብት ወጣቱ ማህበራዊ መገናኛወች በሚያቀርቡለት የተለያዩ ፖለቲካዊ መረጃወች ድሮ ከማውቀው በተለየ መልኩ የፖለቲካ ግንዛቤው ከመንደሩ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ ሁነቶችን ለመረዳት እና ለመተንተን ደረጃ ደርሷል።

ከዚህም በላይ ወጣቱ ኢህአዴግ በተለይም ደግሞ ህወሓት የሚያራምዳቸውን እኩይ የፖለቲካ እንቅስቃሴወች ከመረዳት አልፎ የሚበሳጭባቸው መሆኑና ራሱን ክፉ በማይሰጥበት መልኩ የህወሓት/ኢህአዴግን መንግስት በሚችለው አቅሙ ለመታገል የሚፈልግ ነገር ግን እምነት የሚጥልበት የሚያታግለው የፖለቲካም ድርጅት ያለመኖር እና በመንግስት በኩል ያለው አፈና መፈናፈኛ ያሳጣው መሆኑን ለመረዳት ችዬ ነበር። በዚህ ደረጃ ምሬት ያለበት ወጣቱ ክፍል የክለብ እግር ኳስ ጨዋታወችን ራሱን ሳያጋልጥ ምሬቱን እና ለመንግስት ያለውን ተቃውሞ በህብረት የሚገልጥበት ምቹ አጋጣሚወች ሆነውለታል። የሰለጠነ መንግስት ቢኖረን ኖሮ ከእነዚህ ዓይነት የተቃውሞ አጋጣሚወች የህዝቡን ስሜት ተረድቶ ተቃውሞውን ለማርገብ መፍትሄ ያፈላልግ ነበር፤ ነገር ግን እንዳ አለመታደል ሆኖ እብሪት እና ትዕቢት የተጣናወተው ህወሓት/ኢህአዴግ ስድብ እና ሰላማዊ ተቃውሞ ስልጣኑን የሚያሳጡት ይመስል የሰውን ድምጥ ለማፈን ሁሉ የሚሞክርበት አጋጣሚ በርካታ ነው።

የቅርብ ጊዜው ህዝባዊ ቁጣ እና ተቃውሞ ዋና መነሻ ምክንያት ባአለፉት 26 ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ ዘረኝነት እና አድሏዊነት የነገሠበት አምባገነናዊ አገዛዝ የፈጠረው ጥላቻ ሲሆን፤ በመቀጠልም ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት በጎንደር እና በጎጃም አካባቢወች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ከመቄት አካባቢ ውጭ ሌላው የዚህ አካባቢ ሰው በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ጥብቅ አፈና እና ቅድመ ዝግጅት ይኽ ነው ተብሎ የሚቆጠር እንቅስቃሴ በማድረግ በወቅቱ ለነበረው የህዝብ ቁጣ አጋርነቱን ባለማሳየቱ ቁጨት የነበረው መሆኑ ነው። ይሁንና ባለፈው ጊዜ ወልዲያ ላይ ሊካሄድ በነበረው የመቀሌ እና የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ ተከትሎ የመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥርዓት የጎደላቸው ደጋፊወች “አማራ” እያሉ የጅምላ ስድብ በመሳደባቸው እንዲሁም ደግሞ ከራያ/አላማጣ ጀምሮ ወልዲያ እስኪገቡ ድረስ በዋናው መንገድ ላይ ባሉ ከተሞች ያደረጉት ጋጠወጥ ተግባር ወልዲያ ከተማ ላይ ወደ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀይሮ የሰው ህይወት ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል።

በዚያን ወቅት በተፈጠረው ችግር የመቀሌ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊወች ጥቃት እንዳይደርስባቸው የመከላከያ ሠራዊት ሁሉንም ሰብስቦ ትልቅ ግቢ ወዳለው ላል ሆቴል አስገብቶ አድኗቸዋል። ነገር ግን ደጋፊወቹ መከላከያ ሠራዊቱን መከታ አድርገው ከላል ሆቴል ግቢ ውስጥ ሆነው ውጭ ላይ ወዳለው ሰው ድንጋይ እየወረውሩ ጉዳት ሲያደርሱ ነበር፤ ይኽን ሲያደርጉ በዙሪያቸው ያለው ወታደር ተው ብሎ አላስቆማቸውም ነበር (ይህን እብሪተኝነታቸውን የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ በእጄ አለኝ ጠንካራ የኢንተርኔት ኮኔክሽን ካለ መጫን ይቻላል)። የመቀሌ እግር ኳስ ደጋፊወች የላል ሆቴል ስላስጠለላቸውና ስለታደጋቸው ማመስገን ሲገባቸው በዚያን ዕለት የሆቴሉን የሚሰባበሩ ነገሮች በሙሉ አውድመው፣ በሁሉም አልቤርጎወች ውስጥ ገንጥለው በመግባት ያሉትን 31 inch flat screen TV በአልጋው ቁጥር ልክ ያሉትን፣ የታሸጉ ውድ የአልኮል መጠጦችን፣ ካሽ ሪጅስተር እና ደስክቶፕ ኮምፒውተር ሳይቀር ዘርፈው በመጡበት መኪና ጭነው ሄደዋል ይኼን ሲያደርጉም ዙሪያውን ከቦ የነበረው ወታደር ያደረገው ነገር አልነበረም።

