ንጉሥ አብይ አህመድ ሰባተኛው ከታላቁ ስደተኛው ወገናቸው ጋር የታሰበው ታሪካዊው ጉብኝት ስለመተላለፍ ፤ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ ውሳኔን አስመልክቶ
በዘውገ ፋንታ
ሰኔ 6 2010 ዓ. ም
በፒ ዲ ኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
ክቡር ጠቅላይ ምንስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ሕዝብ እንደሰየማቸው ንጉሥ አብይ አህመድ ሰባተኛው ወይም ባጭሩ ንጉሥ አብይ በማለት፣ ይህ ጸሐፊ በዚሁ ቢቀጥል እጅግ ይደሰት ነበር። ይህን ፍላጎቱን ገልጾ፣ ፕሮቶኮልን መከተል ተገቢ ስለሆነ፣ ክቡር ጠቅላይ ምንስትር (ጠ/ም) በማለት ይቀጥላል ።
ክቡር ጠ/ም አብይ በዓለም የተሰራጨው ወገናቸው በዳላስ ከተማ በሚመጣው የሰሜኑ የስፖርትና ባህል ላይ እንዲገኙ በፈለቀው ዕንቁ ሀሳብ ላይ፣ የፌደሬሽኑ አስተዳደር ቦርድ ድንገተኛ ስብሰባ አድርጎ፣ ይህን ታላቅ መሪ ለማስተናገድ ሰፊ ውይይት አድርጎ ነበር። አንድን መሪ ለማስተናገድ ከባድ ስራና ስለሆነ ቦርዱን ብዙ እንዳከራከረ ታውቋል። በመጨረሻ ቦርዱ ጠ/ም አብይን ማስተናገድ የማይቻል መሆኑን ቢወሰንም፣ ሕዝብ ይህን ውሳኔ ሌላ ትርጉም እንዳይሰጠውና ምክንያቱን በሚገባ እንዲረዳው ለማድረግ፣ ይህ ጽሑፍ አቅርቧል። መሪውን ማስተናገድ አስፈላጊ መሆኑን በማየት ሀሳቡን የደገፉት፣ እጅግ የሚደነቁ የሕዝብን የልብ ትርታና አፍላ ስሜት የተረዱ አድርጎ ማሰብ ተገቢ ነው። በሌላ አስተያየት፣ ‘ለማስተናገድ በቂ ጊዜ የለንም’ በማለት ታሪካዊው ጉብኝት እንዲተላለፍ ሲወሰን፣ የረቀቀና ጠለቅ ያለ ሀሳብን አመዛዝኖ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ቦርድ ከመወሰኑ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታና የሕዝብ መንፈስ፣ እንዲሁም ውስብስብ ያሉትንም ሁኔታዎች በውይይቱ ያንጸባረቀ መሆኑ ታውቋል። የሚደነቅ ውይይትና ግሩም ውሳኔ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቤ፣ የፌደሬሽኑ የቦርድ አባል ሆኖ ብዙ አመት ያገለገለና የድርጅቱን መንፈስ በመጠኑ ስለሚያውቅ፣ ከዚያም በላይ፣ ስለሀገራችን የፖለቲካ ችግሮችና ዕለታዊ ጉዳዮችን እንዲሁ በመጠኑ ስለሚረዳ፣ ሁኔታውን ተንትኖ እንደሚከተለው ለመግለጽ ይሞክራል። በኢትዮጵያ ሰንፎ የቆየው ሁኔታ ድንገት እየተቀየረ መሄዱ ቢታይም፣ ሀገሪቱ አሁንም ከተናወጠ ባህር ላይ እንዳለች የምትወዛወዝ ታንኳ ትመስላለች። ለውጥ ሲመጣ፣ ለጊዜውም ቢሆን ብዙ ውጥንቅጥና ውጣ-ውረድን ያስከትላል። ሀገራችን በዚህ ወቅት ላይ እንዳለች ተረድተን ለውጡ በሰላም እንዲደረግ ታላቅ ጥረት ማድረግ ይገባናል። ጠ/ም አብይ አህመድን ፈጣሪ በተአምሩ ወይም ሕዝብ በትግሉ ያፈራቸው ማለት ስህተት አይሆንም። ዳሩ ግን፣ እንደሚታየው፣ የኒህ መሪ ዕለታዊ ድርጊት እጅግ የላቀና ሕዝብ ከአሰበው ወይም ከገመተው በላይ ስለሆነበት፣ ለማመን እየተሳነው ነው። እያደር ረገብ እያለ ሄደ እንጂ፣ ጥርጣሪው ተፋፍሞ ደስታውን ለማቀዝቀዝ በለውጡ የከፋው ብዙና ክፉ አውርቷል። መደሰት ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመን ነው። ተጀምሮ የሚታየውም የዚይ ሁኔታ ነው። ፌደሬሽኑ ለዚያ ዕቅድ አለው።
