spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትአስገድዶ መድፈር እና የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት በኢትዮጵያ እስርቤቶች የማሰቃያ ዘዴ...

አስገድዶ መድፈር እና የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት በኢትዮጵያ እስርቤቶች የማሰቃያ ዘዴ ነውን? በፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ

አስገድዶ መድፈር እና የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት በኢትዮጵያ እስርቤቶች የማሰቃያ ዘዴ ነውን?የህሊና እስረኞች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና ሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች በእስርቤት ስለመሰቃየታቸው ጠቋሚ ማስረጃ

የህሊና እስረኞች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና ሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች በእስርቤት ስለመሰቃየታቸው ጠቋሚ ማስረጃ

በፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ
ሚያዚያ 24 2010 ዓ ም

አጠቃሎ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ወንድና ሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሕሊና እስረኞች እና ታዋቂ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እያሉ በአስገድዶ መድፈር የማሰቃያ ዘዴ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ጉዳቱ ምን ያህል ይዘወተር ስለመሆኑ በትክክል ባናውቅም፣ ከዚህ ቀደም እስረኛ ከነበሩ ሰዎች መካከል ያጋጠማቸውን በማጋለጥ ረገድ ጥቂት ፈቃደኞች አልታጡም።አስገድዶ መድፈር፣ የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት ወይንም እንዳይሰራ ማድረግ እና ግብረ ሰዶማዊ ደርጊቶችን ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃት መፈፀም በተመለከተ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ይደረጋል ከሚባለው ጥቃት በታች ነው የሚነገረው።ሃፍረት፣ ጭንቀትና የጥፋተኝነት ስሜት መገለጫቸው በሆኑ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ (Callender & Dartnall 2011)1ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል ጥቃቱን አስመልክቶ በወንዶች የሚገለጸው ከሴቶችና ልጃገረዶች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ጥናት ተፈጽሟል የተባለውን ጥሰት በመመርመር ረገድ የግለሰብ መረጃዎችንና ገጠመኞችን የበማስረጃነት/በፍንጭነት ይጠቀማል፡፡ ጭብጡ እንደሚያመለክተው የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት እና አስገድዶ መድፈር የሚካሄደው የጥቃቱ ሰለባዎችን ተቃውሞ ለማፈንና ለማዋረድ ነው፡፡ ይህ ጥናት የአባላዘራዊ አካልን መጉዳት፣ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ሌሎች በእስርቤቶች የሚታዩ አስነዋሪና የጭካኔ ድርጊቶችንና ኢ ስብዓዊ አያያዞች ጉዳይ አሳሳቢነት የአለምአቀፉ ህብረተሰብ እና በአካባቢው ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአስቸኳይ በአንክሮ እንዲያጤኑት አስፈላጊነቱን ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መገመት የሚቻለው ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ የሚያደርሰውን ሰብዓዊ ኪሳራና ከጥቃቱ የተረፉትን መገለል የሚመለከተውን ብቻ ነው፡፡

ማጠቃለያና ቀዳሚ መደምደሚያ

ይህን በተመለከተ ፕሮጀክቱ በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ሥራ ማስቀመጥ የምንችለው መደምደሚያዎች ሊቀየሩ እንደሚችሉ ነው፡፡ የህሊና እስረኞችን፣ ጋዜጠኞች እና የተቃዋሚ ድርጅት አባላት እስረኞችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የእስርቤቶች ሃላፊዎችና መርማሪዎች አግባብነት የሌለው የምርመራና የእስረኞች አያያዝ ዘዴ ስለመጠቀማቸው ለብዙ ዓመታት በስፋት ሲወራ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት(ሁሉም ዓይነት) ነውር ቢሆንም፣ እስረኞች ግን ለማይነገርለት ጥሰት መጋለጣቸው ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ጊዜም ህዝቡ እንዲያውቀው ማድረግም አይቻላቸውም፡፡ የዚህ አሰቃቂ ድርጊት የማሰቃያ ዘዴዎች ደግሞ አስገድዶ መድፈርና የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት ናቸው፡፡ አግባብ ያልሆኑት ዘዴዎች ወሲባዊ ብቻ አይደሉም፡፡ ድርብ ድርብርብ ናቸው፡- ውሃ ማስጠማት(ሰውነት ውስጥ ያለ ፈሳሽ እንዲሟጠጥ ማድረግ)፣ ምግብ መከልከልና በብቸኝነት አግልሎ ማቆየት፤ መሠረታዊ ህክምና መከልከል፤ ለዕርዳታ የሚያቃስቱ ድምፆችን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት እንዲሁም የተለያዩ ዓይነቶች የሥነ-ልቦና ሰለባ ዘዴዎች ይገኙባቸዋል፡፡

