spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትአቶ አንዳርጋቸው ጽጌንም፤ እኛንም ፍቱን (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንም፤ እኛንም ፍቱን (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ -አሜሪካ)

ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
አሜሪካ
ግንቦት 14 ፤ 2010 ዓ.ም

“አንድ ኢትዮጵያዊ ታሰረ ማለት፤ ኢትዮጵያ ታስራለች ማለት ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ።

የኢትዮጵያን መንግሥት በጠመንጃ አፈሙዝ የተቆጣጠረው የወያኔ መራሹ ገዥው ቡድን፤ 27ኛ የሥልጣን ዘመኑን ሊያስቆጥር የቀሩት ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው። ገዥው ፓርቲ ገና ከመነሻው ይዞ የመጣው አደገኛ የዘር ፖለቲካና ለ27 ዓመታት ሲከተለው የቆየው ‘የከፋፍለህ ግዛ‘ አደገኛ መርህ፤ ሃገራችንን ከማትወጣበት የችግር አረንቆ አፋፍ ላይ ሲያደርስ፤ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ባልበገር ባይነት የተንቀሳቀሰው ሕዝብ፤ በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶች በከፈሉት ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ፤ ከ27 ዓመታት ግፍና ስቃይ በኋላ፤ እነሆ ጨለማው የመገፈፍና ብርሃን የመፈንጠቅ አዝማምያ እያየን ነው። ዛሬ ሃገራችን ለፈነጠቀላት ተስፋና አዲሱ “የእርቅና የሰላም ፍልስፍና” ከፍተኛ ዋጋውን የከፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ያጠላበት የስጋት ጉም እየተገፈፈ እፎይታ እየተነፈሰ ቢሆንም፤ ከእስር የመፈታቱ ጽዋ ያልድረሰንና፤ ገዥው ፓርቲ የሰነዘረብን የጥቃት በትር ገና ያልተመከተልን ዜጎች ግን ከስጋቱ አልተላቀቅንም።

ወቅቱ አዲስ ነው፤ ቀደም ሲል ገዥው ፓርቲ ያቀነቅን የነበረው የጥላቻና የዘር ፖለቲካም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፤ ከኢትዮጵያ ምድር ሊወገድ፤ ወደ ከርሰ መቃብሩም ሊገባ እየተቃረበ ለመሆኑ በርካታ ምልክቶች ፈጠው ይታያሉ። ከጥላቻ ፖለቲካ ወደ ፍቅር ፖለቲካ፤ ከትዕቢት ወደ ትሕትናና የእርቅ መንፈስ ወደ ሚሰብኩ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተሸጋግረናል። “ከመሪነት ዙፋኑም” ተቀምጠው የሚናገሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከቀድሞው የገዥው ፓርቲ አመራሮች በተለየ፤ ከዘለፋና፤ ከድንፋታ ይልቅ፤ በሳል የሆኑ፤ ትልቅ ራእይ ያዘሉ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ ማዳመጥ፤ በሕዝቡ ስሜት ውስጥ የጫረው ድስታና ተስፋ ለዓመታት ያላየነው እና ያልጠበቅነውም ነው። ብዙዎቻችን እኝህ ሰው የት ነበሩ? ብለን እንድንጠይቅም አድርጓል። ፍጹም ቀናነት የተላበሰው በጎ ሃሳባቸው፤ የብዙዎቻችንን ልብም አሸንፏል ለማለት ያስደፍራል። በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተደረገ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት “የምሁራን ስብሰባ” ላይ፤ አንድ የዩኒቨርስቲው መምህር፤ አቶ መለስን ‘ከእርሶ የሚጠበቀው ቀናነት ብቻ ነው፤ እርስዎ ቀና ከሆኑ፤ ብዙ ነገር ይስተካከላል’ ሲሏቸው አድምጬ ነበር። አቶ መለስ ግን ያንን ምክር ባለማዳመጣቸው፤ ለዓመታታ በርካታ ዜጎች በእስር ማቀቁ፤ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችም ሕይወት ተቀጠፈ፤ ብዙዎችም ተሰደዱ።

