ቦርከና
የካቲት 5 2010 ዓ ም
ትላንት በሃማሬሳ ሃረር በሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ “መንግስት የሚገባውን ትኩረት አልሰጠንም፤ ለችግራችን አፋጣኝ መልስ እንፈልጋለን” በማለት ሰልፍ የወጡ ከኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በተፈናቀሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን ላይ የመንግስት ታማኝ ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ አስር ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እና እስከ አስራ አንድ የሚደርሱ ሰዎች እንደቆሰሉ በማህበራዊ ሚዲያ የወጡ መረቻዎች አመልክተዋል።
ከሟቾች ውስጥ አንደኛው የክልሉ ፖሊስ አባል መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከአካባቢው ምንጭ አለን በሚል መረጃ በማህበራዊ ድረ ገጽ እንዳጋሩት የመብት ተሟጋቾች ከሆነ ፖሊሱ የመከላከያ ሰራዊትን ጥቃት በመቃወም ሲታኮስ ነው የተገደለው።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከሃማሬሳ ጋር በተያያዘ የሟቾችን ቁጥር አራት ነው ያለ ሲሆን በሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ ባሉ ወጣቶች እና በፖሊስ እና መከላከያ በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ እንደተከሰተ አስታውቋል።
ምክንያቱን በሚመለከትም ወጣቶች ወደ ስደተኛ ጣቢያው ምግብ በማመላለስ ላይ የነበሩ የጭነት መኪናዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር መኪኖችን በማቃጠላቸው ነው ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ያሉ የመንግስት አፈቀላጤዎች ይሟገታሉ።
እንዲህ ባሉ ጉዳዮች በማህበራዊ ሚዲያ ፈጣን መረጃ በማካፈል የሚታወቁት የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ቅጤሳ እስካሁን በጉዳዮ ላይ ያጋሩት መረጃ የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት የተጠራው ህዝባዊ አመጽ በስራ ላይ ውሎ በክልሉ በተለያዮ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል፤ የህዝብ ማጓጓዣዎች ዝውውርም እንደተገታ ታውቋል። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሁኔታውን አምኖ “ምክንያቱን እያጣራ እንደሆነ” አሳውቋል።
———
ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።
ከኢትዮጵያ መረጃ ለማካፈል የምትፈልጉ በሚከተለው አድራሻ መላክ ይቻላል info@borkena.com