በዳንኤል ሃይሌጊዮርጊስ
የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በደቡብ ኮርያ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ
ሰኔ 11 2010 ዓ.ም
መግቢያ
የኮርያ ጦርነት ከቆመበት ከ1953 ላለፉት 65 አመታት ደቡብ ኮርያ እጅግ ድንቅ (ተአምር) የሚባል የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችላለች።
በ1956 የአንድ ሰው አማካይ አመታዊ ገቢ (GDP per capita) 67ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን በ2018 ይህ አሃዝ ከ400 እጥፍ በላይ በማደግ 30,000 ዶላር ደርሷል። የአገሪቷ ቆዳ ስፋት ከኢትዪጵያ በ10 እጥፍ የምታንስ ትንሽ አገር ብትሆንም ምጣኔ ሃብቷ ግን በትሪሊየን ዶላር የሚገመት ሃብታም ሀገር ነች። አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በአለም ከፍተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሃገራት መካከል መሰለፍ ችላለች። ከስድስት አስርት አመታት በፊት የደቡብ ኮርያ ነብሰ ወከፍ ገቢ ከኢትዮጵያ እጅግ ያነሰ ነበር። በርግጥ በኮርያ ጦርነት ወቅት (ከ1950 እስከ 1953) ኢትዮጵያ 6000 አካባቢ ወታደር የያዘዉን የቃኘው ክቡር ዘበኛ ጦር በመላክ ከሌሎች የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች ጋር ከደቡብ ኮርያ ወገን በመሰለፍ የኮሚኒስቱን ሃይል በመውጋት ድጋፍ አድርጋለች። የኢትዮጵያ ወታደሮች በጀግንንነታቸው እና የመዋጋት ብቃታቸው የተመሰከረላቸው እንድነበረ የተለያዩ የኮርያ ትርክቶችና ድርሳናት ያሳያሉ። ይህም አኩሪ ገድል በኮርያ ሃገር በየአመቱ የሚዘከር ሲሆን በጦርነቱ የተሳተፉ አገሮች የሚወክሉ ሰዎችን በመሰብሰብ የምስጋና ዝግጅት ይካሄዳል።
የአለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ ድርጅት (IMF) ባወጣው የአገሮች የኢኮኖሚ ደረጃ መሰረት ደቡብ ኮርያ ኢኮኖሚ በአለም 11ኛ ከፍተኛ ኢኮኖሚ እንደሆነ ሲገልጽ አመታዊ ጠቅላላ ገቢ (GDP) 1.5 ትሪሊየን እንደሆነ ይገልጻል። በሌላ አንጻር በአለም አቀፍ ንግድ የ7ኛ ይዛ ትገኛለች። አውቶሞቢሎችን በማምረት ደግሞ 5ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን መርከቦችን፣LCD Screen, ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እና የሜሞሪ ቺፕ በማምረት ደግሞ የአለም ቁንጮ በመሆን አንደኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች። በተጨማሪም ደቡብ ኮርያ በአለማችን እጅግ ፈጣን ብሮድባንድ ኢንተርኔት ያላት በመሆን ቀዳሚውን ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እንዲሁም በአለም 8ኛዋ የትላልቅ ቢዝነስ ኩባንያዎች (Large business conglomorates) ባለቤት በመሆን ትታወቃለች። የሳምሰንግ፣ኪያ፣ ሃዩንዳይ እና አየር መንግዱ ጨምሮ ሌሎችም በአለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው የገነነ ግዙፍ ካምፓኒዎች ሙሉ በሙሉ ንብረትነታቸው የግለሰቦች እና የአክሲዬን ባለይዞታዎች መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል። በ2012 በፐርሺያ የትምህርት አገልግሎት ድርጅት ባወጣው ሪፓርት መሰረት በትምህርት ጥራት ከፊንላንድ በመቀጠል በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የኢንቾን አለምአቀፍ አየር መንገድ ከ1700 የአለማችን አየር መንገዶች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መስፈርቶች በመወዳደር ላለፉት ተከታታይ አመታት ምርጥ አየር መንገድ በመሰኘት የመጀመሪያ ደረጃ ይዞ ይገኛል። የአለም ባንክ, የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና WHO የመሳሰሉ አአለማቀፋዊ ድርጅቶችን የመሩ ኮርያዎችም ማበርከት ችላለች።
