spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትየጠ/ሚ አብይ ነገር.... (በመስከረም አበራ)

የጠ/ሚ አብይ ነገር…. (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ
ንግግር አዋቂነት የስኬታማ ፖለቲከኝነት አንድ ግብዓት ነው፡፡የአቶ ሃይለማርያምን ወንበር የተኩት ጠ/ሚ አብይ ከቀዳሚያቸው በተሻለ ንግግር ይጥምላቸዋል፡፡ይሄው ጥዑም ንግግራቸው አድማጫቸው የንግግራቸውን ይዘት ወለፈንዲ ይመረምር ዘንድ ፋታ የሰጠው አይመስልም፡፡ሰውየው የፖለቲካ ፈውሳችን ሊሆኑ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ አርቆ የጣለብን የኢህአዴግ አባል እንደመሆናቸው መጠን የተናገሩትን በጎውን ከማዳነቅ ጎን ለጎን በመርማሪ ልቦና ማየቱ አትራፊ ያደርግ ነበር፡፡

ጠ/ሚ አብይ በበዓለ ሹመታቸው ቅን ፓርላማ ቀርበው ያደረጉት ንግግር ላይ ላዩን ሲያዩት ድንቅ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን በተመለከተ ያመጧቸው ሃሳቦች የሚወደው ኢትዮጵያዊነቱ ሲበሻቀጥ እንጅ ሲሞካሽ ሰምቶ የማያውቀውን ህዝብን ቀልብ ስቦ ኖሮ የንግግራቸውን ብልት ለመመርመር ፋታ አልተገኘም፡፡በዚህ ላይ ሃገራችንን የመታት የገለልተኛ ተንታኝ ድርቅ ስሜትን በምክንያት ለመተካት አላስቻለም፡፡ ቢቸግረን ወገንተኝነቱን ለአንድ ጎሳ አድርጎ “ካልሆነ ሜንጫ አንሱ” የሚለውን ሁሉ፣የስሜት መረጋጋት የሚያንሰውን፣ የፖለቲካ አቋሙ እንደ ገበቴ ውሃ የሚዋልለውን፣ ዛሬ ያለውን ነገ የማይደግመውን፣ስሜት ምክንያትን አርቆ የጣለበትን፣ጥላቻ እና የተበድየ ተረክ ናላውን ያዞረውን ሳይቀር የፖለቲካ ተንታኝነት ካባ አልብሰናል፡፡የአክቲቪስት እና የተንናኝ ቦታ አደባልቀናል፡፡

ኢህአዴግን የምንወቅስበት ሃቁን ችላ ብሎ የፈለጉትን ብቻ የመስማት አምሮት ኢህአዴግን አምርሮ በሚቃወመው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ጎራም የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሃገራችን በርካታ በሳል ምሁራን ቢኖሯትም አብዛኛው ህዝብ በገና አንስቶ፣ከበሮ አንግቶ የሚዘምርለትን ክስተት ሌላ ገፅታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት ቢነሱ ውግዘት ስለሚከተላቸው እውነታውን ወዲያው ለማሳየት ይቸገራሉ፡፡ ከሰሞኑ በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው የጠ/ሚ አብይን ነገር ከመነሻው በተለየ ሁኔታ ያዩት እንደነበረ ዘግይተው የተናገሩ ምሁራን ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ሰዎቹ ጠለቅ ባለ ሁኔታ የነገሩን ብልት ተረድተው እንደነበር ከንግግራቸው ያስታውቃል፡፡ ነገር ግን ይህን የመሰለ ምጡቅ መረዳታቸውን እና ሃሳባቸውን ለጠ/ሚ አብይ ማህሌት በተቆመበት ሰዓት ቢናገሩ ኖሮ “ከህወሃት የባሱ ሴረኞች፣የሴራ ፖለቲካ በሽተኞች” ተብለው ውግዝ ከመዓሪዎስ መባላቸው አስግቷቸው ዝምታን መርጠው ሰንብተዋል፡፡ በዚህ ከቀጠልን ከስህተት መዳኛዋ እውቀት ለስሜት ቦታዋን ለቃ ዳር ሆና ከማየት በቀር ምንም ምርጫ የለም፡፡

