spot_img
Saturday, April 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትጥንቃቄ የሚያሻው የኤርትራ ጉዳይ። (የመጨረሻ ክፍል ሁለት)- ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ (ከአሜሪካ)

ጥንቃቄ የሚያሻው የኤርትራ ጉዳይ። (የመጨረሻ ክፍል ሁለት)- ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ (ከአሜሪካ)

ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ (ከአሜሪካ)
ቦርከና
ሃምሌ 1 2010 ዓ ም

በዚህ ርዕስ፤ በክፍል አንድ ላይ የተጠቀሱትን ጭብጦች ስንመለከት፤ የኤርትራ መንግሥት የድንበር ግጭቱ ሰበቡ እንጂ፤ ትክክለኛ እና እውነተኛ ጥያቄውና ዓላማው፤ ኢትዮጵያን እንደ ጥገት ላም በማለብ፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጀርባ ላይ፤ የኤርትራን ኢኮኖሚ፤ ለመገንባት ነበር። ከግንቦት 1983 ዓ.ም ጀምሮ፤ የወያኔ ኢሕአዲግ መራሹ መንግሥት፤ ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ፤ የኤርትራን ጥቅም በማስጠበቁ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣና፤ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ያነጋገር መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በተለይ፤ ክ1989 ዓ.ም ጀምሮ፤ ሻዕብያን “እምቢ” ማለት የጀመሩ በሕወሃት ከፍተኛ አመራር ውስጥ ብቅ በማለታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ለሻዕብያ መራሹ መንግስት፤ ወለል አድርጎ የከፈተውን “የዘረፋ በር” ማጥበብ ጀመረ። የሻዕብያ መራሹን መንግሥትም ያስቆጣው፤ በኢትዮጵያ መንግስት እምቢተኝነት መታየቱ ነበር። “ጌታ፤ ሎሌዬ፤ እንዴት ደፈረኝ” ብሎ የሚቆጣውን በሚሰምስል ሁኔታ፤ ሕወሃት ደፍሮ፤ “ለሻዕብያ አልታዘዝም” ማለቱ፤ አቶ ኢሳያስን እና ግብረ-አበሮቹን አስቆጣ።

“የኤርትራ መንግስት” ለውድቀቱ መንሰኤ የሆነውን ትልቁን ቁማር የቆመረው፤ ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሃትን አይደግፍም’፤ “እኛ ያሰለጠንናት ሕወሃት፤ ጉልበታችንን ካሳየናት፤ ለእኛ መታዘዟን ትቀጥላለች” የሚል እምነት ስላሳደረ ነው። የግንቦት 1990ው ጦርነት በድጋሚ አንዳሰመሰከረው፤ ኢትዮጵያውያን የፈለገ ውስጣዊ “ቅራኔ” ቢኖራቸው፤ “የውጭ ጠላት” ሲመጣ፤ ለሃገራቸው እና ለድንበራቸው ሲሉ አንድ ላይ እንደሚቆሙ ነው። ሻዕብያ ታሪክን እየበረዘ የኖረ እና፤ በውሸት ታሪክ ተፈልፍሎ ያደገ በመሆኑ፤የኢትዮጵያውያንን ታሪክ አለማስተዋሉ አይግርምም። ከግንቦት 1990 ዓ.ም. በፊት፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃል ግልጽ የሆነ የተሰመረ ድንበር እንደሌለ እየታወቀ! አሁን ኤርትራ ይገባኛል የምትለው መሬት፤ ከግንቦት 1983 ዓ.ም. የደርግ መውደቅ በኋላ እንኳን፤ በኢትዮጵያ የሚተዳደሩ አካባቢዎች መሆናቸው እየታወቀ! ባልተጠበቀ እና ባልታሰበ ሁኔታ፤ በግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም. ሰራዊት እና ታንክ ይዞ ወደ ድንበሩ የመጣው የኤርትራ ጦር መሆኑ እየታወቀ! ዛሬም የኤርትራ መንግስት የሚዘምረው መዝሙር፤ በግንቦት 5 1990 ዓ.ም. ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ ላይ ጦርነት አወጀች ብሎ ነው።