በሙዚቃና መዝናኛ ዘርፍም በአለምአቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆኑ አርቲስቶችን ማፍራት ችላለች። እዚህ ላይ በዩቲዩብ ላይ ጋንግናም ስታይል የሚለው ዘፈኑ ከ3 ቢሊዬን በላይ በመታየት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው PSY ልብ ይሏል። እንዲሁም K-Pop እና የኮርያ ማእበል ወይም ሃልዩ (Korean wave-Haliu) በመባል የሚታወቁት በተለያዩ የአለም ክፍላት በአድናቂዎቻቸው ከሰውነት በላይ “የሚመለኩት” አርቲስቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ደቡብ ኮርያ በአለምአቀፉ የእርዳታ ሰጭ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ከተረጂነት ወደ ረጂነት የተሸጋገረች ብቸኛዋ አገር ናት። ይህም ከሌሎቹ አባል አገራት ለየት ያደርጋታል። የደቡብ ኮርያ ኢኮኖሚያዊ ተአምር በHan Kang (ታዋቂው የኮርያ ወንዝ) ብቻ የታጠረ ሳይሆን ከአምባገነናዊ ስርአት ወደ 20ኛው ክፍለዘመን እጅጉን ዴሞክራሲያዊ አገር ወደመሆን ያሸጋገረ ድንቅ ተሞክሮ ነው።
የኮርያ እድገት ትንትና- ከታሪካዊ፣ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች አንፃር
ከባህላዊ ሁኔታዎች አንፃር ስንመለከተው ኮርያ ጠቃሚ የሚባሉ ባህላዊ እሴቶችን ከቻይና በመውሰድ ለእድገታቸው ተጠቅመውበታል። ከነዚህ ውስጥ የቻይና ፊደላትን ከመጠቀም ጀምሮ የህብረተስባዊነት የህይወት ዘይቤና አስተሳሰብ (Confucianism) ወደራሳቸው ሁኔታ ወስደው መጠቀም መቻላቸው አንዱ ምክንያት ነው። Confucianism በኮርያ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በ ምስራቅ እስያ አገሮች በሙሉ የዘመናዊ ካፒታሊዝም እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።ደቡብ ኮርያዎች የራሳቸውን ፊደል ቀርፀው መጠቀም እስከጀመሩበት 1446 ድረስ የቻይና ፊደላትን ሲጠቀሙ ነበር። ቀደምት ነገስታቶቻቸው አገር ወዳዶች ከመሆናቸው በተጨማሪ የምጡቅ አእምሮ ባለቤት እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ከነዚህ ቀደምት ነገስታት በቀደምትነት ስሙ የሚጠቀሰው ንጉስ ሴ ጆንግ ሲሆን ሃንግል በመባል የሚታወቀውን የኮርያ ፊደላትን ከመፍጠሩ በተጨማሪ በሳይንስ፣ፍልስፍና፣ሙዚቃና ቋንቋ እድገት ላይ የሰሯቸው ስራዎች ለአሁኗ ኮርያ ትልቅ መሰረት የጣለ ነበር። ይህ ንጉስ ምርምር እና ሳይንስ እንዲስፋፋ የግንዘብ ድጋፍ ስርአት (Funding and scholarship system) አቋቁሞ እንደነበር ይነገርለታል። የዝናብ መጠን መለኪያ፣በውሃ ሃይል የሚሰራ ሰአት፣ የስነ ከዋክብት ጥናት ካርታዎችን ማሰራት ችሎ ነበር።
ኮርያዎች በታሪካቸው የተመዘገቡ ፈታኝ ጊዚያቶችን ለእድገታቸው እንደ በጎ አጋጣሚ በመውሰድ ተጠቅመውበታል። ደቡብ ኮርያ በሩቅ ምስራቅ ንፍቀ አለም የምትገኝ አገር እንደመሆኗ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊው ሁኔታው በከፍተኛ ውድድር ላይ የተመሰረተ ነው። በአካባቢው በተደረጉ ታሪካዊ ጦርነቶች ምክንያት ችግርን የመቋቋም አቅም(ጥበብ) እንዳዳበሩም ይታመናል። በሩቅ ምስራቅ ከተደረጉ ጦርነቶች መካከል የኮርያ ጦርነት (1950ዎቹ) እና የቬትናም ጦርነት(1960ዎቹ) በጣም አውዳሚነታቸው ተጠቃሽ ናቸው።
አሁን በኮርያ ያሉት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከጦርነቱ በኋላ በአዲስ መልኩ የተቋቋሙ ናቸው። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ Hyundai የወታደሮችን ጉልበት በመጠቀም በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ድልድዬችን በመስራት እና በመጠገን እንዲሁም መንገዶችን እና የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በመገንባት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ከአገር ውጭ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍም (ለምሳሌ Alaska ላይ የተሰሩ ፕሮጀክቶች) ሃብት መፍጠር የቻለ ሲሆን ፤ የድርጅቱ ባለቤት በ1991 ላይ Fortune የተባለው መፅሄት ባወጣው የሃብት ሰንጠረዥ ደረጃ ላይ በአጭር ጊዜ ከአለም 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሎ ነበር።
