spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየት“ሕገ መንግሥት”፣ ሥርዓተ አልበኝነትና የለውጡ አመራር (ተስፋዬ ደምመላሽ)

“ሕገ መንግሥት”፣ ሥርዓተ አልበኝነትና የለውጡ አመራር (ተስፋዬ ደምመላሽ)

- Advertisement -

ተስፋዬ ደምመላሽ
ሃምሌ 3 ፤ 2010 ዓ.ም

የሕገ መንግሥት ቅየራ ነገር ባለፈው ሰሞን የሽብር ጥቃት ከተሰነዘረበት የጠ/ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የለዉጥ አመራር ጋር የተያያዘ ወይም ሊያያዝ የሚችል ስለሆነ መሠረታዊ የአገር ጉዳይ ነዉ። ጉዳዩን በጨረፍታም ቢሆን የሚመለከት “ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰጠን ተስፋና ጥርስ አልባዉ አንቀጽ 39” በሚል ርዕስ ዶ/ር ጌታቸዉ ኃይሌ በቅርቡ የጻፉት ወጥ ድርሰት አንዳንድ ዋና ዋና ጥያቄዎች ጫሪ ሆኖ አገኘሁት። ጥያቄዎቹ ዶ/ር ጌታቸዉ በተለይ ስለ አንቀጽ 39 ያቀረቡትን አስተያየት ዘልቀዉ በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥትን ምንነትና ሥራ የሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች የሚያነሱ ናቸዉ። በኔ ግምት፣ ጉዳዮቹን ትንሽ ቀረብና ገባ ብሎ መገንዘብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ የሚያደርገዉን የሥርዓት ለዉጥና የአገር አንድነት ጥበቃ ትግል ዘላቂ የአስተሳሰብ ቅርጽና አቅጣጫ ለማስያዝ ይረዳል።

የፖለቲካ ሥርዓት ከአገዛዝ ባሻገር

በብቸኝነት ወገንተኛም ዘረኛም የሆነውና በኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም ተጠልቶ በቁሙ የሞተው የሕወሓት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ምንም አገራዊ ሥርዓተ ፖለቲካ እንደሌለውና ኖሮትም እንድማያውቅ ግልጽ ነው። አገዛዙ ይባስ ብሎም ሽብርተኝነትን የፖለቲካ መሣሪያ ከማድረግ ወደኋላ እንድማይል እጁ ነበረበት ተብሎ በሚጠረጠረው በቅርቡ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በተደረገው የቦምብ ጥቃት አሳይቷል። አገዛዙ አለኝ የሚለው “ሕገ መንግሥት” ራሱ ከጽንሱና ከአቀራርጹ የኢትዮጵያን ሕዝብ የተቀደሰ አንድነትና ግዛታዊ ሉአላዊነት የጣስም ያረከሰም ነው። የተገላቢጦ ለአገዛዙ ሥርዓተ ቢስነት ስስ ሽፋን ከሆነ የቃላት ክምችት ከማበርከት ያለፈ ፋይዳ ኖሮት አያውቅም። ሆኖም እዚህ ላይ “ሥርዓት” ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ማድረጉ ጠቃሚ ነዉ።

በቅጡ ታሳቢ ሆኖ የተጸነስና የታነጸ፣ እንዲሁም በአቀራረጹ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ቅቡልነትነት ያለዉ አገር አቅፍ ፖለቲካዊ-ተቋማዊ መዋቅር ከተወሰነ ወገንተኛ ወይም ጐሠኛ አገዛዝ ይለያል። አገዛዞች ወይም መስተዳድሮች በየወቅቱ ተለዋዋጭ ሲሆኑ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ በአንጻር ከወገንተኝነት የተገለሉና የራሳቸዉ ተጽእኖ ያላቸዉ ቋሚ፣ ግን በሂደት ሊሻሻሉ የሚችሉ ሃሳቦች፣ እሴቶች፣ መርሆች፣ ገቢሮች፣ የአተረጓጐም አማራጮችና የተለያዩ ፓርቲዎችን ለሥልጣን ማወዳደሪያ ህጎችና ደንቦች አሉት። እነዚህ ሥርዓታዊ አካላት በወረቀት ላይ ለስፈር ሕገ መንግሥት ተጨባጭ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ባህላዊ መሠረተ መዋቅር ሊሆኑ ይችላሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሰነድን ነፍስ ሊዘሩበት፣ ማለትም ተንቀሳቃሽ ተተርጓሚና ተፈጻሚ ሊያደርጉት ይችላሉ።

የኢትዮጵያን ነባርና ወቅታዊ ሁኔታ ስናይ፣ ከሆኑ ያልሆኑ አምባገነናዊ አገዛዞች ዉጪ በእዉን ሕገ መንግሥት የሚመራ መደበኛ የፖለቲካ ሥርዓት ኖሮን አያዉቅም። ስለዚህም አገዛዞቹ ሲወድሙ የፈጠሩዋቸው ሕገ መንግሥት ተብየዎችም (ያፄ ኃይለሥላሴና የደርግ) አብረዉ አከተሙ። የሕወሓት አገዛዝ በፈላጭ ቆራጭነት በነአንድርያስ እሼቴና ክፍሌ ወዳጆ አስረቅቆ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫነዉ አገር ከፋፋይ ዘር ተኮር ሕገ መንግስትም ከዚህ የተለየ እጣ ፈንታ አይኖረዉም። አገዛዙ ከጅምሩ በሥርዓተ ቢስነት ከራሱ ሕግ መንግሥት አካቶ ዉጪ በማናለብኝነት በመንቀሳቀስ የዜጎችንና የባህል ማኅበረሰቦችን መብቶች ብቻ ሳይሆን የጋራ ኢትዮጵያዊነታችንን የተጻረረና ያሰናከለ ነዉ።

ይህን ባሕሪውን በይበልጥ ትኩረት ለመረዳት የአማራው ማኅበረሰብ አካላት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየደረሰባቸው ያለዉን እጅግ አስከፊ መፈናቀልና በገዛ አገራቸው ዉስጥ ስደተኛ ሆኖ መሰቃየት ሕገ መንግሥት ተብየው በአንቀጽ 32 ካሰፈረው እዉን ትርጉም የለሽ የወረቀት ነጻነት ጋር ማነጻጸር ይበቃል። ሕገ መንግሥት ተብየው ቃል በቃል የሚለው ወዲህ፣ የአገዛዙ ተፈጥሮ፣ ማለትም ሥርዓተ አልበኝነቱ፣ ጨርሶ ውዲያ!

