advertisement
ቦርከና
ሚያዚያ 26 2010 ዓ.ም
በደቡብ አፍሪካ ከጆሃንስበርግ ከተማ 28 ኪሎሜትር ገደማ በስተደቡብ ምስራቅ በምትገኘው የቶኮዛ ከተማ 48 ሰዓት ባልሆነ ጊዜ ውስጥ ሰባት ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ ተሰማ::
ኢሳት ከአካባቢው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አመራሮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ግድያው የተፈጸመው ትላንት አኩለ ሌሊት ላይ ነው:: ሰለባዎቹ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ እንደነበሩ ሱቆች እንደነበሯቸው እና ከግድያው በኋላ ንብረታቸው እንደተዘረፈም ታውቋል::
ግድያውን ያደርሱት የተደራጁ የሚመስሉ ዘራፊዎች እንደሆኑ ቢታመንም ፤ ግድያው ሙሉ በሙሉ ከዘረፋ ጋር የተያያዘ ለመሆኑ የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ እና ጉዳዮ በምርመራ ላይ እንዳለ ኢሳት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ የሆኑንት አቶ ታምሩ አበበን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል::
በተያያዘ ዜና የዛሬ ሳምንት ገደማ በቅጥር ነብሰ ገዳይ የተገደለው አፍቃሪ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ ተሟጋች ገዛኸኝ ገብረመስቀል ግድያው በተቀነባበረ ሁኔታ ለመፈጸሙ ስም መግለጽ ያልፈለገ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አባል ተናግሯል፤ ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ ሜይል ኤንድ ዘጋርድያን ሚዲያም በግድያው ላይ ሰፊ ዘገባ ይዞ ወጥቷል::