ያልበሰለው የሃሳብ ብዝሃነትን የማስተናገድ ልምዳችን ትንታኔን ከሟርት አይለይም፡፡ትንታኔ ሟርት የሚሆነው በበቂ ማስረጃ ካልተደገፈ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የሃሳቡን ባለቤት በደፈናው ለማሸማቀቅ ከመራኮት ይልቅ ደካማ ክርክር ላይ የቆሙ የመሰሉንን ሃሳቦቹን ነቅሶ አውጥቶ የተሻለ የተባለውን ክርክር በማምጣት መሞገቱ መንገድን ለማጥራት ይጠቅማል፡፡በዚህ በኩል ነጮች እጅግ ይበልጡናል፡፡ ከአፍ የወጣ የፖለቲከኞችን ንግግር ቀርቶ የሰውነት መወራጨታቸውን(Gusture) በማጤን የፖለቲካ አቋማቸውን ይተነትናሉ፡፡ በግልፅ ከተባለው የፖለቲከኞቻቸው ንግግር በግልፅ ያልተባለውን (ግን ሊባል የተፈለገውን) ፈልፍለው አውጥተው ህዝባቸውን ያነቃሉ፡፡ ለምን ይህን አሉ ተብሎ ውርጅብኝ የለም! ስለዚህ ከስህተት ይድናሉ፣ፖለቲካቸው ከሞላ ጎደል የተፈወሰ ነው፡፡

በበዓለ ሹመቱ ንግግር ያደረገ መሪ ከሞላ ጎደል የፖለቲካ አቋሙ እና የትኩረት አቅጣጫው እሳት በላሱ ተንታኞች ብልቱ ተፈታቶ ምርቱ ከግርዱ ተለይቶ ይታወቃል፤ የንግግሩ ተዛነፎች ካለው የፖለቲካ ልማድ ጋር ተሰናስሎ ይብጠረጠራል እንጅ “ቀኑ ሲደርስ የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል” ማለት የሚያበዛ ተንታኝ የላቸውም፡፡ ቀኑ ሲደርስ ጉዳቱን አብሮ ለማየት ተንታኝ መጥራት ለምን አስፈለገ? በርግጥ ቀኑ ሲደርስ የሚታዩ ፣በፖለቲካ መሪዎች ልብ ብቻ ትክክለኛ ሁኔታቸው የሚታወቁ በጣም ጥቂት ጉዳዮች አሉ፡፡ እዚህ ጥቂት ጉዳዮችም “ሲደርስ እንያቸው” ተብለው ከመታለፍ ይልቅ ካለው እና ከነበረው የፖለቲካ ከባቢ በመነሳት አንዱ ካልሆነ ሌላው የሚሆንበትን አማራጭ የቢሆን አቅጣጫዎችን(scenario) ማሳየት ለሚችሉ በሳል ምሁራን እድል መስጠት እየመላለሱ ከመሳሳት ይታደጋል፡፡

የመሪዎች የበዓለ ሹመት ንግግር ትንታኔ እኛን በአሁን ወቅት እያነታረከ ያለውን ለጠ/ሚ አብይ ምን ያህል ጊዜ እንስጥ ለሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ጥሩ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ የጠ/ሚው ንግግር አስተዳደራቸው ሊፈታቸው የሚችላቸውን እና የማይችላቸውን፣የእኛ ብርቱ ፍላጎት እና የሰውየው ትኩረት መግጠም አለመግጠሙን፣የሰውየው ስልጣን ምን ያህል ጉበታም ነው የሚለውን፣የሰውየው እውነተኛ ወገንተኝነትስ ለህዝብ ነው ለድርጅታቸው ወዘተ የሚሉ በጣም ጠቃሚ ሃቆችን ለመመርመር ጥሩ ፍንጭ ይሰጣል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከስሜት እና ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ እንመርምረው ከተባለ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ በበኩሌ ከጠ/ሚ ባዕለ-ሹመት ንግግር ውስጥ ስሜት ሰጭ ሆኖ ያገኘሁት ስለ ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መስተጋብር ያነሱት እና ስለ እናታቸው እና ባለቤታቸው የተናገሩትን ብቻ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ ስለኢትዮጵያ የተናገሩትን ያዳመጥኩት ከጥያቄ ጋር ነው፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት እና ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ልባዊ ዕምነት ያለው ሰው እንዴት ከኢህአዴግ ጋር ተስማምቶ የጠ/ሚነት ማማላይ እስከመድረስ ደረሰ ከሚል ጥያቄ ጋር! የሆነ ሆኖ ንግግሩ ራሱ ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ነገር ስለሆነ በይሁንታ ቢታለፍ ችግር የለው፡፡