ይህን ስንል ግን በአብዮቱና በድህረ አብዮቱ ዘመን በኢትዮጵያ የተለያዩ ፓርቲዎች (ሕወሓትንም ጨምሮ) ከሞላ ጎደል የተጋሩት አጠቃላይ የፖለቲካ ፓራዳይም ወይም ሥርዓተ ርዕዮትና ፖለቲካ ምንም አልነበረም ማለታችን አይደለም። ነበረ፣ አለም። ዛሬ ሥርዓቱ ከሥር መሠረቱ ለለዋጭ ውይይቶችና እንቅስቃሴዎች መከፈት ያለበት ነው። የጎሣ ፖለቲካው/አገዛዙ ፓራዳይም ግብአቶች ወይም መገለጫዎች ተራማጅ የተባሉ፣ ባመዛኙ ስታሊናዊ ቅርጽ ያላቸው፣ አምባገነናዊና በብቸንነት ወገንተኛ የሆኑ የአሰተሳሰብ፣ የአነጋገር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ፎርሙላዎችን፣ ልምዶችን፣ እንዲሁም የጎሣ ፓርቲዎችን ማቆሚያ የሌላቸው የተጎጅነት ትርክቶችንና ክርክሮችን ያካትታሉ። እነዚህ ተጠራቅመው፣ ተሳስረውም፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ተብትቦ የያዘ መረብ የጣሉ ናቸው። የሕወሓት አገዛዝ ርዕዮታዊና ድርጅታዊ ምሰሶ የሆነው የጎሣ ማንነት ፖለቲካ፣ በተለይ በህገ መንግሥታዊ አሰፋፈሩ፣ ባመዛኙ የዚህ አገር ጠማጅ መረብ ፍጡር እነደሆነ የምናውቀው ነገር ነው። ይህ ግንዛቤያችን ግን የወያኔ ጎሠኛ ብሔርተኝነት በአምባገነናዊ “ተራማጅ” ርዮት ብቻ ሳይሆን በተራ ዘረኝነትም የተበከለ መሆኑን የሚያስረሳን አይደለም።

ጥገናዊ ወይስ መሠረታዊ (ሕገ መንግሥታዊ) ለዉጥ?

ነገደ ብዙው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይ አማራውና ኦሮሞው (አማሮሞው?) ወጣት፣ በተጨባጭ ግልጽ ያደረገው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በብዙሃን ማኅበረሰቦች ስብጥርና ትስስር (በአንድ ደም) የተገነባች አገር መሆንዋን ነው። ስለዚህም ዛሬ የሚያስፈልጋት ለሌላ ዘር ተኮር ፓርቲ የገዥነት ተራ የሚሰጥ ወይም የሆነ የጎሣ ክልልን የበላይ የሚያደርግ ወይም ደግሞ ክልሎችን የሚደማምር የማንነት ፖለቲካን ጠጋግኖ መቀጠል ሳይሆን መሠረታዊ የሥርዓት ቅየራ ነው። ከዶ/ር ጌታቸዉ ኃይሌና ከአንዳንድ ሌሎች፣ በተለይ ኦሮሞ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን እንደተረዳሁት ግን ተፈላጊው፣ ተገቢውና እየተኪያሄደ ያለው የጥገና ለውጥ ነው። ምሁራኑ ይህን አቋም ሲይዙ የተነሱበት የሕገ መንግሥት ተብየው አመለካከታቸው አጠያያቂ ነው።

“ኢሕአደጎችን ያልተቀበልናቸው”፣ ይላሉ ዶ/ር ጌታቸዉ፣ “በሁለት ምክንያት ነው፣ አንደኛ፥ በሕገ መንግሥታቸው ስለከፋፈሉን፤ ሁለተኛ፥ በሕገ መንግሥታቸው በወረቀት ያጸደቁልንን መብት በሥራ ስለነፈጉን ነው”። ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል የራሱን ሕገ መንግሥት አካቶ የሚጥስ እንደሆነ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲው አገሪቱን በተጨባጭ የገዛው በእዉነቱ ያለሕገ መንግሥት እንደሆነ ነግረውናል። በተለይ አንቀጽ 39ን ሲተቹም “ሃያ ስባት ዓመት ሙሉ ያወዛገበን…[ይህ አንቀጽ] አቅም ኖሮት ሳይሆን በጥላው ብቻ” ነው የሚል ትክክል ክርክር አቅርበዋል። ሆኖም ክርክሩ በሕወሓት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሥር “ሕግ መንግሥት” የሚባለዉን ነገር ምንነትና ሥራ፣ ወይም ጨርሶ መኖር አለመኖሩን የሚመለከቱ መሠረታዊ ጥያቄዎች ያስነሳል። ጥያቄዎቹን የምናነሳው ነባሩን ሕገ መንግሥት ተብዬ ለመንቀፍ ብቻ ሳይሆን የሚተካውን ይበልጥ አገራዊና ዲሞክራሲያዊ ሰነድ መንድፍ የሚያስችል የአስተሳሰብ አውታር ወይም ቅርጽ መፍጠር እንዲረዳንም ነው።

አንቀጽ 39ን አክሎ ሕግ መንግሥቱ ቃል በቃል ያለዉን ቢል ምንም ሕጋዊ፣ መርሃዊና ተቋማዊ አቅም የሌለው ከሆነ በምን መንገድ ነው፣ በአስመሳይነት ወይም በግልብ የፖለቲካ መሣሪያነት ሳይሆን በሕገ መንግሥትነት፣ ወያነዎች አገር ከፋፍይ መሆን የቻሉበት? ወይም ደግሞ፣ ገዢዎቻችን በወረቀት ያጸደቁዋቸውን መብቶች በሥራ ነፈጉን ካልን የሕገ መንግሥቱ በጎም ሆነ ጎጂ ተጽዕኖ እምኑ ላይ ነው? ሕገ መንግሥቱ እንዳለ የወረቀት ነብር ከመሆን ያለፈ ህልውና ከሌለው ዶ/ር ጌታቸዉ እንደሚመክሩት ጠ/ሚንስትር አብይን በጥገና እርምጃ “ሕገ መንግሥቱን…[ወይም] የምንወዳቸውን አንቅጾች… አስከብር” ልንለው የምንችል በምን ስሌት ይሆን? አስቀያሚ ፈላጭ ቆራጭ አገዝዝ ማሳመሪያ ወይም ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ማስመሰያ ከምሆን ባሻገር በእውን የሌለና የማይሠራ የውረቀት ሕገ መንግሥት እንደመን ብሎ ነው በማንም ሊከበር ወይም ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው?

