spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየትየኦህዴድ ጉዞ ስንክሳር (በመስከረም አበራ)

የኦህዴድ ጉዞ ስንክሳር (በመስከረም አበራ)

- Advertisement -

በመስከረም አበራ
መጋቢት 24 2010 ዓ.ም.

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ
ህወሃት አንጉቶ ከጋገራቸው አጋር እና አባል የብሄር ፓርቲዎቹ ውስጥ እንደ ኦህዴድ አጉረምራሚ የለም፡፡ “የማይገሰስ የማይደፈር” አምባገነንነት ላይ ደርሶ የነበረውን የአቶ መለስ ዜናዊን ጠንካራ ክንድ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሃይ” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ከኦህዴድ ወገን ናቸው፡፡መቃለል መናቁ የሰለቻቸው ዶ/ር ነጋሶ ስልጣናቸው ቀርቶ ህይወታቸው ሊገጥመው የሚችለውን አደጋ ለመቀበል ቆርጠው ልክ የመሰላቸውን አድርገዋል፡፡ይህ የመጀመሪያው ኦህዴድ ለህወሃት የላከው የእምቢተኝነት መልዕክት ነው፡፡ ሆኖም ጌታን አንጓጦ በጌታ እልፍኝ መምነሽነሽ አይቻልምና ዶ/ር ነጋሶም ሁሉን ትተው ክብራቸውን ብቻ ይዘው ይኖራሉ፡፡

ከዶ/ር ነጋሶ ሌላ አቶ ሽፈራው ጃርሶ እና አቶ ጁነዲን ሳዶም “ድርጅቱ” እስከመባል ገዝፈው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ይጠየቁ ዘንድ የማይሿቸውን፣ካድሬ ሁሉ “ውሾን ያነሳ” ብሎ የተዋቸውን እንደ ኢፈርት ጉዳይ ያሉ አይነኬ አጀንዳዎች በህዝብ ዘንድ ምን ያህል እያነጋገሩ እንደሆነ አንስተው አቶ መለስን ቱግ ያደርጉ እንደ ነበር በኮብላይ ካድሬዎች ተፅፎ አንብበናል፡፡ ከምርኮኛ መኳንንት ነፃ የወጣው የአሁኑ ኦህዴድ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ይኖሩ የነበሩ ኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀል በጌታው ህወሃት ላይ ክፉኛ እንዲያመር ሳያደርገው አልቀረም፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስቆጣ ምን ቢክሱት የማይጋርዱት ክፉ ግፍ ነው!

ኦህዴድን ከጭቃ አቡክቶ እስትንፋስ እፍ ያለበት ህወሃት ቢሆንም ታሪክ የመዘገበው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እድሜ ከዚህ ዘለግ ያለ ነው፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ በብሄር ተደራጅቶ ማህበር አቋቁሞ ስለዘውጉ ለመምከር፣የዘውግ ብሄርተኝነትን መንፈስ ቆሜለታለሁ በሚለው ህዝብ ልቦና ለማስረፅ የኦሮሞው ሜጫ ቱለማ ቀዳሚው ነው፡፡ሜጫ ቱለማ ሄዶ ሄዶ ኦነግን ወለደ፡፡ኦነግ ደግሞ ስሜትን ከእውነት እደባለቀ በተበዳይነት ላይ የቆመ ሆደባሻ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን አጧጧፈ፡፡

በአካል በህወሃት የተነጎተው ኦህዴድም የዚሁ የኦነግ የተበድየ ፖለቲካ መንፈሳዊ ውላጅ ነው፡፡ይህ ነገር ነው አቶ መለስን በአንድ ወቅት “ኦህዴዶች ጀርባችሁ ቢላጥ ኦነግ ናችሁ” እስከ ማለት አድርሷቸው ነበር የሚባለው፡፡ኦህዴድ ብዙ ገንዘብ አፍስሶ የአኖሌን የቂም ሃውልት ያስቆመውም የኦነግ መንፈስ እንጅሌላ አይደለም፡፡ዛሬ ዋናውን የስልጣን እርካብ ለመርገጥ ዳርዳር ሲሉ ኢትዮጵያዊነትን ይሰብኩ የያዙት የኦህዴድ ካድሬዎች እነ ኦቦ ለማ መገርሳም የአኖሌን ሃውልት ከበው ፎቶ ከሚነሱት ወገን ነበሩ፡፡ከሜጫ ቱለማ ጀምሮ ስሩን የተከለው እና እያደገ የመጣውን የኦሮሞ ብሄርተኝትን ማንገቡ ለኦህዴድ ከሌሎች አቻ የኢህአዴግ ፓርቲዎች በተሻለ የብሄር ፖለቲካውን ብልት ለመረዳት ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ይህም በጎሳ ፖለቲካ ደቆንኩ በሚለው ህወሃት ላይ ኦህዴድ ቄስ ለመሆን መሞከርን እንዲደፍር አድርጎታል፡፡

የተሟላ አምባገነንነትን ጨብጠው የነበሩት አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት ኦህዴዶች ከመመኘት በቀር ጮክ ብለው ተናግረውት የማያውቁትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ዛሬ የጌታን ክንድ መዛል ተንተርሰው ከመመኘት አልፈው ጨብጠውታል፡፡ከኦሮሞ የተወለደ ሰው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና ሆኖ ማየት በኢህአዴግ እልፍኝ ያለውን ኦህዴድም ሆነ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን የኦነግ ስብርባሪ ፓርቲዎች፣ ግለሰብ አክቲቪስቶች በጋራ የሚወዘውዝ ብርቱ ናፍቆት ነው፡፡

አሁን የዶ/ር አብይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር መውጣት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሽው ያለበትን ሁሉ ልብ በደስታ እያዘለለ ነው፡፡የሃሳብ ብልጫ ሳይሆን የዘር ሃረግን ቆጥሮ ፖለቲካን ለሚቀምር ይህ በቂ የደስታ ምክንያት መሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ወንበሩ ምን አይነት ነው? ምን ሊያሰራ ይችላል? ወደ ስልጣን የመጡት ሰውየስ በምን አይነት ፖለቲካዊ ዳራ የሰነበቱ ናቸው? የሚለውን ለማጤን የብሄር ፖለቲካው የስሜት ፈረስ ፋታ አይሰጥም፡፡ይሄው የስሜት ፈረስ ለውጥን አጥብቆ የመሻቱን ያህል አጥብቆ መስራቱ ወደ ማይሆንለት፣ይልቅስ ለውጥን በቀላሉ እና በአቋራጭ ወደ ሚመኘው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውንም ሳይጋባ አልቀረምና ምኞትን እና እውነት ያላማጠኑ የሚመስሉ ትንታኔዎችን እንሰማ ይዘናል፡፡