የክቡር ጠ/ም ዶር አብይ አህመድ አድማሶች
የክቡር ጠ/ም ዶር አብይ መልካም ስራ ከቀጠለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰለትን በረከት እንደ ተአምር ለአለም የሚያስተጋባ ይሆናል። ጠ/ም አብይ በአጭር ጊዜ ያሳዩት ለውጥና የለውጥ ድርጊቶች ማናቸውንም ኢትዮጵያዊ ከጥርጣሪ ላይ ቢጥለው አያስደንቅም። ጠ/ም አብይ የራሳቸውን የጦር ኃይል ይዘው ከስልጣን አልወጡም። ያለውን የሕዝብ ድጋፍና ኃይል አገኝተዋል። ከተፎካካሪው (ይሳቸው ቃል) ክፍል ሆድ የፈለቁ ባይሆኑም፣ ወያኔ ከዘነጋውና ካላሰበው ንዑስ ክፍል መፍለቃቸው ለሕዝብ ጥርጣሬ፣ ድንገት ለደረቀውና መከነው ወያኔ ዕንቆቅልሽ ሆኗበታል። ለውጡ ሕዝብን ቶሎ ያጠገበው ይመስላል። የሚበላው ጥሬ ቆሎ ተነስቶት የኖረው አሁን፣ እነሆ ዳቦ ሲባል፣ ‘የት እለ ቁርጡ?’ ብሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገባውን ስለሚያውቅ ይጠይቃል። በቀላሉ አይታለልም፣ አይደለልም። ‘ነገ አይንህ ያያል’ቢሉት ‘ዛሬ እንዴት አድሬ?’ አለ አይነስውሩ፣ የተባለው ታሪክ የሰውን (የኢትዮጵያ ሕዝብን?)ጠባይ የሚገልጽ ይመስላል። የኢትዮጵያ ሰው ታላቅነቱን የሚያሳንስበትን አይወድም። አጨራረሱ ያላማረው ፖል ሄንዝ፣ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ራሱን እንደንጉሥ ይቆጥራል” ያለው ብዙ ዘመን ተመልክቶና አጥንቶ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውን ሰው ወይም ሕዝብ በከንቱ የሚሸነገል አይቀበልም። ይህን ታሪክ አጥብቀው የሚረዱት ጠ/ም አብይ የጀመሩትን ታላቅ ስራ አድማሱን እያሰፉ ናቸው። ከቤት ውስጥ ያለው ስባሪ ኃይል ሳያውቅ ወይም በድንቁርና እንዳይባልግ የሰጡትን ምክር ካልሰማ እግሩ ለሰንሰለት ይዳረጋል። ስለዚህ፣ ጠ/ም አብይ የሚፈልጉትን ተወዳጅነት፣ ተቀባይነት፣ ተከባሪነትና ተባባሪነት ሲጠይቁ ሊነሱ አይገባም። እንደውም ሕዝብ ሰራዊት ሆኖ እኒህን መሪ የሚጠበቅበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አለበት። ከዚህ ውጭ፣ ከወደቀና እየተገረመሰ ካለው የሙታኖች አካል ጋር መሪውን አቀላቅሎ ማየት ትልቅ የፖለቲካ ቅስፈት አስከታይ ስህተት ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠ/ም አብይን አቅፎ የኔ ብሎ ሙጥኝ ማለት አለበት። ያልታወቀ የኋላ ኃይል ቢኖር ባይኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድ አይኖረውም። ፈላጭ ቆራጭ የሚሆነው የመንበሩ ስልጣን በራሱ እና በወከል መሪ እጅ ነው።
