(በመስከረም አበራ )
ግንቦት 29 ፤ 2010 ዓ.ም.
በሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች ልማድ የፖለቲከኞቻቸው ቁርጠኝት ጥግ የሚለካው ያለምንም ማገናዘብ ኢትዮጵያ መፈራረስ እንዳለባት በአደባባይ በመናገር ይመስላል፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ጠላት፣የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዝ ስብሃት ነጋ የእሱ ሰፈር ሰዎች ዘረፋ “ለምን?” በተባለ ቁጥር ኢትዮጵያ መፈራረስ እንዳለባት ይዘባርቅ ነበር፡፡ ስለ ሃገር መፍረስ ማውራት በህግ ሳይቀር የሚያስጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም የጎጥ ፖለቲከኞች ተጠራርተው የከተቡት ህገ-መንግስት ሃገር የማፍረስን ወንጀል እንደ መብት የፃፈ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም የጎጥ ፖለቲከኞች ሃገር የማፍረስን ወንጀል እንደ ደህና ነገር ተዝናንተው በየአደባባዩ የሚናገሩት፡፡
አንድ የጎጣቸው ሰው ባጠፋው ጥፋት ሲተች “ሆ..!” ብለው ለስድብ እና ለአምባጓሮ የሚጠራሩት የጎሳ ፖለቲካ ጄሌ ደጋፊዎችም መሪያቸው ስለ ሃገር መፍረስ መናገሩ አንዳች ስህተት ያለበት ነገር አይመስላቸውም፡፡ ይልቅስ ምጥቀቱ ይታያቸዋል፡፡ይሄ በብዙ መንገድ ስህተት አለው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሃገር የማፍረስ ጥሪ ወንጄል ከመሆኑም ባሻገር የሌላውን መብት መጋፋት ነው፡፡የጎጥ ፖለቲከኞች በክልላቸው፣በባህላቸው በአጠቃላይ የጎጣቸው ህልው እና ክብር ላይ አንዳች ክፉ ነገር የተነገረ ሲመስላቸው የሚሆኑት ነገር የሚታወቅ ነው፡፡ እነሱ በማንነታቸው ላይ አንዳች ክብረ-ነክ ነገር የተባለ ሲመስላቸው የሚናገሩትን እስከማያውቁ ድረስ ስሜት ውስጥ እንደሚነከሩት ሁሉ ህልውናውን ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የፈተለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ወገንም የእናት ሃገሩን መፍረስ እንደ መልካም ሙዚቃ አንገቱን እየወዘወዘ የሚያዳምጥበት ምክንያት እንደሌለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን የደመ-ነፍስ ንግግር ከመናገር በፊት ግራ ቀኝ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በሚያክል ግዙፍ ተቋም የሚያስተምር እንደ አቶ በቀለ ገርባ አይነት ሰው መምህርነትን የመሰለ ሃላፊነት ተሸክሞም ይህን መሳት የለበትም፡፡ የራስን ሲያከበሩ እና ሲያስከብሩ የሰውንም ማክበር እንጅ እግር እጅ የሚችለውን ያህል ተንጠራርቶ የሌላውን መብት እየነኩ የእኔን ብቻ አክብሩልኝ ማለት እንደ ልጅ ያስቆጥራል፣ያስገምታል፣ያስንቃልም!
የኢትዮጵያ ብሄርተኝት ጎራው በደመ-ነፍስ የማይመራ፣ዝምብሎ እያጨበጨበ የሚከተላቸው የሰፈር ሰዎች ስለሌሉት መመሪያው ምክንያታዊነት፤መዳረሻው ለሁሉም የምትበቃና የምትመች ኢትዮጵያ ነች፡፡ መዳረሻውን ላፍርስ የሚል ሰው ደግሞ አይንህን ላጥፋ፣ድካምህን ሁሉ ከንቱ ላድርግ ባይ ባላጋራ ስለሆነ እንዲህ ያለውን አካል በትዕግስት መመልከቱ ማብቃት አለበት፡፡ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሟረት ቢበዛ ያስወግዝ ይሆናል እንጅ ምንም ችግር የሌለው ነገር ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህ የሆነው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው በትንሽ ትልቁ የማያላዝን፣በራስ መተማመን ያለው፣ቶሎ የማይበረግግ ስለሆነ፣ነገሩ በጣም ከአቅም በታች ስለሆነ በንቀት ማየትን በመምረጡ ነበር፡፡
ሆኖም ሃገር ማለት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ስሜትም ጭምር ነውና ነገሩ ሲበዛ ሃይ መባል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ንቀው ዝም ሲሉት ልክ የሆነ የሚመስለው ሰው ስለማይጠፋ መሰለኝ ሃገር ትፈርሳለች የሚለው አስገማች ንግግር እንደ ደህና ነገር ተይዞ የቀጠለው፡፡ ስለዚህ በዝምታ መነጋገር ለማይችለው የህብረተሰብ ክፍል በንግግር እና በተግባር ማናገር ያስፈልጋል፡፡ በግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅቶ ኦሮሚያን እገነጥላለሁ ብሎ መነሳት፣ ለዛም መታገል እድሜ ለህወሃት ህገ-መንግስታዊ መብት ነው፡፡ መብት ያልሆነው ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት በሌላው ኢትዮጵያዊ እጣ ፋንታ ላይ ልወስን የማለት እብሪት ነው፡፡ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ሊረዱት የሚገባው አንድ ሃቅ አለ፡፡ ስለ ኦሮሚያ አዛዥ ናዛዝ ነኝ ማለት እና የኦሮሞን ህዝብ ወቅታዊ ፍላጎት ማወቅ ለየቅል ናቸው፡፡ እንደምኞታቸው ሆኖ ኦሮሚያ ላይ የማዘዝ መብት አላቸው ብንል እንኳን ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሚያ ብቻ አይደለችም፡፡ይህ ረገጥ ተደርጎ መታመን አለበት !
ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚል ሰው ትዕግስቱ ቢበቃ ደግ ነው፡፡ በበኩሌ ሃገሬን ስለማፍረስ የሚናገር ሰው የትም ይወለድ የትም ስብሃት ነጋን እና መለስ ዜናዊን ይመስለኛል፡፡ ሩቅ ሲኬድ ደግሞ ከዚያድባሬ እና ሞሶሎኒ ለይቼ የማይበት ነገር አይታየኝም፡፡ እናም ሃገሬን ለመፍረስ መዘጋጄት እንዳለባት ኮራ ብሎ የሚያወራን ሰው እንደ ጠላት ፋሽስት እንጅ እንደ ሃገሬ ሰው ላየው እቼገራለሁ፡፡ በዚህ ላይ ራሱ ከሰፈሩ ሰዎች ውጭ ያሉትን ሁሉ “ሌሎች” ብሎ የጥላቻውን መንገድ እስከ ከፈተ ድረስ በግድ ውደደኝ፣ወገንህ አድርገህ ቁተረኝ ብየ በአንድ ወገን ፍቅር የምቸገርበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ይሁን ቢባል እንኳን የአንድ ወገን ፍቅር የትም አያደርስም!
“የእኛ ሰው” በቤተ-መንግስት፣በመስዋዕት ሜዳ….
አቶ በቀለ ገርባ ከሰሞኑ ለ“OMN” ቴሌቭዥን በኦሮምኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ብዙ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳይ የያዘ ንግግር ተናግረዋል፡፡ይህ የአቶ በቀለ ንግግር ለመማማርም ሆነ የሃገራችን ፖለቲካ የሚሄድበትን መንገድ ለማጤን ሲባል ተፍታቶ መታየት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ በንግግራቸው መሃል “…ከእኛ ወገን የሆነ ሰው ስልጣን ላይ መውጣቱን ጠልተን አይደለም…” የሚሉት አቶ በቀለ ገርባ የጠ/ሚ/ር አብይን ፓርቲ ኦህዴድን እቃዎማለሁ ብለው ተቃዋሚውን ኦፌኮ የተቀላቀሉ ሰው ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ጠ/ሚ/ር አብይ የአቶ በቀለ ገርባ ሰው የሆኑት ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለአቶ በቀለ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ የእርሳቸው ሰው ነው፤ኦሮሞ ያልሆነ ደግሞ በተቃራኒው፡፡
እንዲህ የሚያስቡት አቶ በቀለ ከኦህዴድ ጋር በተለያየ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ ያውም ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ጉልበት መጨረሱ ለምን እንዳስፈለገ ግልፅ አይደለም፡፡በዚህ እሳቤ ጥምረት፣መድረክ እያሉ ከኦፌኮ ጋር ተጣምረው ኦህዴድ ያለበትን ኢህአዴግን እንታገላለን የሚሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ፓርቲዎች እንደ አቶ በቀለ ባሉ ሰዎች እንዴት እንደሚታዩ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ንግግር በወረቀት ላይ ያለ ጥምረት እና ህብረት ብቻ ጉልበት እየመሰላቸው በቅንነት ለሚታለሉ በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ለሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ትልቅ ትምህርት ሰጭ ንግግር ነው፡፡
ከተወልጄ የደመ-ነፍስ ስሜት ወጣ ብሎ፣ምክንያትን ተመርኩዞ ለማየት ፋታ ላገኘ ሰው ግን ኦሮሞነት ብቻ የህብረት መሰረት እንደማይሆን ኦፌኮን እና ኦህዴድን ጨምሮ አእላፍ የኦሮሞ ፓርቲዎችን ማስተዋሉ ብቻ በቂ ነው፡፡ በልብ እየተዋደዱ በፓርቲ መለያየት ከሆነም ነገሩ ያው ፍሬቢስ ከመሆን እንደማይዘል አቶ በቀለ ሊጨብጡት ሲጓጉ የነበረው የጠ/ሚ/ር አብይ እጅ አቶ አንዳርጋቸውን ቀድሞ መጨበጡ የተወልጄ ፖለቲካ እየመሸበት ይሁን እየነጋለት ለመገመቱ ቀላል ማስረጃ ነው፡፡ እኔ የሰፈር ሰው ሆኜ ሳለ ሳልጨበጥ እንዴት እንቶኔ የሩቁ ሰው ተጨበጠ ብሎ ከመብገን ሌላው ምን ቢይዝ ቀድሞ ተፈለገ እኔ ምን ብይዝ ልፈለግ አልቻልኩም ብሎ ማጤኑ ተሻይ ነው፡፡