የኢሕአዲግ መራሹ መንግሥት፤ እንደ አንድ ሏአላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ከጅምሩ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ፤ ከኢርትራ ጋር ድንበር በተገቢ ሁኔታ አለማካለሉ፤ ማንም ሊክደው የማይችል ታሪካዊ ስህተት ነው። ይህ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት፤ ለብዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ሕይወት መጥፋት፤ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፤ ሁለቱንም ሃገራት ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ውስጥ ጥሏል። የዚህ ታሪካዊ ስህተት ውጤት፤ ለብዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንም የስቃይ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በስህተት ላይ ስህተት ሲሰራ ቆይቶ፤ ዛሬም፤ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

የኢሳያስ መራሹ መንግሥት፤ በተለያዩ መንግሥታት፤ በአፍሪካ አንድነት እና በተባበሩት መንግስታት ከግንቦት 4 1990 ዓ.ም. በኋላ፤ በሰራዊቱ የተቆጣጠራቸውን፤ በኢትዮጵያ መንግስት የሚተዳደሩ አካባቢዎችን፤ እንዲለቅ ቢለመንም፤ “የደርግን ሰራዊት ያሸነፈ ሻዕብያ፤ እኛው ያሰለጠንናትን ወያኔን ማሸነፍ አያቅተንም” በሚል ትዕቢት፤ አሻፈረኝ አለ። ሆኖም፤ በየካቲት 1991 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ የሻዕብያን ጦር ከባድመ ፈንቅሎ ሲያሰወጣ፤ አቶ ኢሳያስ፤ የአፍሪካ አንድነትን እና የተባበሩት መንግስታትን፤ የመፍትሔ ሃሳብ እቀበላለሁ ሲሉ ተማጸኑ። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን፤ የጸረ ሻዕብያ ቡድን የፖለቲካ ሃይል ሚዛን ያጋደለ ስለነበር፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተራው፤ “ኤርትራ የመፍትሔውን ሃሳብ” የተቀበለው ብዙ ጥፋት ካጠፋ በኋላ ስለሆነ፤ አልቀበልም አለ። ጦርነቱ ተጋግሎ፤ በኢትዮጵያ ጦር ድል አድራጊነት፤ ሻዕብያ በግንቦት 4 ቀን 1990 የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ተደረገ። የሻዕብያ ትዕቢትና፤ በምዕራባውያን አድናቂዎቹ ይለፈፍለት የነበረው “የአፍሪካ ስፓርታነቱም” ባዶ ልፈፋ ብቻ መሆኑን አሳበቀበት። አቶ መለስ ዜናዊ ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ እየተጠናከረ የሄደው የጸረ ሻዕብያ ቡድን፤ ግቡ፤ አስመራ ድረስ ለመግባት እና ኤርትራን ለመቆጣጠር ነበር። ምንም እንኳን፤ አቶ መለስ በብዙ ነገር ባይስማሙኝም፤ አሸናፊው የኢትዮጵያ ጦር ወደ አስመራ እንዳይገስግስ ማድረጋቸው፤ ኢትዮጵያ ሌላ ከፍተኛ ስህተት እንዳትሰራ አድርጓል። ሻዕብያ በጦርነቱ ከተሸነፈ እና፤ ኢትዮጵያ ጦርነቱን በአሸናፊነት ከተወጣች በኋላ፤ በተለይም በአሜሪካው ፕሬዝዳንት በክሊንተን አስተዳደር ግፊት፤ እና በሌሎች መንግስታት ጣልቃ ገብነት፤ የተኩስ ማቆም ስምምንት ተደርጎ ወደ ሰላም ድርድር ተኬደ። ሊታለፍ የማይገባው ነገር ግን፤ በኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት መሃከል፤ ‘ወደ አስመራ መገስገስ ነበረብን’ በሚለው ቡድን እና፤ ‘ወደ አስመራ መገስገሱ ዋጋ የሚያስከፍል ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም መንግስታት የሚያስወግዝ፤ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ፤ እንዲሁም አቶ ኢሳያስን፤ ከወደቁበት የፖለቲካ አዘቅት የሚያስነሳ ነው’ በሚለው ቡድን መካከል ሊፈታ የማይቻል ቅራኔ ውስጥ በመገባቱ እና፤ በተለይም በአልጀርስ በተደረገው ድርድር፤ ኢትዮጵያ ውሳኔውን ያለምንም ይግባኝ እቀበላለሁ ማለቷ፤ የወያኔን አመራር ለሁለት ሰነጠቀ።