የማይታለፉትን ስናነሳ ጠ/ሚው ንግግራቸውን የጀመሩት “ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግስት አስተዳደር ስርዓቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህንን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እውዳለሁ።…….. የመንግስታዊ ስልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫዋቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ህዝባችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ”(መስመር የእኔ) ብለው ነው፡፡ ቀጠል አድርገው “ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!” ይላሉ፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ ሃገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እያደረገች እንደሆነ የተቀመጠበት መንገድ ግር ሲያሰኝ ጭራሽ የስልጣን ሽግግሩ የሁለት ካድሬዎች የቦታ መለዋወጥ መሆኑ ቀርቶ መንግስታዊ የስልጣን ሽግግር እንደሆነ መነገሩ አስገራሚ ነው፡፡

መላላክ የደከመው ካድሬ ‘እስኪ አንተ ደግሞ ሞክረው’ ብሎ ከወንበር መነሳቱ የመንግስት ለውጥ ተደርጎ የሚቀርበው ለየትኛው ጥርስ ያላበቀለ ህፃን ነው? ነው ጠ/ሚው የመንግስት ለውጥ ማለት የሰው ብቻ ሳይሆን ፖሊሲ ለውጥ መሆኑን ያጡታል?አብዮታዊ ዲሞክራሲን የመሰለ ችኮ እና አርጄቶ የፖለቲካ መስመር አንግቦ ‘አዲስ መንግስት ነኝ’ ማለት እንዴት ነው? አዲስ መንግስት እና አዲስ ካድሬ ምን አገናኘው? ለዛውስ አብይ አዲስ ካድሬ ናቸው? ይሄንኑን የካድሬ ለውጥ ታሪካዊ ያደረገውስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት ላይ ተንጠላጥሎ የከረመውን የኦህዴድ የስልጣን ሃራራ ማርካት ታሪክ ተሰራ የሚያስብለው ጥሙ ለረካለት ስልጣን አምላኪ ብቻ እንጅ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አንቅሮ ለተፋው የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም፡፡ይህ የስልጣን ሽግግር እንደተካሄደ የማስመሰል ንግግር ህዝብ የሚፈልገው እውነተኛ ለውጥ የመጣ በማስመሰል የህዝብ ጥያቄ ተዳፍኖ እንዲቀር ማድረጊያ ኢህአዴጋዊ ዘዴ ነው፡፡

በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ውስጥ ተሁኖም ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ሰው ካለ በዱላ ቅብብል ተሰናበቱ የተባሉት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ክርስትና አባቶች ምን ተብለው እንደሆነ መልስ በሌለው ሁኔታ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ውስጥ መገኘታቸው፣ ሄድኩኝ ያሉት አቶ በረከት ፖለቲካዊ ህልውና በሃገራች ፖለቲካ ላይ መመለሱን የሚያመላክቱ ነገሮች መኖራቸው፣ሰው ባልጠፋበት ሃገር ዲሞክራሲን አስረው የሚገርፉ ሰዎች የዲሞክራሲ አስተናባሪ ተብለው ለውጥ አመጣለሁ በሚሉት ጠ/ሚ አናት ላይ ጉብ መደረጋቸው፣በፓርላማ ስለነፃነት እየተወራ ባለበት ቅፅበት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መኖራችን፣ ስለ አስተሳሰብ ነፃነት እየተወራ ለኢትዮጵያ ደግ በማሰባቸው ብቻ ነፃነት ቀርቶ የእግዜር ፀሃይ ብርቅ በሆነበት እስርቤት የታጎሩ እንደ አንዳርጋቸው ፅጌን የመሰሉ ብዙዎች መኖራቸው፣ ይህ ንግግር ከተደረገ በኋላ፣ዶ/ር አብይም እውነተኛ ጠ/ሚ ነኝ ካሉ ማግስት እነ ስዩም ተሾመ፣እነ እስክንድር ነጋ ወደ እስር መጋዛቸው ወዘተ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ለውጥን መጠበቅ ህወሃት ስታገል ሞቱብኝ የሚላቸውን ስልሳ ሽህ ሰማዕታት ከሞት ከማስነሳት ጋር ቁርኝት እንዳለው ያመላክታል፡፡ ሰማዕታቱን ከሞት አስነስቶ ለህወሃት የመመለስ “ብቃት” ያለው ብቻ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር እውነተኛ ለውጥ መጠበቅ ይችላል፡፡

