ቦርከና
ሰኔ 17 2010 ዓ.ም
ትላንት በመስቀል አደባባይ በተጠራ ሰልፍ ላይ በተወረወረ የእጂ ቦንብ አንድ መቶ ስልሳ አምስት ያህል ሰዎች ቀላል እና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ፤ እስካሁንም የሁለት ሰዎች ህይወት አልፎአል።
ጠቅላይ ሚኒስትር እርሳቸውን እና አለኝ የሚሉትን ጥገናዊ የለውጥ ርምጃ በመደገፍ በመስቀል አደባባይ ለተገኘ አራት ሚሊየን ለሚደርስ ህዝብ ንግግር አድርገው እንደጨረሱ ነው ከመደረኩ በቅርብ እርቀት ፍንዳታው የደረሰው።የጥቃቱ ኢላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነበሩም ተነግሯል።
በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው በጥቁር አንበሳ የተኙ ዜጎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮነን ትላንት አመሻሹ ላይ ጎብኝተዋል።
የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ ጠንካራ ነበር የተባለውን ፍተሻ አልፈው ጥቃቱን አድርሰዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና ምርመራው ሲጠናቀቅ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አህመድ ሼዴ አስታውቀዋል።
በጠጨማሪም መንግስት ለጥቃቱ መፈጠር ክፍተት ፈጥረዋል ያላቸውን የአዲስ አበባ ምክትል ፖሊስ ኮሚሺነር እና ሌሎች ስምንት የፌደራል ፖሊስ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በናዝሬት ፤ በጎንደር ፤ ደብረማርቆስ እና ደሴ በደማቅ ሁኔታ እንደተደረገም ታውቋል።
ዛሬ ደግሞ በድሬዳዋ ስታዲዮም ተመሳሳይ ሰልፍ እንደተደረገ ታውቋል።
__
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።