spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትበለውጥ ወቅት ሊመረመሩ የሚገባቸው ጥቂት የውይይት ሃሳቦች (ዶ/ር አበባ ፈቃደ)

በለውጥ ወቅት ሊመረመሩ የሚገባቸው ጥቂት የውይይት ሃሳቦች (ዶ/ር አበባ ፈቃደ)

ዶ/ር አበባ ፈቃደ
ሰኔ 4 ፤ 2010 ዓ ም

ለውጥ በሚታይም ሆነ በማይታይ ረቂቅ ነገር ውስጥ፣ በትንሽም ሆነ በትልቅ፣ በወል፣ በተናጠል በጋራም ሆነ በግል ህይወት ውስጥ ሁሉ የሚከሰት የተፈጥሮ መሰረታዊ ህያው የጊዜ ባህሪ ነው። ለውጥ ካልሆነ ወደ ሆነ ካልነበረ ወደ ነበረ የሚያሸጋግር እምቅ የጊዜ ሂደትና ውጤት ነው። በጥቅሉ ለውጥ በዙ ገጽታዎችም ደረጃዎችም አሉት። በውስጥና በውጭ በሚፈጠሩ ነባራዊ ሁኔታዎች አነሳሽነት የለውጥ ወቅት ይከሰታል፣ የለውጥ ትርጉምም ለውጡን ከሚፈለገው፣ከሚፈጥረውና ከሚጠቀምበት አካል ጋር የተያያዘና የተሳሰረ ነው። ሁሉም ለውጥ የምንፈልገው ስለማይሆን፣በችሮታም የሚታደል ሰላልሆነ በሂደቱ ሙሉ ተሳታፊ በመሆን የምንፈለገውን ከማንፈለገው ለይተን በማወቅ አስፈላጊ የሆኑትን የለውጥ መሳሪያዎችንና ውጤታማ መንገዶች በግልጽና በጥራት ማየት እጅግ አስፈላጊና ተቀዳሚ ተግባር ነው። ሃሳብና ተግባርን የሚያንኮላሹና የለውጥን የቀና ሂደት ከሚያደናቅፉ ነገሮች ውስጥ አንደኛው የአተያየት ብዥታና ውዥንብር በሰፊው መሰራጨት ሲበዛ ነው። ስለሆነም ምን አይነት ለውጥ በማን፣ ለማን ጥቅም የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎችን መፈተሽና በጥልቅ መመርመር ከነፈሰው ጋር በደመ ነፍሰ እንዳንነፍስና የለውጡም ተጣቃሚ እንድንሆን ይረዳናል። ሁለንተናዊ የለውጥ ባለቤትነት የሌለው፣ እውነተኛነት የተጎደለው የለውጥ ሂደት የተፈለገው ለውጥ መገኘትን አያረጋግጥም። ችግር በመፍትሄ የማይቀይር ለውጥ ፋይዳ የለውም፣የበለጠ ችግሩን ከማስፋትና ከማጠናከር በስተቀር።

