spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካፀደቀ የህወሃትን ገመድ በአንገቱ ላይ በገዛ እጁ እንዳሰረ...

ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካፀደቀ የህወሃትን ገመድ በአንገቱ ላይ በገዛ እጁ እንዳሰረ ይቆጠራል

Ethiopian Parliament

ከአኦትይፕ (ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት)
የካቲት 18 2010 ዓ ም

በፒዲኤፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህወሃት የወታደራዊ አገዛዝ አዋጅ ማለት። እንኳን የሰው ልጁ እንስሳትም ቢሆኑ አንገታቸው ላይ ገመድ ሊታሰር ሲል በፀጋ አይቀበሉም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላ ኢትዮጵያውያን ያልተደገፈና ከውጭ አገራትም ሆነ ከአለም አቀፍ ድርጅቶችም ጠንካራ ተቃውሞ የተነሳበት መሆኑ በሚገባ ይታወቃል። የአዋጁ ዋና ዓላማ ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ የተነሳበትን ተቃውሞ ለመጨፍለቅ፤ በኦህዴድና ብአዴን እየተነሳ ያለውን የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ትግልን ለማጨናገፍ፤ ኦህዴድና ብአዴን የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ ከክልላቸው ሕዝብ ጋር ተቀራርበው ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ እና ለህወሃቶችና ለሸሪኮቻቸው አገሪቷን የመዝረፍ ዘመቻቸውን በስፋት የሚቀጥሉበትን መንገድ ለማረጋገጥ ነው። ይህ አዋጅ የአገር ወይም የሰፊው ሕዝብ ደህንነት አዋጅ ሳይሆን የጥቂቶችን የበላይነት ለማስጠበቅ የታለመ አዋጅ ነው። ምክንያቱም በቅርቡ እንኳን እንደተረጋገጠው የፌደራል የፀጥታና የመከላከያ ኃይል በማይኖርበት ጊዜ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉንም ይሁን ተቃውሞውን አሳይቶ በሰላም ወደ ቤቱ እንደሚመለስ በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች በግልፅ የሚታወቅ ነው። በአብዛኛው ረብሻና ግጭት የሚቀሰቅሰው የአጋዚና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች በሚያዳርጉት ግድያና ትንኮሳ ምክንያት ነው።

ያለምንም ጥርጣሬ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህወሃትን የዘረፋና የግፍ አገዛዝ ለማስቀጠል የታለመ ነው። ህወሃት ከዚህ በፊት እንደለመደው ብአዴንና ኦህዴንን በመጠቀም የበላይነቱን የሚያስጠብቅበት የፖለቲካ ቁማርና ጫወታ መቀጠል ባለማቻሉ አሁን ወታደራዊ አቅሙን በመጠቀም የበላይነቱን ለማስጠበቅ ነው። ይህንን ህወሃትና የህወሃት የጦር አለቆቹ ከፈለጉ በቀጥታ ያድርጉት እንጂ ፓርላማውን መጠቀም አይኖርባቸውም፤ ወታደራዊ አገዛዙ በግልፅ እንዳይወጣ ፓርላማው ሽፋን ሊሰጥ አይገባውም። በአለማችን ታሪክ የወታደራዊ አገዛዝ እንዲመሰረት የወሰነ ፓርላማ ቢኖር አንድ ብቻ ነው። እሱም እኤአ በ1933 የጀርመኑ ሬችስታግ የናዚ ፓርቲ ጀርመንን በወታደራዊ አገዛዝ ስር እንድትሆን ለሂትለር የሰጠው ድምፅ ነው። ይህም በአለማችን ላይ ያደረሰውን እልቂትና ጥፋት ሁልም የሚያውቀው ነው። በኢትዮጵያም ፓርላማው ይህንን የእልቂትና የጥፋት መንገድ ለህወሃቶች ለማፅደቅ ድጋፉን በእጁ ከሰጠ፤ ከአሁን በኃላ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ለሚፈሰው ደምና ለሚደርሰው ጥፋት የፓርላማው አባላቶች ቀጥተኛ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ምንም ሊያጠራጥር አይገባም። ሕዝብን ጨፍጭፉ ብሎ ሕግ ማፅደቅ ታላቅ ወንጀል ነው። በታሪክ እንዳየነው በግፍ ሕዝብ በሚጨፈጭፍበት ወቅት ከጨፍጫፊው ተኳሽ ወታደር በላይ ጭፍጨፋው እንዲፈፀም ሕግ ያወጣውና ትእዛዝ የሰጠው ዋና ተጠያቂ ነው።

