ቦርከና
ግንቦት 21 2010 ዓ.ም
በገዥው የኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ ብዙ ውዝግብ እና ተጨማሪ ቁርሾ እንደፈጠረ የሚነገርለት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር የመፈታት ሁኔታ በመጨረሻ እልባት አግኝቶ ትላንት ተፈተው በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ወደሚገኘው የአባታቸው ቤት ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በደማቅ ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል።
ከአራት አመታት በፊት በየመን ታፍነው በደህንነት ቁጥጥር ስር በነበሩበት ጊዜ “ሰው እየሳቀ ለመብቱም ለሕዝቡም መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ” በማለት ለአሳሪዎቻቸው እንደነገሩአቸው የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ችግር አንጻር የበለጠ መስዋዕትነት መከፈል እንደሚገባ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ውርደት ከማየት ሞት እንደሚሻል ከአራት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
በጸሃፊነት ይመሩት የነበረው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ፓርቲም ትላንት “በጓዳችን መፈታት ደስ ብሎናል፤ የሚጠብቀን ብዙ መሆኑን እናውቃለን” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ከቢቢሲ የእንግሊዝኛ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እስካለ ድረስ በመቶ ዓመት እድሜም ቢሆን ፓለቲካ እንደማያቆሙ ተናግረዋል።
አንዳርጋቸው ጽጌ ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ደሞ «መታሠሬ በሕይወቴ ልጽፈው የማልችለውን መጽሐፍ እንድጽፍ ረድቶኛል። የሕዝቡ መልካም እና ደማቅ አቀባበልም አኩርቶኛል።» ማለታቸውም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባልተጠበቀ ሁኔታ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ተገናኝተው እንደተወያዮ ታውቋል ። ሆኖም የፖለቲካ ውይይት ከመሆኑ ውጭ በምን በምን ጉዳዮች ጉዳዮች ላይ እንደተወያዮ አልታወቀም ፤ አቶ አንዳርጋቸውም ጉዳዮን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እጂ በመጨባበጥ በፈገግታ የተነሱት ፎቶ ግራፍ በማህበራዊ ድረ ገጽ በስፋት ተሰራጭቷል ፤ ብዙዎችንም አስደስቷል።
በብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ልዮነትን በሰለጠነ መንገድ የምትፈታበት ዘመን መባቻ ላይ ናት የሚል እይታንም የጫረ ይመስላል።
በሌላ በኩል አፍቃሪ ህወሓት የሆኑ ፖለቲከኞች በአንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት እና ከተፈታም በኋላ በኢትዮጵያ መቆየቱ ቁጭት እንደፈጠረባቸው ከሚጽፏቸው መልዕክቶች መረዳት ተችሏል። አንዳንዶቹም እንደገና እንዲታሰር እንደወተወቱ ይነገራል።