የኦህዴድ የማርሽ ለውጥ

አብዛኛው ለውጥ ፈላጊ ዜጋ የአቶ ለማ መገርሳን ኦህዴድ የለውጥ ተስፋ ማድረግ የጀመረው ኦህዴድ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ የሚታወቅበትን የተበድየ ፖለቲካ ውላጅ የሆነውን የአግላይነት ስብከት ቀየር አድርጎ ድንገት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማቀንቀን በመጀመሩ ነው፡፡ይህ የማርሽ ቅየራ በሚገባ ተሰላስሎ የተደረገ ሳይሆን ፈጣን እና ድንገቴ ሆኖ ይሰማኛልና እንደወረደ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ጥርጣሬየን የሚያበረታው ደግሞ በአጠቃላይ ለኢህአዴግ አባልም ሆነ አጋር ድርጅት ካድሬዎች የግንዛቤ ደረጃ ያለኝ ግምት ነው፡፡ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የኢህአዴግ ካድሬዎች የፖለቲካ እምነታቸውን የሚያነሱትም ሆነ የሚጥሉት በነጠረ ሳይንሳዊ ግንዛቤ ላይ ተመርኩዘው አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ የኢህአዴግ ካድሬዎች ‘ምን ብል የበለጠ አተርፋለሁ?’ በሚል ስሌት ይመስለኛል ፖለቲካዊ መንገዳቸውን የሚነድፉት፡፡ይህ በኢህአዴግ ቤት መኖር የሚያመጣው አድርባይነት ወለድ ችግር ነው፡፡አድርባይነት የኢህአዴግ ካድሬዎች ዋና ምልክት ነው፡፡
የኢህአዴግ ካድሬ አድርባይነት ልማድ መጥፎ ገፅታው የአቋም ለውጥ ሲደረግ የአቋም ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት በአጥጋቢ ሁኔታ አያስረዳም፡፡ይህ የሚሆነው አንድም የቀድሞው አቋምም የሆነ ቀን አትራፊ ነገር ይዞ ሊመጣ ስለሚችል እርግፍ አድርጎ ለመተው ስለማይፈልግ ይሆናል ሁለትም ፖለቲካዊ ትርፍን ከማለም ባለፈ የአቋም ለውጡ ያነገበው አንዳች ሳይንሳዊ ግንዛቤ ስለሌለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት አቋም ቀይረናል ካሉ በኋላም ሳያውቁት የቀድሞው እምነታቸውን በንግግራቸው መሃል ሲደነቅሩ ያጋጥማል፡፡ለምሳሌ አቶ ለማ መገርሳ አዲሱን አቋማቸውን ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው ሲሉ የተናገሩት ከህዝብ ጆሮ ሳይወርድ በሁለት ሳምንቱ በኢህአዴግ ስራ አስፈፀሚ ስብሰባ ላይ መግለጫ በሚሰጡበት አጋጣሚ ደግሞ ‘ኢትዮጵያዊነት የተጫነብን ማንነት ስለሆነ ቀስ እያለ ነው በህዝቡ ውስጥ መስረግ ያለበት’ ብለው ቁጭ አሉ፡፡በምክንያት ለሚያምን ሰው ደግሞ ይህን አይነቱን የመገላበጥ እና ምክንያት አልቦ ስሜት ተከትሎ ለማጨብጨብ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡

የኢህአዴግ አድርባይ ካድሬዎች ሌላው ችግር ቀድሞ ያራምዱት የነበረው አቋም እና እምነት ላስከተለው ችግር ሃላፊነት ወስደው፤ለጥፋታቸው ይቅርታ ሳይጠይቁ ለሰሚ የሚያስደስት የሚመስላቸውን አዲሱን አቋም ልክ አብሯቸው የተወለደ ሃሳብ አስመስለው ማነብነባቸው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ ላይ ድንገት የኢትዮዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሱስ ወረደብኝ የሚለው የነለማ መገርሳ ቡድን ደርሶ አዲስ አቋም ማራመዱ ሃያ ስድስት አመት ሙሉ ከህወሃት ስር ስር እያለ ሲያራምደው የነበረው የጎሳ ፖለቲካ ላስከተው ሃገራዊ ኪሳራ ከህወሃት እኩል ተጠያቂ ከመሆን አያድነውም፡፡ ዛሬ አዲስ አቋም ማራመዱ እሰየው ቢያስብልም ከዚሁ ጎን ለጎን የቀድሞ አቋሙ ያመጣውን ጥፋት አምኖ፣ከህወሃት እኩል ተጠያቂ መሆኑንም አድምቆ አስምሮ ለጥፋቱ ሃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡

ለመስማት ደስ የሚለው እነ ኦቦ ለማ መገርሳ ደርሶ ወረሰን የሚሉት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሱስ በጭራሽ እውነት ሊሆን አይችልም ማለት ባይቻልም እውነት ነው ብሎ መቀበል የሚቻለው በተግባራዊ እርምጃዎች መታጀብ ሲችል እና የማይዋዥቅ የሁልጊዜ አቋም ሲሆን ነው፡፡ የሁልጊዜ አቋም መሆኑን ያተራጠረኝ አንድ መረጃ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ያለው የኦቦ ለማ መገርሳ አንደበት መቼት ቀይሮ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ጭነት ነው ሲል በጆሮየ መስማቴ ነው፡፡ይህ ነገር ከኢህአዴግ ካድሬዎች ተገላባጭ አድርባይነት ጋር ሲደመር የተባለን ሁሉ ዝም ብሎ ከማመንም ጭልጥ አድርጎ ከመጠራጠርም ቆም ብሎ መመርመሩ እንደማይከፋ ያመላክታል፡፡