አቶ በቀለ አጥብቀው እንደሚመኙት የሰፈሩን ሰዎች ሰብስቦ ቤተ-መንግስት ሲገባ ያልታየው ጠ/ሚ/ር አብይ የዘረ-መል ፖለቲካን አታሳዩኝ የሚል፣ ሰብዓዊነትን ብቻ አንግቦ በፖለቲካው አለም የተወለደ ሰው አይደለም፡፡ይልቅስ በጥላቻ ፖለቲካው ሻምፒዎን በመለስ ዜናዊ እግር ስር ተቀምጦ ሲሰለጥን ያደገ፤ የመምህራቸውን የከፋፍለህ ግዛ ወንጌል ሰንቀው በኦሮሚያ ዳርቻ ከሰበኩት ከነጁነዲን ሳዶ ጋር ሆኖም የሰራ ሰው ነው -ጠ/ሚ/ር አብይ፡፡
የአብይ ልዩነት ግን ዘግይቶም ቢሆን ከመለስ ዜናዊ ሌላ የእውቀት ምንጭ አለ ብሎ ማመኑ፣አርቆ የሚወስደውን መንገድ ማወቁ፤እንደ ተወለደ ለመሞት አለመፈለጉ፣ለፍቅር የተዘረጋ እጅን አለመገፍተሩ፣ የኦሮሞ ሰፊ ህዝብ(የጥቂት አክራሪ ብሄርተኞች የመለያየት አጀንዳ እንዳለ ሆኖ) ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በሰላም የመኖር እንጅ ተከፋፍሎ “እኛ” “እናንተ” እየተባባለ መናቆር እንደማይፈልግ ያሳየውን ምልክት መረዳቱ፣ ዛሬ የቆመበት ወንበር በማን የፍቅር መዳፍ ተደግፎ እንደቆመ ማወቁ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የአብይ/ለማ ቡድንን ምክንያታዊነት እየጎበኘው እንደሆነ ምልክት ነው፡፡ ምክንያታዊነት የጀመረ ሰው ደግሞ ከጎሳ ፖለቲካ ቅርፊት ለመውጣት መንገዱን ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደ አቶ በቀለ ገርባ ካሉ ሰዎች ጉሽሚያ የገጠመው፡፡
ጠ/ሚ/ር አብይ እና ኦቦ ለማ መገርሳ በኦነግ መንፈስ ደቁነው ኦህዴድን ቢቀላቀሉም በኦነግ ዘመን ደንቁረው በኦነግ ስም እየማሉ መኖርን ያልፈለጉ የአዲሱ ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ባለ አዲስ ልቦና የአዲስ ትውልድ ሰው ደግሞ መምህሩን ኦነግን እድሜ ብቻ ያደረገውን የመነጣጠል ፖለቲካ ይዞ መንገታገትን አይፈቅድም፡፡ እንደ አብይ-ለማ ያለ ወጣት ፖለቲከኛ ገና ብዙ የመኖር ተስፋ አለውና ሃገር አፍርሼ ልፍረስ አይልም፡፡ ተስፋ የቆረጠ ብቻ ሃገር ለማፍረስ ይመኛል፡፡ ተስፋ ያለው ሰው በሃገሩ ላይ ወደፊት ስለሚኖረው ብሩህ ተስፋ ያልማል፤ ለዛው ይሰራል፤ ሃገር የሁሉም እንድትሆን የጎበጠውን ሊያቀና ይጥራል፡፡ በተቃራኒው በሰፊው ህዝብ ዘንድ የማሸጥ አርጀቶ ሃሳብ ያዘለ ብቻ የያዘውን ይዞ ወደ ሰፈሩ ሰዎች ጎሬ ያዘግማል፡፡ ሌላው ምን ቢለፋ ከመንደሩ ሰዎች አስተዋፅኦ በቀር አይታየውም፡፡
ደግነቱ ይህ አስተሳሰብ ጥቂት ለውጥ የማይዘልቃቸው አክራሪዎች እሳቤ እንጅ የመላው ኦሮሞ ህዝብ አቋም አለመሆኑ ነው፡፡ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ እኩልነቱን የሚሻ እንጅ ሌላውን ረግጬ ልቁም የሚል እበልጣለሁ ባይ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በልሂቃን የሚዘወረው ፖለቲካችን ሰፊውን ህዝብ አዳምጦ አያውቅምና የህዝብ በጎነት ያለው አቋም ብቻውን ለሃገር እጣፋንታ መልካምነት ማስተማመኛ አይሆንም፡፡ስለዚህ የልሂቃን አንደበት ሲስት በጊዜ መገራት አለበት እንጅ “የአንድ ሰው ሃሳብ ነው”፣ “አነጋገሩ ተሳስቶ ተተርጉሞ ነው”፣”የጎሳ ፖለቲከኛ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ቢል ምን ክፋት አለው?” የሚለው ቂልነት አይሉት ማድበስበስ የሚጠቅመን ነገር የለም፡፡ አስቦ መናገር የሁሉም ሰው ግዴታ ነው፡፡ አስቦ ያልተናገረ ደግሞ ታገስ ተመለስ ሊባል ግድ ነው፡፡
