ቦርከና
የካቲት 23 2010 ዓ ም
አፍቃሪ ህወሓት በመባል ከሚታወቁት ዜና አውታሮች አንዱ የሆነው ፋና ብሮድካስቲግ ዛሬ በሰበር ዜና እንደዘገበው ለአንድ ወር ያህል እረፍት በመውሰድ ላይ እያለ “ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል” ተዘጋጂቷል የተባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለማስደቅ አስቸኳይ ሰብሰባ የተጠራው ፓርላማ ረቂቁን አጽድቆታል ብሏል።
እንደ ፋና ዘገባ “ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) መሰረት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በምክር ቤቱ ከተገኙ 490 አባላት መካከል በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ታእቅቦ አፅድቆታል።”
በሌላ በኩል ምንጭ ባላቸው ወገኖች በማህበራዊ ሚዲያ በወጣው መረጃ መሰረት መንግስት (ኮማንድ ፓስቱ እንደማለት ነው አሁን ባለው ሁኔታ) አዋጁን ለማስጽደቅ የሚያስፈልገውን ሁለት ሶስተኛ ድምጽ አላገኘም።
ፓርላማው 547 አባላት አሉት። ከዚህ ውስጥ ፋና እንዳቀረበው ሳይሆን 106 ያህሉ አባላት አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው ስብሰባ ላይ አልተገኙም። 88 አባላት ረቂቂ አዋጁን ባለመቀበል የተቃውሞ ድምጽ ሰጥተዋል። 7 አባላት ደሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል። የዚህ ስሌት የሚያሳየው አዋጁን ለማጽደቅ የሚፈለገው ሁለት ሶስተኛ ድምጽ እንዳልተገኘ ነው።
ሆኖም መንግስት የፈለገውን ረቂቅ በፈለገበት ሰዓት ያለምንም ተቃውሞ ህግ ያወጣ በነበረበት ፓርላማ ህዝብ የተቃወመውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ ህግ ላለማጽደቅ 88 የተቃውሞ
ድምጽ መሰጠቱ በራሱ ያልተለመደ እና በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለውን ስር የሰደደ ልዮነት የሚያመላክት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።
———
ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።