spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትጥንቃቄ የሚያሻው የኤርትራ ጉዳይ። (ክፍል አንድ) (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

ጥንቃቄ የሚያሻው የኤርትራ ጉዳይ። (ክፍል አንድ) (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
ሰኔ 21 ፤ 2010 ዓ.ም.

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው ብሩሕ ተስፋ እና ለውጥ፤ በተለያየ አቅጣጫ መራራ ትግል የተደረገበት፤ ከፍተኛ የሕይወት የሕሊና እና የአካል መስዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑን ለማንም ማስታውስ አያሻም። ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርም የዚህ መራራ እና የረጅም ጊዜ ትግል እና የመስዋእትነቱ ውጤት ናቸው። የተከፈለውን መስዋእትነት እና ሕዝቡ ላይ ለዓመታት የደረሰውን ግፍ፤ ግምት ውስጥ በማስገባት፤ እየሰጡ ያሉት አመራርም ሕዝቡን ያስደሰተ እና ሊበረታታም የሚገባው ነው። ዶ/ር አብይ በአጭር ጊዜ ውስጥ፤ የተጀመረው ለውጥ መሰረት እና አቅጣጫ እንዲይዝ እየሰጡት ያለው አመራር የብዙዎቻችንን ልብ አሸንፏል። በጎ ስራቸውም መደገፍ እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለኝም። መደገፍ አለበት ሲባል ግን፤ በጭፍን ይደገፉ ማለት ሊሆንም አይገባውም። አንዳንዶች፤ ዶ/ር አብይን እንደ ትግሉ ግብ በመውሰድ፤ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ግቡን አቅጣጫ እንዳያስቱት ስጋት አለኝ። ምንም እንኳን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ቢያበረታቱም፤ ከደጋፊዎቻቸው አንዳዶቹ ግን፤ የሃሳብ ነፃነትን ለመንፈግ፤ ዶ/ር አብይን በመቃወምም ሆነ፤ አንዳንድ እንቅስቃሲያቸው ላይ እርምት እንዲያደርጉ ሃሳብ የሚሰጡ ዜጎችን ሲያዋክቡ እና አላስፈላጊ ታርጋ ሲለጥፉ ይታያሉ። ይህ ታርጋ የመለጠፍ እና ሰዎችን የማሳቀቀ፤ የወደቀ የፖለቲካ ባሕል፤ በአንድ ሌሊት ይቀየራል የሚል እምነት የለኝም። የተለየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች፤ ወከባውን ወይም ታርጋ ልጠፋውን በመፍራት፤ ሃሳባቸውን ከማጋራት ወደ ኋላ እንዳይሉ ላሳስብ እወዳለሁ።

እስካሁን ድረስ የዶ/ር አብይ አመራር ከወሰዳቸው እርምጃዎች፤ ትኩረት ያላገኙ ትኩረትን የሚሹ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ሆነው፤ በተለይ ሁለት ጉዳዮች ትኩረት ሊያገኙ ይገባል ብዬ አምናለሁ። አንደኛው ጊዜ የማይሰጥ እና አሰቸኳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጥንቃቄ እና ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ነው። በእኔ እምነት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ ትኩረታቸው ሃገር ውስጥ ያለውን፤ በተለያየ አካባቢ ብቅ ጥልቅ እያለ የሚታየውን የጎሳ/ብሔር ግጭት ማስቆም ብቻ ሳይሆን፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት እና በአስተማማኝ ሁኔታ የተርጋጋ ሃገር ለማድረግ፤ ወደ ብሔራዊ እርቅ የምንሔድበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው።