የዚህ ጥናት ዓላማዎች፦ (ሀ)የአስከፊውን ድርጊት ደረጃ መረጃ መውሰድ፣ (ለ)የህብረተሰብ ግንዛቤን መፍጠር፣ (ሐ)የጉዳቱን ሰለባዎች ማገዝና (መ)በህይወት ያሉ ተጠቂዎች የደረሰባቸውን በደል ለተመራማሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲናገሩና እንዲያካፍሉ ማበረታት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተጠቃሽ ፍትህ ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ ይህ መረጃ የማሰባሰብና የማጠናቀር ተግባር የጉዳቱ ሰለባዎች ለዓለም አቀፉ የፍትህ ዘዴዎች ዕድል እንዲያገኙ በማገዝ ረገድ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ተጠቂዎች ክስ መሥርተው እና በወንጀል ክስ ሂደት ወሲባዊ የማሰቃያ ዘዴ በሥራ ላይ እንዲውል ትዕዛዝ የሰጡና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ይቻላቸዋል፡፡ በበርካታ ሂደቶች እንደታየው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፌደራል የፍትህ ተቋም እንደነዚህ ዓይነት ወንጀሎችን ለመክሰስ ነፃነቱና ብቃቱ ይጎድለዋል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፉ ሥርዓት የወንጀል ክሱን በመከታተል 2 ረገድ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው ተስፋ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

ከላይ የተቀመጡትን ዓላማዎችና ግቦች በማሳካት ረገድ ብዙ ተግዳሮቶች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪያው የተዓማኒ መረጃ ወይም ፍንጭ መጓደል ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ተጠቂዎች የደረሰባቸውን ስቃይ እንዲናገሩ ማግባባቱ አዳጋች በመሆኑ በዘገባው ላይ የሚካተቱ አብዛኛዎቹ ማስረጃዎችና ጭብጦች ስለችግሩ ከሚነገረው የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ ተጠቂዎች ያጋጠማቸውን በዝርዝር ለማካፈል ፍላጎቱ የሌላቸው በመሆኑ የተወሰኑት ዘገባዎች ትክክለኛነት ይጎድላቸዋል፡፡ ሁለተኛው ተግዳሮት ደግሞ በረቀቀ ዘዴ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ማረጋገጥ መቻሉ ላይ የሚመሰረተው ነው፡፡ “ዛዋቲ (Zawati)“ እንደተመለከተው “ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ህግ እንደሚገልጸው ወሲባዊ ጥቃት በሰዎች ላይ የሚፈጸም ወንጀል የሚሆነው በረቀቀ ዘዴ ስለመፈጸሙ ተጠቂዎቹ ማረጋገጥ ሲችሉ ነው”፡፡ 3 በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ እነዚህን የግፍ ድርጊቶች መመልከት ያለብን በአካሄዳቸውና በአጠቃላዩ ፖሊሲ የተካተቱ ወይም በተከታታይ የኢሰብዓዊነት መገለጫዎች ወይም ይልቅም የተለዩና አልፎ አልፎ የሚፈጸሙ ጭካኔዎችን ያካተቱ ስለመሆናቸው በማረጋገጥ ነው፡፡ 4 በዚህ ጥናት ውስጥ የሚገኘው ውሱን ጭብጥ የጭካኔ ድርጊቶቹ የታቀዱ፣ ሥርዓታዊ፣ ሂደታዊና የትም የሚታዩ(የሚፈጸሙ) መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ የትም የሚታዩ የሚለው ተሟጋቾችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት በታሰሩባቸው በሁሉም እስር ቤቶችና በማንኛውም ጊዜ ጥቃቶች የሚፈጸሙ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ የፀረ-ሽብር አዋጁ (አዋጅ ቁጥር 652/2009) 5 ተቃውሞን ለመደምሰስን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፀጥ ለማሰኘት የሚያገለግል መሣሪያ ነው፡፡ አዋጁ የመናገር ነፃነትን የሚገታ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው፡፡

ይህንን ተከትሎ የሚፈጠረውም ውጤት የጋዜጠኞችና የተቃዋሚዎች ሰቆቃ በመሆን መሠረታዊ መብቶችን በማራመዳቸው ብቻ ለእስር የሚዳርጋቸው ነው፡፡ መንግሥትም ከሃዲዎችና አሸባሪዎች የሚል መለያ ለጥፎባቸዋል(ድሪቶ ደርቶባቸዋል)፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው በእስር ቤት ውስጥ አስነዋሪና ጭካኔ የተመላባቸው ማሰቃያዎች ተግባር ላይ ይውላል፡፡ ይህ አግባብነት የሌለው ድርጊት የሚፈጸመው ሰለባዎቹን ለማዋረድና ሌሎችንም ለማስፈራራት ነው፡፡

