ቦርከና
በመስከረም አበራ
መጋቢት 15 2010 ዓ.ም.
እድል ቀንቷት ራመድ ካለ ቤተሰብ ተፈጥራ ማህበረሰቡ ከመደበላት የመታየት እጣ ፋንታ አፈንግጣ እውቀትን ከሻተች፣እሱም የተሳካላት እንደሆነም መሰናክል አያጣትም፡፡ከመሰናክሎቿ አንዱ ይካድ ዘንድ የማይቻለውን ስኬቷን አሳንሶ ማየት፣እውቅና አለመስጠት ነው፡፡ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም ጭምር ሴት የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ከወንድ ጓዶቻቸው እኩል እየሰሩ እኩል የማይከፈልበት ሃገር እስከዛሬ አለ፡፡ የፊውዳሉ ስርዓት ከዓለማችን ሲወገድ ሁሉም የሰው ልጆች መሪዎቻቸውን የመምረጥ መብት ይኑራቸው ሲባል የዚህን መብት እፍታ ያጣጣሙት ወንዶች ነበሩ፡፡ሴቶች ከወንድ እኩል መሪዎቻቸውን ለመምረጥ ሌላ ሴታዊ ትግል ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በዚህ በኩል ሃገሬ ኢትዮጵያ አትታማም- ሴትን ምርጫ እንዳትመርጥ የሚከለክል ህግ አልነበረምና! በመንግስት ፔሮልም የሴት እና የወንድ ደሞዝ ብፌ በታሪክ አልተመዘገብ፡፡
ሆኖም በግል አሰሪዎች ዘንድ እንዲህ አይነት የሴት ሰራተኛን ክፍያ የማሳነስ አካሄድ የለም ማለት አይደለም፡፡ በደንብ አለ! ሴቶችን በአምስት ብርም ሆነ በአስር ብር አሳንሶ መክፈል የሚጎዳው ኪስን ሳይሆን አእምሮን ነው፡፡ በተግባር እንደማታንሰው ልቦናው እያወቀ፣የምታበረክተውም ከወንድ ቅጥሮቹ ያነሰ እንዳልሆነ ልቦናው እየነገረው የሴቷን ክፍያ በሽራፊ ሳንቲም አሳንሶ እሱና የጾታ መሰሎቹ እንደሚበልጧት ምስክር ሊያደርግ የሚሞክር አሰሪ ራሴ ገጥሞኝ አይቻለሁ፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብየ ሙግት መግጠሜ አልቀረም፤ ማን ነገሬ ቢለኝ! ጭራሽ በሰው በምጠላው ገንዘብ ወዳድነት ተከስሼ ቁጭ ….! እንዲህ ያለው የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ያለው ሰው የአደባባይ ስሙ “የሰብዐዊ መብት ተሟጋች” ሆኖ ስሰማ ከሳቄ ጋር ያታግለኛል!
ሌላው ሴቶችን የማሳነሻ ዘዴ ለስራቸው በከፊል ወይም በሙሉ እውቅናን መንፈግ ነው፡፡ ይህ እንደ ጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር የህግ አንቀፅ ጠቅሰውለት በወንጄል የማይከሱት ወንዳወንዱ አለም የሴቶችን ችሎታ የሚያዳፍንበት ረቂቅ ልማድ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት ወንዶች ብቻ አይደሉም ሴቶችም ጭምር እንጅ! እንዴውም ሴት ለሴት ያለውን ችግር ቢፅፉትም የሚያልቅ አይመስለኝ፡፡ ወንዶች ሁሉ የሴት ሥራ ያዳፍናሉ ማለትም አይደለም፡፡ ስልጣኔ ከፀጉራቸው እና ከልብስ ጫማቸው አልፎ ልቦናቸውንም የጎበኘው፣ በጥልቅ ያነበቡ፣ ከመጠምጠም እውቀት ያስቀደሙ፣ከማወቃቸው የተነሳ ራመድ ያሉቱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለጥሩ ስራ ሁሉ እውቅና ይሰጣሉ፡፡የሰራችው ሴት ስትሆን ደግሞ ስንቱን መሰናክል አልፋ እዚህ እንደ ደረሰች ያውቃሉና ለስራው ያላቸው ክብር ይጨምር ይሆናል እንጅ አይቀንስም፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ የሃገሬ ሰዎች እንዳሉ በጣም አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ያረጄውን አስተሳሰብ ለማሸነፍ የሞራል ስንቆችም ጭምር ናቸው፡፡