ጠ/ም አብይ ከላይ የተጠቀሱትን ተወዳጅነት፣ ተቀባይነት፣ ተከባሪነትና ተባባሪነትን ከወገናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከውጩ ዓለም ጭምር የሚፈልጉት ትልቅ ጉዳይ ነው። ይህንን ለማገኘት ብዙ ሀገሮችን መጎበኘት ጀምረዋል። መልካም ነገር ነው። የሀገር መገንብያ ዕቅዶችን ለሟሟላት ብዙ ድጋፍ ይፈልጋሉ። እንኳን የታላቅ ሀገር ቀርቶ የመንድርም ችግር ያለ ሕዝብ ድጋፍ አይፈታም። አንዳንድ ሰው ጠልቆ በብዙ አንጻር ተመራምሮ ካላየው፣ ያልሆነ ሀሳብ፣ ትችትና ቅንቃኔ ውስጥ ይገባል። የሀገር ጉዳይ እያንዳንዱን ዜጋ ስለሚመለከት፣ ማንም ሰው ሀሳቡን ለመግለጽ መቻል አለበት። ይኽም ሲሆን፣ የሰው አስተሳሰብ ዝቅና ከፍ ስለሚል ይህን አቅም መረዳትና ማስተናገድ ይገባል። ማንንም ሰው በአቅሙ ምክንያት ሀሳቡን ማጣጣል አይገባም። በአንጻሩ ማንም ሰው ባለው አቋም አስቸጋሪም መሆን አይገባውም። ሳይረዳና ሳይገነዘብ አንድ ሰው በግብዝነት ተንስቶ ምኞቱን ይገልጻል። ጠንቁን ሳይመራመር የቆመበትን ድንጋይ ልፈንቅል ይላል። ሳይመራመር ይህ ይለወጥ ይላል፣ መተኪያውን ሳያውቅ። ራሱ ተጨማሪ ችግርና እንቅፋት ይሆናል። ይህ ሆኖ፣ በስርዓት፣ በቅጡና በተጨበጠ ጉዳይ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ የሚወተውቱ አሉ። ያለ እነሱ ኢትዮጵያ ጠባቂ አይኖራትም። ለውጡ አነሰ ማለቱ የነሱ ሚና ነው። ይኽ ወደር የሌለው አስተዋጽዖና ተፈላጊ ድምጽ ነው። ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ጧፍና ሻማ ናቸው። ስማቸው ተጠቅሶ የማያልቀው የኢትዮጵያዊነት ህልውና ጠባቂ የሆኑት እነ አበበ ገላው፣ አበበ በለው፣ ታማኝ በየነ፣ ቶሎሳ ኢብሳ፣ ጆሴ ሌሎችም የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲነሳና ሲናገሩ አካላቸው የሚግለው ስማቸው ተዘርዝሮ አያልቅም። አሁንም ብዙዎችን አለመጥቀሱ ይቀፋል። ሆኖም፣ የዚህ ትውልድ ታሪክ ያለነሱ ገድል አይጀመርም። ኢትዮጵያ ለዚህ ያበቃት፣ ለወደፊትም ከታለመው የሚያበቃት የነዚህ ጀግኖች ኃይል ነው። ስለዚህ እኒህ ጀግኖች ኢትዮጵያ ‘እፎይ!’ እስክትል ማቆም የለባቸውም።
የፌደሬሽኑ የውሳኔ አቋሞች
ጠ/ም አቢይ በኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ሰፍኖ የቆየውን አቆርቋዥ ስርዓት ለመለወጥ እስከአሁን የወሰዱት የሽግግር እርምጃ ወደር የሌለው ነው ቢባል ፈጽሞ ማጋነን አይሆንም። ባጭር ጊዜ የፈጸሙትን ብንመዝን በዕውነቱ በማንም ሌላ ኃይል ይከናወን ብሎ መገመት አይቻልም። ይህን ዕርምጃ ላለመቀበል ማንም ሰው ህሊና ያግደዋል። ይህ ማለት ኢትዮጵያ መሪዎች የሏትም ወይም ጠ/ም አብይን የሚያስንቁ በምድሯ አይፈጠሩም ለማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የፈላስፋዎችና የጥበበኞች ጫካ ናት። የኢትዮጵያ ማህጸን ገና ዓለምን የሚያስንቁ መሪዎችን ታፈራለች። ያሏት ጥበበኞች ካሏት ደን ምርጥ ዛፎች ይበዛሉ። “ኢትዮጵያ ላንቺ ካልሆንኩ አልኑር! ደምህ ደሜ ነው!ወዘተ” እያለ የተነሳውን ወጣት ዙሮ መቃኘት ህሊናን ያረካል፣ በተለይ ደግሞ የወደፊቱን ያስተማምናል።