የኦህዴድ የማርሽ ለውጥ ሌላ መገለጫ በኢትዮጵያ ታሪክ የኦሮሞን ህዝብ ቦታ ወይ የሁልጊዜ ተበዳይነት አለያም የመገለል ብቻ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርበውን ሲደጋገም እውነት የመሰለ የኦነግ ተረክ የሚያናጋ አቋም ማራመዱ ነው፡፡ኦህዴድ በመሰረቱ የኦነግ የመንፈስ ልጅ ቢሆንም ኦነግን እድሜ ብቻ ያደረገው መንገድ እንደማያዋጣ ተረድቶ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈልገውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን መስመር ገብቶ ጉዞውን ማፋጠን መርጧል፡፡የተሳካለትም ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ህወሃትም ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ይሄው ተገልጦለት ነው ኢህአዴግ የሚለውን ማዕቀፍ የቀለሰው፡፡ሆኖም ትግራዊነቱ ሲብስበት እንጅ ሲሻለው አላየንም፡፡የህወሃት ንግግር በተግባር ሲፈተሸ ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው በዛው ባደቆነው ትግራዊነቱ ላይ እንደሆነው ሁሉ የኦህዴድ ኢትዮጵያዊነት ሱስም በተግባር የመፈተሻ ዘመን ሊቀመጥለት ይገባል እንጅ በመናገር ብቻ ጠግበን የታሪክ ስህተት ስንደጋግም መኖር የለብንም፡፡

የታሪክን ስህተት ላለመድገም ደግሞ ሁነትን ተከትሎ ከመንጎድ ገታ ብሎ ሁነቱን ያመጣውን እውነት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ እነ አቶ ለማ መገርሳ ከኢህአዴግ ካድሬ ለዛውም ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ መንደር ተሰምተው የማይታወቁ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቁ ሁለት አዳዲስ ነገሮችን በአንዴ ሲያዥጎደጉዱ በግሌ የተመለከትኩት በከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር፡፡ አንደኛው እና የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ዝንባሌያቸው ሲሆን ሁለተኛው ከባለጠበንጃው ህወሃት ተፅዕኖ ለመላቀቅ እና በራሳቸው ልቦና አስበው በራሳቸው አፍ የሚያወሩ ድርጅታዊ ነፃነት ያላቸው አካላት መስለው የታዩበት ሁኔታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የማቀንቀናቸው ነገር ‘ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መቀንጠስ’ አይነት መፍጠኑ ሳያንስ በጣም ጎኖ ሱስ ሆኖ መገለፁ በልቦናቸው ጊዜ ተሰጥቶት ተብሰልስሎ፣በጥልቅ ግንዛቤ ላይ ተምርቶ የተደረገ ተፈጥሯዊ የአቋም ለውጥ አይመስልም፡፡

ይልቅስ የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ህዝባዊ ትግል ከማዶ ማዶ እየተጠራራ ወንድምነቱን አንድነቱን ማስተጋባቱን ተከትሎ በተለመደው ካድሬያዊ አዋጭ መንገድን አፈፍ አድርጎ ትርፍ ለመሰብሰብ ሲባል ህዝብ የሚፈልገውን እየዘመሩ ደጋፊንም አባዝቶ ወደ ስልጣን የመገስገስ አካሄድ ያደላል፡፡ ስለዚህ የኦህዴድ የአሁኑ ኢትዮጵያዊነትን የመስበክ አካሄድ ምንጩ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚወደው ህዝብ ትግል እንጅ የለማ መገርሳ ካቢኔ አይደለም፡፡ የለማ መገርሳ ቡድን ይህን የህዝብ ፍላጎት ከህወሃት ክርን ማምለጫ አምባ አደረገው እንጅ እራሱ ፈጥሮ ለእውንነቱ የሚታገልበት ነገር አይደለም፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ኦህዴድ በማጉረምረም አንዳንዴም በግልፅ እምቢኝ በማለት(ዶ/ር ነጋሶ ያስታውሷል) ለህወሃት የሚያስቸግር ድርጅት ነው፡፡ማስቸገሩ ስረ-ምክንያት ደግሞ የህዝቤን ቁመና የሚያክል ቁመታም ስልጣን ይገባኛል በሚል ቁመት እና ወርድ የሚያንሰውን ህወሃት ወንበር መመኘቱ ነው፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገርን ህዝብ ብዛት ብቻ ተመርኩዞ ለሰው ልጅ የትልቅነት እና ትንሽነት መደብ የሚመድበው የጎሳ ፖለቲከኞች ግንዛቤ እዚህ ድረስ ነውና ኦህዴድ ለምን ይህን አለ ማለት አይቻልም፡፡በዚህ መሰረት ኦህዴድ ለራሱ ረዝሞ የሚታየውን የራሱን ቁመት የሚመጥን ስልጣን ሲመኝ ኖሯል፡፡ ሆኖም የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዙ ህወሃት ይዞ የሚጓዘው የጎሳ ፖለቲካ ተረክ ከማንም በፊት ኦህዴድን ወደሚወደው ስልጣኑ እንደሚጋብዝ አሳምሮ ስለሚያውቅ ጠመንጃውን ከአጠገቡ አያርቅም፡፡ ኦህዴድም የህወሃትን የብሄር ፖለቲካ ተረክ ተቀብሎ ወደስልጣን እንዳይመጣ ደንቃራ የሆነበት ‘አማራ የሚባለው ጭራቅ ትምክህት ነው’ ሲባል አሜን ብሎ ጭራቁን ከፖለቲካው ስዕል በማስወገዱ ለነገ የማይባል ስራ ላይ እጁን ከህወሃት አጣመምሮ ኖሯል፡፡