ይኽ ከሆነ በኋላ በአዲግራት ዩኒቨርስቲ እና እዚያው ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ላይ በተፈጠረው ግድያ የውርጌሳው ተማሪ ከአዲግራት ዩኒቨርስቲ ሬሳው ተጭኖ ወደ ቀየው መንጣቱና እሱን ተከትሎ በአካባቢው የነበረው አመጥ ወጣቱ የነበረው ቁጣ ጨምሮታል። እንግዲህ እነዚህ ክስተቶች ከአለፉ በኋላ ወልዲያ ላይ በተገኘሁበት ወቅት ወጣቱ ያለ ፍርሀት መንግስትን ሲነቅፍ ሳይ ከዚህ በፊት የነበረው መንግስታዊ አፈና እና ፍርሀት በመጠኑ የተበረገደ እንደሆነ ተረድቻለሁ። እኔ ወልዲያ ከተማ በተገኘሁበት ወቅት ወልዲያ ላይ ሳይካሄድ የቀረው የመቀሌ እና የወልዲያ ክለቦች ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ አዲስ አበባ ላይ ተካሄዶ ወልዲያ የተሸነፈበትና ከዚህ ሽንፈት በኋላም የፌደራል ፖሊስ የወልዲያ ከተማ ደጋፊወች ከስታዲየሙ ሲወጡ እነሱን ነጥሎ ሆን ብሎ እንክትክታቸው እስኪወጡ የደበደባቸው ሲሆን፤ ሁኔታው ወልዲያ ላይ በተሰማ ጊዜ ወጣቱ በየቦታው እጅግ ከሚገባው በላይ ሲበሳጭ እና የእልህ እና የቁጣ ስሜት ሲያሳይ አይቻለሁ።

የወጣቱ ስሜት በዚህ ሁኔታ እንዳለ ጥምቀት ከመድረሱ ከቀናቶች በፊት ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት በላንድክሩዘር መኪናወች እየሆኑ ከባድ መሳሪያወችን መኪናወቹ ላይ አጥምደው በከተማው የተለያዩ መንገዶች እየተዘዋወሩ ህዝቡን ለማስፈራራት የሚያደርጉት ነገር በሙሉ ለሚመለከተው ሰው በሙሉ እጅግ የሚያበግን ነበር። ወንድሞቻችንን በአዲስ አበባ ስታዲየም ደብድበው ደግሞ እዚህ ምን ሊያደርጉን ነው የሚል ስሜትም በወጣቱ ላይ ነበር። የጥምቀት ዋዜማ ታቦቱ ሲወርድ የወታደሮቹ የእብሪትና ወዮላችሁ ዓይነት እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን በዚህ የተበሳጬ ሰወች ድንጋይ በመወርወራቸው የተመቱ ወታደሮች ነበሩ። ወዲያውኑ ማታም መናኸሪያ እና ጎንደር በር በሚባሉት ሠፈሮች ወጣቶች እየታፈኑ ወደ እስርቤት ተወስደዋል ይኽ ነገር ወጣቱን እንኳን ሊያስፈራራ ይቅር ቁጣውን የሚጨምር ሆኖ ነው የተገኘው። የጥምቀት የዕለቱ ዕለት ወጣቱ በጭፈራው ወያኔ ሌባ፣ የወያኔ ኑሮ ይለያል ዘንድሮ ወዘተ በማለት መንግስትን ከመስደብ ውጭ የተለየ ነገር አላደረገም።