ጠ/ም አብይ ከኢትዮጵያ ተስፋዎች አንዱ ምናልባትም በዚህ ዘመን የመጀመሪያው ናቸው። ኢትዪጵያን ለመገንባት የሚጎላቸው አቅምም ሆነ ፍላጎት አይታይም። የኢትዮጵያ ሰው ‘ሕዝብ?’ሰባተኛው ንጉሥ ብሎ ሲሰይማቸው በዕውነቱ ታሪክን አነጻጽሮና ተገንዝቦ ነው ቢባል ትክክል ነው። ጠ/ም አብይ ይህ ትወልድ ከቅርሱና ከዕድገቱ ሕልም ጋር እንዲራመድ ለማድረግና የዕለቱን ችግር ለማራገፍ የተነሱ ናቸው። በውጭ ያለው ወገን ልቡንና ኃይሉን ያገር ስሜቱን በመገንዘብ እንደ አስፈላጊ ጥላና ጋሻ አርገው ያዩት ይመስላል። በቅርቡ መለዮ ለባሾችን ሰብስበው ሲመክሩና ሲያስተምሩ፣ “እናንተ የመንግሥት ተቀጣሪ ሰራተኞች ናችሁ። መሪ ሲቀየር ተጠያቂነታችሁ ላዲሱ መሪ ነው፣ ወዘተ” በማለት መክረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መልዕክቱ የዓለም ሕዝብ እንደተገነዘበው ይገመታል።
ጠ/ም አብይ በኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በዐል እንዲስተናገዱ ሀሳብ ፈለቀ። ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ጠ/ም አብይን መጋበዝ እጅግ በላቀና በደመቀ መሆን እንደሚገባው አያጠራጥርም። የኢትዮጵያ የውስጡና የውጩ ወገን ትግል ውጤት ናቸው። ጠ/ም አብይ ከውጩ ወገኖቸው ጋር በሚገናኙበት ዕለት ከዓለም ዙሪያ በሚሰበሰቡ በሚልዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያኖች ተከብሮ መሆን አለበት። ታሪካዊ ወቅት ስለሚሆንና መሆንም ስለሚገባው፣ በዚች ጊዜ ይህን መሳይ ድርጊት ለማካሄድ የነበረው አጭር ጊዜ የሚበቃ አልነበረም። ስለዚህ፣ ይህን በመረዳት የፌደሬሽኑ ቦርድ ያደረገው ውሳኔ ዕንቁ ነው።
ሌላም አሳሳቢ ሀሳቦች ሳይፈልቁ አልቀሩም። የታላቂቱ ሀገርና ሕዝብ መለያ ቅርሷ፣ የቀጣይነቷና የዘላለም ኗሪነቷን የሚያንጸባርቀው አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩ አርማዋ ነው። ኢትዮጵያኖች አንከባክበውና ከፍ አርገው በማውለብለብ ክብር ቦታውን ጠብቀው ይገኛሉ። የወያኔ መለያ ጨርቅ ወደ መጣበት ሸለቆ ይመለስ እንጂ በፌደሬሽኑ ግቢም ሆነ አዳራሽ እንኳን መስቀያ መቀበሪያም ቦታ አይኖረውም። ይህ ችግር በቅርቡ ስለሚፈታ በሚቀጥለው ጊዜ የሚያሳስብ አይሆንም። አሁን ግን በዚህም በዚያም ምንም አይነት እንከን እንዳያመጣ ተደርጓል።