ዶ/ር አብይ በአሁኑ ስዓት የሃገሪቱን የሰው ሃይልም ሆነ የገንዘብ ሃይል፤ በኢትዮጵያውያን መካክለ ያለውን ግድግዳ በማፍረስ፤ ድልድይ መገንባቱ ላይ ቢያተኩሩ እና የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተም፤ ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚቴ ቢያቋቁሙ ይሻላል ባይ ነኝ። የኤርትራንና የኢትዮጵያን የድንበር ጉዳይ አሁን ለምን ለማየት እንዳስፈለግ ለዚህ ፀሃፍ ግልጽ አይደለም። የኤርትራ ጥያቄ ከድንበር መሬት ጥያቄ የዘለለ ብዙ የተውሳሰቡ ነገሮች ያሉበት ነው። ከዚህ ፀሃፍ ግላዊ ሕይወትም አንፃር፤ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ዛሬ ሁሉ ነገር ቢስተካከል ምርጫው ነው። ፀሃፊው የኢርትራ ተወላጅ ከመሆኑ አንፃር፤ የእነዚህ የሁለት ሃገሮች ጉዳይ ሃገራዊ ብቻ ሳይሆን ግላዊም ነው። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ዘላቂ ሰላም፤ እንዲሁም የማያቋርጥ የኢኮኖሚ ትሥሥር እንዲኖርም ይፈልጋል። ልክ እንደ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የኤርትራም ሕዝብ ተስፋ የሚሰጠው መሪ እንዲኖረው እና፤ ኤርትራም ውስጥ “የሕዳሴ አብዮት” እንዲኖር ይጠራል። “የኤርትራ ጥያቄ” ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ እንጂ ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ “ቦምብ” እንዳይሆንም ነው፤ ይህንን ደወል የሚደውለው።

ታሪክ እንደሚያስተምረን፤ ብዙውን ጊዜ ሃገራት በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ የሚዋዥቁት፤ በተገቢ ሁኔታ፤ በዘላቂ መፍትሔ መቋጨት የሚገባቸው ጉዳዮች በአግባብ ባለመቋጨታቸው ነው። ሕዝብን እሳቤ ባላደረገና፤ በተለይም ሕዝብ ያልወከላቸው መንግስታት፤ ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ የሚወስዷቸው ችኩል እርምጃዎች፤ የአስተዳደር፤ ወይም የሰዎች የሥልጣን መተካካት ሲፈጠር፤ ቁስሉ እያመረቀዘ ወደ ሌላ ግጭቶች ያመራሉ። በሃገራችንም ያየነው የተደጋገመ የእርስ በእርስ ጦርነት የእንደዚህ ዓይነት ችኩል የፖለቲካ እርምጃዎች ውጤቶች ናቸው። ቋሚ በሚመስሉ፤ ግን፤ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም በሚወሰዱ ውሳኔዎች ለሃገራችን የማይሽር ቁስል ሆኖ የቆየው የኤርትራ ጉዳይ ነው። የኤርትራ ጉዳይ፤ በ1960ዎቹ በተገቢ ሁኔታ፤ በረጅም እይታና፤ ዛሬ ሁለት የሆነውን አንድ ሕዝብ፤ ፍላጎትና ጥቅም እሳቤ ውስጥ አስገብቶ፤ መፍትሔ ቢያገኝ ኖሮ፤ ሃገራችን አሁን ያለችበት አረንቆ ውስጥ አትገባም ነበር። ለ60 ዓመታት ገደማ የኤርትራ ጉዳይ፤ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ራስ ምታት የሆነና ለብዙ ሕይወትና ንብረትም መጥፋት ምክንያት ሆኖ የቆየ ነው። ያ “ደም የጠማው መሬት” ግን የነዚህን ብርቅዬ ልጆች ደም ጠጥቶ የጠገበ አይመስልም። ሥር ለሰደደው የኤርትራ ችግር፤ አሁንም ለጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የይድረስ ይድረስ “መፍትሔ የሚመስል” ግን ዘላቂ መፍትሔ የማይሆን ውሣኔ እየተሰጠ ነው። ዛሬም ሕዝብን እሳቤ ውስጥ ያልከተተ፤ ከሕዝብ ጋር ያልመከረና ኑ “እንታረቅ” በሚል ቅን ፍላጎት፤ ግን፤ ጊዜን ጠብቆ በሚፈነዳ ቦምብ የተጠቀለለ ለመሆኑ፤ በተለይ በነዚህ ሃገራት ድንበር ላይ ያሉ ዜጎች አሁን የሚያሰሙት ዋይታ የወደፊቱን ችግር ያመላክታል።

የኤርትራን ጉዳይ በሰከነና በረጋ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንዲችል፤ በተለይ የግንቦት 1990 ዓ.ም ጦርነት ለምን እና በማን እንደተጀመረ መፈተሽ ያስፈልጋል። እርቅ የተቀደሰ ነገር ነው፤ በእርቅ ስም ግን ማንም ከሃላፊነት መሸሽ የለበትም። በዚህ ርእስ ስር፤ ፀሃፊው ወደ ሃላ በመሄድ የጦርነቱን መንስኤ ይጎበኛል፤ መፍትሔ የሚለውንም ይጠቁማል። አንባቢን እንዳያሰለች፤ ጽሑፉ በሁለት ተከፍሏል፤ ይህ የመጀመርያው ክፍል ነው።