በአቶ መለስ ዘመነ መንግሥትም ሆነ፤ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ዘመነ መንግሥት” በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥና በጋዜጠኝነት ሙያ ጉልህ ሚና ያላቸው ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን፤ በሃገር ውስጥ ታስረው ከመስቃየታቸውም በላይ፤ ብዙዎች ደግሞ ታስረው በስቃይ ከኖሩበት እስር ሲወጡ፤ የተሰደዱና፤ ከመታሰራቸውም በፊት ለስደት የተዳረጉ በርካታዎች አሉ። በስምና በዝና የሚታውቁት ብዙዎቹ እንዲፈቱ፤ ብዙዎቻችን ለዓመታት ስንጮህ፤ በሃገር ውስጥ ያሉ በርካቶች ደግሞ፤ በአደባባይ ወጥተው ሰልፍ በማድረግና፤ በተለያየ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመሳተፍ፤ እና ለዚህም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው፤ ሌላውንም ሕዝብ በዚህ የትግል እንቅስቃሴ ለማሳተፍ በመቻሉ እና፤ የገዥው ፓርቲም የሥልጣን ብልግናና ጭካኔ ከልክ በማለፉ፤ ከውስጣቸው “በቃ” ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች በማስነሳት ትግሉ ፍሬ አፍርቷል። ገዥው ፓርቲም ሳይወድ በግዱ፤ ለዓመታት የሰራቸውን ግፎች ለማመንና ሕዝቡንም ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ገዥው ፓርቲ “የሃገሪቱ ነቀርሳ” በመሆን በሰራቸው ስህተቶች፤ እና፤ የሰላም የትግል መድረኩን በማጥበቡ ምክንያት፤ ሃገርን ለማዳን፤ ሕዝቡን ለመታደግ፤ የሃገራቸው ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያውያን ከሰላማዊ አማራጭ ይልቅ፤ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለዋል።

ገዥው ፓርቲ በውጭና በሃገር ውስጥ፤ በሕዝብ በተፈጠረበት ከፍተኛ ግፊት፤ በራሱ ውስጥ ለውጥ ለማድረግ እየተውተረተረ ነው። እስካሁን ድረስ ጥገናዊ ለውጦች ቢታዩም፤ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ትግሉ ቀጥሏል። ከዚህ የፖለቲካ ትርምስ፤ ከገዥው ፓርቲ ውስጥ የወጣው “የሰላምና የእርቅን መንፈስ የያዘ ቡድን” ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ በማግኘቱ፤ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳማጥ በተቻለው መጠን ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመሰጠት እየሰራ ነው። ገዥው ፓርቲ በሃገርና በሕዝብ ላይ የሰራውን ግፍ ሲናዘዝ፤ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ በገባው ቃል መሰረት፤ በሕዝብ ግፊት በርካታ እስረኞችን ፈቷል። በሺህ የሚቆጠሩ በስምና ዝና የማይታወቁ በርካታ እስረኞች ግን በየክልልና ፌደራል እስር ቤቶች አሁንም እየማቀቁ ነው። ሕዝቡ በስም ከሚያውቃቸውና፤ ከእስር እንዲፈቱለት ከጠየቃቸው ጀግኖቹ እስረኞች መካከል፤ አንጋፋው ታጋይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኛሉ።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቀደም ሲል ለሃገሬ በጎ ነገር አበረክታልሁ በሚል፤ ከገዥው ፓርቲ ጋር ይሰሩ ነበር፤ የገዠው ፓርቲ የጥፋት መንገድ ስለታያቸውና ለመታረምም ዝግጁ እንዳልሆነ በመረዳታቸው፤ ከገዥው ፓርቲ ወጥተው፤ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ትግላቸውን ቀጠሉ፤ ምርጫ 97 ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ተስፋ እንዲፈነጥቅ በማድረጉ፤ አሁንም ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲን በመቀላቀል፤ በሰላማዊ ትግሉ ለሃገራቸው የበኩላቸውን አደረጉ። ገዥው ፓርቲ ግን ለራሱ ሕግና፤ ሕገ መንግሥት ለመገዛት ዝግጁ ያልሆነ፤ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ ለማስረከብ ያለፈቀደ በመሆኑ፤ ምርጫ 97ን አጭበረበረ፤ በርካታ ብርቅዬ ዜጎችንም ለእስርና ለሞት ዳረገ። በገዥው ፓርቲ ግፍ ተስፋ በመቁረጥ፤ አቶ አንዳርጋቸው እንደገና ተሰደዱ። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ በሃገር ውስጥ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ብለው ድምዳሜ ላይ በመድረስ ነበር፤ ወደ ትጥቅ ትግሉ ዝንባሌ የተደረገው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን፤ ለሃገር ክብርና ለሕዝብ ነጻነት፤ ሕይወታቸውን ለመገበር ቆርጠው በመነሳት ወደ ትጥቅ ትግሉ ገቡ። ለዚህም ዋናው ምክንያት፤ የገዥው ፓርቲ ግፍ፤ የስልጣን ብልግናና፤ የሰላማዊ ትግሉን አንገት ሸምቅቆ መተንፈሻ ማሳጣት ነው።