‘ጭራቁ’ የሚፈለገውን ያህል ከወንበር ርቆ መገፋቱ ከተረጋገጠ በኋላም ግን ኦህዴድ ወንበሩ ላየ ከመቁለጭለጭ በቀር ያገኘው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ወንበሩን አርቆ የሰቀለበትን ሌላውን ደንቃራ ሲፈልግ ህወሃት ከነጠመንጃው ወንበር ከቦ መቆሙ ዝግ ብሎ ተገለፀለት፡፡ ይሄኛውን ደንቃራ ለመታገል እንደ አልባሌ ነገር ስርቻ ውስጥ የተቀበረውን ክቡሩን ነገር ኢትዮጵያዊነት ጎትቶ ማውጣት ግድ ብሏል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ስም የራሱን የበላይነት ሲጭን ኖሯል እየተባለ ሲብጠለጠል የኖረውን የአማራ ህዝብም ሆነ ይህን ህዝብ ወክሏል የሚባለው ብአዴን አጋርነትም ያስፈልጋል ተብሎ የኦቦ ለማ መገርሳ ቡድን አባይን ይሻገር ዘንድ አስገድዷል፡፡ ‘የመጣነው ስለምታስፈልጉን ነው፤ይህ ደግሞ ለማለት ብቻ ሳይሆን ከልብ የመነጨ አባባል ነው’ ያሉት ኦቦ ለማ መገርሳ ጥዑም ንግግራቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ጨክኖ የማይጨክነውን፣የተደረገበትን በደል እያነሳሳ በማላዘን የማይታወቀውን የአማራን ህዝብ ልብ ለማግኘት አልተቸገረም፡፡በአማራ ክልል መዲና ላይ ቆመው የተናገሩን ይህ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ወገንተኝነት አዲስ ዝንባሌ በተቀረው የሃገሩ አንድነት ጉዳይ የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የኦህዴድን ተቀባይነት ጨመረው፡፡ የኦህዴድ በህወሃት ፊት ቆሞ የመከራከር ሞገስ ምንጩም ይሄው ነው፡፡ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ህወሃት ካነገበው ጠበንጃ የሚበረታው የህዝብ ክንድ አለ፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የሃገሩን አንድነት እንደሚወድ ይታወቃል፡፡ሃያ ሰባት አመት ዘረኝነት ሲያቦካ ኖሮ ከምጣድ አልወጣ ሲለው ኢትዮጵያዊነትን ድንገት ሲዘምር ለተገኘው ኦህዴድ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የተዘረጋው የተቀባይነት እጅ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃገሩን ለማዳን ሲሆን የቀደመ በደልን አይቆጥርም፡፡ይህ የህዝብ ወገንተኝነት ኦህዴድ የህወሃትን ጠበንጃ ተገዳድሮ ወደ ስልጣን የሚያዘግምበት አምባ ሆኖታል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ወንበሩላይ ተቀምጦ ምን ይፈይዳል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ከዶ/ር አብይ ሹመት ጀርባ ያሉ እውነታዎች

አመዛኙ የኢትዮጵያ ህዝብ የዶ/ር አብይን ሹመት እውን መሆን በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ነበር፡፡ ለሩብ ምዕተ-ዓመት ዘረኝነት ሲነዛባት በነበረችው ሃገራችን የዶ/ር አብይ ጎሳ ዘለል ተቀባይነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል ዘረኝነት እንዳገሸገሸው የሚያሳይ ነው፡፡ወደ ወንበር መምጣቱ እየተፈለገ ያለው ድህረ-አባዱላ/ሙክታር ኦህዴድም ቢሆን ኦሮሞነቱን አስቀድሞ በኦህዴድ ጥላ ስር መሰባሰቡ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የማይጠፋው ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ በጎሳ ከረጢት ያሉትንም፣አጥብቆ በታከተው ኢህአዴግ ጥላስር የተሰለፉተንም ሳይቀር፣የኢትዮጵያን ስም ከሃያ ሰባት አመት በኋላ ትዝ ብሎት ለሚያነሳም ጭምር ኢትዬጵያን የሚታደግ የሚመስል አዝማሚያ እስካሳዩ ድረስ የበዛ ይቅርታ እና ሆደ-ሰፊነት ያለው ህዝብ እንደሆነ ያሳያል፡፡የዚህ ማሰሪያው የኢትዮጵያ ህዝብ የሃገሩ ህልውና እና የአብሮነቱ ማገር ከምንም በላይ አስቀድሞ የሚያሳስበው ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ይህ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚመለሰው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ነው ለሚሉ፣አማራውን ኦሮሞ ስልጣን ላይ እንዳይወጣ ዘብ ቆሞ የሚያድር ባለጋራ አድርገው ሲሰብኩ ለኖሩ አማራ-ጠል የኦሮሞ ብሄርተኞች የማፈሪያ ሰዓት ነው፡፡

ዶ/ር አብይ እንደተመረጡ በተነገረ ማግስት ተሰናባቹ ጠ/ሚ አቶ ኃ/ማርያም የወጡበት የደቡብ ኢትዮጵያ እምብርት ሃዋሳ ከተማ ምናልባትም ከኦሮሚያዋ አዳማ እኩል በደስታ ሰክራ ነበር፡፡ ከማህፀኗ ወጣው የቀድሞ ጠ/ሚ መሰናበትም ሆነ ሌላው የደቡብ ሰው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኦህዴዱ ዶ/ር አብይ መሸነፍ ኢትዮጵያዊነቱን ለሚያስቀድመው የደቡብ ህዝብ ከቁምነገር የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚረባ ነገር እስካላየበት ድረስ የወንዜ ልጅ ስለሆነ ብቻ በከፍታ ይቀመጥ የሚልህዝብ ያለመሆኑ ኢትዮጵያ ከዘር ፖለቲካ ተዋጅታ የችሎታ ፖለቲካን ለማራመድ እድል እንዳላት ተስፋ ያጭራል፡፡ ወደ ሌላው የብአዴን እጩ አማራው አቶ ደመቀ ሲኬድ የአማራ ህዝብ ከዶ/ር አብይ ሊያስቀድመው ቀርቶ ብቻውን ቢወዳደር እንኳን ጠ/ሚ እንዳይሆን የሚጸልይበት ሰው ነው፡፡ የአማራ ክልል ህዝብ የለማ/ዶ/ር አብይ ቡድን አዲሱ ፖለቲካዊ መንፈስ ከማተቡ እኩል አንገቱ ላይ አስሮት የኖረውን፣ጦሱ ሲያሳስር ሲያስገድለው የኖረውን መፍቀሬ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ዘግይቶም ቢሆን በማነሳሳቱ ወከልኩህ የሚሉትን ብአዴኖችን አስረስቶ በየመኪናው መስኮት ላይ የኦህዴድ ባለስልጣናትን ፎቶ እስከመለጠፍ እንዳደረሰው አይናቸው ያየ ሰዎች አጫውተውኛል፡፡በግልባጩ በዶ/ር አብይ ቦታ ኦሮሞ ያልሆነ ሰው ቢቀመጥ ኖሮ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ተመሳሳይ ስሜት ስለመንፀባረቁ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡የሆነ ሆኖ የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ያስተዋልኩት ደስታ ተጋብቶብኝ ደስታውን ልጋራ ባልችልም አንድ ወሳኝ ነገር ግን ተረድቼበታለሁ-የኢትዮጵያዊነት ዳግም ትንሳኤ እንደቀረበ!!! ምክንያታችን ቢለያይም የሃገሬ አመዛኝ ህዝብ ደስታ እኔንም ሽው እንዲለኝ ያደረገው ይህ እውነት ነው፡፡