የኤርትራ ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ያስከተለው ጉዳት ብዙ ስለተባለለት፤ የዛሬ ትኩረቴ አሁን ለኤርትራ ይሰጣል የተባለው የአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ የድንበር መሬት ነው። ብዙዊች ስለግንቦት 1990 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያላቸው ግንዛቤ ውስን ነው ብዬ እገምታለሁ። በተለይም የኤርትራ የፕሮፖጋንዳ ሃይል “ኢትዮጵያ ግንቦት 13 1998 (እንደ አውሮፓ) ኤርትራ ላይ የጦርነት ክተተ አወጀች” እየተባለ የሚነገረው ምንም መሰረት የሌለው ዲስኩር ብዙዎችን አሳስቷል፤ ዛሬም እያሳሳተ ነው። በተለይም መላውን ኤርትራን፤ በሕገ ወጥና፤ ሕዝብ ባለመከረበት ሁኔታ፤ ለሻእብያ ያስረከበ የመለስ ዜናዊ መራሹ መንግሥት፤ ለምን ከሰባት ዓመታት በኋላ፤ ኤርትራን ለመውረር ፈለገ? ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ በቂ መልስ የሚሰጥ የለም። ‘ኢትዮጵያ አሰብን ስለፈለገች ነው’ ወረራ ያካሄደችው የሚለው የብዙ ኤርትራውያን ወገኖቼ መላ ምትም ውኃ አይቋጥርም። ከፖለቲካም አንፃር፤ የወያኔ/ኢሕአዲግ መራሹ መንግስት ሳይወድ በግዱ የገባበት ጦርነት፤ በተለይም በወያኔ እና በሻዕብያ፤ በአጠቃላይ ደግሞ በትግራይ ሕዝብና በኢርትራ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ መቃቃርን የፈጠረና ብዙ የፖለቲካ ዋጋም ያስከፈለ ነው። በብዙዎች እንደተነገረው፤ የጦርነቱ ምንጭ የድንበር ግጭትም አይደለም፤ አልነበረም። አንድ የምዕራባውያን ጋዜጠኛ እንደገለፀው፤ የድንበር ጦርነት ከሆነ፤ ሁለት መላጦች ለማበጠርያ ሲሉ የመገዳደልን ያክል ነው የሆነው።

እኔ እንደሚገባኝ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ድንበር መከለል የነበረበት፤ ኢዲሞክራሲያዊው “የኤርትራ” ሕዝበ ውሣኔ ከመደረጉ በፊት ነበር። አንድ ሕዝብ፤ የራሱ የሆነ ሃገር ለማቋቋም፤ ሕዝበ ውሣኔ ሲያደረግ፤ ከዚህ ዳር እስከዚህ ዳር ያለው መልከአ ምድር የእኛ ስለሆነ፤ በዚህ መልከአ ምድር ክልል የራሳችንን ነፃ መንግሥት እንመሰርታለን ከሚል መነሻ ሃሳብ መሆን ነበረበት። ኤርትራ ግን በሕገ ወጥ መንገድ በተወሰነ ውሣኔ በ1985 ዓ.ም. “የራሷን መንግሥት” ስተመሰረት፤ በሻዕብያ መራሹና፤ በወያኔ መራሹ መንግሥታት መሃል፤ በተደረገ የጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ስምምነት ምክንያት፤ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር በተገቢና ሕጋዊ በሆነ መንገድ አልተካለለም። ለነገሩ እስከ 1989 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ፤ ኢትዮጵያ በሻእብያ ቁጥጥር ስር ነበረች ለማለት ይቻላል። በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል፤ የኤርትራ ድንበር የት ድረስ ነው የሚለው ስምምነት ያልተደርሰበት ጉዳይ ስለነበር፤ ይህንን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት በሁለቱ መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተቋቋመ የድንበር ጉዳይ ኮሚሽን አማካኝነት ድርድር እየተደረገ ነበር። በጣም የሚገርመው እና ለብዙዊች እንቆቅልሽ የሆነው፤ በኤርትራው የመከላከያ ሚኒስትር ጄነራል ስብሐት ኤፍሬም የሚመራው የኢርትራ የድንበር ኮሚሽን ቡድን አዲስ አበባ ከወያኔ መራሹ መንግስት ጋር እየተደራደሩ ነበር፤ ግንቦት 4 1990 ዓ.ም. በሺህ የሚቆጠረው የኤርትራ ሰራዊት ታንክና መትረየሱን ይዞ ባድመ ድረስ ገፍቶ የመጣው። በወቅቱ፤ የሻዕብያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ሳውዲ አረብያ ውስጥ ነበሩ።