ጠ/ሚ አብይ ስለዚሁ “የስልጣን ሽግግር፣የመንግስት ለውጥ” ሲቀጥሉ ይህን ይላሉ “ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው። ክስተቱ፣ በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፤ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የህገ-መንግሥትታዊ ስርዓት መሰረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በህዝብ ፍላጎት፤ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል። …………. መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ ሀገራችንን ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል። ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ ሀገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን፡፡” ከላይ የእሳቸውን ወደስልጣን ያመጣው ክስተት እንዴት እንደሆነ ባልገባኝ መንገድ በሃገራችን ዘላቂ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግሰታዊ መሰረት ስለመጣሉ ማስረጃ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የተረጋጋ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የጣለ መንግስት አለም ጉድ እስኪለው ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ ድረስ ማጣፊያ ያጠረው ለምንድን ነው? ወይስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማግተልተልም የመረጋጋት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የመገንባት ምልክት ነው ልንባል ነው? ስምንት መቶ ሽህ ኦሮሞዎችን በቅርቡ ከኢትዮ-ሶማሌ ክልል፣ ማንም ነገሬ ብሎ ያልቆጠራቸውን አማሮች ከመላ ሃገሪቱ ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ሲያሰድድ ሲያፈናቅል የኖረውን የጎሳ ፌደራል ስርዓትም በሁሉ መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግስታዊ ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡ ይሄን ሁሉ ህገ-መንግስታዊ መረጋጋት መሪ ድርጅታው ኢህአዴግ እንዳመጣ የነገሩን ሰውየ ወዲያውኑ ዓለም ስጋት እና አድናቆት በተሞላበት ግርታ ያየናል ይላሉ፡፡ አድናቆቱ መጣ ባሉት ድንቅ መረጋጋት ነው ቢባል ስጋቱ በምንድን ነው?

አጋር ድርጅት በሚባል አግላይ አካሄድ ጠ/ሚ አብይ ሃሴት ያደረጉበትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ለመመኘት እንኳን የማይችሉ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ባሉበት ሃገር ‘እኔ መሾሜ ሁሉን አቀፍ ህገመንግስታዊ ስርዓት የመምጣቱ ማሳያ ነው’ ማለት ምን ማለት ነው? ይህን በተመለከተ ጠ/ሚው አቶ ለማን አስከትለው ወደ ኢትዮ-ሱማሌ በተጓዙ ጊዜ አንድ የኢትዮ-ሱማሌ ተሰብሳቢ “የእርስዎ እናት የሃገር መሪ እንደሚሆኑ እንደነገረችዎት የኢትዮ-ሱማሌ እናቶችም ጠ/ሚ ልጅ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ እኮ!” ሲል በነገር አዋዊ ሰው ንግግር ብዙ ያወሩለትን ስርዓት አግላይነት በደንብ ነግሯቸዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት አመጣ የተባለው ህገ-መንግስት ራሱ የአማራን ህዝብ የሚያክል ብዙ ቁጥር ባለው ህዝብ ላይ በር ተዘግቶ የተፃፈ የቂም-በቀል ዶሴ እንደሆነ ለማን ይጠፋዋል? በሁለተኝነት የተቀመጠው እና አሁን በሃገራችን ያለው ስርዓት ከኢኮኖሚ፣ከፖለቲካ እና ከማህበራዊ ለውጦችን አገናዝቦ እኩል የሚጓዝ ነው ተባለው የተለመደው የካድሬ ስድብ ይመስለኛል፡፡