ወያኔ/ የትግሬ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ከሌሎች የአገራችንን አንድነትና ነጻ ህልውናችንን ከሚቀናቀኑ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ድጋፍ ጋር በመሆን የመንግስት ስልጣንና መዋቅርን በመያዝ ኢትዮጵያን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ፣ የሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብን ድጋፍ በጭራሽ ያላገኘ እጅግ የተጠላ ጸረ ኢትዮጵያዊ መንፈስ የሰረጸው ቡድን መሆኑ በመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ የተቀረጸ ሀቅ ነው። ሆኖም ግን የወያኔን ማንነት ከማወቅና ከመጥላት ባሻገር፣ ይህን አጥፊ ስርአት ለመቋቋምና ለመቀየር ብዙ ሙከራ ሲደረግ ቢቆይም፣ ተመጣጣኝ የሆነ፣ የቆረጠ ወሳኝ ትግል ለማካሄድ የሚያስችል የተቀነባበረ የሀሳብ፣የስልትና የተግባር አቅም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልተሟላም ነበር። ላለፉት ጥቂት አመታት ግን እነዚህ ተጨባች ነባራዊ ሁኔታወች እየተቀየሩ ወያኔን ከመቃወም ወደ ማስወገድ የሚያስችል የለውጥ ግፊትና ደረጃ ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያዊነትን ራሱን መሳሪያና ማእከል ያደረገ፣ የአንድነት መንፈስ ያዘለ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተነሳሳ ጠንካራ ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ባንጻሩም በተለይ ላለፉት ጥቂት ወራት ይህን የህዝብ ተነሳሽ ትግል ግብ እንዳይመታ፣ የለውጥ አቅጣጫን ለማሰናከልና ለመቀልበስ ወያኔና ተባባሬዎቹ ከፍተኛ ጥረት በግልጽና በስውር፣ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ዘዴዎችን በመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ የተፈጸመው ደባና ወንጀል በበለጠ ለሁሉም ገሃድ እየሆነና እየተጋለጠ ሲመጣ፣ በህዝቡ ስነ ልቧና ውስጥ ፍጹም ተቀባይነት ያጣው ወያኔና ኢትዮጵያን የማይወክል የወያኔ ህገ መንግስትና ስርአትን መቀየር አይቀሬ ሃቅ እየሆነ መጣ። ኢትዮጵያዊነት የማይጠፋ የማንነትና የአንድነት ማህተማችን፣ ብሎም የነጻነት መሳሬያችን መሆኑን ህዝብ በኩራትና በጀግንነት መግለጽና ማንጸባረቅ ሲጀምር፣ የአማራው ህዝብ ህልውናውን በጀግንነት ለማስከበር በጠላቱ ላይ ወሳኝ እርምጃ መውሰድን ሲጀምር፣ የጎሳ ክልል አቀንቃኞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የኦሮሞ ህዝብን ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ለመነጠል የተሸረበውን ሴራ ህዝቡ ሲያፈርስና አንድነቱን በድፍረት ማንጸባረቅ ሲጀምር ነው ወያኔ/ኢህአዴግና ይህን ወሳኝ የህዝብ የለውጥ ሃይል ለመገደብ ብሎም ለማዳከም ብዙ ወራት የፈጀ ዝግጅት በማከናወን እርምጃውችን መውሰድ የጀመሩት። ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነቱን ሲያስመሰክር ማለት ነው። ክወያኔ የትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር የስልጣን ዘመኑን ለማራዘምና የመሰረተውን ከፋፋይ የጎሳ ክልል ስርአትን ለማቆየት፣ የዘረፈውን የአገር ሃብት ለማሸሽ፣ ከፈጸመው ብሄራዊ ወንጀል ለመደበቅ እንደምናየው ያማይፈነቀለው ድንጋይ ያማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። ወያኔ የህዝብን መሰረታዊ የመታገያ ጥያቄዎችንና መሪ ሃሳቦችን ሳይቀር በመንጠቅ፣ስርአቱን የማያናጋ አስመሳይ የለውጥ ቀሚስ የተላበሱ ሹም ሽሮችን በመፍጠር፣ ጥቂቶችን ፈቶ ብዙዎች በማሰር፣በሽንግልናና በአዘናጊ የቃላት ፕሮፖጋንዳዎችን በመንዛትና አጀንዳዎችን በመስጠትም ሆነ በመቀማት ይህን እምቅ የለውጥ ማእበል ቀልብሶ ትግሉን ከህዝብ እጂ ፈልቅቆ ለማውጣት ክፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ወያኔና ግብረ አበሮቹ እናራምዳለን የሚሉት ለውጥ፣ የተመሰረቱበትን ስርአትና ከሰርአቱ የመነጩትን መሰረታዊ የመጨቆኛ መዋቅሮችና አገር አፍራሺ ሀገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን የማይቀይር፣ የችግሩን ምሰሶዎች የማይነቅልና በመፍትሄ የማይተካ የተደበስብሶ ለውጥ ነው። ወያኔ የላይ ላይ አስመሳይ ለውጦችን እንደ እውነተኛ ለውጥ አስመስሎ በማቅረብ የህዝብን ቀልብ ለመሳብ የለውጡን ሂደት ለማኮላሸት፣የውዥንብርና የማደናገር ዘመቻን በሰፋት ተያይዞታል። ሆኖም የወያኔ/ኢህአዴግ የማስመሰልም ሆነ መለስተኛ ለውጥ መሰል ተግባራትን ማሳየት የህዝብን መሰረታዊ ችግርን ሊፈታ አይችለም፣ ምክንያቱም የችግሩ መንስኤ የሆነውን ራሱ የቆመበት የፖለቲካ ስርአት ስለሆነና ራሱን የማይቀይር የለውጥ ደረጃና ሂደት ላይ የሚገኝ ስለሆነ። በተጨማሪ ወያኔ ለውጥ ከሚለው መጋረጃ ጀርባ በኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በአማራው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ለሞት ለመፈናቀልና ለስደት የሚዳርግ ጥቃት አሁንም በማደረስ ላይ ነው (ይህ የህዝብ መፈናቀል ደግሞ በአማራው ህዝብ ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀረም፣ የወያኔ ጎሳዊ የክልል ስርአት ትርፈ ውጤት ስልሆነ)። እንዳውም ህዝብንም አገርንም ለሽያጭና ለባእዳን የበላይነት አሳልፎ በመስጠት አገርን ለማፈረስና ለመበተን የሚያመቻች ሁኔታዎችን በበለጠ በመፍጠር ወያኔ/ትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር ከተነሳበት ዋና አላማ የማያዛልፍ ስልጣንና ጥቅምን የሚያስጠበቅ የለውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።