በተለይ ከ1989 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በሻእብያና በወያኔ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ከርሮ መምጣት፤ የኤርትራ ወረራ፤ ለሻእብያ ተሟጋች የነበሩትን መለስ ዜናዊን መቆምያ አሳጣቸው። በድርጅታቸው ከፍተኛ አመራሮች በተፈጠረባቸውም ጫና አቶ መለስ፤ የኢትዮጵያን ፓርላማ የአስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት፤ በግንቦት 5 ቀን 1990 ዓ.ም. ሻዕብያ፤ ወደ ኢትዮጵያ ያዘመተውን ሰራዊቱን በአስቸኳይ እንዲያስወጣ፤ ይህ ካልሆነ ግን፤ ኢትዮጵያ፤ የተቃጣባትን ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ ገለጹ። በጊዜው፤ ይህ ብዙዎችን ያደናገረ እና ሻእብያንም ጨምሮ፤ ብዙዎችን ያስደነገጠ መግለጫ ነበር። ሻዕብያ ወታደሮቹን ሲያዘምት፤ “ወያኔ ይፈራል፤ የምንፈልገውንም ይፈጽማል” ከሚል ትእቢትም ነበር ወረራው የተጀመረው። በወቅቱ በሳውዲ የነበሩትን ኢሳያስ አፈወርቂን፤ ከምንም ነገር የበለጠ ያናደዳቸው፤ የአቶ መለስ ወራራውን ለሕዝብ ማሳወቃቸው እንደነበር በብዙ የዜና አውታሮች ተዘግቧል። ወረራው ለሕዝብ ይፋ ከሆነ፤ መለስ በሚስጥር ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሌለ ግልጽ ሆነ። ኢትዮጵያ ወደ ጦርነቱ ለመግባትም ፍላጎት አላሳየችም፤ ለዚህም ነበር፤ አቶ ኢሳያስን በአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤት በኩል እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማስመከር የተሞከረው። የአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤት፤ የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ፤ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፤ ሁለቱም ሃገራት ከግንቦት 4 1990 ዓ.ም. በፊት ይዘዋቸው ወደ ነበሯቸው ግዛቶች እንዲመለሱና፤ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ። አቶ ኢሳያስ ግን ለዚህ ዝግጁ አልነበሩምና እምቢ አሉ። ጦርነቱ ካልተጀመረ፤ የአቶ ኢሳያስ የሥልጣን እድሜ እንደሚያጥር ቁልጭ ብሎ ነበር የታያቸው። በባድመ ሰበብ የተጀመረው ጦርነት፤ ለአቶ ኢሳያስ የተንኮል ምሽግ ሆነ፤ እስከዛሬ ድረስም ምሽጋቸው ሆኖ እያገለገለ ነው።

ስለ ግንቦት 1990 ዓ.ም. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ስናስብ፤ ልንጠይቀው የሚገባ ጥያቄ፤ ለምን ጦርነቱ ተጀመረ፤ ወረራውስ የተጀመረው በማን ነው? የሚል መሆን አለበት። ሁሉም በአንድ ነገር የሚስማማ ይመስለኛል። የኤርትራ ሕዝበ ውሣኔ ሲደረግ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ድንበር በቅጡ አልተሰመረም። ሌላው ጭብጥ ደግሞ፤ ድንበሩን በተመለከተ፤ ለሁለቱም ሃገራት አውዛጋቢ ጉዳዮች ነበሩ፤ ለዚህም ነበር የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የተቋቋመው እና በሥራም ላይ የነበረው። በነዚህ ነገሮች ላይ ከተሰማማን፤ ቀጣዩ ጥያቄ፤ ማነው ጦሩን መጀመርያ ያንቀሳቀሰው የሚል ነው። በይፋ የሚታወቀው፤ በግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም. በሺሆች የሚቆጠር የኤርትራ ሰራዊት ከታንክ እና መድፉ ጋር በወቅቱ በኢትዮጵያ ሥር ወደ ነበረው ድንበር ዘልቆ መግባቱ ነው። ይህ በቅጡ መጤን ያለበት ጭብጥ ነው። እነዚህን ጭብጦች በሃቅ ለተመለከተ መልሱ ግልጽ ነው። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ባድመ እና ሌላው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር እውነተኛ ምክንያት ሆኖ ጦርነት እንዳላስነሳ ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው።

