ቦርከና
የካቲት 7 2010 ዓ. ም
ትላንትና በቀለ ገርባ እና ጓደኞቹ ከእስር መፈታታቸው ይታወቃል:: በዛሬው ዕለትም መንግስት ተጨማሪ ሰባት መቶ አርባ ስድስት የፖለቲካ እስረኞችን ፈቷል::
ማሙሸት አማረ ፤ አንዱዓለም አራጌ ፤ እስክንድር ነጋ ፤ እማዋይሽ ዓለሙ ፤ ክንፈሚካኤል ደበበ ከተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ ይገኙበታል::
በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በር ተሰባስበው ለተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ደማቅ አቀባበል አድርገዋል::
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሰላማዊ ትግሉን እንደሚቀጥል ወኔ እየተናነቀው ለደጋፊዎቹ ተናግሯል:: እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም ጌታቸው መንግስትን በኃይል ለመጣል አሲራችሁአል በሚል የሃሰት ውንጀላ የአስራ ስምንት እስራት ተፈርዶባቸው ለሰባት ዓመታት ያህል በግፍ መታሰራቸው ይታወቃል::
ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ከነ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው ብዙ ግፍ እና መከራ ተቀብለዋል:: የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጂት አመራር የሆኑት ማሙሸት አማረ ለበርካታ ዓመታት ሲታሰሩ እና ሲፈቱ የቆዮ ሲሆን ዛሬ በመፈታታቸው የተለየ ደስታ እንዳልተሰማቸው እና ደስተኛ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ ሲሆን መሆኑን ተናግረዋል::
የፖለቲካ እስረኞቹ የተፈቱት መንግስት በታህሳስ ወር የ”ዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት” እና “ለብሔራዊ መግባባት” እስረኞችን እለቃለሁ በማለት ካሳወቀ በኋላ ነው፥፥ ሆኖም አሁንም ቢሆን እነ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች አልተለቀቁም::