advertisement
ቦርከና
ግንቦት 15፥ 2010 ዓ.ም
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሚቀጥለው ሳምንት ከእስር እንደሚፈቱ ተሰማ። የፖለቲካ እስረኞች በተፈቱ ሳምንታት ውስጥ ጅምሮ እንደሚፈታ ሲወራ እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፈታ ወደ እርግጠኝነት የቀረበ መረጃ የተገኘው ግን በትላንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በብሔራዊ ቤተ መንግስት የትግራይ ተወላጆች ጋር የምክክር ስብሰባ ባደረጉበት ሰዓት ጉዳዮን አንስተው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰራችን የተጠቀምነው ምንም ነገር የለም ፤ ጥላቻን እና ከኢንግሊዝ መንግስት እናገኘው የነበረውን እርዳታ ነው ያጣነው” እንዳሉ በቦታው ታድመን ነበር ያሉ ሰዎች ካሰራጩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአራት አመታት በፊት በየመን ሰንዓ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በትራንዚት ላይ እያለ በየመን የጸጥታ ኃይሎች ታፍኖ ለህወሓት መራሹ መንግስት ተላልፎ ከተሰጠ ቀን ጀምሮ ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኝ ተደርጎ ለብቻው በጠባብ ክፍል ውስጥ መታሰሩ ይታወቃል።