የዶ/ር አብይ ሹመት የሚያሳየው ሌላው እውነታ ህወሓት የፈለገውን ብቻ ከማድረግ ወደ መደራደር እንደ ወረደ ነው፡፡እስኪነክስ ማነከስ የሚያውቀው ህወሃት ወትሮም የቆመው መሳሪያውን በደምባደምብ ከልሎ ነውና ለደምባደምብ ተደራደረ ማለት ተሸነፈ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡በዋናነት የቆመበት መሳሪያው አብሮት እስካለ ድረስ የህወሓት ክንድ ዛለ ብሎ መደሰት ለመርካት መቻኮል ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ የኦህዴዱ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ህወሃት ሳይቀባው ወደ ስልጣን የመምጣት ጅማሮ ለመሆኑ የተራዘመው የሊቀመንበር ምርጫ፣የዶ/ር አብይን ስም ሲሰሙ እንደዛር የሚያደርጋቸው መፍቀሬ ህወሃት ድህ-ረገጾች ደምፍላት፣የአዲሱን ሊቀመንበር ምርጫ ተከትሎ ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ ዋና ፀሃፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስራውን የሚሰራው ግለሰብ ሳይሆን ድርጅት ነው የሚለው የበዛ ውትወታ አመላካች ነው፡፡

የአቶ ሽፈራው ውትወታ ‘ከዶ/ር አብይ ብዙ አትጠብቁ’ የሚል እውነትነት የማያጣው መልዕክት አለው፡፡ እንደሚታወቀው በኢህአዴግ ቤት “ድርጅት መንግስትን ይመራል”፡፡ሆኖም ግለሰብ(አቶ መለስ) ድርጅቱ የሚባል ስም እስከሚሰጠው ድረስ ድርጅትን ከመምራት አልፎ ራሱ ድርጅት ሆኖ/አክሎ ገዝፎ መንግስትንም ሃገርንም ረግጦ ሲገዛ ኖሯል፤የጦር ስትራቴጅስት፣ስነ-ትምህርት ፖሊሲ ቀያሽ፣ የግብርና ባለሙያ፣የህግ ሊቅ፣አየር ንብረትለውጥ ጉዳይ ቀማሪ፣የውጭ ግንኙነት ቄሰ-ገበዝ፣የሊጉም የክንፉም አሰልጣኝ፣ሴቱም የወንዱም ካድሬ የክርስትና አባት ሆኖ ከሊጡም ከወጡም ሲል ኖሯል! ዛሬ ከህወሃት ወገን ያልሆኑት ዶ/ር አብይ ወደ ወንበር የተጠጉ ሲመስል ደግሞ ግለሰብ ኮስሶ ድርጅት ይጎላ ዘንድ ተደጋግሞ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ማለት ህወሃት ሲፈልግ ድርጅት ተረስቶ ግለሰብ ከመጉላት አልፎ ይመለካል ሳይፈልግ ደግሞ ድርጅት ጎልቶ ግለሰብ ችላ እንዲባል ይደረጋል፡፡ለዚህ ነው ያልተፈለጉት ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ጠጋ ሲሉ “ድርጅት መንግስትን” ይመራል የሚለው ሙዚቃ እየተሞዘቀ ያለው፡፡

የአቶ ሽፈራው ድርጅት እንጅ ግለሰብ ብቻውን ምንም አይፈጥርም የሚለው ንግግር የሚያመላክተው የዶ/ር አብይ ወንበር ከአቶ ኃ/ማርያም ወንበር የተለየ እንደማይሆን ነው፡፡ከአቶ ኃ/ማርያም በመጠኑም ቢሆን የተለየ ማንነት ያላቸው የሚመስሉት ዶ/ር አብይ አቶ ኃ/ማርያምን የማይመስሉ ከሆነ ድርጅታዊ አመራር በሚል ሰበብ የሚቀመጡበት ወንበር አለቃ እና ምንዝሩ የማይለይበት በተግዳሮት የተከበበ እንደሚሆን አመላካች ነው፡፡ይህ ደግሞ በዶ/ር አብይ ወንበር እውነተኝነት ላይ ሃሳቡን ጥሎ የስራ ዝርዝር እስከማውጣት ለደረሰው ለውጥ ፈላጊ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ጠቅለል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ነፍስ የሚዘራው ከህወሃት ወገን የሆነ ሲቀመጥበት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ይህን መረዳት ብዙ የሚያስቸግር ባይመስልም እውነታው ግን አብዛኛው ለውጥ ፈላጊ ዶ/ር አብይ ብዙ ማድረግ እንደሚችሉ እያሰበ መገኘቱ፡፡

የኦህዴድ ለስልጣን መቃተት ለምን?!

አቶ ኃ/ማርያምን ያየ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ለመቀመጥ መጓጓቱ በግሌ ግራ የሚያባኝ ጉዳይ ነው፡፡ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ስልጣን ነፍስ የሚዘራው የደም መስዕዋትነት ከፍሎ ስልጣን የያዘው፣ዛሬም የህግ ፍፃሜ ሁሉ የአፈሙዝ ባለቤትነት እንደሆነ የሚቆጥረው ህወሓት አባል ሲይዘው ነው፡፡በኢህአዴግ ክንፍ የተኮለኮሉ፣ሁለተኝነታቸውን ያመኑ እህት ተብየ ፓርቲዎች ሁሉ ይህን ከእኛ ከሩቆቹ ይልቅ በደምብ አሳምረው የሚያውቁት የኑረታቸው አካል ነው፡፡