ያ ወቅት ሻዕብያ፤ በጦርነቱ ክፉኛ ከመመታቱ ጋር በተያያዘና፤ ጦርነቱ፤ በኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ ከፈተኛ ጫና በመፍጠሩ፤ በሻዕብያ አመራር ውስጥ ክፍፍልን ፈጠረ። በኋላም እንዳየነው፤ እንደ አቶ ጴጥሮስ ሰለሞን ዓይነት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ የሻእብያ የግፍ እራት ሆኑ። ሻዕብያ፤ በተለይም በበርካታ ኤርትራውያን “እንደ እግዚአብሔር” መመለክ የቀራቸው አቶ ኢሳያስ፤ የሕዝብ ድጋፍ እያጡ መጡ። የሻዕብያ ዋና ደጋፊ የነበሩት፤ እንደ ዶ/ር በረከት ሃብተስላሴ ዓይነት ምሁራን፤ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ ሻዕብያን በተለያዩ የሕዝብ መገናኛዎች ማውገዝ ጀመሩ። እንደ ኃይሌ መርቆርዮስ እና ባለቤታቸው፤ እንደ የቀደሞው የመከላከያ ሚኒስትሩ መስፍን ሃጎስ ዓይነት ሰዎች እና የሳቸው ተከታይ የነበሩ 15 የሚሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፤ ከሻዕብያ ከድተው በመውጣት፤ አቶ ኢሳያስን እና አገዛዛቸውን በአደባባይ ማብጠልጠል ጀመሩ። ይህ ሁኔታ፤ ኢትዮጵያ በምትፈልገው መልኩ፤ ከኤርትራ ጋር ያለውን ድንበር ማስመር የምትችልበት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በአልጀርሱም ድርድር፤ ማንም አሸናፊ መንግስት እንደሚያደርገው፤ ኢትዮጵያ የራሷን ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ሲገባት፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት፤ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ሰራ። ለሻዕብያ ሌላ የሚተነፍስበት ሳንባ ከማስገጠሙም በላይ፤ ሻዕብያ፤ ጦርነቱን ያሸነፍነው እኛ ነን የሚለውን ፕሮፖጋንዳ እንዲያናፍስ እድል ሰጠው።

ከታሪክ እንደምንማረው፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1783 ፓሪስ ላይ፤ በአሜሪካ “አብዮተኞችና” በጦርነቱ በተሸነፈው የእንግሊዝ መንግስት የተደረግው ስምምነት፤ አሸናፊው የራሱን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ነበረ ስምምነት የተፈራረመው። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ስትሸነፍ፤ በጥቅምት 1919 (አውሮፓ አቆጣጠር) ስምምነቱ ሲፈረም፤ አሸናፊው ኃይል ካስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ፤ ጀርመን እና አጋሯቿ በጦርነቱ ምክንያት ላደረሱት ጥፋት እና ጉዳት ሃላፊነት እንድትወስድ፤ ለጉዳቱም ካሳ እንድትከፍል፤ ከድንበሯም፤ የተወሰነ መሬት እንድትሰጥ፤ እንዲሁም ትጥቋዋን እንድትፈታ የደነገገ ነበር። በዓለም ላይ በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ፤ አሸናፊው ቅድመ ሁኔታ ባማስቀመጥ ነው ወደ ሰላም ድርድር የሚገባው። ይህ ፀሃፍ እስከሚያውቀው ድረስ፤ ጦርነቱን በማያዳግም ሁኔታ አሸንፋ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሳለም ድርድር የገባች እና፤ ያለይግባኝ፤ “የአስታራቂዎችን” ውሣኔ እቀበላለሁ ያለች ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ይህ ለምን ሆነ ብለው የታሪክ ተመራማሪዎች ጉዳዩን በማጣንት እና በመፈተሸ፤ ፖለቲካዊ ሳይሆን፤ ታሪካዊ እና አድሎዋዊ ያልሆነ፤ ትክክለኛ ግኝታቸውን ጽፈው ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ታሪክ ሃላፊነት ጥሎባቸዋል።