ይህ መሠረታዊ ጥያቄ አንዳንድ ጥገናዊ ለውጥ ብቻ ፈላጊ የሆኑ የኦሮሞ ምሁራን በጉዳዩ የያዙትን የማንነት ፖለቲካ ወገንተኝነትንም የሚመለከት ነው። እነዚህ የኢትዮጵያ ውቅታዊ ጉዳዮች ተመልካቾች እንደሚሉት፣ “ሕገ መንግሥት አለ”፣ ተፈላጊም ነው፣ “ክልሎች ይቀጥላሉ”፤ የሕገ መንግሥቱ ችግር ወይም ጉድለት የሕወሓት አገዛዝ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት በሚለው ስታሊናዊ መንገድ ተፈጻሚ መሆኑ ብቻ ነው።

እዚህ ላይ ለተመልካቾቹ የማይመቸው ሃቅ ወይም “የሚረሱት” ዋና ነገር ሕገ መንግሥት ተብይዉ ስታሊናዊ “የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት” መነፈስ የተላበሰው በአፈጻጸሙ ብቻ ሳይሆን ከጽንሱ ዘር ተኮር በሆነ አምባገነናዊ የማንነት ፖለቲካና ርዕዮት የኢትዮጵያን መንግሥታዊ-ሕዝባዊ ምህዳር በማጣበቡና በማጨናነቁ ነው። በአብዛኛው የቃል በቃል አባባሉም ባይሆን ከጀርባው በነበር የሕውሓት “አብዮታዊ” አላማ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት፣ በተለይ ደግሞ የአማራን ሕዝብ ደህንነት የተጻረረ ሰነድ ነው። ለዚህም ነው የይምሰሉ ሕገ መንግሥት ራሱ ዛሬ የሥርዓታዊ ለውጥ ኢላማ መሆን ያለበት። ሳያውቁም ሆነ እያውቁ በችኮ ጎሠኝነት ክፍለ አገራዊ ራስ ገዝነትንና አካባባዊነትን ከዘር ጉረኖ ወይም “ክልል” ጋር ዛሬም ለሚያምታቱ የማንነት ፖለቲካ ወገንተኞች አንድ መሠረታዊ ልዩነት ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፣ አእምሯቸውን ትንሽ ከፈት አድርገው ማሰብ፣ መወያየትና መረዳት የሚችሉ ከሆነ።

ልዩነቱ እንዲህ ነው፥ በአንድ በኩል የአገሪቱ ብዙሃን ማኅበረሰቦች በታሪካዊ ዝዉዉርና ግንኙነት በፈጠሩት ግብታዊ የለት ለት ስብጥርና ትስስር ከሞላ ጎደል አብሮነትን፣ መቻቻልንና የባህል ልውውጥን ያካተተ ባንዴ አካባባዊም አገራዊም የሆን ማንነት አዳብረዋል። በሌላ ብኩል ደግሞ እንደ ሕወሓትና ኦነግ ያሉ በርዝራጁም ቢሆን ስታሊናዊ የአብዮተኛነት ባህል አካቶ ያልተለያቸው የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያራምዱት ሆን ተብሎ የተሰላ ወገንተኛ፣ ቢችል የሚገነጠል ደሴታዊ የዘር “ማንነት” አለ።

የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ራስን በራስ አተያይና አለያይ እንግዲህ በተደራጁ ወገንተኞች የማንነት ሕንፀቶችና ትርክቶች የሚተኩ ወይም የሚጣጡ አይደሉም ማለት ነው። ማንኛውም “ብሔር ነፃ አውጪ” ነኝ ባይ የፖለቲካ ግንባር ወይም ስብስብ ማንኛውንም የኢትዮጵያ ነገዳዊ ማኅበረሰብ በሞኖፖል አይወክልም። ለምሳሌ የኦሮሞ ውይም የአማራ ወይም የትግሬ ማኅበረሰብነት ከተወሰነ የኦሮሞ ወይም የአማራ ወይም የትግሬ ዘር ተኮር ወገንተኝነት/ብሔርተኝንነት ይተልቃል። ከኢኮኖሚ ሕይወት፣ ከማኅበራዊ ኑሮና ከብሃላዊ ግንኙነት አኳያ ማንኛውም የአገሪቱ ባህላዊ ማኅበረሰብ በፍጹም ልዩነትና ብቸኝነት ደሴታዊ ማንነት ወይም ብሔርተኝነት የለውም። ነገደ ብዝው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ አይጠፋውም፣ በስሙ የሚፖተልኩ ነኡስ ብሔርተኛ “ምሁራን” ወይም “ሊህቃን” ብዝውን ጊዜ መሪው ከመሆን ይልቅ ተጎታች እየሆኑበት ነው እንጂ።

ባጭሩ እንግዲህ፣ “አብዮታዊ” ወይም “ተራማጅ” የተባለ ቀኖናዊ የአስተሳሰብና አነጋገር ፎርሙላ ወይም ልምድ አማካኝነት የተፈጠረ ርዕዮታዊ ፈርጅ (እነበል “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ወይም “ሕገ መንግሥት”) ያለው ፍቺ በዚያው በብቸኝነት ወገንተኛ የሆነ ዝግ ፎርሙላ የታመቅ ስልሆነ መርሃዊ ይዘቱ ውይም ትርጉሙ የመነመነ፣ እንዲያውም ከጽንሱ የተጨናገፈ ነው የሚሆነው። አለያም ፈርጁ ከተወሰነ ስውር ወገንተኛ መልዕክትና ገቢር ውጪ በሰፊው ለሕዝብ ወይም ለተለያዩ ፓርቲዎች የሚተርፍ በጎ ጽንሰሃሳባዊም ሆነ ተቋማዊ ይዘት ምንም ያህል አይኖረውም። አስተሳሰቡና ከጅርባው ያለው በቅን ልቦና ያልተቀረጸ አላማ በጥልቅ የተዛባ ስለሆነ የሚጠገን ሳይሆን በሌላ የተሻለ፣ በእውን አገራዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ፣ የጽንሰሃሳብ ግንዛቤና አቅራረጽ መተካት ያለበት ነው።

ከሥር መሠረቱ ተለውጦ በአማራጭ የሃሳቦችና የተቋማት ሥርዓት የሚተካውን ነባር የፖለቲካ ርዕዮትና ገቢር መዋቅር ቀድም ብዬ እንደጠቆምኩት በሁለት እርከን ልናየው እንችላለን። ቅስ በቀስ በረጅም ጊዜ አገራዊ-ሕዝባዊ ንቅናቄ የምንሄድበት መሠረታዊ የለውጥ ጉዞ የሚያተኩረው የሕወሓት አገዛዝ ላይ ብቻ አይደለም። አኪያሄዳችን አገዛዙን ዘልቆ ሕወሓት የሚንቅሳቀስበትን የፖለቲካ ፓራዳይም አነሰም በዛም የሚጋሩ ሌሎች የጎሣ ብሔርተኝነት እቅዶችን መዋቅረ ርዕዮት የሚገጥም ነው። በቀደምትነትና አስቸኳይነት የለውጡ ኢላማ ግን የሕወሓት ዘረኛ አገዛዝ ራሱ ነው። በሕዝብ የተቃውሞ ትግልና ተያይዞም በኢሕአዴግ ዉስጣዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ሕወሓት ባለፉት ጥቂት ወራት ዋና ዋና የሃይልና ተጽእኖ ጥፋቶች ደርሰውበት እንደለመድው በፈላጭ ቆራጭነት መንቀሳቅስ የማይችልበት የውጥረት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

