ከአኦትይፕ (ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት)
የካቲት 10 2010 ዓ ም
አሁን አገሪቷ ትተዳደርበታለች በሚባለው ሕገ መንግስት አንቀፅ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛው ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል ይላል። በሕገ መንግስቱ መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅበት ምክንያትንም የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፤ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብ ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት ነው ይላል። በዚህ ወቅት ምንም የሕዝብንና የአገርን ደህንነት የሚፈታተን ሁኔታ በሌለበትና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች አደባባይ ወጥቶ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ በሆነው ክስተት ንብረት ሳይወድም፣ የሰው ህይወት ሳይጠፋና ሰላም ሳይደፈርስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ህወሃት ላይ ያለውን ተቃውሞ በማሳየት ሕዝቡ ሰላማዊ መሆኑን ባረጋገጠበት ወቅት፤ በዚህ ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዮ ከተሞች አደባባይ በመውጣት ጀግና ታጋዮቹን ከአስከፊው የህወሃት እስር ቤት ነፃ በመውጣታቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ደስታውን በሚገልፅበት ጊዜ እና በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርሃትን አሸንፎ በሰለጠነና በሰላማዊ በሆነ መንገድ ሀሳቡን መግለፅ በጀመረበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ማለት የሕዝቡን ሰላማዊ ትግል ለመጨፍለቅ፤ የሕዝቡ የደስታ ስሜት ወደ ሀዘን ለመቀየር እና ሕዝቡን እነደገና ወደ ፍርሃት ውስጥ ለማስገባት የታለመና የህወሃትን የበላይነት ለማስቀጠል የታለም ተንኮልና ሴራ እንጂ ከአገር ደህንነት ጋር በምንም መልኩ የተያያዘ አይደለም። በተቃራኒው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአገሪቷ ደህንነት አስጊ የሚሆንና የሕዝቡን የሰላማዊ ትግል ወደ አመፅ ትግል እንዲቀየር የሚገፋፋ እንጂ አገሪቷን ወደተረጋጋ ሁኔታ የሚወስድ በፍፁም ሊሆን አይችልም። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህወሃት ደህንነት አዋጅ እንጂ የአገር ደህንነት አዋጅ አይደለም። ስለዚህ ፓርላማው ይህ አዋጅ የአገሪቷን ደህንነት የሚጎድ፤ ሕገ መንግስቱን የሚፃረርና የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርስ መሆኑን በመገንዘብ፣ የህወሃት የበላይነትን ለማስጠበቅና የህወሃትን የግፍ አገዛዝ ለማስቀጠል ሲባል ብቻ የአገርና የሕዝብ ደህንነትን የሚጎዳ አዋጁ ማፅደቅ በፍፁም ተገቢ አይሆንም። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 54 ቁጥር 4 መሰረት የፓርላማው አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው። ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል። ማንኛውም የፓርላማ አባል በፓርላማ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም። አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድበትም።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ እየጠየቀ የሚገኘው የህወሃት የሃያ ሰባት ዓመት የግፍ፣ የዘረፋና አገርን የሚያፈርስ የበላይነት ተወግዶ አገሪቷ ወደ ተረጋጋ የፓለቲካ ሥርዓት ልትሸጋግር የምትችለው ፍትህ፣ እኩልነትና መከባበር የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን የመገንባት ሰላማዊና ወቅታዊ ጥያቄ ነው። ይህንን የሕዝብ ፍላጎትና ምኞት በመፃረር የቆመው ህወሃት ሲሆን፤ ህወሃትም አገርን እየዘረፈ፣ ሕዝቡን እያሰቃየና እያሸበረ አገዛዙን መቀጠል ነው የሚፈልገው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማም ይህንን የህወሃት የግፍና የዘረፋ አገዛዝ ለማስቀጠል የታለም ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሃት ግፍ ሞልቶ እየፈሰሰ በመሆኑ ከአሁን በኃላ ህወሃትንና ጀሌዎቹን ሊሸከም የሚችልበት ትዕግስትም ሆነ አቅም የሌለው ስለሆነ ከሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ውጭ የሕዝብን ሰላማዊ ጥያቄ በኃይል መጨፍለቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ ፓርላማው ለአገሪቷና ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል የሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባዋል። ይህ አፋኝ የሚሆነውና የህወሃትን የበላይነት ለማስጠበቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የታለመ የህወሃትን ተንኮልና ሴራን በማክሸፍ አገሪቷ ወደ ሰላማዊ ሽግግር እንድትገባ ፓርላማው ታልቅ አገራዊና ሕዝባው ሀላፊነት ተደቅኖበታል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆም እጅግ አስፈላጊ ነው። ፓርላማው ከሕዝብ ጎን በመቆም ታሪክ መስራት ይጠበቅበታል። የተጀመረውን የለውጥ መንፈስ ህወሃት ሊቀለብሰው በፍፁም አይችልም። ነገር ግን ፓርላማው ከሕዝብ ጎን በመሆን የሚከፈለውን የሕዝብ መስዋዕትነት በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል። አገሪቱም ወደ ተረጋጋ የፓለቲካዊ ሽግግር እንድትገባ የሚቻለውን ሊያደርግ ይችላል። የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግም ይገባዋል። ህወሃት የሕዝብ ጠላት በመሆኑ የህወሃት የአፈናና የግፍ አገዛዝ እንዳይቀጥል ፓርላማው የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይገባዋል። ከሕዝብ ጎን መቆም እንዴት እንደሚያስከብር በቅርቡ ከህወሃት እስር ቤት ነፃ ለወጡትን ጀግኖች ሕዝቡ እያደረገ ያለው አቀባበል ታላቅ ምስክር ነው።
የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማ በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በኦሮሞና በአማራ የፖለቲካ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው ያለፈ ታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድና በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን ጠንካራ ትብብር የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ነው።
የአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com
___
ማስታወሻ : ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com