ከ1965-1973 የተካሄደው የቬትናም ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የነበረውን የኮርያ ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተፅእኖ ማሳደር የቻለ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ በአረቢያን በረሃ ላይ የሰራቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ኢኮኖሚው ባጭር ጊዜ እንዲያንሰራራና ወደነበረበት ሊመለስ ችሏል።
ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪም ከጦርነቱ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ኮርያን ያስተዳደሩ መሪዎችም ብቃት ያለው አመራር በመስጠት ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። ደቡብ ኮርያን ከ1963-1979 ያስተዳደረው ፕሬዝደንት ፓርክ ቻንግ ሂ አዳዲስ ፓሊሲዎችን እና አሰራሮችን በመፍጠር ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉ ባሻገር እገሪቱ ዘመናዊነትን እንድትላበስ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ፕሬዝደንት ፓርክ አውራጎዳናዎችን እና የፍጥነት መንገዶችን ቅድሚያ ሰጥቶ መገንባት ለኢኮኖሚው እድገት ያለውን ጥቅም በመረዳት ከዋና ከተማው (ሶኡል) እስከ የወደብ ከተማዋ (ቡሳን) ድረስ ያለውን የፍጥነት መንገድ በ60ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በማስገንባት ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ሞተር ሆኖ እንዲያገለግል አስችለዋል። ይህም እንደታሰበው የብረታብረት እና የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙና ምርቶቻቸው በፍጥነት ለአለም ገበያ እንዲደርስ አግዟቸዋል። የመጀመሪያው የኢኮኖሚያዊ እቅዳቸው ከ1962-1966 ባለው ጊዜ በ7.1% ማደግ የነበረ ቢሆንም የዚህን እቅድ ግብ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሊደርሱበት በመቻላቸው እቅዱን በማሻሻል በቀሪው የእቅዱ ዘመን ኤክስፓርት መርህ ያደረገ ግብ በማስቀመጥ ተጨማሪ እቅዶችን ማሳካት ቻሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኮርያ ኢኮኖሚ ወደ ውጭ በሚላኩ እቃዎች (Goods and products) ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሎታል። የግብርናው ኢኮኖሚ እድገት ለብዙ ዘመናት በድጎማ የመጣ ቢሆንም የኢንዱስትሪውን እድገት ተከትሎ ግብርናውም ማደግ በመቻሉ ምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።ለኢንዱስትሪዎቹ ግብአት የሚሆን ጥሬ እቃ በብዛት ከውጭ የሚገባ ሲሆን ለምግብ አገልግሎት የሚውል ግብአት በአብዛኛው በአገር ውስጥ ምርት ለማሟላት ጥረት ይደረጋል። ነገር ግን አሁንም ይህም ሴክተር ከውጭ ግብአት ጥገኝነቱ የተላቀቀ አይደለም።