አቶ አንዳርጋቸው እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ በስደት ሃገራቸው፤ መደበኛ ሥራቸውን እየሰሩ፤ ልጆቻቸውን ማሳደግና የግል ሕይወታቸውን መገንባት በቻሉ ነበር። ግን የሕዝቡ ስቃይ ስላንግፈገፋቸው፤ ሃገሪቱ ትከተል የነበረው አደገኛ አቅጣጫ ስላሳሰባቸው፤ የግል ኑሯቸውን፤ ቤተባቸውንና፤ የግል ምቾታቸውን ትተው፤ ኤርትራ በርሃ ገቡ። ይህንን ተከትሎም ነው፤ በገዥው ፓርቲ የስለላ ቡድን ከየመን ተጠልፈው ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱትና ለእስር የተዳረጉ።

እኝህ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ከሌሎች ከሃገር ውጭ ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር፤ በኢትዮጵያ ፌደራል ፍርድ ቤት፤ በሌሉበት ፍርድ ተፈርዶባቸውል። ብዙዎቹም ላይ የተፈረደው ፍርድ ከእድሜ ልክ እስራት እስከሞት የሚያስቀጣ ቅጣት ነው። ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ ለሃገራችን እየሰጡት ያለው ተስፋና፤ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረ እና የታገልንለት የብሄራዊ አንድነት መንፈስ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው፤ በሃገር ውስጥ ያሉ የሕሊና እስረኞች ብቻ ሳይሆኑ፤ ከሀገር ውጭም ያሉ “የሕሊና እስረኞች” ከእስር ሲፈቱ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ። ከእነዚህ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም፤ “ያለአግባበ የታሰርን” በርካታ ኢትዮጵያውያን አለን። እስከዛሬ ስለዚህ ጉዳይ ማንሳት፤ ካለው ትልልቅ ጉዳይ አንጻር ኢምንት በመሆኑ ዝም ብዬ ቆይቻለሁ።

በቅርቡ፤ ዶ/ር አብይ፤ አዲስ አበባ በሚሊንየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር፤ ዲያስፖራውን፤ ሕዝቡ መኪና ገዝቶ አስፋልት አንጥፎ ሊቀበል እንደማይችል፤ ግን ዲያስፖራው ሃገሩ ገብቶ ይስራ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ዲያስፖራው በምንም ወቅት መኪና ግዙልኝ፤ አስፋልት አንጥፉልኝ ብሎ የጠየቀብት ወቅት የለም፤ ይልቅስ፤ ልምጣና “አስፋልት ላንጥፍ” ፋብሪካ ልገንባ፤ የትምህርት እድል ላጡ ሕፃናት የትምህርት እድል ላመቻች፤ የአገልግሎት ዘርፉን ላስፋ፤ ቴክኖሎጂ ላስገባ፤ በእውቀቴ፤ በጉልበቴና፤ በገንዘቤ፤ ሃገሬን ላገልግል ነው ያለው። ከዲያስፖራው በርካታ ሰዎች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆስፒታል እንዲገነባ አድርገዋል፤ ዲያስፖራው በሚሰጠው ገንዘብ፤ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ለበርካታ ወጣቶችና ሕጻናት የትምህርት እድል እንዲያገኙ፤ ሕክምናም እንዲያገኙ አድርገዋል። ዲያስፖራው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር፤ ለወገኖቹ በመላኩ፤ ሃገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛም ምንጭ ነው።