አገር ኦና እስኪቀር ድረስ ወጣቶቿን በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ እግራቸውን ነቅለው በሚሰደዱባት ሃገር፣ሰው በፖለቲካ አቋሙ ብቻ ታስሮ በሚገረፍባት ሃገር፣ወዳጅ ዘመድ እንዳይጎበኘው ዘመዶቹ በቀላሉ በማያገኙበት እስርቤት በሚወረወርበት፣ ከቤተሰብ ተመርጦ የሰማኒያ አምስት አመት ሽማግሌ ብቻ ስንቅ ያቀብል በሚባልበት የመርገም ሃገር፣ ራሳቸው አዲስ ነኝ ባዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ስራቸውን የጀመሩት ዘመን አመጣሹን ማህበራዊ ድህረ-ገፅ በመርገም መሆኑን እያወቅን ‘ከለውጥ ጋር ተራምዶ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያረካ ስርዓት መስርተናል’ ማለት የተለመደ ካድሬያዊ ልብ-አውልቅነት ነው፡፡

በሌላው በንግግራቸው ያነሱት ሃሳብ ዲሞክራሲን፣ሰብዓዊ መብትን እና የሃሳብ ልዩነትን በተመለከ ነበር፡፡ ይህን ይላሉ “አሁንም ዲሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም ሀገር በላይ ለኛ የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ። ……. መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው። ምክንያቱም ገዥ መርሃችን የህዝብ ሉዓላዊነት ነውና። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ፣ የመጀመሪያው የመጨረሻውም መርህ፣ በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት።”

ዲሞክራሲ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተቃዋሚ እግር ሲያወጣ እግሩን፣ምላስ ሲያበዛ ምላሱን እቆርጣለሁ ሲሉ የነበሩት አቶ መለስም የተናገሩት በተግባር የማይታይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊያን የአፍ ማሟሻ ነው፡፡ዲሞክራሲ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ እየተነገረ አምባገነንነቱ እያደር ብሶት በአስቸኳጊዜ አዋጅ የሚመራ ወታደራዊ ቅጥ አስተዳደር ላይ ደርሳለች፡፡ ይህን የሚያወሩት ሰውየም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን ስልጣን ላይ ለመሰየም ከሃይኛው ጋር ተፋልመዋል፡፡ የሴት ልጅ አስር ጥፍር የሚነቅል፣የመነኩሴ ቆብ በድብደባ የሚቀድ፣ወንድ ልጅ የሚያኮላሽ፣የሰውን ልጅ እንደክርስቶስ የሚሰቅል ስርዓት አልጋይ ሆኖ ሩብ ምዕተ አመት የኖረ ሰው ስለ ሰብዓዊ ክብር ለማውራት ቢያንስ ዛሬ ያለሃጢያታቸው የምድር ገሃነም ውስጥ የሚሰቃ የፖለቲካ እስረኞችን ፈቶ ማሳየት አለበት፡፡ ጠ/ሚ አብይ የተቀመጡት በአቶ ኃ/ማርያም ሳይሆን በአቶ መለስ ወንበር ከሆነ፣ስለ ሰብዓዊ/ዲሞክራሲያዊ መብት ሚያወሩት ከልባቸው ከሆነ የፖለቲካ እስረኛ ፈቶ መልቀቀ የግማሽ ቀን ስራ የማይጠይቅ ቀላል ጉዳይ ነው፡፡ይህን ካላደረጉ የተቀመጡት በአቶ ኃ/ማርያም እንጅ በአቶ መለስ ወንበር ላለመሆኑ አስረጅ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ወንበር የተቀመጠ ሰው ደግሞ የስልጣን ጥሙን ከማርካት በቀር አንዳች አይፈይድምና የሚናገረውን ቀነስ አድርጎ ስልጣን ላይ የመወዘት ስሜቱን ማጣጣም ብቻ ነው ያለበት- ንግግር ዕዳ ነዋ!