ሁኔታው የወያኔን ፓርቲ ተስፋ ሊያስቆርጥ፣ ብሎም ወደ አስጊ አጥፍቶ ጠፊነት ሊመራ ይችላል። ፓርቲውን የጥግ ጥግ በማስያዝ ማምለጫ እንዳጣ የቆስለ አውሬ (“የቀን ጅብ”) አደገኛ አድርጎታል። ስለዚህ በጠ/ሚንስትር አብይ የሚመሩ የአገሪቱ የለውጥ ኃይሎች ይህን ተገንዝበው ሕወሓት እነሱንም አገርንም አጥፊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንዳይችል ሳይውሉ ሳያድሩ ከወዲሁ ቆራጥ እርምጃዎች መውሰድ አለባቸው። በእውንም ሆነ በእምቁ አስጊ ጥቃት እየተቃጣበት ያመነታ ተመታ ነውና! ይበልጥ አደገኛ በሆነ መልክና መጠን የሕወሓት አጥፊነት በተለይ የተነጣጠረበት አማራውማ ራሱን ሲያተርፍ ለአገር አዳኝነትም እንዲበቃ በያለበት አካባቢ ነቅቶ መጠባበቅና ለማንኛዉም አስፈላጊውን ሁሉ መንገድና ዘዴ ተጠቅሞ ህልውናውን ለመታደግ ዝግጁ መሆን አለበት። ዝግጅቱ መደራጀትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የአማራዉን ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊና ማኅብረሰባዊ ደህንነት ንቁ ጥበቃ ያካትታል።

በጠቅላላ የአገርና ሕዝብ ደህንነት ጥበቃው እንግዲህ ፍቅርንና እርቅን በሚያቀነቅን ሰበካም ሆነ በመለስተኛ የጥገና ለውጦች ብቻ የሚሆን አንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል። እንዲያውም የማይረቡ (ማለትም የማይዋለዱና የማይወራረሱ ወይም በሥርዓት የማይጠቃለሉ) ተናጠል ለውጦች የቁጥር “ድምር” ለውጡን አደገኛ ለሆነ ቅነሳና ቅልበሳ ሊያጋልጠው እንደሚችልም መረሳት የለበትም።ይህ አይነት የለውጥ ክትትል ጦርነት ሲዋጉ ያለአጠቃላይ ስልት በታክቲክ ደረጃ ብቻ ተንቀሳቃሽ በመሆን ይመሰላል። በአገር አድን የፖለቲካ ሥርዓት ትግሉ ስልታዊ አስተሳሰብ ከታክቲካዊ ስሌት በአይነትና ደረጃ ስለሚለይ ስልት ዝምብሎ የታክቲኮች መጨማመር ሊሆን አይችልም፤ ከታክቲኮች የቁጥር ድምር ያለፈ ቅርጽና ይዘት (ምንነት) አለው።

እገረ መንገዳችን የመደመርን ጉዳይ ካነሳን አይቀር፣ ላላ ባለ የመተባበርና የአብሮነት ፍቺው “እንደመር” ሳቢ፣ የሕዝብ ስሜት ቀስቃሽ መፈክር ነው። መፈክሩ ከንግግር ዘይቤነት ያለፈ ጽንሰሃሳባዊ ይዘት እምብዛም ስለሌለው ምንም ያህል ትንተና ወይም ትርጎማ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ነገር ግን እንደሃሳብ አገራዊ አንድነታችንን ከጎሣ ማኅበረሰቦችና ክልሎች ጥርቅም ባሻገር ማየት በማይፈልጉ ወይም በማይችሉ የማንነት ፖለቲካ ወገንተኞች አካባቢዎች ይዘዋወራል። ስለዚህ አውቀንም ይሁን ሳናዎቅ እነዚህን ውገንተኞች በመከተል የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ወደ “ብሔሮች” እና “ሕዝቦች”ድምር እንዳናወርድ ጠንቀቅ ማለት ይበጃል። ብሎም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከነገዶች ወይም የጎሣ ስብስቦች ጥርቅም/ድምር ያለፈ ህልውና እንዳላት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የሕገ መንግሥት ህላዌና ሥራ

የተለያዩ ዝርዝር የአገር ጉዳዮችን በጽንሰሃሳቦች አጠቃሎ መቅረጽ የሚያስችለን ምሁራዊ-ፖለቲካዊ ጥረት የጉዳዮቹን ተለያይነት ተሻግሮ የወል ታሪካዊና መዋቅራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጎላ ነው። የእውኑ ዓለም ተጨባጭ መረጃዎችና ሁኔታዎች በብዝሃንነታቸውና ውስብስብነታችው ከፊታችን ምንጊዜም አይጠፉም፤ ሆኖም ግን የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም ንድፈሃሳብ ፈርጆች የነገሮችን ልዩነት፣ ብዛትና ውስብስብነት ጠቅለል ባለ መንገድ አደራጅቶና አቃሎ የማሳወቅ ሥራ አላቸው። ለምሳሌ ውጤታማ የሕገ መንግሥት ዲስኩር የኢትዮጵያን ሕዝብ በርካታና ፈታኝ ጉዳዮች በልዩነታቸውና በአካባባዊነታቸው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ አገራዊ ትስስራቸውና አኪያሄዳቸው ሰፋ አድርጎ የማጤን፣ ሥርዓታዊ በሆነ የአመክንዮ ወይም የጽንሰሃሳብ አቀራረብም የመቅረጽና የማደራጀት (ብሎም ጉዳዮቹን ለተገቢ መስተዳደር የማመቻቸት) ሚና አለው።