የአብዛኛው ዲያስፖራ ጥያቄ፤ አትከፋፍሉን፤ ሕዝቡን አትግደሉት፤ አትሰሩት፤ አታሰቃዩት፤ የሥልጣን ብልግና፤ የዘር አድልዎ ሙስና ይብቃ፤ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበር፤ የሕግ የበላይነት ይኑር ነው። ይህንንም ስላልን ነው ብዙዎቻችችን፤ ረጅሙ የኢሕአዲግ እጅ ያረፈብን። የእድሜ ልክ እስራት እና ሞት ከተፈረደባቸው ዲያስፖራ ነዋሪ ክሆኑ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ፤ ፓስፖርታችንን የተከልከልንና የዜግነት መብታችንን የተነጠቅን ኢትዮጵያውያን አለን። “እናቱ የሞተችበትና፤ ወንዝ የወረደችበት እኩል ያለቅሳል” እንድሚባለው እንዳይሆንብኝ፤ ይህንን ጉዳይ አደባባይ ሳላወጣ ቆይቻለሁ። አሁን ግን ያንጋፋዎቹ እስረኞች ጉዳይ ምላሽ እያገኘ በመምጣቱ፤ የእንደ እኔ ዓየነቶቹ ደቂቃን ዜጎች ጉዳይም ትኩረት እንዲያገኝ በሚል ነው ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት፤ ከእኔ በተጨማሪ፤ ሁለት ሌሎች እኔ የማውቃቸው ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ሃገር እንዳይገቡ ታግደዋል። እኔም ፓስፖርቴን ለእድሳት ከሰጠሁ እነሆ ሁለት ዓመታት ተኩል ተቆጥረዋል፤ ዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሆነ፤ አዲስ አበባ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ላቀረብኩት ጥያቄ የሰጡኝ መልስ የለም። እኔም እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስረኛ ሆኛለሁ። እኔም ሆንኩ ሁለቱ ግለሰቦች ፓስፖርታችንን የተከለከልነው ባንጸባረቅነው የፖለቲካ አመለካከት ብቻ ነው። ሌላ ምንም ምክንያት የለም።

ዶ/ር አብይ፤ ሣውዲ ሄደው ላቀረቡት 10 ጥያቄዎች ለዘጠኙ መልስ አግኝተው መመለሳቸውን ሲያበስሩን ባደረጉት ንግግር፤ “አንድ ኢትዮጵያዊ ታሰረ ማለት፤ ኢትዮጵያ ታስራለች ማለት ነው” ብለውናል። ስለዚህ፤ አንዳርጋቸው ታሰረ ማለት ኢትዮጵያ ታስራለች ማለት ነው። እንደ እነ ታማኝ በየነ፤ ብርሃኑ ነጋ፤ ነአምን ዘለቀ፤ አበበ ገላው እና ሌሎችም ላይ የፖለቲካ ፍርድ ተፈረደ ማለት፤ ኢትዮጵያ ላይ ተፈረደ ማለት ነው። እንደ እኔ ዓይነት ደቂቃንንም ሃገራችን እንዳንገባ ማገድና “በዘዴ ማሰር” ኢትዮጵያን ማሰር ነው ብዬም እተርጉመዋለሁ። ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ አሁን የጀመሩት የፍቅር፤ የእርቅና፤ የሰላም መንገድ ከግብ እንዲደርስ፤ አቶ አንዳርጋቸው፤ ሌሎች እስረኞችና፤ እኛም ገዥው ፓርቲ ከጣለብን ኢፍትሃዊ የእስር ቀንበር እንድንፈታ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከሱዳንና ከሳውዲ እስረኛ ማስፈታት ከቻሉ፤ ሌሎቻችንንም ማስፈታት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ይህ አዲስ ጅምርም ዘላቂ እንዲሆንና የጥላቻንና የዓመጽን አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ለመስበር፤ ወደ ብሔራዊ እርቅ እንዲያሸጋግሩን የበኩሌን ጥሪ አቀርባለሁ።

___
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here