ወደ አዳፋኞቹ ስንመጣ ያልሰለጠነው ጭንቅላታቸው ከሴት የማይጠብቀውን ስኬት ሴት ልጅ ስታስመዘግብ ካዩ የሚያዩዋትን እሷን ትተው ከጀርባዋ ለስራው ባለቤት የሚሆን ስውር ወንድ ይፈልጋሉ – እከሌ ሰርቶላት ነው፣ እንቶኔ አግዟት ነው፣ እንትና አስገብቷት ነው ሲሉ የወንድ ሞግዚትነት ያማትራሉ፡፡ ግፋ ሲልም በግልፅ እንደማትችል ይነገራታል፡፡ በዚህ አንፃር በግሌ የገጠመኝን ሁሉ ባነሳ ወርዶ ያወርደኛልና አንዱን ብቻ እንደማሳያ ላንሳ፡፡ ከሶስት አመት በፊት ስልኬ የማላውቀውን ሰው ስልክ ቁጥር እያመላከተኝ ሲያቃጭል አፈፍ አድርጌ “አቤት” ስል እኔ ወደምኖርበት ከተማ ከጓደኞቹ ጋር መምጣቱን እና ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ አንድ የወንድ ድምፅ ሲነግረኝ “ስልኬን ከየት …” ብየ ሳልጨርስ “ስልክሽን የሰጠን እንትና አጠገባችን ደውሎልሽ ነበር ረሳሽ?” ሲለኝ “እሽ ይቅርታ! አስታዎስኩ በቃ ነገ ይሻላል” ብየ በማግስቱ አገኘሁዋቸው፡፡ ስለሃገራችን ፖለቲካ አውርተን ፣አንዳንዴ የምጫጭራቸውን ነገሮችም እንደሚያነቡ ነግረውኝ፣በርቺ ግን ተጠንቀቂ የሚል የበጎ ሰው ምክር ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡
ከአንድ ሁለት አመት በኋላ ከመሃላቸው አንዱን በሆነ አጋጣሚ አግኝቸው ስንጨዋወት እኔ አምደኛ ሆኜ ከምፅፍበት መፅሄት ውስጥ የሚጽፉ ሰዎች እየጠራልኝ የምንስማማባቸውን አብረን ስናደንቅ በማልስማማባቸው ልዩነቴን እየገለፅኩ ስንጫወት ቆየንና በስተመጨረሻ የሁሉንም አምደኞች ፅሁፍ ሲያነብ የኔን ፅሁፍ ነገሬ ብሎ ተመልክቶት እንደማያውቅ ነገረኝ፡፡ እኔም “እኔኮ የምፅፈው እንደ አንተ መርጠው ለማያነቡ፣ ጊዜ ለተረፋቸው አሰሱንም ገሰሱንም ለማያልፉ ነው፡፡አንተማ መቼ አዳርሶህ የእኔን ዝባዝንኬ ታነባለህ” ብየ መከፋቴን ለማየት ፊቴ ላይ የሚሯሯጡ አይኖቹን ደስታ ነፈግኳቸው፡፡ ነገሬ ቀልድ እንዳልሆነ ሁለታችንም ብናውቅም ቀልድ አስመስለን ሳቅንበት እና ወደ ሌላ ጨዋታ አለፍን፡፡ በጨዋታ መሃል “ባለፈው ሳምንት የፃፍሽው ፅሁፍ ግን ሴት የፃፈው አይመስልም” ሲል መልሶ ወደማዳፈን ስራው ገባ:: አሁንስ በዛ ! “ፅሁፌን አንብበህ እንደማታውቅ ነግረኽኝ ነበር፤ነው ያነበበ ነገረህ?” ብየ በነገር ወጋ አደረኩትና “ሴት የፃፈው መልኩ ምን አይነት ነው?!” አልኩት ንቀቴን መደበቅ እያቃተኝ፡፡ እሱ ድንግጥ እኔ ፈርጠም …. ! ሌላ ረዥም ሳቅ ! “አንች አትቻይም ከሚያዋሩሽ ፅሁፍሽን ማንበብ ይሻላል” ሲለኝ፤ የአፉን ሳይጨርስ “አዎ ሲያሳንሱኝ አልወድም!” አልኩኝ ሳቄን አባርሬ እውነተኛ ስሜቴን እየገለፅኩ፡፡በዚሁ ተለያየን፤ከዛ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም፤ ወደፊትም የምንገናኝ አይመስለኝም በኔ በኩል፡፡
ይህ ወዳጄ እንዲህ የሚቸገረው በግሉ ክፉ ሰው ስለሆነ ላይሆን ይችላል፡፡ ይልቅስ እሱ የለመደው የወንድ ቦታ ላይ ሴት የተቀመጠ ስለመሰለው የሆነ “የተዛባ” ነገር ይታየዋል፡፡የተዛባው ነገር እረፍት ነስቶታል፡፡ ይህ ሁሉ የመጣው ደግሞ ከኖርንበት ስርዓት ነው፡፡ የኖርንበት ስርዓት የተገመደው ደግሞ ሴትን ማየት ወንድን መስማት ከመውደድ ነው፡፡ መታየት አለባት ተብላ የምትታሰበዋ ሴት መናገር ከጀመረች መሰማት ያለበትን ወንድ ቦታ ያጣበበች፣ ህግ ያፈረሰች የሚመስለው ብዙ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መፈንቅለ-ፆታ የተደረገበት ይመስለውና በወንበሩ የተቀመጠች ለመሰለችው ሴት በጎ እይታ አይኖረውም፡፡ በቀላሉ የምትወድቅ አይነት ከሆነች በንቀቱ፣በማሳነሱ እና በማዳፈኑ አጣድፎ ሊጥላት መመኘቱም መሞከሩም አይቀርም፡፡ ይህን ስሜት ያልሰለጠኑ ወንዶች ሁሉ ይጋሩታል፡፡ በነገራችን ላይ ያልሰለጠኑ ወንዶች ማለት ዲግሪ ያልደራረቡ ማለት አይደለም፡፡ ተምረው ያልሰለጠኑ በርካታ ናቸው፡፡ ሳይማሩ የሰለጠኑም እንደዛው፡፡ እና ጉዳዩ የመማር ያለመማር ነገር አይደለም፡፡ ያልሰለጠኑ ወንዶች የሴቶችን ስራ ለማዳፈን ሲተጋገዙ ቢጤዎቻቸው ሴቶችም ያግዟቸዋል እንጅ “ነግ በኔ” ብለው ላለመውደቅ ከምትታገለዋ ሴት ጎን አይቆሙም፡፡ይህ ብዙ ያልተወራለት የሴቶች ፈተና ነው!
ጸሃፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል meskiduye99@gmail.com
__
ማስታወሻ: ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena ወይንም
editor@borkena.com ይላኩልን