ሃገራችን አሁን ያለችበት ለውጥ ባለቤቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙ የሚወደሱት አቶ ለማ መገርሳ እና ጠ/ሚ/ር አብይ ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ኮስተር ያለ ትግል ውጤት ናቸው እንጅ እነሱ ታግለው ለውጥ ያመጡ ሰዎች አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ሙቀት እነሱን አበሰላቸው፣የህዝብ ጉልበት ህወሃት የሚባለውን ጣኦት እንዲያፈርሱ የልብ ልብ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እያየው ያለው የለውጥ ጭላለንጭል የራሱ የትግል ውጤት እንጅ ለማ፣ገዱ ወይም አብይ በወርቅ ሰፌድ የሰጡት ገፀ-በረከት አይደለም፡፡በተቃራኒው ህዝብ ነው እነሱ ባርነት በቃኝ እንዲሉ ድፍረት የሰጣቸው፡፡ ይህ ሳይምታታ ነው መነጋገር ያለብን፡፡
አቶ በቀለ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ የሸለሙት ታግሎ ለውጥ የማምጣት ፀጋም ልክ አይደለም፡፡ህወሃትን መርዙን የተፋ እባብ ለማድረግ የሚደረገው ትግል ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ፣ብዙ ተዋናዮች ያሉበት እንጅ አቶ በቀለ እንዳሉት የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ታግሎ ያመጣው ነገር አይደለም፡፡“….እኛ የደከምንበትና የሞትንበትን ትግል ሌሎች ናቸው የተጠቀሙበት…..ልጆቻችን ደማቸውን ያፈሰሱበትና አጥንታቸውን የከሰከሱበት ትግል ሌሎች ባዕዳን ናቸው እየተጠቀሙበት ያለው፡፡ሞትንበት መስዕዋትነት ከፈልንበት እንጅ ፋይዳ አላገኘንበትም” የሚለው የአቶ በቀለ ገርባ ትልቅ ክህደት ያዘለ አስተዛዛቢ ንግግር ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሃት/ኢህአዴግ የባርነት እና አፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅ ትግል የጀመረው አቶ በቀለ ገርባ እንደሚያስቡት በኦሮሞ ቄሮዎች እንቅስቃሴ አይደለም፡፡እንደ ህወሃት ያለ በኢኮኖሚውም፣በፖሊቲካውም፣
በውትድርናውም፣በዲፕሎማሲውም ስሩን የተከለ ከዛም የጎሳ ፖለቲካን የመሰለ ህዝቦች በአንድ ቆመው መብታቸውን እንዳያስከብሩ የሚደርግ መንፈስ ያሰረፀን መሰሪ ፓርቲ ለመታገል የአንድ ወገን ጡንቻ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የሆነውም እሱ አይደለም፡፡ ህወሃት ዛሬ የምስጋና ድቤ የሚመታላቸውን ገዱን፣ለማን፣አብይን አሽከር አድርጎ በአፋቸው እየተናገረ በሚገዛበት ዘመን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ላይ ነበር፡፡ እነ ለማ-አብይ፣ገዱ ይህን ረዥም የህዝብ ትግል እጅግ ዘግይተው የተቀላቀሉ የድል አጥቢያ አርበኞች ናቸው፡፡