በቦታው የተገኘ ማንም ሰው መረዳት የሚችለው አንድ ነገር ቢኖር የህወሓት/ኢህአዴግ አድራጊ ፈጣሪወች ቀደም ብሎ በነበረው በወልዲያው ግርግር እንደተበሳጩና የወልዲያን ወጣት ትዕቢት ለማስተንፈስ እና ዝም ለማሰኘት ወጣቱን በመተንኮስ የመከላከያ ሠራዊት ግድያ እንዲፈጥም እና የማያዳግም አስተማሪ እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል አቅደው እንደተንቀሳቀሱ ለመገንዘብ ይቻለዋል። እንደሚታወቀው የቃና ዘገሊላ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታወች አንዱ ወልዲያ ሚካኤል ነው፤ በግሌ ጎንደርም አዲስ አበባም አይቻለሁ ራስ ቢትወደድ ዓሊ ጓንጉል ያስተከሉትን የወልዲያውን ኩቢቃሉ ሚካኤል ያክል የሚደምቅ እና የሚከብር በዓል አላጋጠመኝም። እንግዲህ እነዚህ ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች ተልዕኳቸውን ለመፈጠም ይኼን ቀን የመረጡት ይመስለኛል፤ ቀኑን ባይመርጡት ኖሮና ባይተነኩሱ ኖሮማ ሰው ልክ እንደ ጥምቀቱ ስድቡን ተሳድቦ ያለምንም ችግር ወደቤቱ በተመለሰ ነበር።

እነዚህ እጅግ ደምን የሚያፈሉ ወታደሮች በበዓሉ ዕለት የሚያሳዩት ትዕይንት እና ትዕቢት የወጣቱን ስሜት እንዲገነፍል ለማድረግ ሆነ ብለው አቅደው ነበር። ወጣቱም አትከተሉን፣ ታቦታችንን እናስገባበት ሕዝባዊ ፖሊስ ይበቃናል እናንተ አታስፈልጉንም ቢላቸውም ይበልጡን በየጭፈራው ቀለበት ውስጥ እያስገቡ ትንኮሳቸውን ቀጠሉበት፤ ወጣቱም ስድቡን እና ተቃውሞውን እየጨመረ እነሱ ጋር እስከመገፋፋት ሲደርስ እነዚህ ወታደሮች ዕቅዳቸውን የሚፈጥሙበት ደረጃ ደረሱና አስለቃሽ ጭሳቸውን ሲተኩሱ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ። ጦማቸውን የነበሩት ታቦት ተሸካሚ ካህን በባዶ ሆዳቸው አስለቃሽ ጭሱ ሲተኮስባቸው እስከታቦቱ መሬት ላይ ተዘረሩ ወጣቱም ያገኘውን ነገር በሙሉ በመወርወር አጠፋውን መለሰ። ከዚህ በኋላ የሆነው ነገር ግድያ ነው፣ በየቦታው እንዲገድሉ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች በታዘዙት ቁጥር ልክ ገደሉ የሚደበድቡትን ደበደቡ።

ገብረመስቀል ጌታቸው ኃይሌ ከዚህ ግርግር ወደቤቱ ሲመለስ መናኸሪያ አቅራቢያ ላይ በእሱ የሚተዳደርን ትንሽ ልጅ ወታደር በዱላ ሲደበድበው ተወው ልጅ እኮ ነው ለምን ትደበድበዋለህ ብሎ ሊያግባባ ሲሞክር ግደል የተባለ ወታደር ቃታ ስቦ ጥይቱን አርከፈከፈበት። እስከ አራት ቀን ድረስ የፈሰሰው ደሙ ደርቆ ይታይ ነበር፤ አንዲት የመቻሬ እናት ልጇን ፍለጋ እሪ እያለች ወደ ከተማው ስትመጣ በጥይት ተቀብለው ገደሏት፣ ሌላው እንዲሁ ከእነሱ ጥይት ለማምለጥ ሮጦ ጣብቂያ ውስጥ ሲገባ ተከትለው የጥይት እሩምታ አወረዱበት፤ በተለያየ ቦታ የታዘዙትን የሚፈልጉትን ያክል ቁጥር ከገደሉ በኋላ ግድያቸውን አቆሙ። የገብረመስቀልን ሞት የሰማ ወጣት ሁሉ እንደ አራስ ነብር ሆኖ ተነሳ፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ንኪኪ ያለው አካል ላይ ትግሬ/አማራ ሳይል እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ነገሩን ይበልጥ ያጋጋለው በወጣቱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው የገብረመስቀል ሞት ሲሰማ ነው።