ኮርያዎች በታሪካቸው ደጋግመው እንደሚያነሱት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ እቅዶቻቸውን ለመተግበር በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸው በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ የብድር ጥያቄ ቢያቀርቡም ብድሩን መመለስ አይችሉም በሚል ሰበብ መከልከላቸው ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ እድርጓቸዋል። በመጨረሻም ከጀርመን አገር ለተገኘው የ40 ሚልየን ዶላር የባንክ ተያዥ ያስፈልግ ስለነበር 5000 የሚሆኑ የመአድን ሰራተኞች እና 2000 ነርሶችን በተያዥነት ለመላክ ተገዳ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ትርፍ ገንዘባቸውን ወደ አገር ቤት በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ለኢኮኖሚው እድገት አስትዋፅኦቸው ከፍተኛ ነበር።
የኮርያ ስነመልክአምድራዊ ተፅእኖ በምንመለከትበት ጊዜ የጂኦግራፊ አቀማመጧ ለውጭ ተፅእኖ ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል። ነገር ግን ይህን ተፅእኖ ለበጎ ሁኔታ ተጠቅመውበታል። ደቡብ ኮርያ በሁለት ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቶች (ቻይና እና ጃፓን) መካከል የምትገኝ መሆኗ የኮርያዋ ዋና ከተማ (ሶኡል) የእስያ ዋና መናሃሪያ እንድትሆን አስችሏታል። ከሶኡል ወደ ሻንጋይ፣ ወደ ኦሳካ፣ ወደ ቶክዮ እና ወደ ወደ ቤይጂንግ የሚደረገው የአየር በረራ ከ3 ሰአት የማይበልጥ መሆኑ ለዚህ ትስስርና ግኑኝነት አስተዋፅኦ አድርጓል።
ጄቦል (Jaebeol) በመባል የሚታወቁት በግለሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች (Conglomerates) ለኢኮኖሚው እድገት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም። እነዚህ ግዙፍ ካምፓኒዎች በሁለት መንገድ ሊገለፁ ይችላሉ፦
1)ንብረትነታቸው የግለሰቦች መሆኑና
2)የሚሳተፉበት ዘርፍ እጅግ ብዙ መሆኑ ልዩ ባህሪያቸው ነው።
የነዚህ ካምፓኒዎች በጠቅላላው የአገሪቷ ደህንነትና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አላቸው። ለምሳሌ ሳምሰንግ የኮርያ ካምፓኒ ባይሆን ኖሮ የኮርያ ኢኮኖሚ ከፊሊፒን ጋር እኩል ይሆን ነበር። በሌላ አገላለፅ በሳምሰንግ አስተዳደር ላይ ችግር ቢፈጠር ባጠቃላይ ኢኮኖሚ እና መንግስታዊ አስተዳደሩ ላይም በግልፅ የሚፈጠር ውድመትና አለመረጋጋት ይኖራል።
ከዚህ በተጨማሪ የኮርያ ዜጎች ለኢኮኖሚው እድገት ተጠቃሽ ነው። ኮርያዎች ረጅም ሰአታትን በመስራት ከአለም 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የኮርያ ዜጎች አገር ወዳድ መሆናቸውና የዘር፣ የቋንቋ እና የባህል ልዩነት የሌላቸው ህዝቦች መሆናቸው ለእድገታቸው አንዱና ዋናው ምክንያት ነው። በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በተፈጠረው አገራዊ የኢኮኖሚ ውድቀት በራስ ተነሳሽነት ከ3.5 ሚልየን ህዝብ የተሳተፈበት የወርቅ ማሰባሰብ ዘመቻ በማድረግ ከ2.17 ቢልየን ዶላር ማሰባሰብ በመቻላቸው ችግሩን መቋቋም ከመቻላቸው ባሻገር አገር ወዳድነታቸውን አስመስክረውበታል።
የኮርያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ኮርያ ዋና ስጋት ከሰሜን ኮርያ ይቃጣብኛል ብላ የምታስበው ጥቃት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ስጋት እየቀነሰ ቢመጣም እሁንም ይህ ባህረ ገብ (Peninsula) አካባቢ ከአደጋ ስጋት የፀዳ ነው ማለት አይቻልም። ከሰሜን ኮርያ ጠቅላላ ህዝብ ጋር የሚመጣጠነው የደቡብ ኮርያዋ ዋና ከተማ ሶኡል ኗሪ ህዝብ ለአድጋ ተጋላጭንቱ ሰፋ ያለ ነው ይህም ከተማዋ ከሰሜን ኮርያ ድንበር በቅርብ ርቀት በመገኘቷ ጋር የተያያዘ ነው።
ከኢኮኖሚ ብስለት (Economic maturity) ጋር ተያይዞ በአሁኑ ጊዜ ያለው የኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ የሚጠበቅ ቢሆንም ህዝቡን ግን ያላስደሰተ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የኮርያ ኢኮኖሚ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በሀለት ዲጅት ማደግ የማይታሰብ እና ሊደረስበት የማይቻል ነገር ነው። በዚህም ምክንያት የበሰለ ኢኮኖሚ መለያ ባህሪ ወደሆነው ቀሰስትኛ እድገት እንዲመጡ አስገድዷቸዋል።