እነ አብይ ራሳቸው ትልቅ ዓለም በሚመስላቸው የህወሃት እልፍኝ ውስጥ ባሮች እንደሆኑ ይገባቸው ዘንድ የሃገሪቱ የግል ፕሬስ ብዙ ብዙ ወትውቶ ነው የማታ ማታ የገባቸው፡፡ አውዳሚው የሲቪክ ማህበራት ህግ ከመምጣቱ በፊት ብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዲሞክራሲ ምፅኣት ደክመዋል፡፡ ቅንጅት፣ህብረት እና ሌሎች ፓርቲዎች ስልጣንን በህዝብ እጅ ለማድረግ ባይሰምርላቸውም ህዝብን ለማንቃት፣ህወሃት መራሹን መንግስት ለመገዳደር ብዙ አበርክተዋል፡፡የሙስሊሙ የሃገራችን ህዝብ ለሃይማኖቱ ነፃነት በአስደማሚ መናበብ፣ የማንንም ክብር ባልነካ ጨዋነት፣ ፅናት በተሞላበት መንገድ ረዘም ላለ ጊዜ መታገሉ አሁን ለታየው የለውጥ ጭላንጭል ትልቅ ግብዓት ነው፡፡
አቶ በቀለ በጣም የተመኩበት የቄሮዎች ቆራጥ እና ኮስተር ያለ ትግል ከፅናቱ መናበቡ፣ከመናበቡ ማስፈራቱ የገዥዎችን ጉልበት ያራደ ነበር፡፡ ጠመንጃ ያነገቡ ገዳዮች ግራ እስኪገባቸው ድረስ ኦሮሚያን መዝረፍ ተረት እንደሆነ ተነግሯቸዋል፡፡ብዙዎች በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡበት፣ እልፎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ዝናብ ፀሃይ የሚፈራረቅባቸው የሆኑበት፣ለሰው ይተርፍ የነበረ ንብረት ያፈሩ ወገኖቻችን ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ በማያውቁት ነገር የቂም በቀል መውጫ መሆናቸው እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም የትግሉ አካል ሆኖ በታሪክ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ወጣቶች ከባለጠመንጃ ጋር በጠመንጃም ሆነ በባዶ እጅ ተናተንቀው መሰዕዋት ሆነዋል፡፡ አቶ በቀለን ከሚያስተምሩበት እየነዱ የወሰዱ የወያኔ ባለጠመንጃዎች በሌሊት ቤቱ የመለጡበት አልሞት ባይ ተጋዳዩ ደመቀ ዘውዱ ዘጠኙን ባለጠመንጃዎች ወደ ማይመጡበት ሸኝቶ እንደ ጥጃ እየጎተተ ማሰር የለመደውን ስርዓት የጀግና እጅ አሳይቷል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ ከመቶ በላይ የሆኑ የባህርዳር ወጣቶች ደም ከጣና ጋር ተቀላቅሎ ጣናን የደም ገበቴ አድርጎታል፡፡ በጎንደር ዘሎ ያልተገበ ወጣት አናት እንደበሰለ ድንች ተፈርክሶ አይተናል፣ ብዙ ወጣቶች በጥይት የሚያወርዳቸው ቅጥር ነፍሰገዳይ ፊት የሃገር ባንዲራ ሲሰቅሉ አልፈሩም፡፡ የሃገራቸውን ባንዲራ እንደያዙ እንደ አሞራ ከዛፍ ላይ በጥይት ወርደው መሬት ሆነዋል፡፡ይህን አቶ በቀለ ቢረሱት የሞተባቸው እናቶች፣ሰብዓዊነት የሚሰማው ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ አይረሳውም፡፡ ይህ የወንዝን ልጅ ብቻ ለማጀገን ሲባል የሚራከስ መስዕዋነት አይደለም፡፡
የኮንሶ ህዝብ መብቱን ለማስከበር ሆብሎ ወጥቶ ብዙ ቀናትን ጎዳና ላይ አሳልፏል፣ቤቱ ተቃጥሎበታል፣ልጆቹ ሞተዋል፣ታስረዋል፣ተሳደዋል፡፡ የጉራጌ ወጣቶች ዘርማ በሚል ስም ራሳቸውን አደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል፣ የአፋር ህዝብ ምሬቱ ቢጠናበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ነገሬ ሳይል አደባባይ ወጥቶ ጩኽቱን እያሰማ ነው፡፡ በክረምት ቤታቸውን በጉልበተኛ ሊያጡ እንደሆነ የተነገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሁን ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ወደ ቤተመንግስት እየተመሙ ነው፡፡የአብዲ ኢሌ አምባገንነት ያበረራቸው የኢትዮ-ሱማሌ ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ፈሰው አቤት እያሉ ነው፡፡ ይሀ ሁሉ ትግል ተጠራቅሞ ነው ሃያ ሰባት አመት የገነነውን አምባገነን አስተዳደር እያራደው ያለው፡፡ ይህን ማገናዘብ በጣም ከባድ ነገር አይመስለኝም፡፡