ጠ/ም አብይ ባሁኑ ወቅት ትልቅ ትብብርን ይሻሉ። ይህን አለማድረግ፣ በሀገር ውስጥና ውጭ እየተፋፋመ ያለውን ታላቅ የለውጥ መንፈስ አለመደገፍ ይመስላል። ይህ ስህተት አስተሳሰብ ጉድለትና ጉዳትን ያስከትላል። ጠ/ም አብይን ‘ተባባሪና ደጋፊህ ነን፣ አለንልህ’ ማለት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን በጥንቃቄ ነው። በእስር ቤት እየተሰቃየ ያለው፣ በደረሰበት በደል የሚበሳቆለውን ሳይረሱ መሆን አለበት። ችግርህ እስከሚፈታ ድረስ አሁን በታየው ተስፋ ከተደሰተው ጋር አብረህ ተደለቅ ማለት አይገባም። ወያኔዎች መላው ወገናቸው እየተሰቃየ እነሱ ሲደልቁና ሲጨፍሩ እንደነበሩት መሆን ይሆናል። ሀገርና ሕዝብ ሰፊ ነው። ዕርዳታ ባንድ ጊዜ ለሁሉም ሊዳረስ አይቻልም። ይህን ለአንባቢዎች ማስረዳት አያስፈልግም። ግን ችግሩን አጉልቶ ለማሳየት፣ ይህ ጸሐፊ ያጋጠመውን አንድ ዕውነተኛ ምሳሌ ለመጥቀስ ይፈልጋል። በአንድ ከተማ በአንድ ረጅም መንገድ መብራት መዘርጋት ተጀምሮ፣ በመንገዱ መጀመሪያ ላይ ግራ-ቅኝ የነበሩ ቤቶች አስቀድመው መብራት አገኙ። ከመንገዱ ጫፍ ያሉ ቤቶች ገና መስመሩ ስላልቆመ መብራት አላገኙም። በመንገዱ መጨረሻ ላይ ያንድ ታላቅ ሰው መኖሪያ ቤት ነበር። እኒህ ሰው የሌላው ሰው ቤት በመብራት አንጸባርቆ ሲያዩ በጣም ተናደዱ። ወደ መብራት ኃይል መስሪያ ቤት ሂደው፡ “የማንም መሸታ ቤት ሲያንጸባርቅ የኔ ቤት ጨለማ ውስጥ ለምን ቀረ?” ብለው ትርምስ በመስሪያ ቤቱ ግቢ ፈጠሩ ይባላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ የተለያየ ችግር አለው፣ ግን ሁሉም የራሱን አብልጦ ያያል እንጂ የመንግሥትን አቅምና ዕጥረት አይረዳም። ይኽም ሆኖ ማንም ሰው የችግሩን መፍትሄ አይጠይቅ አይባልም። ጥያቄው ተገቢና መልስ ባስቸኳይ እንዲገኝለት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሀገሪቱ አቅሟን ስታጠነክርና ኃይሏን በስነስርዓት በትክክል ማዋል ስትጀምር ምናልባት በአንድ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ከችግሩ እንዲድን ለማድረግ ይችላል። ከሰፊ ዕድገት የሚጠበቀው ይህ መሻሻል ነው።
የፌደሬሽኙን ውሳኔ አስመልክቶ፣ ሌላ አንድ ትልቅ የሀገር ጉዳይ አለ። ፌደሬሽኑ የሌሎችን የኢትዮጵያ ድርጅቶች ሂደት እንዳያከሽፍ ወይም እንዳያበላሽ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ምንም ምግባሩ የስፖርትና ባህል ቅርስን ማዳበርና የስደተኛውን ወገን አንድነት ማጎልበት ቢሆንም፣ ውሳኔው የኢትዮጵያኖችን ሂደት እንዳያጨናጉልና እንዳይጻረር መጠንቀቅ አለበት። የኢሮፓው ፌደሬሽ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሰሜን አሚሪካውን ውሳኔ አይተን እንወስናለን ማለቱ የሚደነቅ አቋም ነው። በጣም የሚያኮራ አንድነትን የሚያስተጋባ ውሳኔ ነበር። በኢትዮጵያኖች ኃይል የአሜሪካ መንግሥት በኢትይጵያ መጥፎ ገዥ ኃይል ላይ የተለያዩ ዕገዳዎችን አድርጓል። መስፍን መኮንን እና ወገኖቹ ይህ ውሳኔ እንዲደነገግ ያበቁ ለዓመታት የደከሙበት ስለሆነ ይህን የሚያከሽፍ ስራ መደረግ የለበትም። ይህ ህግ የወያኔን ጀርባ የሰበረ ስለሆነ ተጽዕኖው ቀጥሎ ወያኔ ብን እንዲል የሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ ለጠ/ም አብይ ባንድ በኩል እጂግ ጠቃሚ ነው። ጉዳቱ ግዜአዊ ነው፣ ጥቅሙ ግን ዘላቂ ነው። በዚህ አንጻር የፌደሬሽኑ ውሳኔ ሲታይ ትክክለኛ ሆኖ ይገኛል።