በኢትዮጵያና በኤርትራ በግንቦት 1990 ዓ.ም. ለተጫረው ግጭት ባድመ ሰበብ እንጂ፤ ዋናው ምክንያት አይደለም። በሻዕብያ ፊት-አውራሪነት፤ በወያኔ እና አጋር ድርጅቶቹ (ኦነግን ጨምሮ) ተባባሪነት፤ ደርግ ከሥልጣን ሲወገድ፤ ሻዕብያ በኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ኤርትራ ላይ ጊዜያዊ መንግሥት ቢመሰርትም፤ እራሱን ከኢትዮጵያ ጥገኝነት ሊያላቅቅ ያልቻለ መንግስት ነበር። እንደውም ብዙ ጊዜ፤ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፤ ፖለቲካዊ፤ አስተዳደራዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውሣኔዎች እንዲወሰኑም አድርጓል። ሻዕብያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ከፍተኛ “ሥልጣን” ስለነበረው፤ በተለይ በሻዕብያ ትምክህትና ትዕቢት በሚበሳጩና፤ ሻዕብያን በሚደግፉ የወያኔ ባለሥልጣናት መሃከል ከፍተኛ መቃቃርን ፈጥረ። በወቅቱ፤ ወያኔ መላውን ሃገር በቅጡ ባለመቆጣጠሩና፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ “ሙሉ ለሙሉ” ተቀባይነት ባለማግኘቱ፤ የሻዕብያን ድርጊቶች በዝምታ ከማለፍ ውጭ፤ ወያኔ የማንገራገር ምልክት አላሳየም። ምንም እንኳን እስከ ሚያዚያ 1985 ዓ.ም. ድረስ ኤርትራም የኢትዮጵያ አካል የነበረች ቢሆንም፤ ከግንቦት 1983 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 1985 ዓ.ም. ድረስ፤ በአንድ ሃገር ሁለት መንግስታት ነበሩ፡ አንድ በአስመራ፤ አንድ በአዲስ አበባ። እነዚህ ሁለት መንግሥታት፤ ሥልጣን የያዙት በሕዝብ ምርጫ ሳይሆን፤ በጠመንጃ አፈሙዝ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

ኤርትራ እንደ ሃገር፤ የራሷን መንግሥት ካቋቋመች በኋላም፤ የወያኔ መራሹ መንግሥት፤ ኤርትራንም ሆነ የኤርትራን ዜግነት የመረጡ ኤርትራውያንን እንደ ውጭ ሃገር እና እንደ ውጭ ዜጎች ከማየት ይልቅ፤ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ከኢትዮጵያ የበለጠ ተጠቃሚ፤ አንዳንድ ኤርትራውያንም ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ተጠቃሚ ሆኑ። ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው ዜጎች፤ የኤርትራውያን የዜግነት ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ቢያሳስቡም፤ የወያኔ መራሹ መንግሥት፤ እነዚህን ዜጎች “ፀረ ሰላም” የሚል ታርጋ እየለጠፈ ቁም ስቅላቸውን አሳይቷቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አንድ የአሜሪካንን ዶላር በ6.00 የኢትዮጵያ ብር ሲመነዝር፤ የኢርትራ መንግስት ደግሞ በ7.25 ብር ይመነዝር ነበር (ለማስታወስ፤ በወቅቱ ኤርትራ የምትጠቀመው የኢትዮጵያን ብር ነበር)። ይህም ማለት፤ ኢትዮጵያ ማገኘት የሚገባትን ጠጣር ገንዘብ (hard currency) የምታገኘው ኤርትራ ነበረች። በጣም የሚገርመው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የኤርትራ መንግስት ኤምባሲዎች እና የኮምኒቲ ማህበራት፤ የብር ምንዘራው ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ነበር። ይህ የማንም ሃገር የማይፈቅደው፤ እንደውም በአንድ ሃገር ላይ የተደረገ የኢኮኖሚ ጦርነት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። በአንድ ወቅት ይህ ፀሃፊ፤ ከአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ ጋር ባደረግው ውይይት፤ ጃፓን፤ የአሜሪካንን ዶላር ብትጥል (devalue ብታደርግ)፤ አሜሪካን ያለምንም ማመንታት፤ ጃፓንን በጦር አውሮፕላን ትደበድባለች፤ በማለት፤ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረችው “የኢኮኖሚ ጦርነት” ክብደቱን ለማሳየት ሞክሯል። በዛን ወቅት፤ ኤርትራ ቡና፤ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎች፤ ከሚልኩ ሃገራት ተርታ ውስጥም ተመድባ ነበር። ብዙዊቹ እነዚህ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት የነበረባቸው ምርቶች፤ ኤርትራ በሚታተም የውሸት የኢትዮጵያ ብር ነበር የሚሸመቱትና ለዓለም ገበያ የቀረቡት። በዚህ የውሸት ብር፤ በመቶ ሺሆች በሚቆጠር ኩንታል ጤፍ ለኤርትራ መንግስት ወኪሎች የሸጡ ገበሬዎችም ለኪሣር ተዳረገው ለኢትዮጵያ መንግሥት ላቀረቡት አቤቱታ፤ የደረሰባቸው ወከባና ማስፈራርያ ነበር። ሻዕብያ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የፈለገውን የሚያስርበትና የሚፈታበት፤ እንዲሁም የሚገድልበት ሙሉ ሥልጣን ነበረው። በዛን ሳአት፤ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጥቅም ግን ቋሚም ሆነ ተጠሪም መንግስት አልነበረም።