ኦሮሞ ብቻ ሞቶ ሌላው ዝም ብሎ በተቀመጠበት ቀን የወጣለት ማስመሰል አንድም ራስን ማስገመት ሁለትም የህወሃት ቅጅ የመሆን መንደርደሪያ ነው፡፡በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እኛ እና ሌሎች የሚባል ነገር የለም፡፡ በደል፣መረገጥ፣መዋረድ ሁሉን አንድ አድርጎታል፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው በሰላም እና በእኩልነት አብሮ መኖርን እንጅ ሃገሩን ሁሉ ተፈናቃይ ያደረገውን የ”እኛ” እና “እናንተ” ተረክ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት በህወሃት እግር ገብቶ “ዘሬ ሞቶ ዘርህን ስላዳነ መቶ አመት ናትህ ላይ ሰፍሬ እገዛህ ዘንድ የተገባነው” የሚለው፣ለሞቱ ሰማዕታቶቹ ሃውልት ሰርቶ እያሳለመ፣በቦታው ተገኝቶ ትንሽ እንባ እንዲያፈስ እያስገደደ፣ ከማይታገል “ፈሪ” ዘር በመገኘቱ የበታችነት እንዲሰማው የሚያደርግ ተቀያያሪ ዘረኛ ገዥን ማስተናገድ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃትን በኦህዴድ ለመቀየር የሰኮንድ ትዕግስት አልቀረለትም! በተፈጥሮው ጀግና ሆኖ የሚወለድ ዘርም የለም፤ይህን ሊነግረን ለሚመጣ “የተረት አባት” የሚተርፍ ሽራፊ ጊዜ የለንም፡፡ህዝብ እበልጣለሁ ባይን ላይመለስ የሚቀብርበት ትግል ላይ ነው፡፡ ዘመኑ የእኩልነት ነው!
“የሚዘፍኑ ሌሎች” እነማን ናቸው?
ጠ/ሚ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲወጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በደስታ ሰክሯል፡፡ እኔ በምኖርበት ደቡብ ክልል የሚኖረው ህዝብ የተደሰተው ከአብራኩ የወጡት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወድቀው አብይ በመመረጣቸው ነው፡፡ የአማራ ህዝብ በአብይ መመረጥ ሲደሰት በአብይ የተሸነፉት አቶ ደመቀ መኮንን የክልሉ ሰው ስላልሆኑ አይደለም፡፡ ዛሬ በመላ ሃሪቱ በሚጓዙ ተሸከርካሪዎች ላይ የአቶ ለማ መገርሳ እና የጠ/ሚ/ር አብይ ውብ ፎቶዎች ተለጥፈው የሚታዩት የዚህ ሁሉ መኪና ሹፌር ኦሮሞ ስለሆነ አይደለም፡፡ የጎንደር ህዝብ ዛሬ “ሌሎች” እና “እኛ” እያሉ ያሉትን የአቶ በቀለ ገርባን ፎቶ ይዘው ይፈቱልን ሲሉ የጮሁት የታሰረ የወንዛቸው ልጅ ስላልነበረ አይደለም፡፡ነገሩ ሌላ ነው፡፡ ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ “የእኔ ሰው” ለማለት በኩታ ገጠም ቀበሌ መወለድ፣ አንድ አይነት ቋንቋ መናገር ወይም በአንድ የዘውግ ፓርቲ ውስጥ መስፈር ግዴታ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያን ያለ ሁሉ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ የሚነግስበት ዘመን ነው፡፡ አብይ የተረዱት አቶ በቀለ ግር እንዳላቸው የቀረው እውነት ይህ ነው፡፡
አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች ትቂት መሰሎቻቸው ለመረዳት ያዳገታቸው አዲስ እውነት ነው አብይን ጠ/ሚ/ር ያደረጋቸው፡፡ አብይ ለጠ/ሚ/ርነቱ ፍልሚያ ነፍስ ሲዋደቁ ብአዴን ደርሶ ባይደግፋቸው ኖሮ የሆነው ሁሉ አይሆንም ነበር፡፡የአብይ ጠ/ሚ/ርነት የሰመረው የእኛ ሰው የሚለው የትም የማያደርስ እሳቤ በመቅረቱ እንጅ ብአዴንም ደኢህዴንም የ”እኔ ሰው” በሚለው ጥበት ውስጥ ገረው ቢቀሩ ኖሮ ማን እንደሚጠቀም ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ “የእኛ ሰው” የተባለው አብይ ወደ ቤተ-መንግስት መምጣቱ ብቻ ሳይሆን አመጣጡም መጤን አለበት፡፡ ‘የእኛ ሰው በእኛ ሰዎች ትግል ብቻ ወደ ስልጣን መጣ ግን የእኛን እጅ ይዞ ቤተመንግስት አልገባም’ የሚለው ቅሬታ እውነት ላይ የቆመ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህን የተሳሳተ ቅሬት ማስወገድ አንድ ነገር ሆኖ አብይ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ያገዘውን ሁሉ እጅ ይዞ ቤተ-መንግስት መግባት እንደማይችል መገንዘብም አስፈላጊ ነው::ለአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ያላበረከተ ስለሌለ “ሌሎች” የሚለው አበባል ራሱ ልክ አይደለም፡፡ ለአብይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገን ነው፤ ይህን በደንብ የተረዳው አብይ ራሱም “የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ” ብሎ ነገሩን ጨርሶታ፡፡ከዚህ በሁዋላ የጎጡን ሰዎች ሰብስቦ በቤተ-መንግስት ሽው እልም እንዲል መመኘት ገድለ-ደደቢትን በገድለ-ቄሮ ተክቶ ሌላውን ህወሃት በሌላ ልብስ ለማምጣት መፋተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛውን የኦሮሞ ህዝብ ጨምሮ በማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በጥብቅ የሚጠላ፤ዕለቱን የሚገድል ነገር ነው፡፡
“ጦር ይዞ ሲወጋቸው የነበረውን መሪ ፈትተው ቤተ-መንግስት አስገብተው ሲጨባበጡ ፎቶ ተነስተው ማየት በጣም የሚያሳዝን ነው…የኦሮሞ ልጆች እስርቤት አሸባሪ ተብለው እያሉ ከባድ ወንጄል የሰሩት ተፈተው ቤተ-መንግስት ፎቶ ይነሳሉ” የሚለው ንግግራቸው እጅግ በጣም ያሳዘነኝ ንግግር ነው፡፡ አቶ በቀለ ለብቻቸው የሚያውቁት አንዳርጋቸው የሰራው ከባድ ወንጄል ምንድን ነው? ወንጄል ከተባለ የእሱ ወንጄል አፈር ላይ እስከመተኛት፣ያለ እድገቱ እንጨት እስከመፍለጥ ድረስ ሃገሩን መውደዱ ብቻ ነው! ይህ ሰው በመታሰሩ ልጆቹ በጥንድ አይናቸው የሚያለቅሱለት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነው፡፡ አቶ በቀለ ገርባም ልጆች አሏቸው፡፡አንዳርጋቸው ለምን እና እንዴት ጦር አንስቶ ወያኔን ለመውጋት እንደ ደረሰ ለሁሉም ሰው እኩል ግልፅ ላይሆን ይችላል እና ወደዛ አንሂድ፡፡ ዝም ብለን በስብዕና እናስበው፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት እና ቤተ-መንግስት ገብቶ ፎቶ መነሳት በጣም የሚያሳዝነው እንዴት ነው? በኦሮምኛ እና በOMN ይህን የሚሉት አቶ በቀለ ገርባ ከሳምንት በፊት በአማርኛ እና በVOA የተናገሩት ሌላ ነው፡፡ የወጣላቸው ክርስቲያን እግዚአብሄርን አማኝ ከመሆናቸው የተነሳ ልጆቻቸውን በእግዚአብሄር መንገድ የሚያሳድጉ፣በወያኔ ላይ ጭምር ቂም እንዳይዙ፣በአባታቸው አሳሪዎች ላይ ክፉ ስሜት እንዳያዳብሩ የሚመክሩ ሰው እንደሆኑ ሲናገሩ ጆሮየ ሰምቷል፡፡ ታዲያ የአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት፣የሌሎች መጨፈር ያሳዘናቸው እንዴት? ወይስ የአንዳርጋቸው ፅጌ ታስሮ መማቀቅ በአምላክ ወንጌልም የታዘዘ እና የሚደገፍ ነው?!