ለሀቀኛ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ ወያኔ/ትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር የዘረጋውን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን የጎሳ ክልል ስርዓትን መለወጥ የመጀመሪያና የለውጦች ሁሉ ለወጥ የሆነ ወሳኝ የነጻነት ምእራፍ ነው። ይህ የጎሳ ክልል ስርአት ነው ወገንን ከወገን የሚለያየው፣ የማያስፈልግ የርስ በርስ ቅራኔና ግጭትን የሚፈጥረውና ህዝብን ለድህነት፣ ለመፈናቀልና ለባርነት የሚዳርገው። ይህን አጥፊ ስርአትን መሰረት አድርጎ የሚመጡ መለስተኛ ለውጦች ለዘላቂ ችግራችን መፍትሄ አይሆኑም። ጥቂት እስረኞችን መፍታት መልካም ቢሆንም ለእስር የሚዳርገውን የፖለቲካ ስርአት መለወጥ ግን ወሳኝና ዋነኛ ህዝበ የሚሻው ለውጥ ነው። መለስን በሀይለ ማርያም፣ሀይለ ማርያምን በአብይ መተካት መለስተኛ የተክለ ሰውነት ለውጥ እንጂ ለቆሙለት የወያኔ የጎሳ ክልል፣ህገ መንግስትና የፖለቲካ ስርአት እንደ አቅማቸው ሁሉም አስፈጻሚ ወኪሎች ናቸው። በመሆናቸውም የቆሙበትን የስርአት መሰረቱን አይለውጡም፣ ለውጥ የሚሉትም ስርአቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እንጂ። ተግባራቸው ከንግግራቸው ንግግራቸው ከውስጣዊ አስተሳሰባቸውና ስሜት ጋር ያልተዋሀደ፣ ውስጠ ቅራኔዎችን ያዘለና በእምነትና በተግባር የተራራቀ፣ የማይጣጣሙና ከመነሻው ውጤተ ቢስ ሂደቶች ናቸው። የስርአቱ ወኪሎች ዋና ተግባራቸው የሚያተኩረው ስርአቱን ለማዳን በሚደርጓቸው ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴና የመለዋወጥ ስራ ላይ ነው፣የመነጋገሪያ አጄንዳ በመሆንም ጭምር። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ለውጥ ማያት የሚሻው ሃይል በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ሊህቃንና ተንቀሳቃሾች በጭፍን ጉጉት፣ ከተዳከመና ተስፋ ቢስ ከሆነ ተሸናፊ አስተሳሰብ የተነሳን የለውጥ ሂደትን መከተል ዘላቂ ለህዝብ ጠቃሚ የሆነ ለውጥን እንደማያመጣ ማስተዋል እጅግ አስፈላጊ ስልታዊ ግንዛቤ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ የተነሳው የወያኔን ብልሹ ስርዓት ለማስወገድ ሰለሆነ፣ ለትግሉ ያለውን ቁርጠኝነትና ጽናትን የሚያላሉና የሚያዘናጉ ከወያኔም ሆነ ከተቃዋሚ ነን ከሚሉ ድርጅቶችም በኩል የሚከሰቱትን ማደናገሪያ ሂደቶችን ለይቷ ማወቅና ማሳወቅ ኢትዮጵያዊ ምሁራንና የፖለቲካ ሊህቃን ሊያደርጉ የሚገባቸው አስፈላጊ የማስተዋል ስራ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ላላፉት ሃያ ሰባት አመታት በህገ መንግስት ተደንግጎ፣ ሰብአዊ ሆነ አገራዊ ነጻነቱን ተገፎ በባርነት በክልል/አፓርታይድ፣ በወያኔ ጎሰኛ ስርአት ሲፈናቀል፣ ለድህነትና ለሰደት ተዳርጎ፣ፍትህና ርትእ ተንፍጎት አሰቃቂ የመከራ ኑሮን እንዲኖር ሆኖል፣አሁንም በመኖር ላይ ነው። ዛሬ ህዝቡ ይህንን ስርአት ነው ለአንዴም ለሁልጊዜም ለማስወገድ የተነሳው። የአገርን ልኦላዊነት የህዝብን አንድነትና ሙሉ ሰብአዊ ነጻነቱንና መብቱን ማስከበር ነው ዋናውና ህዝብ የሚፈለገው መሰረታዊ ወሳኝ ለውጥ። ህዝብ ከሚኖርበት ቦታ እንዳይፈናቀል በመላ ኢትዮጵያ ወስጥ የመኖር መብቱን ማስጠበቅ መሰረታዊ የዜግነት ነጻነት ስለሆነ ህዝቡ የሚሻውና የሚጓጓጎለት ይህን መሰል እውነትኛ ለውጥን ነው። ለዚህም ምሰሶ የሆነውን የወያኔ ትግሬ ነጻ አውጭ ግንባርን ከፋፋይ፣ ጠንቀኛ አገር በታኝ ህግ መንግስትን ባስቸኮይ ማንሳት ቅድመ ሁኔታን የማይጠይቅ የአገር ህልወናንና ልኦላዊነትን የሚያረጋገጥ የመጀመሪያ ወሳኝ የለውጥ ተግባር ነው።

