
ቦርከና
የካቲት 6 2010 ዓ ም
በኢትዮጵያ እየተከሄደ ያለው አመጽ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ሲይዝ መንግስት በቀለ ገርባን ጨምሮ ጥቂት የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ለቋል:: የገዢው መንግስት ዜና ማሰራጫ እንዳስታወቀው የፌደራል መንግስቱ ይቅርታ ቦርድ ይቅርታ እንዲደረግላቸው የመረጣቸውን ሰዎች ለፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አቅርቦ ካጸደቀ በኋላ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ሆነዋል::
አመጹ በብዙ ከተሞች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን አስተጏጉሏል፥ በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ከአዲስ አበባ እና ወደ አዲስ አበባ የሚደረግን ጉዞ ሙሉ በሙሉ በማስቆሙ መዲናዋ በአትክልት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንደተሰተዋለ የከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ::
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ጸሃፊ አቶ በቀለ ገርባ ምንም እንኳን የተከሰሱበት ወንጀል ክስ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ቢቋረጥም በክሱ ሂደት ወቅት ፍርድ ቤቱን ዘልፈዋል በሚል የስድስት ወር እስራት ተበይኖባቸው ነበር::
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና ለብሄራዊ መግባባት ሲባል የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን እለቃለሁ ካለ በኋላ አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት በመዳፈር ወንጀል የእስር ቅጣት ስለበየነባቸው ምናልባት በዚህ ሰዐት ላይፈቱ ይችላሉ የሚል ገምት በብዙዎች ዘንድ ነበር::
በአቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ ከነበሩት ባልደረቦቻቸውም አቶ ጉርሜሳ አያና ፤ አቶ አዲሱ ቡላላ ፤ አቶ ደጀኔ ጣፎ ፤ አቶ ጌቱ ጋሩማ ፤ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ አብረው እንደተፈቱም ታውቋል::
ሆኖም አሁንም ቢሆን ቁጥራቸው ከተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች የሚበልጥ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በእስር ላይ እንዳሉ ራሳቸው አቶ በቀለ ገርባ ከተፈቱ በኋላ ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል::
የፈረሰው የአድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ጸሃፊ የነበረው አቶ አንዱዓለም አራጌ ፤ ክንፈሚካኤል ደበበ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በተመሳሳይ አንዲፈቱ ተወስኖ የነበረ ሲሆን መንግስት እስር ቤቱን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት የግንቦት ሰባት አባል ነን ብላችሁ ፈርሙ የሚል ቅጽ አንዲፈርሙ በማቅረቡ ምክንያት አንፈርም በማለት ሳይወጡ ቀርተዋል::
የክንፈሚካኤል ደበበ እናት ልጃቸው ከእስር ባይለቀቅም ፈርም የተባለውን ቅጽ ባለመፈረሙ የተሰማቸውን ደስታ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ተናግረዋል::
አቶ በቀለ ገርባ እና ጓደኞቻቸው የኦነግ አባል ነን ብለው እንደፈረሙ እና አንዳልፈረሙ ያልታወቀ ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ እንደዚያ አይነት ቅጽ ፈርመው ይወጣሉ የሚል ግምት ግን የለም::