ከጅምሩ ግን መሠረታዊ የሆነ የሕገ መንግሥት ህላዌ ወይም መኖር አለመኖር ጉዳይ ገጥሞናል። ትርጉማቸው በአግባቡ ታሳቢ ሳይሆን፣ ስይስተዋልና በአገሪቱ ፓርቲዎች፣ መንግሥታዊ አካላትና ዜጎች በቅጡ ሳይሰርጽ በድግግም በመባል ተለምደው ባመዛኙ ያነጋገር ዘይቤ ብቻ ሆነው የቀሩ የፖለቲካ ቃላትና ሃረጎች እጥረት የለንም። “ዲሞክራሲ”፣ “እኩልነት”፣ የማኅበረሰቦችና አካባቢዎች “ራስ ወሳኝነት” “ፌደራላዊነት” እና “ሕገ መንግሥት” ከነዝህ ዋኖቹ ናቸው። በተለይ ሕገ መንግሥት ላይ ለማተኮር፣ መኖር አለመኖሩን ወይም ምንነቱን ለመገንዘብ የምናነሳው ጥያቄ ዝምብሎ ምን በወረቀት የሠፈረ ጽሑፍ አለ? የሚል ሊሆን አይችልም። አንድን ሕገ መንግሥት ፍሬያማ ትርጉም አዘል የሚያደርገውና አለ የሚያስብለው በወረቀት መቀረጹ ሳይሆን በተያያዙ የጽንስሃሳብ፣ የመርህ፣ የተቋማትና የገቢር ደረጃዎች በሙሉነት የሚገለጽና የሚሠራ ሲሆን ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ አገርና ሕዝብ ላይ በጎ ተጨባጭ ተጽእኖ ሊኖረው የሚችለው ቃል በቃል በያዛቸው ሃሳቦች ብቻ አይደለም። ይልቅስ በአቀራረጹ በነበረ የሕዝብ ተሳትፎ አይነት፣ መጠንና አመራር ነው።

በነዚህ ሁኔታዎች ቋሚ ቅርጽ የያዘ የመንግሥት ሕግ የተለያዩ የአገር፣ የኅብረተሰብና የዜጎች ጉዳዮችን፣ ብሶቶችን፣ ጥቅሞችንና እንቅስቃሴዎችን በአጠቃላይ ጽንስሃሳባዊ/መርሃዊ ገጽታቸው ብቻ ሳይሆን በግል፣ ልዩና ዝርዝር ምንነታችውም በቅጡ ማስተናገድና ማስተዳደር ይችላል። ለምሳሌ በድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ አገባቡ የክፍለ ሃገራዊ ራስ ገዝነትን መርህ አገሪቱ ወደፊት ከሚኖራት ማእከላዊ መንግሥት ጋር በሚገባ ያጣጥማል። የግለሰብ መብቶች በሕጋዊ፣ መንግሥታዊና ማኅበረሰባዊ ተቋማትና ገቢሮች ራሳቸዉን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ በእዉን ይፈቅዳል፣ ያመቻቻልም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና ሌሎች መሠረታዊ የመንግሥት ተቋማትን የሆነ አገዛዝና ወገንተኛ ፖለቲካ ተለጣፊ ወይም ተቀጥላ አያደርግም።

በአገራችን ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አለ ወይም የለም ለማለት እንግዲህ አንዳንድ ዋና ዋና ትያቄዎችን መመለስ አለብን። ከጥያቄዎቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፥ አንደኛ፣ ሕገ መንግሥት የተባለው የማእክላዊም የክፍለ ሃገራዊም መስተዳደሮችንና ባለሥልጣናትን ፖሊሲዎችና ድርጊቶችና፣ እንዲሁም ኃይልና ሥልጣን አጠቃቀም ሕጋዊነት እንዳስፈላጊነቱ በእውን የሚበይን፣ በአንጻር ነጻ የሆነ፣ ተቋማዊ ህላዌ አለው ወይ? ሁለተኛ፣ የራሱን ተቋማዊ ብቃትና አንጻራዊ ነፃነት ለማረጋግጥ ወገንተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም የሚያስችለውን የሕግ ሙያተኝነትና አገራዊ ንቃተ ህሊና ያካተተ ነው? ሦስተኛ፣ ለተፎካካሪ አተረጓጎሞች ወይም ለሕገ መንግሥታዊ ሊቃውንት ክርክሮች አንጻራዊ ክፍትነትንና ቅቡልነትን ያሳያል? አያይዞም የነፃነት፣ የፍትሕ፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት ጽንሰሃሳቦች በተለያዩ የፖለቲካ፣ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ ዘርፎች፣ እንዲሁም በመላ የአገሪቱ ዜጎች ኑሮ በእውን ተገላጭና ተፈጻሚ እንዲሆኑ ይፈቅዳል ውይም ያስችላል? አምስተኛና መጨርሻ፣ በሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ሉአላዊ ሕዝብ ራሳችንን እንለያለን ወይም እናያለን? ማለትም፣ ሕገ መንግሥቱ አገራዊ አንድነታችንን እና ሉአላዊነታችንን ከጎሣ ማንነቶች የቁጥር ድምር ባሻገር በግልጽ እውቅና ስጥቶ ያረጋግጣል?

የሥርዓታዊ-ጽንሳዊ እሳቤ ሙከራዎች ክሽፈት

መንግሥትን በሃስቦች ሥርዓት መመሥረት የተለያዩ አገራዊ እንቅስቃሴዎችንና ድርጊቶችን አንድ ላይ የማስተዳደር ሙከራ አካል እንደሆነ እንገነዘባለን። ሙከራው ተለዋዋጭ ጉዳዮችን፣ ችግሮችንና ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም ነገዳዊ፣ ባህላዊና አካባባዊ ብቸኝነትን ተሻግሮ ሁሉንም በአንድ አጠቃላይ አገራዊ የሃሳብ፣ የመርህና የሕግ ሥርዓት አማካኝነት አገናኝቶ ለመግዛት ነው።

ከተማሪው ንቅናቄ ጊዜ ጃምሮ በአብዮቱና ድህረ አብዮቱ ዘመን ያየነው ይህንኑ የሕዝብና የአገር አገዛዝ ሙከራ ነው። ከሞላ ጎደል ይህን አይነት የአገር ችግሮች አቀራረብና አፈታት የፖለቲካ መንገድ ተከትለው ነው ኢሕአፓ፣ ደርግና ሚኤሶን፣ የኋላ ኋላ ድግሞ ሕወሓት በልሉ የፖለቲካ ጽንሰሃሳቦች የተባሉ ማንሜናዎችን (“ዲሞክራሲ”፣ “የብሔሮች ራስ ዉሰና”፣ “ተራማጅነት”፣ ወዘተ) በፉክክርና ግጭትም በተጨባጭ ትብብርም በኢትዮጵያ ያሰራጩት።

ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች በወልም ሆነ ለየቅል ያሰራጯቸው የፖለቲካ ጽንሰሃሳቦች ፖለቲካዊ ተሞክሮዎቻችንን ወደ አጠቃላይ አገራዊ የሥርዓት አንድነት አላሸጋገሯቸዉም። ፓርቲዎቹ ቃል በቃል ባንደረደሯቸው የርዕዮት ፈርጆች ከሞላ ጎደል “አንድ ገጽ ላይ” ነበሩ ቢባልም፣ በስምምነት የደረሱበት በእውን የሚሠራ የጋራ መግባቢያና መተባበሪያ የሆነ ሥርዓታዊ ፖለቲካ ቋንቋ ወይም ገቢር አልነበራቸውም። እንዲያዉም እንደ “ዲሞክራሲ” እና “ተራማጅነት” የመሳሳሉ ከአገራዊነት አልፈው ዓለም አቀፍ የሆኑ ሃሳቦችንና እምነቶችን በጠባብ፣ ብቸኛ የወገንተኝነት ወይም የጎሠኝነት ጉረኖዎች ከልለው መያዝ ይቀናችው ነበር። ዛሬ በጠ/ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አመራር ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጅምሮች እያየን ቢሆንም ለአስርት ዓመታት ካልተለይን የሥርዓተ አልበኝነት አባዜ አለጥርጥር እየተገላገልን ነው ማለት አዳጋች ነው።

በአገር አሳናሽነትና አሰናካይነት ሳይወሰን የሃሳቦችና መርሆች አጨናጋፊ የነበርው የፖለቲካ ሥርዓተ ቢስነት በተለይ በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሕወሓት አገዛዝ ተባብሶ የቀጠለ መሆኑ ግልጽ ነው። ዋናው ዉጤቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መደብ የተለያዩ የአገር ጉዳዮችንና ሁኔታዎችን፣ ባህላዊ ማንነቶችንንና ብዙህንንትን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ሥርዓታዊ መርሆች፣ እሴቶች፣ ተቋማትና ገቢሮች አቀራርቦ፣ አገናኝቶና አዛምዶ ማስተዳደር አለመቻሉ ነው።

የሕወሓት-ኢሕአዴግ “ሕገ መንግሥት” የአገር ጉዳዮችን በግልነታቸው፣ ዝርዝርነታቸው፣ ተለዪነታቸውና አካባባዊነታቸውም ሆነ በጥቅል ጽንሰሃሳባዊ፣ መርሃዊና አገራዊ ግንኙነቶቻቸው ሊወክላቸው ወይም ሊያስተዳድራቸው ቀርቶ በሥርዓትዊ መንገድ ታሳቢና ተገንዛቢ ሊያደርጋቸውም አልቻለም። ይህ አለመቻል የሚያሳየን የሕወሓትን ድክመት ወይም “ስህተት” ብቻ ሳይሆን ይህ የትግራይ “ነፃ አውጪ” ነኝ ባይ ወገን ሆን ብሎ ያሰላውን የቅኝ አገዛዝ መንፈስ የተላበሰ አገርንና ሕዝብን ከፋፍሎ የመጨቆንና የመበዝበዝ እቅድ ነው። አያይዘን የምናየውም በድህር አብዮት ኢትዮጵያ ይህ እቅድ ያስከተለውን የፖለቲካ ሃሳብ መጥበብና መደኽየት ነው።

ድክመቱን አጠቃለን ስንመለከተው ግን በተማሪው ንቅናቄ ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ ክተፈጠሩ የተለያዩ አብዮተኛ ፓርቲዎች ፉክክርና ግጭትም ሆን ተጨባጭ የአስተሳሰብና የአሠራር ተወራራሽነት ጋር ተያይዞ እናየዋለን። ይህ ለምን ሆነ? የፖለቲካ ሥርዓት ሙከራው ለምን ፉርሽ ሆነ? ችግሩን እንዴት መወጣት ይቻል ይሆን? ዛሬ በኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ የምንደግፍ አገር ወዳድ ወገኖች እነዚህን ብርቱ ጥያቄዎች መመለስ ግድ ሊለን ይገባል። የምንስጠው መልስ አገሪቱን ለአስርተ ዓመታት የተጠናወታትን የፖለቲካ በሽታ ከሥሩ ለመመርመር ይረዳል፤ ብሎም አማራጭ፣ በእውን አርገራዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት የማቋቋም ጥረታችንን ያግዛል። እንደ አገር ለተጠናወተን ሥር የሰደደ የፖለቲካ በሽታ ፍቱን ፈውስ ለማበጀት የሕመሙን ምርመራ ጠጋና ጠለቅ ብሎ ማኪያሄድ ወሳኝ ነው።

ካለፉ ስህተቶች ለመማር፥ የሥርዓታዊ አስተሳሰብ ሙከራው ለምን ከሸፈ?

የፖለቲካ ሕመማችን አንድ ዋና ምንጭ ከተራማጅነት ልምዳችን የወረስነውና ዛሬም አካቶ ያልተለየን የአገር ጉዳዮችና ችግሮች አገላለጽ፣ ብሎም “አፈታት” ቅርስ ነው። የአገላለጹ ዋና አላማ የታዩ ጉዳዮችን በቀጥታና በአንድ አፍታ በተወሰነ አምባገነናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ፎርሙላ ዘግቶ መቆጣጠር እንጂ ሰፋና ጠለቅ ላለ ነፃ ውይይት ወይም የሃሳቦች ልውውጥና ስምምነት መክፈት አልነበርም፤ ሆኖ አያውቅም። አኪያሄዱ የአገርና የሕዝብ ችግሮችን ሲገልጽ ሥርዓት ተኮር ቃላት (ለምሳሌ ባላባታዊነት) አልተጠቀመም ባይባልም፣ በትርክቱ ያጎላው የነገዳዊና ባህላዊ ማንነቶችን ወይም ማኅበረሰቦችን አጥቂነትና ተጠቂነት ወይም ጎጂነትና ተጎጂነት ነው። የሚያቀነቅነው በተንቀሳቃሽ ውገኖች ድርጊቶች ዙሪያ እንጂ በአጠቃላይ መዋቅራዊ (ማለትም፣ የኢኮኖሚ፣ የኅብረተሰብ፣ የባህልና የፖለቲካ) ግንኙነታቸውና ትስስራቸው አይደለም። ባጭሩ የአገርና ሕዝብ ችግሮች አገላለጻችን በሰፊው መዋቅራዊ ሳይሆን ባመዛኙ የችግሮቹ አድራጊ ፈጣሪ የተባሉ ነገሥታቶች፣ አገዛዞች፣ መደቦችና ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ላይ ያተኮረ ነበር።

ለአገር ጉዳዮች “ተራማጅ” መፍትሔዎች አፈላለጋችንንም ስንመለከት ባመዛኙ ያየነውና ዛሬም ከሞላ ጎደል የምናየው የፖለቲካ አዝማሚያ አጠቃላይ የሥርዓት ቅየራ ሙከራ ሳይሆን ከተቻለ የነገድ ማንነቶችን ለያይቶ “ነፃ ማውጣት” (ከአገር መገንጠል) ካልተቻለ ደግሞ ከልሎና ደማምሮ መግዛት ይሆናል። ስለዚህም የአገር ጉዳዮች አገላለጻችን ልምድ የችግሮችን ሰፊ መዋቅራዊ “ግዛት” ወይም አገራዊ ወርድና ስፋት አጣቦ ያየ ብቻ ሳይሆን፣ አያይዞም የሥርዓታዊ ለውጥ አስተሳሰብን ያደኸየና ያቀጨጨ ነው። ጠባብ፣ ብቸኛ ውገንተኝነትና ጎሠኝነት ርዕዮታዊ (ሃሳባዊ) ጠባብነትን፣ ምሁራዊ ዉስንነትን አስከትሏል።