በስህተት ላይ ስህተት መስራት የማይደክመው የኢሕአዴግ መራሹ መንግስት፤ ሌላ የሰራው ታሪካዊ ስሕተት፤ ለአልጀርሱ “የሰላም ድርድር” የመደባቸው ሰዎች ብቃት ያልነበራቸው መሆናቸው ነው። በዚህ ቡድን፤ የመልክአ ምድር ምሁራን፤ የታሪክ እና የፖለቲካ ጠበበቶችን እና የሕግ ባለሙያዎችን ማካተት ሲገባው፤ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት፤ ምንም ልምድ ያልነበራቸው “የሕግ ባለሙያዎች”ከመሆናቸውም ሌላ፤ የታሪክ እና የመልክአ ምድር ምሁራንን ያላካተተ፤ እንዲሁ ለይስሙላ ብቻ የተዋቀረ ቡድን ነበረ። ይህ ፀሃፍ የሚያውቀው፤ ለድርድሩ ከተላኩት የሕግ ባለሙያዎች አንዱ፤ ገና ለሁለት ዓመት ተኩል በአቃቤ ሕግ ረዳትነት የሰራ እና፤ ምንም ዓይነት የዓለም አቀፍ ሕግ ልምድም ሆነ እውቀት ያልነበረው፤ ለዚሁ ጉዳይ ሲባል፤ ከፍትሕ ሚኒስትር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በፍጥነት የተዛወር መሆኑ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለድርድሩ ምንም ዓይነት ክብደት እንዳልሰጠው የሚያሳይ ጭብጥ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ፤ አቶ መለስ ዜናዊን ያስወቀሰ እና ያስወገዘ ብዙ መላ ምት አለ፤ የጽሁፉ ዓላማ፤ ይህ ስላልሆነ፤ ለአሁኑ ስለዚህ ጉዳይ የምለው የለም። ሆኖም፤ የአቶ መለስ አመራር፤ በአልጀርሱ ድርድር የሰራው ታሪካዊ ስሕተት፤ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፤ የኢትዮጵያን ጥቅም ያላሰጠበቀ ለመሆኑ አከራካሪ አይደለም።

በዚህ ፀሃፊ እምነት፤ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ፤ እንዲሁም የኢሕአዴግ ድርጅት እና የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት፤ እንደገና ታላቅ ታሪካዊ ስሕተት ሊሰሩ ነው። የሚሰሩትም ስሕተት፤ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ዘላቂ ሰላም የማያስገኝ እና ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የጊዜ ቦምብ ነው የሚል ሥጋት አለኝ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝብ፤ በመንግሥታቱ ሃላፊነት የጎደለው ሥነምግባር፤ በራሱ የሃገር ጉዳይ እንዳይሳተፍ እና እንዳይወስን በመደረጉ፤ ባልወከላቸው መንግሥታት ውሣኔ ብዙ ተሰቃይቷል። ይህን ስቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማብቃት የሚቻለው፤ ፍትሃዊ የሆን የድንበር ከለላ ሲደረግ እና በሌሎች በሚያስተሳስሩን ጉዳዮች አብረን ስንሰራ ብቻ ነው። በተወሰኑ ሰዎች በጎ ፍላጎት እና፤ ባለጉዳዩ ባልሆኑ የዓለም መንግሥታት ግፊት፤ እንዲሁም ለጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል የጥድፍያ ውሣኔ መኖር የለበትም። ከዚህ በተጨማሪም፤ የዚህን አንድ የሆነ፤ በደም እና በታሪክ የተሳሰረ ሕዝብ ጉዳይ፤ ከድንበር ከለላ ባሻገር ማየት እና፤ በማህበራዊ ኑሮው እንደገና የሚተሳሰርበትን እና በኢኮኖሚም አብሮ ሊበለጽግበት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ሃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ነው። አሁን የተፈጠረው አዲሱ ግንኙነት፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመስራት ትልቅ እድል ፈጥሯል። በዚሕ ፀሃፊ እምነት፤ ወደፊት ሌላ ግጭት ሊፈጥር የሚችለውን የአልጀርሱን ስምምነት “ለመተግበር” ከመጣደፍ ይልቅ፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል ሕዝቡን ሊያስተባብር እና ሊያስተሳስር በሚችል ነገር ላይ ስራ ቢሰራ፤ “የሚገነባው ቤት፤ በአሽዋ ላይ ሳይሆን፤ በአለት ላይ የሚገነባ ይሆናል”።