አሁን ብዙ ተስፋ እየተጣለበት ያለው ኦህዴድ የሃገራችንን ፖለቲካ በእጅጉ ከሚዘውረው አፈሙዝ መንደር ራቅ ብለው ከቆሙት ከሁለተኞቹ ወገን የሆነ እንጅ ሌላ ማንነት ያለው ፓርቲ አይደለም፡፡ ስለሆነም በመቀመጡ ብቻ የአቶ ኃይለማርያምን ወንበር ነፍስ ዘርቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ አይሆንም፡፡ሆኖም ኦህዴድ የወንበሩ በድንነት ሳይበግረው ወንበሩ ላየ ለመቀመጥ አይሆኑ ሆኗል፡፡ ነፍስ አልቦው ዙፋን ላይ ለመሰየም እንቅፋት የሆነበትን የደምባደምብ እግድ ለመሸሽ የፓርላማ መቀመጫ የሌላቸው አቶ ለማ መርሳ በዶ/ር አብይ እንዲተኩ ሆኗል፡፡እንዲህ መከራ የሚታይለት ወንበር በአቶ መለስ ዘመን በማወቅ፣ በአቶ ኃ/ማርያም ዘመን ባለማወቅ ብዙ ደም ያለበት ወንበር ነው፡፡ አንድም እንዲህ በተበከለ ሁለትም በድን በሆነ ወንበር ላይ ለመቀመጥ በመሸሽ ፋንታ መሟሟት ትርጉሙ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ኦህዴድ በአካል የህወሃት ጥፍጥፍ ቢሆንም በመንፈስ የኦነግ ቁራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ከመሪነት ቦታ ተገልሎ የኖረነው ብሎ ያስባል፡፡ነገሩን ሲያጎነው ኦሮሞ የቁመናውን ያህል በኢትዮጵያ መንግስታዊ ስልጣን ላይ ተንሰራፍቶ ሆኖ አያውቅም ይላል፡፡ ታሪክ ደግሞ ከጥንት እስከዛሬ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኦሮሞ አድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣናትን ይዘረዝራል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ይህ አይዋጥላቸውም፡፡ እነዚህ ታሪክ የፃፋቸው ያለፉት ስርዓት ኦሮሞ ባለስልጣናት ወደስልጣን የመጡት ኦሮሞነታቸውን ለአማራነት ገብረው እንጅ ኦሮሞነታቸውን አስቀድመው ስላልነበር የኦሮሞን የስልጣን ተጋሪነት አያመለክቱም ባዮች ናቸው -የዘመናችን የኦሮሞ ብሄርተኞች፡፡ ለነዚህ ለኦሮሞ ብሄርተኞች ኦሮሞ በቁመናው ልክ ስልጣን አገኘ የሚባለው እንደ ኦነግ ወይም እንደ ኦህዴድ በኦሮሞ ብሄርተኝነት ፓርቲ ውስጥ ታቅፎ ስልጣን ላይ ሲቀመጥ ነው፡፡

ለዚህ ነው ዛሬ በኦህዴድ ታቅፈው ወደ ነፍስ አልቦው ወንበር እያዘገሙ ያሉት የዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትርነት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የኦሮሞ ባለስልጣን የታየ ይመስል የሚያስፈነድቅ የሆነላቸው፡፡ ፍንደቃው በተለያየ መስመር ቆምን የሚሉ ኦሮሞ ብሄርተኞችን አንድ ያደረገ ነው፡፡ የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ኦነግን የሚያስፈነድቀውን ያህል ኦነግን በአሸባሪነት በፈረጀው ኢህአዴግ እቅፍ ያለውን ኦህዴድ በደስታ ያዘልላል፡፡ኦህዴድንም ሆነ ኦነግን አንመሰልም ነገር ግን የኦሮሞን ብሄርተኝነት ፖለቲካ በመዘወሩ፣ለኦሮሞ በመቆርቆሩ የሚያህለን የለም የሚሉ ግለሰብ አክቲቪስቶችንም የአንድ የወንዛቸው ልጅ ወደ ስልጣን መሰል ወንበር መቃረብ አፋቸውን በሳቅ ምላሳቸውን በእልልታ ይሞላል- ማሰሪያው የወንዝ ልጅነት ነውና!ሲጠቃለል ኦህዴድን የልቡን ወደ ማይሰራበት ስልጣን የሚቻኩለው ተነጉቶ የተሰራበት፣ከክርስትና አባቱ ኦነግ የወረሰው የተበድየ ፖለቲካ እንጅ እኛ እንደምንመኘው የህወሃት/ኢህአዴግን ቤተ-መቅደስ የሚያጠራበት ጅራፍ ይዞ ለመግባት፣የምንናፍቀውን የዲሞክራሲ ፀሃይ ለማውጣት የሚያስችል አቅሙም ተፈጥሮውም ኖሮት አይመስለኝም፡፡ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበት ችግር በተለይ ህወሃት ከነጠበንጃው ባለበት ማዕቀፍ፣በአጋርም ሆነ በአባል ፓርቲ ካድሬ አቅም እና ግንዛቤ ይፈታል ብየ ለማመን እጅግ ይቸግረኛል፡፡

ነፃ ያልወጣ ነፃ ያወጣል?

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ኦህዴድ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን በኢትዮጵየ ብሄርተኝት ለውሶ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ሰሚ እንደሚመች አድርጎ አቅርቦ ወደ ወንበር እየባከነ ይገኛል፡፡በድሮ በሬ ማረስ ምርት እንደማያሳፍስ በደንብ የተረዳ የሚመስለው ኦህዴድ ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ዘይቤ ይዞ ስልጣን ላይ መቀመጡ ቢያንስ ጠላትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ሳይገነዘብ አልቀረም፡፡ሆኖም ይህ የሚገሰግስለት ወንበር ምቹነቱ፣ነፃነቱ እና እውነተኝነቱ አጥብቆ ያጥራጥረኛል፡፡ የጥርጣሬየ መነሾ ደግሞ በኢህአዴግ የቤታቤት ደምብ አድራጊ ፈጣሪው ጠበንጃ እንጅ ሌላ አለመሆኑ፤ጠበንጃውን ያነገተው አካል ደግሞ የፈለገውን ለማድረግ ህግጋትን የማይፈራ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ብዙ የለውጥ ተስፋ የተጣለበት ኦህዴድ ደግሞ ዝናር እና መውዜሩን በማጋፈሩ በኩል እጣ ፋንታ ያለውም የሚኖረውም ስለማይመስለኝ ነው፡፡ ይህ የድሮ ዘፈን ነው ዛሬ ባለጠመንጃው ህወሃት ተዳክሟል በሚል የህወሃትን የቀድሞ ጉልበታምነት ለኢህዴድ ሸልሞ በኦህዴድ ላይ ተስፋ የማድረግ ትንታኔዎች በሰፊው አስተውላለሁ፡፡