ይህ ጸረ ኢትዮጵያ ስርአት ደግሞ ለበርካታ ችግሮቻችን ዋና መንስኤና ምንጭ ሆኖል። አማራው የወያኔ የጥቃት ኢላማና ሰለባ የሆነው በዚህ ጸረ አንድነት ህገ መንግስት ላይ በተመሰረቱ ፖሊሲዎች ተፈጸሚነት ነው። የወያኔ ጸረ አንድነት የሆነው በጥላቻ መንፈስ የታነጸው የጎሳ ክልላዊ ስርአትን፣ በኢትዮጵያዊ አንድነት፣ በነጻነትና በፍቅር የታነጸ የአንድ አገር አንድ ህዝብ መንፈስን ያዘለ ስርአት ሲተካ የመጀመሪያው የለውጥ መነሻ ይሆናል። ለዚህም የአገርን ህልውና ማስረገጥ ወቅቱ የሚጠይቀው አስፈላጊ ጥብቅ እርምጃ ነው። አገርና መንግስት የተለያዩ አካሎችና ህልውናዎች ናቸው። አገር በችሮታ ወይም በአቴናዊ የፖለቲካ ሂደት የምናገኘው ነገር ሳይሆን ከእኛ በፊት የነበረ፣አሁንም ያለ፣ ወደፊትም ያለ አንዳች የፖለቲካ ቅድመ ሁኔታ የሚኖር ህያው የራሱ ውክልና ያለው የማንነታችን መነሻ አካል ነው። መሰረታዊ ህይወት ነውና አገር ለፖለቲካ ድርድር አይቀርብም። ወያኔ የትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር የኢትዮጵያን ግዛታዊ ልኦላዊነት ብሄራዊ ህልውናና የህዝብ አንድነት በማፍርስ አገራችንን ለ27 አመት በወራሪነት ይዟታል። የዚህም አስተሳሰብ ያስከተለው ጠንቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ በተለይም የአማራው ህዝብ ብዙ ውድና ክቡር ዋጋ ከፍሏል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል በማድረግ የነጻነትና የህልውና ንቅናቄዎችን፣ በበለጠ ማጠናከርና ማስፋፋት አጣዳፊና ቅድሚያ የሚሰጠው የለውጥ ሃይሎች ተግባር ነው።