የኮርያ ኢኮኖሚ በጥንካሬው እንዲቀጥል ያስቻሉት ምክንያቶች
1)እንደ ሳምሰንግ፣ሃዩንዳይ፣ኪያ የመሳሰሉት ካምፓኒዎች በአለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ማስቀጠል መቻላቸው
2)የኮርያ መንግስት ለምርምር እና ፈጠራ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉ እና
3)የኮርያ ዜጎች ዘላቂ እድገትን የሚወድ፣የሚፈልግ እና የሚቀበልና እነዚህን እሴት ያደረጉ ህዝቦች መሆናቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
የደቡብ ኮርያ የወደፊት የእድገት ማነቆዎች ስንመለከት
1)በጤና አሰጣጥ አገልግሎት መሻሻል ጋር ተያይዞ በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት እና ለኢኮኖሚው እድገት ያላቸው አስተዋፅኦ አነስተኛ መሆኑ
2)የሌላ አገር ዜጎችን ለመቀበል ያላቸው ዝቅተኛ ተነሳሽነት
3)አላግባብ የጉልበት ብዝበዛ መኖር
4)ቤተሰባዊ ትስስሩ ጠንካራ በመሆኑ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም እና አድሏዊነት መኖር
5)ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አስቸጋሪ መሆን
6)በህዝብ ብዛቷና በቆዳ ስፋቷ ግዙፍ ከሆነችው ቻይና ጋር ያለው ከፍተኛ ውድድር ተጠቃሾች ናቸው።
በመንግስት ደረጃ በቀጣይ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ሊወሰዱ የታሰቡ እርምጃዎች
1)በመንግስት ይዞታ የሚገኙ ኮርፓሬሽኖችን፣ዩኒቨርሲቲዎችን እና የጉልበት ገበያውን በድጋሜ ማዋቀር እና ማደራጀት
2)የአገር ውስጥ ኢኮኖሚውን ለሌሎች አካላት ይበልጥ ክፍት ማድረግ
3)የሴቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎና አቅም ማጠናከር
4)አዳዲስ ማህበራዊ ትስስሮችን በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማጠናከር
5)የመንግስት መመሪያዎችን መቀነስ እና ትላልቅ ካምፓኒዎች በጥቅላላው ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ተፅእኖ መቀነስ
6)አለምአቀፋዊነትን(Globalization) ሰብሮ በመግባት ሙሉ ተሳታፊ መሆን-ያልተደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ መድረስ
7)ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት
8)በእድሜ መግፋት ከኢኮኖሚው የሚወጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ሊሳተፉባቸው የሚችሉ ተግባራትን በመለየት የድጋፍ አሰጣጥ ስርአት ማበጀት
8)በሃብታም እና ድሃው መካከል ያለው ሰፊ የሃብት ልዩነት ማጥበብ ወዘተ የሚሉት ይገኝበታል
ደቡብ ኮርያ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እየተሳተፉባቸው ያሉ ዋና ዋና የእርዳታ እና ትብብር ዘርፎች
1)KOICA-በዚህ ድርጅት አማካኝነት ፈቃደኛ ፋኖዎችን (Volunteers) በማሰባሰብ ከ68 በላይ ሃገሮች በእርዳታና ድጋፍ ላይ የሚሳተፍ መሰረቱን ኮርያ ያደረግ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት በይዘቱ ከአሜሪካው የሰላም ጓድ(Peace Corps) ጋር ተመሳሳይነት አለው
2)አዲስ መንደር ምስረታ እንቅስቃሴ (New Village Movement) በመባል የሚታወቀው ደግሞ ከተለያዩ አገሮች ጎብኚዎችን ወደ ኮርያ በማስመጣት የእውቀት እና ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት አሰራር ነው። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በዚህ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍ ተሞክሮውን በመውሰድ ኮርያን ለኢኮኖሚ እድገታቸው ተምሳሌት (Role model) ሲያደርጓት ይስተዋላል።
___
ማስታወሻ: ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።