ለሻዕብያ መራሹ መንግስት፤ የሕዝብ እሮሮ ምኑም አልነበረም። ሻዕብያ የመንን ሲወር፤ ታንኩና፤ የጦር አውሮፕላኑ፤ መድፍና ጠመንጃው ከኢትዮጵያ ተቸረው። ብዙም ሳይቆይ፤ አቶ ኢሳያስ ያንኑ መሣርያ አፈሙዙን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ፤ “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” ዓይነት ነው። ሻዕብያ፤ ለኤርትራ ሕዝብ ፍትሃዊ አስተዳደር አመጣለሁ፤ ሕዝቡን ከጭቆና ነጻ አወጣለሁ፤ ኤርትራ የዜጎች መብት የተከበረባት ሃገር ትሆናለች እያለ፤ ለዓመታት ቢለፍፍም፤ የገባውን ቃል ለመተግበር ባለመቻሉ፤ በተለይም ከኤርትራ ምሁራን፤ ሃገሪቱ በሕግ እንድትተዳደር ሕገ መንግሥት እንዲኖር ግፊት በማድረጋቸው፤ አቶ ኢሳያስ የማይወጡበት አረንቋ ውስጥ ገቡ። ለዚህ ግፊት መልስ ለመስጠትም፤ በዶ/ር በረከት ሃብተስላሴ የተመራ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮምሽን ተቋቋመ፤ ኮምሽኑም ሥራውን አጠናቅቆ፤ ረቂቁን በ1988 ዓ.ም (1996 አውሮፓ አቆጣጠር) ለኤርትራ መንግሥት አስረከበ። ረቂቁ ሕገ መንግሥት ብዙ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን የያዘ ከመሆኑም በላይ፤ የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት ሥልጣን እና የአስተዳደር ጊዜ የገደበ በመሆኑ፤ ለአቶ ኢሳያስ ሊዋጥላቸው አልቻለም። ለሕገ መንግሥት ጊዜው አይደለም በማለትም፤ አቶ ኢሳያስ ረቂቁን ቆለፉበት።