የፌደሬሽኑ አዲስ ግብዣ ለጠ/ም አብይ አህመድ
የኢትዮጵያ የእስፖርት ፌደሬሽን ጠ/ም አብይ አህመድን ለወዳኛው በዐል ላይ የክብር ዕንግዳ አድርጎ ቢጋብዝ ተገቢ ይሆናል። ይህ ዕቅድ የራሱ ድርጊት ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ላይ የኢትዮጵያ ወገኖችን የሚያካትት መሆን አለበት። በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖችና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚሳተፉበት ይሆናል። ስለዚህ፣ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን የሚያጠቃልል በልዩ ኮሚቲ የሚሰራ ትልቅ ዕቅድ መሆን አለበት። በዚያን ጊዜ፣ ከላይ የጠቀሱት ችግሮች ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም የኢትዮጵያኖች ችግሮች ስለሚገባደዱ እንደ አሁኑ የሚያስጨንቁ ሀሳቦች አይኖሩም።
የውጩ ስደተኛው ወገን የሚያደርገውንና ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ስለሚያውቅ ድምጹን በተፋፋመ መልክ ማሰማት አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጠ/ም አብይ እንዲሳካላቸውና ለወገናቸው ያሰሙትን ራዕይ እንዲፈጽሙ ወገኖች በተቻላቸው መጠን አስፈላጊው ድጋፉ እንዳይጓደል ማድረግ ይገባቸውል። ይህ ትልቅ ብልሀትን ይጠይቃል። በዚህ ላይ ሰፊ አስተያየት ሊሰጥበት የሚያስፈልግ ጉዳይ አለ። ግን አሁን ቦታው ስላልሆነ ባጭሩ ለመጥቀስ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ተቀናቃኒ የሆነው የውጩ ኃይል መኖሩንና እሱም የተቀበረ አደጋ ሊያመጣ ስለሚችል፣ ሕዝብ እንዳይዘናጋ ማሳሰብ ያስፈልጋል። የተተከለው ባንዳን አፍርሰው ሌላ ባንዳ መገንባትን ያውቁበታል። ሕዝብን አውድመው በተአምር ሲንጠራራ ካዩ አይዞህ ማለትና ስለበደላቸው ይቅርታን ማጉረፍ ያውቁበታል። ተላላው ሕዝብ ተታለለ። ይህ ታሪክ አይደገምም።
ኢትዮጵያ መሪዋ እንደ ቴውድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምንሊክና ኃይለሥላሴ የውጩን ጥያቄ ሕዝቤ አይቀበለውም እያለ በሕዝብ ኃይል እያሳበበ የውጩን ኃይል የሚሸነግል መሪ መሆን አለበት። ተወዳጅና ተከባሪ መሪ እንዲሆን የጠ/ም አብይ ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የየአንዳንዱ ወገን ብልህነትና ድርጊት ይጠይቃል። መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ግለሰብም