ወሲባዊ ጥቃት በራሱ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትላቸው ሌሎች ጎጂ ውጤቶችም አሉት፡፡ ከሚጠቀሱትም መካከል አካላዊ ጉዳት፣ ሥነ-ልቦናዊ መንቋሸሽ፣ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ተስፋ መቁረጥና መረበሽ፣ ያሳለፉትን ስቃይ በማስታወስ የሚፈጠሩ ሌሎች ጉዳቶች የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ሥነ-ልቦናዊና ሥነ-አዕምሯዊ ህክምና፣ የምክርና ችግራቸውን በመረዳት ልባዊ ተቆርቋሪነት ርህራሄ የማሳየት ድጋፍ መስጠት ባልተለመደበት እንደኛ ባለ ሃገር ተጠቂዎቹ ህይወታቸውን እንደገና ለማቋቋምና በማህበራዊ ሙሉነት ለመንቀሳቀስ እና አዕምሯዊና አካላዊ ብቃት ያላቸው ዜጎች ለመሆን በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ 6 በባህላዊ ዕምነትና በጥብቁ ልማድ ምክንያት የችግሩ ተቀጽላ በተለይ በወንድ ሰለባዎች ላይ ውስብስብ ሊሆን ይችላል፡፡7,8

የዚህ ጥናት ዋንኛ ነፀብራቅና በአመዛኙ ያልተጠበቀ የሚሆነው በኢትዮጵያውያን መካከል የተሰራጨው ጭምጭምታና የመንግሥት ወኪሎች በእስር ቤቶች ውስጥ ግብረ ሰዶምንም እንደ ተጨማሪ ማሰቃያ ዘዴ መጠቀማቸውን የሚገልጸው ነው።የዚህን ጭምጭምታ ተጨባጭነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርምርና ክትትል ያስፈልጋል፡፡ 9 በአሁኑ ጊዜ ያሉት መረጃዎች በጣም ውሱንና የተበታተኑ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ነውረኛነትና ጭካኔ፣ ጎጂ አያያዝና የመሳሰሉት ሌሎች የጾታዊ(ወሲባዊ) እንግልት ድርጊቶች በመረጃነት ተይዘዋል።

ከእስር የተፈቱት የዋልድባ መነኮሳት ከቪኦኤ ጋር ሚያዝያ 12 ቀን 2010 እ. ኢ. አ. (20 April, 2018) ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ይኸንን ከላይ የቀረበውን በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የማሰቃያ ዘዴዎች መንደርደያ ጥናት በከፊል ያጠናክራል። 10

የግርጌ ማስታወሻዎች

1 Callender, T. and E. Dartnall (2011) “Mental health responses for victims of sexual violence and rape in resource poor settings.” SVRI Briefing Paper, Sexual Violence Research Initiative, Medical Research Council, Pretoria, South Africa (e-version).

2 http://justiceforiran.org/english-sexual-abuse-and-torture-of-politically-active-women-in-prisons-crimes-against-humanityshadi-sadr/?lang=en

3 Zawati, Hilmi (2007) “Impunity or immunity: wartime male rape and sexual torture as a crime against humanity.” Torture, 17(1): 27-47.

4 http://www.iranhrdc.org/english/human-rights-documents/ngo-reports/justice-for-iran/3398-sexual-abuse-and-torture-of-politically-active-women-in-prisons-crimes-against-humanity-shadi-sadr.html

5 https://chilot.me/2011/01/a-proclamation-on-anti-terrorism-proclamation-no-6522009/

6 Noll-Hussong, Michael et al. (2010) “Aftermath of sexual abuse history on adult patients suffering from chronic functional pain syndromes: an fMRI pilot study.” Journal of Psychosomatic Research, 68: 483-487.

7 Lewis, Dustin (2009) “Unrecognized victims: sexual violence against men in conflict settings under international law.” Wisconsin International Law Journal, 27(1): 1-50.

8 Sorsoli, Lynn et al. (2008) “ ‘I keep that hush-hush:’ male survivors of sexual abuse and the challenges of disclosure.” Journal of Counselling Psychology, 55(30): 333-345.

9 Walker, Jayne, John Archer and Michelle Davies (2005) “Effects of rape on men: A descriptive analysis.” Archives of Sexual Behavior, 34 (1): 69-80.

10 https://amharic.voanews.com/a/saldeba-gedam-monaster-and-monks-4-20-2018/4358320.html

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here