ስለዚህ ሰፋና ገባ ባለ እሳቤ የተወሳሰቡ የአገር ጉዳዮችንና ሁኔታዎችን በተለያዩ ተያያዥ የአመለካከትና ደረጃዎች አይተን ጉዳዮቹ በዘር ዘለልነት ተደራራቢ ወይም ተወራራሽ መሆናቸውን መገንዘብ ምንም ያህል አልቻልንም። በታሪክ የገዢዎችን ጎጂነትና የተግዢዎችን ተጎጂነት ትርክት የሚያጠብቁ ወገንተኞች በተለይ ጉዳዮቹንና ሁኔታዎቹን አላግባብ በማነት ፖለቲካ ሸንሽነው በማየት ቀላል ያስመስሏቸዋል። ይህ አተያይ በአገርና ሕዝብ ጉዳዮች አቀራርጽና አወሳሰን ሂደት ውስጥ ተጎጂ ነገዳዊ ማኅበረሰቦችን እንውክላለን ለሚሉ የዘር ፖለቲካ አራማጆች የተጋነነ ብቸኛ ሚና ይሰጣል። ሰፋፊና ውስብስብ የወል አገራዊ ጉዳዮችን ከፋፍሎና አቃሎ በማንነት ፖለቲካ ለመፍታት ይሞክራል። ስለዚህ አመለካከቱ ለችግሮቹ ሥርዓታዊ ትንተናና ዘላቂ መፍትሔዎች ፈጠራ ምንም ያህል አስተዋጽዎ ሊያደግ አይችልም።

የአብዮቱና ድህረ አብዮቱ ዘመን የሥርዓታዊ አስተሳሰብ ሙክራችን ክሽፈት ሁለተኛ ዋና ምክንያት ደግሞ በሙከራው ሃሳቦች ከነበራቸው ሁኔታና ቦታ ውይም ሚና ጋር የተያያዘ ነው። የፖለቲካ “ጽንሰህሳቦች” ያልናቸው ነገሮች (ለምሳሌ “አብዮት”፣ “ዲሞክራሲ” እና “ሕገ መንግሥት”) በአገሪቱ ምሁራንም ቢሆን ጠለቅ ባለ ተጨባጭና ተቺ ዲስኩር ወይም ፍልስፍና የተብላሉና የተብራሩ አልነበሩም። ዛሬም አይደሉም። በዚህ አይነት ንግግር ሳይፈተሹና በሰፊው አገራዊ አገባባቸው ሳይዳሰስ የሆኑ ያልሆኑ የፖለቲካ ወገኖችንና አገዛዞችን የትግል ተሞክሮዎች ተቻኩለው ተቀላቀሉ።

ተቀላቅሎው ሁለት ጥልቅ ስህተቶች አስከትሏል። በአንድ በኩል “ሃሳቦች” የተባሉት ከተወሰነ የወገንተኝነት፣ የጎሠኝነትና ያገዛዝ ልምድ ጋር ተቻኩለው በመደባለቃቸው ለአጣሪ አጠቃላይ ክርክር፣ ውይይትና ትንተና ለመከፈት አልበቁም ምክንያቱም አብዛኛዉን ጊዜ በማንነት ፖለቲካ ፉክቻዎችና ግጭቶች ውስጥ በርዕዮታዊ መሣሪያነት ተጠምደው ቀሩ። ስለዚህ በሰፊው ከአገርና ሕዝብ ጥቅም አኳያ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ይዘታቸው ምንም ያህል በሥርዓት ታሳቢና ተፈጻሚ ሊሆኑ አልቻሉም። በሌላ በኩል ደግሞ በሰፊው የኢትዮጵያን ኅብረተሰባዊ ግንኙነቶች፣ ሂደቶችና ለውጦች በሚመለከት ተጨባጭ ዕውቀት ማግኛ የሆነ የማኅበራዊ ሳይንስ ዲስኩር ከወገንተኞች ታክቲካዊ የተቃውሞ፣ የፉክክርና የፕሮፓጋንዳ ክርክር ጋር ጨርሶ ስለተምታታ ዲስኩሩን በአገሪቱ መሠረታዊ የፖለቲካ ዕውቀት ማዳበሪያ አድርጎ ሥራ ላይ ማዋል አዳጋች ሆኗል።

ከዚሁ የፖለቲካ ቋንቋ ደረጃዎች መምታታት ጋር የተያያዘው ሌላ ጣጣ ደግሞ ብዝውን ጊዜ የጽንሰሃሳቦችን መጠሪያ ስም ከጽንሰሃሳቦች ይዘት ጋር መደባለቅ መሆኑን እንገነዘባለን። በተለይ በሕወሓት አገዛዝ እንዳየነው ሃሳባዊ ወይም መርሃዊ ፍሬ ነገር ምንጊዜም ከስሙ የተለየና የራቀ ነው። ለምሳሌ በአገዛዙ ውስጥ “ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል ወይም ስያሜ ተዘዋዋሪ ቢሆንም አገዛዙ ዲሞክራሲን በሚሠራ መርህ ወይም ጽንሰሃሳብ ያካተተ አለምሆኑ ከጅምሩ ግልጽ የነበር ነገር ነው።

በዚህ ምክንያት በድህረ አብዮት የኢተዮጵያ ፖለቲካ ጽንሳዊ ሃሳብ ሰፋና ጠለቅ ብሎ የራሱን አንጻራዊ ነፃነት ማዳበር አልቻለም። ስላልቻለም፣ የተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎችንና ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም የዜጎችን፣ የማኅበረሰቦችንና የፓርቲዎችን ውይይቶች፣ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች ለማደራጀትና ዘላቂ ቅርጽ ለመስጠት አልበቃም። ይህ አይነት ብቃት ስለተጓደለበትም ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ማቋቋም የሚያስችል አቅም አልገነባም። በተለይ በጉድኛው ዘመነ ወያኔ ልክ የአገርና ሕዝብ ችግሮች አገላለጽ በወገንተኛ ጎሠኝነት እንደተጣበበ ሁሉ የፖለቲካ ሃሳብም እንዲሁ በዘረኝነት ተከልሎ ተጣቧል።