በርግጥ ኦህዴድ ከቀድሞው በተሻለ በህወሃት ላይ የማጉረምረሙን ድምፀት ማጉላቱን የሚያመላክቱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በኦሮሚያ የኦሮሞ ወጣቶች ህይወትን የሚያጠፉ የፌደራል የፀጥታ ሃይሎችን ድርጊት በድፍረት ከማውገዝ አልፎ ሳንጠራቸው መጥተው ነው ህይወት የሚያጠፉት እስከማለት መድረሳቸው በማዘዝ መታዘዝ በሚታወቀው ኢህአዴግ ቤት የተለመደ አይደለምና ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተለይ ህወሃት ባልጠበቀበት ሁኔታ የፓርላማ ወንበር ያላቸውን ዶ/ር አብይን በአቶ ለማ መገርሳ ቀይረው ለጠቅላይ ሚንስትርነት ወንበር ፓርቲያቸውን ማዘጋጀታቸው የማይታመን ድፍረት ከመሆኑ የተነሳ ነገሩ በህወሃት ይሁንታ የሆነ ይሆን እስከማስባል ካደረሳቸው ውስጥ ነበርኩ፡፡ ሆኖም ይህን ተከትሎ ኢህዴግ በተራዘመ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስየማ ስብሰባ ላይ መሰንበቱ፣ የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ሰውየውን እንደ ግለሰብ ከማጉላት ይልቅ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ሊያመጣ በሚችለው ለውጥ ላይ መተኮር እንዳለበት በመወትወቱ ላይ እየተሟሟተ ያለው የኢህአዴግ ፅ/ቤት አካሄድ የሰውየውን በኢህአዴግ እውነተኛ ባለቤቶች ዘንደ አለመወደድ ያስመሰክራሉ፡፡
መረሳት የሌለበት ሃቅ ግን ኦህዴድ ህወሃት እምብዛም ያልፈለገውን ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ ተሳካለት ማለት ህወሃት ተዳክሞ በሞት እና በህይወት መሃል ሆነ ለማለት የሚበቃ ምልክት አለመሆኑ ነው፡፡ በግልባጩ ኦህዴድ ህወሃትን ድባቅ መትቶ በቀድሞው የህወሃት የሃያልነት ወንበር ላይ ተንሰራፍቶ ተቀምጧል ለማለትም የሚያበቃ ነገርም አይደለም፡፡ይህ ማለት ህወሃት አስራ ሰባት አመት ጠመንጃ ነክሶ መዋጋቱን እንደ አለፈ ውሃረስቶ፣ወንበሩንም ከነጠመንጃው አስረክቦ ለመሄድ የማያቅማማ ልበ-ቀላል ገራገር ለመሆኑ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ኢትዮጵያ በተጨባጭ ከህወሃት ጋር ያሳለፈችው ፖለቲካዊ ታሪክ ደግሞ የሚያሳየን ይህን አይደለም፡፡

ይልቅስ ህወሃት ደርግን የጣለበትን ብቃቱን የስኬት ሁሉ ጫፍ፣ የጣለውን ደርግ ደግሞ የሃይለኛ ሁሉ መጨረሻ አድርጎ ራሱን በሁልጊዜ የአሸናፊነት ሰገነት ላይ ያስቀመጠ፣በአደባባይ ‘መበለጥን አልወድም’ የሚል የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ያሰከረው ፓርቲ መሆኑ በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ጠበንጃው በክንዱ እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ ህወሃት የማይፈልገው ሰው ወደ ስልጣን መምጣት ሃያልነቱን ለማስመስከር ሌላ መንገድ እንዲፈልግ ያደርገው ይሆናል እንጅ መሸነፉን ተቀብሎ ተረኛው ሃያል የሚያደርገውን ለማየት ሸብረክ የሚል አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ትናንት ስለ አቶ መለስ ዜናዊ ልዕለ-ሰብነት ሲያመልክ የኖረው፣ሰውየውን ከሰውነት ደረጃ ከፍ አድርጎ ድርጅቱ ብሎ እስከመጥራት ደርሶ የነበረው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ጄሌ ካድሬ ሁሉ ዛሬ ከዶ/ር አብይ ግለሰባዊ ማንነት ላይ አይናችንን ነቅለን በድርጅቱ ብቃት ላይ እንድናተኩር ሳይደክማቸው የሚወተውቱን፡፡

ህወሃት የሁልጊዜ አሸናፊ ለመሆን ህግን እና መሳሪያን ከፕሮፖጋንዳ ጋር አሰናስሎ ይጓዛል፤በህግ እና ደምብ ያሸነፈውን በጠመንጃው ያምበረክካል፡፡በጠመንጃው ያምበረከከውን በፕሮፖጋንዳው አንቋሾ የተበዳይ ተወቃሽ አድርጎት ቁጭ ይላል፡፡ይህን ኦህዴድ ራሱም ከህወሃት ስርስር እያለ አብሮ ሲያደርገው የኖረው ጉዳይ ነውና አሳምሮ ያውቀዋል፤ቀዩን መስመር ያለፈ ዕለትም ጠመንጃው ወደራሱም ሊዞርበት እንደሚችል፣የማጉረምረሙ ርቀትም የትድረስ ሊሆን እንደሚችል አሳምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ባለጠመንጃው ጠመንጃ እስኪያነሳ ድረስ የማያደርሰውን ማጉረምረም ብቻ ያጉረመርማል፤የታሰረበትን ገመድ ርዝመት ከእኛ ይልቅ እርሱ ያውቃል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይፀድቅ ዘንድ ለፓርላማ ሲቀርብ ዶ/ር አብይ ፓርላማ ቀርበው ድምፃቸውን ለመስጠት መቸገራቸው ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር ከተቆናጠጡ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሱ በብዙዎች የሚጠበቁት ዶ/ር አብይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ያላቸውን አቋም ከመገመት ባለፈ በገሃድ አይታወቅም፡፡አመዛኙ ገማች ግን ሰውየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አልወደዱትም ስለዚህ ነው መምጣቱን ያልወደዱት የሚል ነው፡፡ የሰውየው በፓርላማ ተገኝተው እውነተኛ ሃሳባቸውን አለማንፀባረቃቸው የሚያሳየው ግልፅ ነገር ግን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቶ እንደ አንድ የፓርላማ አባል ሃሳባቸውን ለማንፀባረቅ እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው በጥብቅ የሚፈሩት አንዳች አካል እንዳለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የነፃነት ምልክት አይደለም፡፡ የዶ/ር አብይ ከፓርላማ መቅረት ሊያስወቅሳቸው ባይችልም ፓርቲያቸው ኦህዴድ የሰጣቸው የተጋፋጭነት ጉልበት ሊወስዳቸው የሚችለውን ርቀት ያሳያል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አለቀለት አበቃለት እየተባለ ያለው የህወሃት ጉልበት ያለበትን ደረጃ ያመላክታል፡፡