ስለ ዲያስፖራው በተነናገሩበት ንግግር ይህን ተናግረው ነበር “ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው።…….አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሃገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሃገራችሁ ቁጭት ሳይሰማቹ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። …..ይሄንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሀገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሃገራችሁ መመለስና ሃገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን።” ኤርሚያስ አመልጋን፣ አቶ ገብረየስ ቤኛን፣የሆላንድ ካርስ ባለቤትን፣ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን መጨረሻ ያየ በዚህ ንግግር ላይ ልብ ለመጣል እነዚህ ሰዎች በስም ተጠርተው በይፋ ይቅርታ ተጠይቀው፣ በደላቸውን በግልፅ ተናግረው ወደ ነበሩበት ቢዝነስ ይገቡ ዘንድ መልካም ፈቃዳቸው እንዲሆን መለመን አለባቸው፡፡ በአንፃሩ ኤርሚያስ አመልጋ ማዕከላዊ መንገላታቱ ሳያነስ ለዚህ ሁሉ የዳረገውን ጠመንጃ ታጣቂም፣ ነጋዴም፣ደላላም የሆነ ባለጊዜ ስም ለመጥራት ሲቸገር በጆሯችን ሰምተናል፤ መበለዱ ሳያንስ ልውጣ እያለ የሚተናነቀውን እውነት፣ ውስጡን የሚያብሰለስለውን በደል ለመዘርዘር ድጋሜ የመታሰር ስጋት ሲወረው አይተናል፡፡ እውን ዶ/ር አብይ የሚመሰርቱት ስርዓት ኤርሚያስን ለዚህ ያበቁ ባለጊዜዎችን የመጋፈጥ ጉልበቱ ካላቸው የኤርሚያስ እውነት ተፍረጥርጦ ይውጣ! የሃገራቸውን ህዝብ ለማገልገል ባህር አቋርጠው የመጡትን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡ ይህ የመለወጥ ምልክት ሆኖ ሌላውን ሊጠራ ይችላል እንጅ ዝም ብሎ ኑኑ ማንንም አያሳምንም፡፡

“በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡” የሚለው የንግግራቸው ሌላ አንጓ ብረት አንጋች ተቃዋሚ ስደተኛ ወገኖችን ይጨምር አይጨምር ከንግግሩ ፍንጭ ማግኘት አይቻልም፤ ሰውየውን አግኝቶ በጉዳዩላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ለማድረግም በሃገራችን ያለውን የመሸዋወድ፣የማድበስበስ እና የማሞኘት ፖለቲካ ከሚያገለግሉ የመንግስት ሚዲያዎች ሚጠበቅ አይሆንም፡፡ሆነ ሆኖ ዲያስፖራው የኢትዮጵያ መንግስት ከሃገር ልጅ ወገንነቱ ይልቅ ዶላሩን አጥብቆ እንደሚወድ አሳምሮ ያውቃል፡፡ መንግስት የዲያስፖራውን ዶላር የሚወደውን ያህል ዲያስፖራው ደግሞ የሃገሩን ፖለቲካዊ ፈውስ አጥብቆ ይሻል፡፡በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኛውን ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አፍኖ አምጥቶ አላየሁም ከማለት ጀምሮ በዘመድ ወዳጅ አላስጎበኝም እስከማለት በደረሰ ጭካኔ እና መገመት በማያዳግት የሲኦል ኑሮ ውስጥ ካስቀመጠ ወዲህ የኢትዮጵያን መንግስት አያሳየኝ ብሏል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ልጆቻቸውን በትነው፣ሞቀውን ከተማ ለንደንን ደህና ሁኚ ብለው ወደ ትጥቅ ትግል ለመውረድ የወሰኑት ዲያስፖራው በአንድ ስብሰባ ላይ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ የምን ትግል ነው የምታወሩት?” ካላቸው ቀን ጀምሮ እንደሆነ በወያኔ እጅ ሳይወድቁ ተናግረዋል፡፡ የትጥቅ ትግል በዞረበት ዞሮ የማያውቅ ይመስል የትጥቅ ትግልን እንደ ሰይጣን ስራ የሚያወግዘው ህወሃት/ኢህአዴግ ታዲያ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በረሃ ያበረረው አላማ ዶላሩን የሚናፍቁት አብዛኛው ዲያስፖራ አማራጭ ከማጣት የተነሳ የሚጋራው መንገድ እንደሆነ ቢያውቅም ማመን አይፈልግም፡፡ ጠ/ሚ አብይም ይህን የህወሃት ሃሳብ እንደሚጋሩ ከሰሞኑ ‘እኛን የሚጠላን ፌስቡክን ብቻ የመረጃ ምንጭ ያደረገው አንድ ፐርሰንቱ ዲያስፖራ ነው’ ባሉት ንግግራቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል እንዲህ ያለውን ነጭ ክህደት እየካዱ በሌላ በኩል ደግሞ ኑ እንግባባ ማለት እንዴት አብሮ ይሄዳል? የውጭ ምንዛሬ ድርቅ የመታው የኢህአዴግ መንግስት ከዲያስፖራው ጋር ለመታረቅ ሳይሆን የጥል ግድግዳን በጣም በመጠኑ ለማቅለል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ነገ ዛሬ ሳይል መፍታት አለበት፡፡