ለኤርትራ ሕዝብ ከአቅማቸው በላይ ቃል የገቡትና፤ ሃገር የማስተዳደር እና የመምራት ምንም ብቃት የሌላቸው የሻዕብያ መሪዎች፤ ሃገሪቱን ከተለያዩ የጎረቤት ሃገራት ጋር እያናቆሩ፤ በሕዝቡ ላይ ስጋትን ፈጠሩ። በተለይም የብሔራዊ ውትድርና ሥልጠናና ርዝመቱ፤ በሃይማኖቶች ላይ የተደረገው ተጽእኖ፤ እንዲሁም ኢዲሞክራሲያዊ የሆነው አገዛዝ፤ ሕዝቡ ለሚያነሳው ተገቢ ጥያቄ፤ ምላሹ እስር ሆነ። የአሰብንም አጠቃቀም በተመለከተ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውዝግብ ተጀመረ። እያረጀ የመጣው የአሰብ ወደብ፤ በኢትዮጵያ መንግስት በሚሊዮኖች ዶላር በሚቆጠር የገንዘብ ፍሰት እንዲታደስ ሻዕብያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተእዛዝ መሰል ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄው በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ አከራካሪ ሲሆን እና ቶሎ ምላሽ ባለመሰጠቱ፤ ሻዕብያ የአሰብ ወደብን የሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ማዋከብ ጀመረ፤ የዚህ ዓላማም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት ለመፍጠር ነበር። በኢትዮጵያ ነጋዴዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርበው አቤቱታ እየበረከተ በመምጣቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የጅቡቲን ወደብ እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ፈቀደ። የነጋዴው ማህበረስብ የጅቡቲን ወደብ ለመጠቀም፤ በነቂስ ተነሳ። ይህ ሻዕብያ መቼም ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ነበር። ኢትዮጵያ አስብን እንደ ወደብ ካልተጠቀመች፤ የኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጫና ቁልጭ ብሎ ታየ። በኅዳር 1990 ዓ.ም፤ የኢርትራ የንግድ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን አዲስ አበባ ላይ በመሰብሰብ፤ ነጋዴው የአሰብ ወደብን እንዲጠቀም፤ ወደቡም ላይ ያለው አሰራር እንደሚሻሻል ቃል በመግባት ተማጸኑ። ወደ ኋላ የሚመለስ ነጋዴ ግን አልተገኘም። ይህ በሻዕብያና በወያኔ መካከል ሌላ ክፍተት ፈጠረ።

ከስብሰባው ከጥቂት ቀናት በኋላም፤ ሻዕብያ የኤርትራን ሕጋዊ ብር ናቅፋን ሲያስተዋውቅ፤ ማንም ባልጠበቀው እና፤ በዚህ ጸሃፍ እምነት፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ትልቅ እርምጃ በመውሰድ፤ የወያኔ መራሹ መንግስት፤ ወድያው የኢትዮጵያን ትልልቅ ኖት ብሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቀየር እና፤ በኤርትራና ቢትዮጵያ ድንበር የሚደረጉ ግብይቶች በዶላር እንዲሆኑ በመወሰን፤ ብዙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚስቶች ያስደመመ፤ ሻዕብያን በጣም፤ እጅግ በጣም ያበሳጨ እርምጃ ተወሰደ። ሻዕብያ፤ በጠጣር ገንዘብ (hard currency) ሊቀይረው የነበረ፤ ኤርትራ ውስጥ ሲሰራብት የነበረ ከአራት ቢሊዮን በላይ የሆነ የኢትዮጵያ ብር፤ ወረቀት ሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ የመቀየርያ የጊዜ ገደብ በማለፉ፤ ሻዕብያ፤ ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የኢትዮጵያን ብር ከሕዝብ አሰባስቦ ለመቀየር አልቻለም። በተለይ፤ የኢትዮጵያ የመገበያያ ብር መቀየር እና፤ ድንበር ላይ ግብይት በዶላር እንዲሆን መወሰን፤ ወያኔ ከሻዕብያ መንጋጋ ለመውጣቱ ትልቅ ምልክት ሆነ።

በኋላም እንደተረዳነው፤ በተለይ በአፋር አካባቢ በ1989 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ግጭቶች ነበሩ፤ ግጭቶቹም በአቶ መለስ እና አቶ ኢሳያስ ፈጣን ጣልቃ ገብነት መብረድ ችለዋለ። ይህ ሲሆን ደግሞ፤ ወያኔ ውስጥ ሻዕብያን በሚደግፉና በሚቃወሙ ሃይሎች መሃከል ውዝግቡ እየባሰ እና እየጨመረ መጣ። እንደ ሃየሎም፤ ገብሩ አስራት እና ሰዬ አብርሃ ዓይነቶቹ፤ ኢትዮጵያ ኤርትራን መደጎም እንድታቆም፤ ሻዕብያ ኢትዮጵያ ላይ የሚይሳየው ማን አለብኝነት እንዲገታ ይሟገቱም እንደነበር ከወያኔ ክፍፍል በኋላ ብዙ ተብሎለታል። ሻዕብያ፤ ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀባይነት ያላገኘ እና የተጠላ ነው፤ ከሚል እምነት በመነሳት፤ በኢኮኖሚ እያሽቆለቆለች የመጣቸውን የሻዕብያን ኤርትራ ለመታደግ፤ በግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም አቶ ኢሳያስ ሰራዊቱን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ላከ። ልብ መደረግ ያለበት፤ በስብሃት ኤፍሬም የሚመራው ቡድን አዲስ አበባ ስለ ድንበር እየተወያየ ነው፤ የኤርትራ ሰራዊት ድንበር ገፍቶ የመጣው። ይህ ወረራ ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላም፤ የኤርትራ መንግሥት ለወረራው ምክንያት ብሎ የሰጠው፤ ድንበር ላይ በነዋሪዎች መሃከል ግጭት ተነስቶ፤ የኢትዮጵያ ሚሊሽያ ኤርትራውያን ገበሬዎችን በማፈናቀሉ፤ ይህ ማፈናቀል እንዲቆም የላክናቸው ሽማግሌዎች (አንድ የኤርትራ ኮሎኔልን ጨምሮ) በሚሊሻዎቹ ተገደሉብን፤ ለዚህም ነው ሰራዊታችንን ወደ ድንበር ያንቀሳቀስነው የሚል ነው።