ተቀናቃኝ መሆን አለበት። ባንዳዎች እንደ ፕላስቲክ ሹካና ማንካ አንድን አፍ አገልግለው የሚጣሉ ናቸው። በጥቅም የተጠመዱና የተለከፉ በህዝብ መካከል ምን ጊዜም አይጠፍ። እነዚህ ግለሰቦች የባንዳነት ባህሪ ምናልባት በአጥንታቸውና በደማቸው አለ። እነሱን ማንጻት አይቻልም። የኢትዮጵያን ልጆች ማጎልመስና ማጠንከር ይጠቅማል። የፕላስቲክ ማንካና ሹካ ለበላባቸው አፍ እንጂ ለሌላ በሽታ ናቸው። ስለዚህ፣ በሀገርና በሀገር ውጭ ያሉትን አደፍራሾች ሌላ ጉዳት እንዳያመጡ ማድረግ ተገቢ ነው። እፄ ኃይለሥላሴ አገር ገንቢ ዜጋው በጦርነት ስላለቀ ባንዳዎችን በመጠቀማቸው ተነቅፈውበታል። ጠ/ም አብይን ይህ ችግር አይገጥማቸውም። ኢትዪጵያን በአስራ አምስት ዓመቶች ምድሯንና የሕዝቧን ገጽ ለመለወጥ ይቻላል ማለታቸው፣ የአፈሯን፣ የአየሯን፣ የውሀዋን፣ የደኗን፣ የሕዝቧን ጉልበት በተለይ በውጭ የሚገኘውን ወገን ያለውን የጥበብ ኃይል ገምግመው ነው። ስራን የማይጸየፍ፣ የጥበብን ስራ ያከማቸ ነው።
መደምደሚያ
የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌደሬሽን የጠ/ም አብይ አህመድን ግብዣ አስመልክቶ ስለማስተናገድ የተደረገውን ውሳኔ ለመግለጽ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ለጠ/ም አብይ፣ በሁለተኛ ደረጃ ለፌደሬሽኑ ከዚያም አልፎ በሀገር ውስጥና ውጭ ለሚገኘው ወገን ውሳኔው እንደሚጠቅም እንዲሁም ውሳኔው በሌላ እንዳይተረጎም ዘለቄታ ጥቅም በለው ሁኔታ ላይ የተወሰን መሆኑን ለመግለጽ ነው።
እስከ አሁን በአስደናቂ መልክ እየተጓዘ ያለው የጠ/ም አብይ ዕቅድ የዚህን ግብዣ መተላለፍ ወርቃማ ጊዜውን መፈለጉ እጅግ በጣም የሚደነቅ ሀሳብ ነው። ይህ ደግሞ ሀሳቡን ለደገፉት ወደር የሌለው ደስታ የሚሰጣቸው መሆን አለበት። ሀሳቡ አልቀረም በታላቅ በዐል ለማክበር እንዲቻል መታሰቡ የሚያስንቅ ውሳኔ ነው።
ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱና ለውጥ መስመር እየያዘ መሄዱን ለመገንዘብ የሚሳነው የለም። በዚህ ጊዜ ጠ/ም አብይ ቢመጡ ውጤቱ ምጥን ይሆን ነበር። አዲሱ ታላቅ መሪ ባልታየ ታላቅ ደስታ ከዙፋን ላይ ሲወጡ አለማየቱ ነበር። ጠ/ም አብይን ኢትዮጵያዊው ሁሉ ተከታይ ወታደራቸው ነው። የወያኔ መጥፎ ስራ ታጥቦ ኢትዮጵያ እስክትጸዳ ድረስ፣ ጠ/ም አብይን መተባበር የያንዳንዱ ወገን ግዳጅ ነው። ወያኔወች ያበላሹት ብዙ ነው። አሁንም ኢትዮጵያኖች ከሚያገኙት ዕድል ይበልጥ የኔ እጣ ከፍ ማለት አለበት ብሎ የሚያስብ የወያኔ ርዝራዥ አይጠፋም። መጥፎ እያሰበ መጥፎ ይመኝ ይሆናል። ወግኖችን የማከፋፈሉን የተወረሰ ጠባይ አለ። ቁጥሩ እየመነመነ ነው፤ ድምጹ እየተሰለበ ነው። ጠ/ም አብይ ከሰጡት ሌላ የላቀ ምክር አይገኝም።
የኢትዪጵያ ሕዝብ ከነቅርሱ ለዘላለም ይኑር!
zegfanta@outlook.com
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።