የኢህአዴግን መንግስት የሚቃዎሙ ተቃዋሚዎችን እና በአውራ ነኝ ባዩ ኢህአዴግ መካከል ስለሚኖረው መስተጋብር በተመለከተ በሰነዘሩት ንግግርም ይህን ብለዋል “ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ ስለሰላምና ፍትህ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡” ይሄ ተቃዋሚዎችን እንደ ወንድም እና ባለ አማራጭ ሃሳብ ሃገር ወዳድ እንጅ እንደጠላት አናይም በሚለው ጠ/ሚ አብይ ንግግር የጠረጠርኩት የኢህአደግን መቀየር ሳይሆን የጠ/ሚውንየአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፅንሰሃሳብ ግንዛቤ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተቃራኒው የቆሙትን ቀርቶ አጋር ድርጅት ብሎ በፓርላማ እጃቸውን እያስወጣ የፈለገውን ህግ እንዲተገብር የሚያደርጉትን አጋር ድርጅቶች እንደሌላ አይቶ ከዋነኛ ስልጣን እጣፋንታ የሚከለክል አግላይ ድርጅት ነው፡፡

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተቃዋሚዎችን መጥፋት ያለባቸው እኩዮች አድርጎ ያያል፣በፀረ-ሰላምነት ይከሳል፣በሃገር ካጅነት ይወነጅላል፡፡ የተቃዋሚዎች መኖር በደሜ በላቤ አመጣሁት የሚለው ልማታዊ መንግስት ተረገግቶ የማቱሳላን እድሜ እንዳይገዛ የሚያደርግ ተደርጎ ይታሰባል-በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወግ፡፡ ልማታዊው የኢህአዴግ መንግስት ማንም ሳይረብሸው ከዚህ በኋላ ለሃምሳ አመት ወንበሩላይ ተረጋግቶ ቁጭ ብሎ፣በአንድ ልቡ ልማቱን ማስቀጠል እንደሚፈልግ ከ1997 በኋላ ሳያፍር የሚያወራው የፖለቲካ መስመሩ ነው፡፡ አውራ ፓርቲ እና ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚሉትን ተግተልታይ ቃላት የወለደው ይሄው ረዥም ዘመን ስልጣን ላይ የመሰንበት እቅዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነፍስ ያላቸውን ተቃዋሚዎች መንጥሮ ወንበሩን ለክፉ ከማይሰጡ ፌዘኛ ተቃዋሚ መሰል ቤተ-ዘመዶች ጋር ማዝገሙን መርጧል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እውነተኛ ማንነት ይህ ሆኖ ሳለ ጠ/ሚ አብይ ይህን ዲስኩር የሚያሰሙት ወይ ራሳቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲን በውል አያውቁትም ወይ ለተቃዋሚዎች ከልክ በላይ የወረደ ግምት አላቸው፡፡ “በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ” የምትለዋ ሃረግ ምናልባት የሃገርቤቱንም የውጭ ሃገሩንም ተቃዋሚ የመጥራት አላማ/ተግባር ካላት ነው ኢህአዴግ እውነትም ተቃዋሚን እንደ ባለ አማራጭ ሃይል ወስዷል ማለት የሚቻለው፡፡ ይህ ደግሞ ገና ሃምሳ አመት ስልጣን ላይ ሊወዘት ባሰበ ፓርቲ የሚደረግ ነገር አይመስለኝም!