የኢርትራ መንግስት በአንድ በኩል በሃገር ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲኖር የረቀቀው ሕገ መንግስት በሥራ ላይ ይዋል፤ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበር፤ የሚለው ግፊት ማየሉ እና፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለኤርትራ ሕዝብ የተገባው “የኢኮኖሚ ተአምር” ቃል፤ እውን ማድረግ የሚችልበት አቅጣጫው ስለጠፋው፤ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ብቃት የሌላቸው እና ራእይ የጎደላቸው ከመሆን አልፈው፤ “ተዋግተን ያመጣነውን ለማንም አንሰጥም” በሚል ደዌ ታመው ሥልጣን ለሕዝብ ለመስጠት ስላልፈለጉ፤ የድንበር ጦርነቱ ጥሩ መደበቅያ ምሽግ ሆናቸው። ምን እንኳን የኤርትራ ባለሥልጣናት፤ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የጀመሩበት ምክንያት “የድንበር ጉዳይ” ነው ብለው በአደባባይ ቢስብኩም፤ በግል ግን፤ ጥያቄው የኢኮኖሚና ሥልጣንን ለኢርትራ ሕዝብ ካለማስረከብ ጋር የተያያዘ መሆኑን አይደብቁም።

በሰኔ 1990፤ Center for Strategic & International Studies የተባለው ዋሽንግተን ዲስ የሚገኘው ተቋም ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ፤ በስብሰባው ከተገኙ ጥቂት ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መካከል አንዱ ይህ ፀሃፍ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አምባሳደሮች እና የኢምባሲ ሹማምንት የተገኙበት ሲሆን፤ ይህ ፀሃፍ፤ ለኤርትራው አምባሳደር ያነሳው ጥያቄ፤ “ወደ ጦርነት ገባንበት የምትሉትን ምክንያት እውነት ነው ብዬ ልቀበል እና፤ ሽማግሌዎቻችሁ ስለተገደሉ፤ ታንክና ወታደር ይዞ መምጣቱ ተገቢ ነው ወይ? ታንክና ሰራዊት ከማዝመታችሁ በፊት፤ ጉዳዩን ለአፍሪካ ሕብረት፤ ወይም ለተባበሩት መንግስታት ለምን አላቀረባችሁም? ዛሬ የምትጠይቁት መሬት ቢሰጣችሁ፤ ጦርነቱን እንደማታቆሙ በእርግጠኝነት መናገር እችላላሁ፤ የኤርትራ ጥያቄ የመሬት ሳይሆን የኢኮኖም አይደለም ወይ?” የሚል ጥያቄ በመጠየቁ፤ በአምባሳደሩና ብሹማምንቱ የታየው ከፍተኛ ቁጣ ነበር። በተለይም ለቁጣው ማየል ምክንያት የሆነው፤ ጥያቄው የኤርትራ ተወላጅ ነኝ ከሚል ሰው መቅረቡ ነበር። ስብሰባው ለእረፍት ሲወጣ፤ ይህ ጸሃፍ ከኤርትራ ሹማምንት ጋር ያደረግው ሙግት የተመላበት “ውይይት” በማያሻማ ሁኔታ በኤርትራ ባለስልጣናት የተረጋገጠለት፤ የኤርትራ ሠራዊት ወደ “ኢትዮጵያ ድንበር” ዘልቆ የገባው ለመሬት ሳይሆን፤ ወያኔ “የኤርትራን አንገት በኢኮኖም ጠምዝዞ ኤርትራን ለማንበርከከ ይሰራል” ከሚል እምነትና ስጋት የመነጨ መሆኑን ነው።
ይቀጥላል።

___
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here