የህወሃት ዓላማ በጣም ግልፅ ነው። ህወሃት በተግባር እያደረገ ሆነ እያቀደ ያለው የፓለቲካ ምእዳሩን ለማስፋት ሳይሆን እንዴት የፖለቲካ ምእዳሩን የሚያጠብበትንና የሕዝቡን፣ የብአዴንና የኦህዴድን ተቃውሞ የሚጨፈልቅበት ዘዴ ነው። ህወሃት ምንም የዓላማና የአቋም ብዥታ የለበትም። ህወሃት ዓላማውን ጠንቅቆ የሚያውቅና ለዓላማውም በፅናት በቡድንና በግለሰብ የሚሰራ ድርጅት ነው። በቅርቡ አባይ ፀሃይ እንደተናገረው በእኩል ተጠቃሚነት ላይ ስምምነት ከማድረግ ኢህአዴግ ቢፈርስ እንደሚሻል የህወሃትን አቋም ሳይደብቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ አድርጓል። ህወሃት የበላይነቱን ለማስጠበቅ የማይፈነቅለው ዘዴ የለም። ማታለል፣ መለመን፣ ማጭበርበር፣ መደለል፣ ማስፈራራት፣ ማሰር፣ ማሰቃየትና መግደል የታወቁ ዘዴዎቹ ናቸው። ይህ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፖለቲካ ምእዳሩን ለማስፋት ይጠቅማል ብሎ የሚያስብ የፓርላማ አባል ካለ፣ ከእንስሳቶች የተሻለ ደመ ነፍስ የሌለው ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ ምእዳር የሚሰፋው ሕዝብን በማስፈራራትና አገርን በሙሉ እስር ቤት በማድረግ አይሆንም። ይህ ሂትለር የናዚን የፋሺዝም አገዛዝ ለመመስረት የሄደበት አይነት መንገድ ነው። ሰው ላይ መሣሪያ ደግኖ ነፃ ውይይት ማድረግ አይቻልም። በእስር ያለ ሕዝብ የፖለቲካ ምእዳር ለማስፋት የሚያስችል ነፃ ውይይት ለማድረግ አይችልም።

በቅርቡ በግፍ ታስረው ለተፈቱ ለነበሩ ታጋዮቹና ጀግኖቹ ሕዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድጋፉን ያሳየበትና አቀባበሉን ያደረገበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ሚዲያዎቻና በዲፕሎማቶች ዘንድ እጅግ የተደነቀና የተዘገበ ጉዳይ ሲሆን፤ ህወሃትን ደግሞ በአለም አቀፍ መድረክ እርቃኑን ያሰቀርው ጉዳይ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አንዱ ዓላማም ይህንን ህወሃትን በአለም አቀፍ ደረጃ እርቃኑን ያስቀረውን ዓይነት የሕዝብ ተቃውሞ በግልፅ እንዳይታይ ነው። ነገር ግን ከአሁን በኃላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርሃት ለህወሃት የማይገዛበት ደረጃ ላይ የደረሰ ስለሆነና ሰላማዊ ተቃውሞውንም የሚቀጥል በመሆኑ ፓርላማው ህወሃት ሕዝቡን እንዲጨፈጭፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማፅደቅ ታላቅ ወንጀልና ፀረ – ሕዝብ ድርጊት ይሆናል።

የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማ በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በኦሮሞና በአማራ የፖለቲካ ልዒቃንና አክቲቪስቶች መሀከል የሚደረገው ያለፈ ታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድና በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃንና አክቲቪስቶች በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን ጠንካራ ትብብር የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። በመተሰሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሰረት ትብብርና አንድነት ቀጣይ፣ እውነተኛና ጠንካራ ኃይል ይሆናል። ተያይዞ ከመውደቅ ተያይዞ መነሳት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይበጃል።

የአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com
___
ማስታወሻ : ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com , info@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here