የማስተባበያው ይባስ
አቶ በቀለ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል ቀርበው ያስተባበሉበት ሁኔታም በበኩሌ ከመጀመሪያው ሃሳባቸው የራቀ ነገር አላየሁበትም፡፡ ማስተባበያ ባሉት ንግግር ላይ አቶ በቀለ ይህን ይላሉ “እንደሚታወቀው ከአራት ዓመታት ወዲህ ብዙ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ ውስጥ ተካሄደዋል። እንቅስቃሴው በአብዛኛው የተከናወነው በአሮሚያ ክልል ውስጥ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ነው። ብዙ ህይወት እና ንብረት የጠፋው፣ ሀገሪቱንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተው ሁኔታ በዚሁ ስፍራ የተከናወነ እንደሆነ ግልፅ ነው።ከፍተኛውን መሰዋዕትነት የከፈሉት፤ ለእስር እና ለቤተሰብ መበተን የተዳረጉት፣ አካላቸው የተጎዳው በአብዛኛው የኦሮሚያ ወጣቶች እንደነበሩ ማንም የሚክድ አይመስለኝም።”
የመስዕዋትነት ከፍተኛ እና ዝቅተኝነት መለኪያው ምንድን ነው? ህዝቦች ከጋራ ትግላቸው ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን ዝቅተኛው እና ከፍተኛው የመስዕዋትነት ስፍር የት ላይ ያርፋል? ትግል አክሲዮን ይመስል ባዋጡት መጠን የሚጠቀሙበት ማህበር ነው? ይህ ህወሃት ከብአዴን እና ሌሎች እህት ድርጅቶች በበላይነት ቂጢጥ ብሎ “ከነዘር ማንዘሬ ለትግሉ ይበልጥ ስለሞትኩ ስለተሰነጠቅኩ የሁሉ ነገር እፍታ ይገባኛል” ከሚለው ክርክር ጋር ልዩነቱ አይታየኝም፡፡እንዲህ ያለው ውለታ የማስቆጠር እና ከፍ ብሎ ለመታየት መሞከር ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው የህወሃት የበላይነት መንፈስ ጓደኛ ነውና በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አይፈለግም፡፡
ሌላው አስገራሚ ማስተባበያ ይህን ይላል “ለምን እከሌ ተፈታ? እከሌ መፈታት አልነበረበትም? ማለቴ ሳይሆን፣ ተመሳሳይነት ወጥነት ያለው ስራ አልተሰራም፣ ትናንት ስንታገለው የነበረው ኢፍትሃዊነት አሁንም አለ፣ዛሬም በዐይናችን እያነው ነው ለማለት ነው።በተመሳሳይ ሁኔታ (ወደ ኢትዮጵያ) ከባዕድ ሀገር ታፍነው እና ተጠልፈው የመጡ አሉ፡፡ አንዱን ፈትቶ አንዱን ማስቀረት አለ። ከዚህ በላይ ኢፍትሃዊነት ለኛ የለም። ኢፍትሃዊነቱም በግልፅ በዘር መስመር የተፈጸመ ነው ”
ጦር ይዞ ሲወጋቸው የነበረው ሰው ተፈቶ ቤተመንግስት ገብቶ መጨባበጡ ያሳዝነኛል ያለ ሰው በዚህ ሃሳብ የቀደመ ንግግሩን ለማስተባበል እና ለመታመን ይችላል ወይ የሚለውን ለአንባቢ የህሊና ፍርድ ልተወው፡፡ ‘ፍቺው ወጥነት ስለሌለው ነው ቅር ያለኝ’ ወደሚለው በመጠኑ የተሻለ ወደሚመስለው ነገር ልለፍ፡፡ ይሄ ክርክር ራሱ ችግር አያጣውም፡፡ ሁሉም ሰው ይፈታ ማለት እና እከሌ ተፈቶ የእንቶኔን እጅ መጨበጡ በጣም ያሳዝነኛል ማለት በምንም አይገናኝም፡፡ “ኢፍትሃዊነቱ በግልፅ በዘር መስመር የተፈፀመ ነው” ማለት ምን ማለት ነው?ለየትኛው ጎሳ ምን ያህል የበለጠ ኮታ ተሰጥቶ ነው የእስረኛ ፍቺ የተደረገው? ለመሆኑ የምን ጎሳ ሰው ነው የኢትዮጵያን እስር ቤት ያረገጠው? ነገሩ የኦሮሞ ቁጥር ይበልጣል የሚል ሃሳብ ያለው ይመስላል፡፡ነገር ግን የሰብዓዊ መብትን ፅንሰ-ሃሳብ የሚያውቅ ሰው በታሳሪ/በተጎጅ ቁጥር ብዛት እና ማነስ የመብት ረገጣን አይለካም፡፡
meskiduye99@gmail.com
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።