ከዚህ ላይ ማለት ያለብኝ ነገር ቢኖር በእነዚያ ቀናት ወልዲያ ላይ ህዝቡ በቁጣ የወሰደው እርምጃ ዘርን ትኩረት ያደረገ አልነበረም። ዳንኤል ብርሃነ የሚሉት የህወሓት ልጅ ያሁሉ ሰው ሞቶ ነፍስ መጥፋቱ ሳያሳዝነው የትግሬዎች ንብረት ወደመ በማለት ነገሩን አቅጣጫ አስቀይሮ ሲያራግብ እንደነበረ ነገሩ ያበገነው ወዳጄ ነግሮኛል። ይኼንን የእሱን እኩይ የሴራ ፖለቲካ ማስቀየሻ በሚደግፍ መልኩም ኮልኮሌ መንጋ ተቆርቋሪ ነን ባዮችም ጉራ ሲነዙ እና ትግሬ እንዲህ ሆነ ትግሬ እንዲህ ደረሰበት ሲሉ እንደነበር አሁን ሰምቻለሁ። በወልዲያው ግርግር የትግሬ ንብረት ወድሟል፣ የአማራ ንብረት ወድሟል። ለአብነት ምሳሌ መስጠት ይቻላል ደብረገሊላ/ፒያሳ ላይ አርሴማ ሆቴል፣ መቻሬ የአህመድ ሆቴል እና በጀርባው ያለ የፈታት የሚስቱ የአልማዝ ሆቴል እንዲሁም ገነተ ልዑል ሆቴል በረድፍ ያሉ ታዋቂ ከሆኑ ሆቴሎች የሚጠቀሱ ናቸው። ገነተ ልዑል እና አርሴማ ሆቴል ሁለቱ ባለቤቶቻቸው ትግሬ ሲሆኑ የአህመድ መቻሬ ሆቴል እና በጀርባው ያለው የፈታት ሚስቱ የአልማዝ ሆቴል ንብረትነታቸው ሁለቱም የዚያው አካባቢ ሰወች ናቸው። የአካባቢው ሰዎች የሆኑት የመቻሬ ሆቴል እና የአልማዝ ሆቴል እንዲሁም አርሴማ ሆቴል የሚባለው የትግሬው እና ከደርግ ዘመን ጀምሮ ለህወሃት መረጃ ሆኖ ሲያገለግል መኖሩን የሰማሁት የኪዳነ ካህሳይ ሆቴል ቃጠሎ ሲደርስባቸው ከኢህአዴግም ሆነ ከህወሓት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው እና ልጆችን ጭምር ለአካባቢው ሰው አጋብቶ አካባቢውን መስሎ የሚኖረው የሌላኛው ትግሬ (ካልተሳሳትኩ ስሙ ብርሃኔ ይመስለኛል) ሆቴል የሆነው ገነተልዑል ሆቴል ግን ቅንጣት ታክል አልተነካም። እነዚህ ተርታውን ያሉ ሆቴሎችን እንደምሳሌ ያስቀመጥኩት የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ለመግለጥ በቂ ናቸው ብዬ ስላሰብኩ ነው እንጂ የካቢኔወች ቤትም ተቃጥሏል፣ ሌላም ምሳሌም መጨመር ይቻላል።

የመቻሬ ሆቴል ባልተቤት ከዚህ በፊት በተፈጠረው ግርግር ወጣቶቹን እየጠቆመ ሲያሳስር ስለነበር እንዲሁም የእሱም ሆነ የፈታት ሚስቱ ሆቴል የብዐዴን ካድሬዎች መዋያ/መናኻሪያ/ እና ባለቤቶቹም አሸርጋጅ ስለነበሩ እና በዚህም እንደተጠቁ ሰምቻለሁ። በዚህ የህዝብ ቁጣ ንብረታቸው ላይ ጥቃት የደረሰባቸው የትግራይ ሰወች ከሁለት ዓመት በፊት ጎንደር እና ጎጃም ላይ ተቃውሞ በነበረበት ወቅት ተሰባስበው በአንድ ላይ ሆነው በወቅቱ የነበረውን ከንቲባ ምንም ሳይሆኑ ደህንነታችን በአስጊ ሁኔታ ላይ ነው ራሳችንን የምንከላከልበት ጦር መሳሪያ አስታጥቁን ብለው የጠየቁ እንደነበሩ እና የከተማው ወጣትም አንድ ነገር ሳይሆኑ እንደዚያ ዓይነጥ ጥያቄ ያቀረቡትና መሳሪያስ ለመታጠቅ የፈለጉት እኛን ለመፍጀት ነው ወይ በማለት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥርስ ነክሶባቸው ይኖር እንደነበር ሰምቻለሁ።

በሁለተኛው ክፍል ስለተገደሉት ሰወች ቁጥር፣ ማንነት፣ ስለ አቶ ገዱ እና ጳጳሱ ንግግር እና የሕዝቡ ቁጣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ በወልዲያ እስካሁን ስለሆነው ነገር እዳስሳለሁ፣ በሦስተኛው ክፍል የቆቦን እና የመርሳ ሁኔታ እዳስሳለሁ።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here