የኤርትራ ፌዴሬሽን ሲፈርስ፤ የኢርትራ ሕዝበ ውሣኔ ሲደረግ፤ እና የአልጀርስ ስምምነት ሲደረግ ታሪካዊ ስህተት ተሰርቷል። አሁንም በጥድፍያ ስምምነቱን መተግባር፤ ሌላ ታሪካዊ ስሕተት ይሆናል። የተሰሩት ስህተቶች ደግሞ፤ ከሁለቱም ወገን በሚሊዮን የሚቆጠር የሕይወት ዋጋ አስከፍሏል። ከአልጀርሱ ስምምነት ባሻገር፤ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል። በክፍል አንድ ለማሳየት እንደተሞከረው፤ ከጅምሩ የኤርትራን መንግስት ወደ ጦርነት የከተተው የድንበር ጉዳይ ሳይሆን፤ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። ይህ መፍትሔ ካልተበጀለት፤ የኢሳያስ መራሹ መንግስት፤ ለኢትዮጵያ ይተኛል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ የለም። ከዚህ በተጨማሪ፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት በሌላ መንግስት ሲተካ፤ የአልጀርሱን ስምምንት ሊያፍረስ እና ወደ ሌላ አላስፈላጊ ግጭት ሊያመራ ይችላል። ምንም እንኳን ኢሕአዲግ የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነውን ውሣኔን በመቃወም ከፍተኛ ጩኸት የሚሰማው ከትግራይ ክልል ቢሆንም፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፤ ተቃውሞቸውን እያሰሙ ነው። በርካታ ምሁራን እና ጉዳዩ ያገባናል ያሉ ዜጎች፤ ከዚህ ቀደምም በተለያየ መልኩ ድምፃቸውን አሰምተዋል። በተለይ ደግሞ ከ55 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሚያዚያ 4 ቀን 1994 ዓ.ም ለተባበሩት መንግስታት እና በጉዳዩ ጣልቃ ለገቡ መንግስታት በፃፉት ደብዳቤ፤ “የአልጀርሱ ስምምነት፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያልተመከረበት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልወከለው መንግሥት የተፈረመ፤ እና የኢትዮጵያን ጥቅም ያላስጠበቀ ነው” በማለት፤ ስምምነቱ ከተተገበረ ወደፊት የሚያስከትለውን ችግር በመጠቆም የማስጠንቀቅያ ደወል ደውለዋል። በዚህ ደብዳቢያቸውም “ የአልጀርሱ ስምምነት፤ ሃሰት እና ማጭበርበር የተመላበት የሴራ ውጤት ነው፤ ስለዚህም ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በኤርትራ ሕዝብ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ስለሆነም የአልጀርሱ ስምምነት ምንም ዓይነት የሞራልም ሆነ ሕጋዊ ሥልጣን የለውም” ሲሉ አስምረውበታል። የእነዚህ በርካታ ምሁራን የማስጠንቀቅያ ደውል በአሁኑ ባለስልጣናት ካልተደመጠና፤ ወደ ተሻለ መፍትሔ የምንሄድበት አቅጣጫ ካልተያዘ፤ የአልጀርሱ ስምምነት፤ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንደማያመጣ አመላካች ነው።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የድንበር ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል፤ መፍትሔው ግን “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት፤ ግድግዳው ሰንበሌጥ” መሆን አይገባውም። በሁለቱ ሃገራት ዛላቂ ሰላም ለመፍጠር እና ጤናማ ግንኙነት ለማጎልበት፤ ከድንበር ከለላ ባሻገር መመልከቱ ይበጃል። ዶ/ር አብይ ከኤርትራ መንግስት ጋር የፈጠሩት ግንኙነት እሰየው የሚያሰኝ ነው። ይህን ጅማሮ፤ በተለይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ምሁራን መካከል ትሥስሩን በማዳበር፤ በጥናት እና በእውቀት የተደገፈ፤ ለሁለቱም ሃገራት ጥቅም የሚያስገኝ፤ ሁለቱን ሃገራት እና ይህን አንድ የሆነ ሕዝብ የሚያሰተሳስር ስራ ቢሰራ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንችላለን ብሎ ይህ ፀሃፍ ያምናል። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር፤ በመንግስታቱ በኩል ስለአልጀርሱ ስምምነት የፈለገ ዓይነት ከበሮ ቢደለቅ፤ ስምምነቱ በተለይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀባይነት የሌለው ነው። በሕዝብ ተቀባይነት ያላገኝ ነገር ዘላቂ ይሆናል ብሎ ማሰብ፤ ከታሪክ አለመማር ነው። በቅርቡ፤ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ገዥው ፓርቲ የራሱን ሕገ መንግስት በመጣስ፤ “ጉልበቱን ተጠቅሞ”ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሥልጣን የያዘ ነው። የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት፤ አዲሱን ጅምር፤ በመንግስታቱ መካከል መተማመን የሚፈጥርበት፤ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያገናኝበት፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ምሁራን አብረው ለጋራ ጥቅም የሚሰሩበትን ድልድይ የሚያበጅ ቢሆን እና፤ የድንበር ማካለሉን የመጨረሻ ውሳኔ፤ ሕዝብ፤ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመረጠው መንግስት ቢተው የሁለቱ ሃገራት ጉዳይ ተገቢ እልባት ያገኛል። ይህ እስኪሆን ግን፤ በሁለቱ ሃገራት ውስጥ ያሉ፤ የታሪክ፤ የዓለም አቀፍ ሕግ፤ የኢኮኖሚ እና የመልክአ ምድር ምሁራን፤ እንዲሁም የፖለቲካ ሃይሎች፤ ግንኙነት በመፍጠር ውይይት ይጀምሩ። በተለይም በሰሜን አሜሪካ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ምሁራን “የኢትዮጵያውያን እና የኤርትራውያን የወዳጅነት መድረክ” በሚል ስያሜ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ቡድን፤ ጥሩ ምሣሌ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፤ የዶ/ር አብይ መራሹ መንግስት፤ በድንበሩ ጉዳይ ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት፤ የዚህ ድንበር መካለል ቀጥተኛ ጉዳት ከሚያደርስባቸው፤ በድንበሩ አካባቢ ከሚኖሩ ዜጎች ጋር፤ ከአሁኑ ውይይት ማድረግ እና፤ የመፍትሔውም ተሳታፊ ማድረግ ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ምሁራንም በግልጽ እና በመከባበር፤ ፍትሃዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል ውይይት ያድርጉ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ፤ በሁለቱም ወገን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት በመሆኑ፤ በስሜት፤ በችኮላ እና በግብዝነት የሚሰራ ስራ፤ ለሁለቱም ሃገራት አይጠቅምም። በሁለቱም ወገን ያሉ ምሁሮቻችን፤ ከድንበር ከለላ ባሻገር፤ የሁለቱንም ሃገራት ሊጠቅሙ እና ሊያስተሳስሩ የሚችሉ ነገሮች ላይ ቢሰሩ፤ የሚያስተሳስረን፤ አብረን ልንበለጽግ የምንችልበት፤ ከድንበር በዘለለ፤ ዘላቂ ጥቅምና መፍትሔ ልናገኝ እንችላለን። ይህ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እጠይቃለሁ።
__
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here