ተዝካሩ ስለተበላው የሃገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ እና እንደማይሆን ሆኖ የተበላሸው የፍትህ ስርዓታችንን እንደቀላል ነገር እናስተካክላለን ሲሉ ቃል የገቡበትን ንግግር በተመከተ ፈጣሪ ይርዳዎ ብሎ ከማለፍ በቀር ምንም ማለት አልችልም፡፡ ይልቅስ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው።” ወዳሉበት ንግግር ልለፍ፡፡ እውነት ነው ሙስና የሃገራችንን ህዝብ አማሯል ግን ነገሩ የሚጠፋው እሳቸው እንዳሉት የምንችለውን በማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ሙስና የሚሞተው ራሱ የእሳቸው ፓርቲ ሲሞት ብቻ ነው፡፡ የነገሩ ጥልቀት እና ስፋት ከእርሳቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ አቅምም በላይ በሆነ ሁኔታ በጠመንጃ ታግዞ የሚደረግ ሥሩ ጠለቅ፣ አሰራሩ ረቀቅ ያለ ወንጀል ነው፡፡ ሙስናን እናጥፋ ከሚለው ንግግራቸው ጋር ያለው ሌላ ወለፈንዲያዊ ንግግር ይህ ነው “ትናንት የተፈጠረን ሃብት ከሌላው በመቀማት ሂሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም። ገበታው ሰፊ በሆነበት፣ ሁሉም ሰርቶ መበልጸግ በሚችልበት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት ይለም። ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና ሀገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና እጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና እንትጋ።” ትናንት የተፈጠ ሃብት ማለት የነማን ሃብት ነው?ይህን የሚሉት ለማን ‘የተረጋጉ’ ዋስትና ለመስጠት ነው? በአሁኗ የሃገራችን ሁኔታ ሚበዙቱ ባለሃብቶች ከጤናማ የንግድ ስርዓት በተፋታ የሙስና መንገድ በአንድ ቀን ሰማይ ጠቀስ የሃብት ማማላይ የሚወጡቱ እንጅ በጤናማ የንግድ ስርዓት፣በእውቀት ላይ በተመሰረተ ንግድ ለፍተው ሃብት የሚያከማቹት መጨረሻቸው አይምርም፡፡ እና ‘ትናንት የተፈጠረ ሃብት በመቀማት ሂሳብ ማወራረድ’ ማለት ምን ማለት ነው? ዘርፎ ቱጃር የሆነው ሁሉ በዘረፈው ምስኪን ህዝብ ከሲታ ኢኮኖሚ እያላገጠ ያለተጠያቂነት ይኑር ማለት ነው? “ወቅቱ የፈጠረው ልዩ አጋጣሚ” ያሉትስ ቢሆን እነዚህን ደራሽ ቱጃሮች ያገለግል ይሆናል እንጅ ለሌላው ህዝብ ምን ፈይዶለታል? ራሱ ወቅቱ የፈጠረው ልዩ አጋጣሚ ማለት ምን ማለት ነው? ስለ የቱ አጋጣሚ ነው የሚናገሩት? ‘እንዲህ ስላሉት ሰዎች ብዙ ሳትመራመሩ ያው በገሌ እያላችሁ ኑሩ’ መሰለኝ አባባሉ! እንዲህ ባለው ንግግር እና “አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እና የተደራጀ ሙስናን፣ መላው ህዝባችንን በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን።” ሲሉ በጠቀሱት ሙስናን የመዋጋት ጥሪ መሃከል እንዴት ያለ ግንኙነት አለ? ነው ሞስነው ግን ገና ሃብት ያልመሰረቱት አዲስ ጅቦች ላይ ነው ትኩረታቸው? እንዲህ የማይገናኝ ነገር ከማውራት አቅማቸው የማይፈቅደውን፣ከማይጋፉት ባለጋራ ጋር የሚያላትማቸውን የሙስናን ነገር አለማንሳት ነበር የሚሻለው-ልክ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ትንፍሽ እንዳላሉት!

በመጨረሻም “ዘረኝነትና መከፋፈልን ከአገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!” ሲሉ ጥሩ ነገር አምጥተውዋል፡፡ ግን ይህም የተነገረው ኦሮሞነታቸው ወደስልጣን ጎትቶ ባመጣቸው ሰው በመሆኑ የሃሳቡ ሞገስ ይኮሰምናል፡፡ ከምክንያታዊነት ጋር አንዳች ተዛምዶ በሌለው የጎሳ ፓርቲ ውስጥ ተቀምጦ፣ዘርን ብቻ ቆጥሮ ስልጣን ላይ ከተሰየሙ በኋላ ዘረኝነትን ከሃገር እናጥፋ፣ምክንያታዊነትን ከሰማይ እናውርድ ማለት የተናጋሪውን ጤንነት ወይም ቅንነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነገር አለው፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here