ዶ/ር አብይ እንደ አንድ የፓርላማ አባል ቀርበው ሃሳባቸውን ለመግለፅ ሲያፈገፍጉ ሌሎች ሰማኒያ የኦህዴድ አባላት የመጣውን ለመቀበል ወስነው ፓርላማ ተገኝተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት ዶ/ር አብይ እነዚህ የፓርላማ አባላት ያላቸውን ድፍረት ማጣታቸው በኢህአዴግ ቤት ስልጣን ከፍ ሲል የባርነት ሰንሰለትም ጠበቅ እንደሚል ሊያሳይ ይችላል፡፡በዚህ መሰረት የዶ/ር አብይ ወደ ጠ/ሚነት ወንበር ከፍ ማለት ይዞ የሚመጣው ነፃነታቸውን ይሁን ባርታቸውን መገመት ካባድ አይደለም፡፡ ዶ/ር አብይ በፓርላማ ውሏቸው ደጋግመው ካመሰገኗቸው የኦህዴድ ጓዶቻቸው መራቃቸው እና በምትኩ የጠ/ሚው አማካሪ ተብለው ወንበራቸውን በከበቡ የቀድሞ ታጋዮች መከበባቸው ጉልበታችን የሚያደክም እንጅ የሚያበረታ ነገር አይመስለኝም፡፡

ባርነትን አልቀበልም ካሉ ደግሞ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ እንደሚመስለኝ ዶ/ር አብይ የአቶ ኃ/ማርያምን ያህል የተገሩ አገልጋይ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የእሳቸው እምቢ ማለት ብቻ በኢህአዴግ ቤት የተለመደውን የሎሌ ጌታ ግንኙነት ቀይሮ ወንበራቸውን የእውነት ያደርገዋል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ሰውየውም እንደ አቶ ኃ/ማርያም መሆንን በጄ ካላሉ አዛዥም ማዘዜን አልተውም ካለ ሊፈጠር የሚችለው ነገር የዶ/ር አብይ መጨረሻም እንደ አቶ ኃ/ማርያም ስልጣናችሁን ውሰዱ ብሎ ውልቅ ማለት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን በመጡበት ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ከተሰናባቹ ጠ/ሚ ጎን ተቀምጠው መስህብ የሌለውን የአቶ ኃ/ማርያም መጀመሪያም መጨረሻም አዳንቀው ማውራታቸው የእሳቸው እድልም ከዚሁ እንደማያልፍ ልቦናቸው ነግሯቸው ይሆናል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚስትር የከበባቸው ፈተና ቀላል ያለመሆኑን በመረዳት ሰውየው ታሪክ ያጠራቀመውን የሃገራችንን የፖለቲካ ችግር ሁሉ እንደጉም አብንነው የሚያጠፉ ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡ ሰውየው ይህን እና ያንን ያድርጉ እየተባለ የሚወጣው መዘርዝርም እውነታውን ያገናዘበ አይመስለኝም፡፡ዶ/ር አብይ የቆሙበት ፖለቲካዊ መሰረት የልባቸውን እዲያደርጉ የማያስችል ሆኖ ሳለ ብዙ እንዲያደርጉ ሲጠበቅ ለሰውየው ደህንነት ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር እንደማንኛውም ሰው በህይወት መኖር የሚፈልጉ፣ የሚወዱት እና የሚወዳቸው ቤተሰብ ያላቸው የሰው ልጅ እንጅ ብረት ለባሽ ፍጡር አይደሉም፡፡ስለዚህ የምንሰጣቸው የቤት ስራ ይህን ሁሉ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡

ዶ/ር አብይ ስልጣን ሲይዙ ከኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ኦህዴድን ይዘው መውጣቱ አንዱ እድል እንደሆነ ተፅፎ አንብቤያለሁ፡፡ይህ የሚሆን አይመስለኝም እንጅ ቢሆንም የሚጠቅመው ህወሃት/ኢህአዴግን እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብንም ኦህዴድንም አይደለም፡፡ ዶ/ር አብይ ኦህዴድን ከኢህአዴግ ገንጥየ ልውጣ ቢሉ ህወሃት ጠፍጥፎ የሰራውን ኦህዴድን ከነነፍሱ ይዘው ይወጡ ዘንድ ዝምብሎ የሚያያቸው ነፈዝ ስብስብ ሳይሆን አጋጣሚውን በእልልታ ተቀብሎ፣ እሳቸውን እና መሰል ጓዶቻቸውን በአንጀኝነት ከስሶ ፣ወህኒ አውርዶ፣የቀድሞውን ኦህዴድ የሚመልስበትና የራሱን የቀድሞ አዛዥነቱን ከነሙሉ ክብሩ እና ጥቅሙ መልሶ የሚያመጣበት ብልጣብልጥ ድርጅት ነው፡፡ ህወሃት ከኦህዴድ ቀርቶ ከራሱ ፓርቲ አኩራፊ ተገንጣዮች የትየለሌ ያተረፈ ድርጅት ነው፡፡ የእነ አቶ ስየ-ተወልደ ቡድን አኩርፎ መውጣት የህወሃትን ገዥ ነጅነት አጠናከረ እንጅ ያሳጣው ነገር የለም፡፡

የኦህዴድ ውበት!

ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣናቸው በሃገሪቱ ፓርላማ ቡራኬ ባገኘበት ወቅት ከሌሎች የኢህአዴግ ካድሬዎች በተለየ ሁኔታ ያደረጉት ህይወት ያለው ንግግር ከአንድ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ርቱዕ አንደበት እንዳላቸው ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ንግግራቸው ቢያንስ የራሳቸውን አለፍ ሲልም ፓርቲቸው በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ያለውን ምኞት እንደሚያሳይ ጥልቅ ስሜታቸውን ያጤነ ሁሉ ይረዳዋል፡፡ የሴት ሚና እምብዛም በማይነሳሳበት ሃገር ባለቻቸው አጭር ሰዓት ስለሴቶች ያላቸውን የሰለጠነ እሳቤ ያቀረቡበት መንገድም እናታቸውን እና ባለቤታቸውን አስቀድመው ያደረጉት ነውና የማስመሰል አይመስልም፡፡ በተለይ በተለይ ስለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጉዳይ ያነሱት ፓርቲያቸው ከኖረበት የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ የማይመጥን የጎሳ ፖለቲካ ጠባብ ከጢረት እልፍ ማለቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በተግባር የሚሆነው ነገር ንግግራቸውን ይምሰል አይምሰል ዋል አደር ብለን የምናየው ሆኖ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ልህቀት፣ጥልቀት፣ውስብስብ ቋጠሮ፣ሩቅነት በተመለከ የተናገሩበት መንገድ እጅግ ግሩም ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ብቸኛ የኦሮሞ ህዝብ ሞግዚት አድርገው የኦሮሞ ህዝብ በጎ ነገር የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እንደሆነ የሚሰብኩ አፍራሾችን አጓጉል መንገድ አይረቤነት ያሳየ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ብሄርተኛው ትልቅ ድል ነው!

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

___
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,864FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here