ማንኛውንም የለውጥ ሂደት ለምንፈልገው ግብ መሸጋገሪያ በማድረግ ወቅቱ በሚጠይቀው ልዩ ንቃትና ትጋትን በማንገብ የለውጥ አወንታዊና ቀና ተሳታፊ አካል መሆን እንችላለን፣ አስፈላጊና ተገቢም ነው። ሌላው የምንሻው ለውጥ ህዝብን ለማስተዳደር የሚያስፍልግ መንግስታዊ መዋቅርና የፖለቲካ ስርአትን በመመስረት ዙሪያ የሚመጣ የለውጥ ሂደት ነው። ፍትህ፣ርትእና እኩልነት በሌለበት የወያኔ አፋኝና ቀማተኝ የዘራፊ ስርአትን በተሻለ ኢትዮጵያዊ መንግስና የፖለቲካ አስተዳደር መተካት ነው። ምን አይነት መንግስታዊ ስርዓትን መመስረት ይሻላል ለሚለው ሃሳብ ኢትዮጵያዊነት ያማከለ ልዩ ልዩ አማራጭ የፖለቲካ ራእዮችንና መርሆችን በፖለቲካ ድርጅቶችና ሊህቃን ለህዝብ በማቅረብ የፖለቲክ ስርአትን መለወጥ ይችላል፣ ይህም ሲሆን ለበለጠ ለውጥ ምቹ ሁኔታዎችን እንፈጥራለን ማለት ነው። በተጨማሪም መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ የምንፈለገው ለውጥ እውን የሚሆነው የለውጡ አንቀሳቃሽ ባለቤት ህዝብ ሲሆን መሆኑን ነው። ነጻነትን የምናገኘው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መሆኑን ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፣ስለዚህ በጎሳ የተዋቀረ የክልል ጦር ሰራዊትን በብሄራዊ ኢትዮጵያዊ የአንድ ህዝብ ጦር መተካት፣ ለለውጥ አሸናፊነት ዋስትና ይሰጣል። በዳዮችችና ወንጀለኞች ለነጻነታችን ይቆረቆራሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ አደገኛ ሞኝነት ነው። ጨቋኞች ያላቸው ዋና የሚጨቁኑበት ከባዱ መሳሪያቸው የተጨቋኞች አእምሮን በመጠቀም ነው ይላል ስቲቭ ቢኮ። ስለዚህ የለውጥ ሃይል የሆንን ሁሉ አእምሮችንን በንክብካቤ እንጠብቅ፣ ለቀላል ፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዳንሆን፣ ብልጭልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለምና። ጥልቅ አስተሳሰብንና ስልታዊ የማሰብ ችሎታን ለትግላችን መሳሪያ እናድረግ። ማስታወስ ያለብን ትግላችን ወያኔን በሌላ ወያኔን መሰል፣ ጸረ ኢትዮጵያ መንፈስ ባለው የጎሳ ኃይል ለመተካት አይደለም። ሆኖም ግን መለተኛን ጠጋኝ መሰል ለውጦች ለዋናና መሰረታዊ ለውጥ ከረዳን፣ አላማችን ሳንለቅ ከአቈማችን ሳንዛነፍ እንደየ ሁኔታው ልንጠቅምባቸው እንችላለን፣አይናችን ከግባችን ሳይነሳ፣ ማለትም ሌሎች በሚሰጡን አጄንዳና የቤት ስራ አዙሪት ውስጥ ሳንሽከረከር።

ለለውጥ ከሚያስፈልጉ መሳሪያዎች አንዱ ጽናት ነው፣በተለይ የአላማ ጽናት። በጽናት የማይጓዝ ትግል የለውጥ ሃይል አይሆነም ከጽናት የሚመነጨውን ጉልበት ያንሰዋልና። የጽናት መላላትና መበረዝ የውስጥ ጀግንነት ማመንመን ብቻ ላይ ሳይወሰን ለውሸትና ለአስመሳይ ነገሮች አእምሮን ለማስጠቃት ምቹና ዝግጁ ያደርጋል። እውነተኛ ህዝባዊ ለውጥ ለማምጣት ሃሳብን ወደ ቃል፣ቃልን ወደ ተግባር ማሸጋገር ሲቻልና የመርህ አላማና የሃሳብ የአንድነት በሁላችንም ህሊና ውስጥ ሲኖር ነው። ይህን ካደረግን፣ ልበ ሙሉነት በተላበሰው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት የወያኔንና የአጋሮቹን የጎሳ አገዛዝ ለማንበርከክ እንችላለን። እንችላለንም ብለን ከተነሳን ግባችንን ከመምታት ምንም የሚሳነንና የሚያዳግተን አንዳችም ነገር የለም። ይህን የወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ ስርዓትን ለማስወገድ የሚስችል የለውጥ የሃይል ምንጭ ራሳችን ሰለሆንን፣ በውስጣችን ያለውን ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦናዊ እምቅ ጉልበት መነሻና የስበት ማእከል በማድረግ አስተማማኝ ህዝባዊ ለውጥን መፍጠር እንችላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

ዶ/ር አበባ ፈቃደ

ሰኔ፣ 2010

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here