እዚህ ላይ የወያኔ አገዛዝ ችግር አስተሳሰብ አጥባቢነቱ ብቻ አይደልም። በአገዛዙ ሥር ሲዘዋወሩ የነበሩ የእሳቤዎችና ተቋማት ስሞች (“ፌደራላዊነት”፣ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” ወዘተ) ዝምብለው እንደ ታርጋ ወይም ምልክት የሆኑ ያልሆኑ ነገሮች ላይ የተለጣጠፉ ይመስላሉ። ግን በፖለቲካ አስተሳሰብ ሜዳ ላይ ከተለጣፊነት ያለፈ አሉታዊ ሚና የተጫወቱ ናቸው። የሕወሓት አገዛዝ በሃሳቦች መስክ እንደ ደፈጣ ተዋጊ ወይም ነጭ ለባሽ የሚንቀሳቀስ ነው። በዚህ አይነት እንቅስቃሴ ለምሳሌ ላይ ላዩን ሕገ መንግሥታዊ መሰል ጨዋታ እየተጫወተ ውስጥ ለውስጥ ግን የሕገ መንግሥትን መሠረታዊ ሃሳብ ከጽንሱ አጨናግፏል። አገዛዙ የተጠቀመበት አጠቃላይ ርዕዮተ ዘዴ እንግዲህ የሃሳቦችን ሃቀኛ ይዘትና ቦታ ቀድሞ በአስመሳይ (ትርጉም የለሽ) ተተኪዎቻችው በመያዝ ጥርስ አልባ ማድረግ፣ ማኮላሸት ነው። የዐብይ “አብዮት” ይህን አገርና ሕዝብ ጎጂ የፖለቲካ ባህል ከሥር መሠረቱ የመለወጥ እቅድና አቅም አለው? ወይም ሊኖረው ይችላል?

ጠ/ሚንስትር ዐብይ አሕመድ – የሥርዓት ጥገና ወይስ ለውጥ አመራር?

አዲሱ ጠ/ሚንስትር መሠረታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አሠራርፓራዳይም ለውጥ የማምጣት እቅድ ይኑረው አይኑረው በእርግጥ ግልጽ አላደረገም። ይሁን እንጂ የጠ/ሚንስትሩ አመራር ሆን ተብሎም ባይሆን በእምቁ ውይም በዉጤት የሥርዓት ለውጥ ዕድል የከፈተ ይመስለኛል።ይህ ግምቴ በጥቅሉ ትክክል ከሆነ የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሳል፥ ነገደ ብዙ አገር ወዳድ ውገኖችና አንድነት ደጋፊ ኃይሎች የተገኘውን ዕድል እንዴት በትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ቅቡልነት ባለው መንገድ መጠቀምና ወደፊት መግፋት እነችላለን? ይህ ጉዳይ በጥሞና ሊያወያየን የሚገባ ነገር ነው።

እንደሚመስለኝ፣ በጠ/ሚንስትሩ ፈጠንጠን ያሉና የተባዙ ለዉጥ አመንጪ ጅምሮች፣ መልክቶችና እርምጃዎች ተስፋ እያደረግንም ቢሆን ተረጋግተን ለውጦቹን ከረጅም ጊዜ መሠረታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ቅየራ አኳያ ማጤንና ማስተዋል ያስፈልጋል። ከመለስተኛ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ረድፍ ብቻም ቢሆን የቀደምትነቶች ቅጥ (order of priorities) ከተጓድለ፣ ማለትም እንቅስቃሴዎቹ በቅደም ተከትል ተራ በመያዝ አንዱ ለሌላው መራመጃ፣ መጠናከሪያ፣ መንደርደሪያና መመንጠቂያ በመሆን ካልተወራረሱና ካልተደጋገፉ የእርምጃዎቹ የቁጥር “ድምር” ብቻ ለለውጦቹ ጥራትና ዘላቂነት ዋስትና አይደለም። ይህን ጠ/ሚንስትር ዐብይና የአመራር ጓዶቹም አማካሪዎቹም ይረዳሉ ብዬ እገምታለሁ። ለውጥን በጥድፍድፉ፣ በትንንሹና ሁሉ ቦታ መዝራት የትም ቦታ ሥር ሰዶ አለመብቀሉንና አለመልማቱን ወይም በቀላሉ ተቀጭነቱን ሊያስከትል እንደሚችል ጠ/ሚንስትሩና ሌሎች የለውጡ መሪዎች ማወቅ አለባቸው።

እዚህ ላይ የለውጥ ደርጃዎችን ወይም አይነቶችን በሚመለከት አንድ ነጥብ ግልጽ ለማድረግ፣ በታክቲክ ውይም “ጥገናዊ” መልክ የሚደረግ መለስተኛ እንቅስቃሴ የግድ ሥርዓት ተኮር ስልታዊ የለውጥ ሂደትን የሚቃረን ወይም የሚያደናቅፍ አይደለም። በሁለቱ እርከኖች የሚኪያሄዱ ለውጦች ምንጊዜም እርስ በርስ የሚጋለሉ ሳይሆኑ ሊመጋገቡ የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ሥርዓት ጠጋኝ የሚመስሉ ታክቲካዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በተጨባጭ የአጠቃላይ ንቅናቄ “ምንዛሪ” ወይም አካላት ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ጉዳይ የእቅዳቸውና ክንውናቸው አገራዊ አመራር ድርጁነት፣ አቅጣጫ ሰጭነትና ቀጣይነት ነው።

ያለዚህ አይነት አመራር የመለስተኛ እንቅስቃሴዎች መፋጠን ወይም መባዛት ራሱ ባንጻር ዝግ ብሎ የሚኪያሄድ መሠረታዊ የለውጥ ንቅናቄን ጅምርና ሂደት ሊያስተጓጉል ወይም ሊያደናግር እንድሚችል መገንዘብ ግድ ይላል። አክለንም ማወቅ ያለብን ሥርዓት ለዋጭ ንቅናቄ የተለያዩ ጥቅሞችና ግቦች የሚያሳድዱ ከዳያስፖራ አገር ገቢ ስብስቦች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች፣ በተለይ በውጭ ኃይሎች መጠቀሚያና ተጠቃሚ ወገኖች ሥራዎች፣ አገራዊ አቅጣጭውን እንዳይለቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

እንግዲህ ቀለልና ፈጠንጠን ያሉ የአጭር ጊዜ ለውጥ እንቅስቃሴዎች፣ ገጠምኞችና ሁኔታዎች እንዴት ነው ቅስ ብለው ከሚኪያሄዱ ይበልጥ ሰፊና ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓት ውይም ባህል ቅየራ ጥረቶች ጋር ቀጣይ ግንኙነቶች የሚያዳብሩት? ዋናው የውቅቱ ጥያቄ ይሄ ይመስለኛል። ተያይዞም የሚነሳውም ጉዳይ ጠ/ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚሰጠው የለውጥ አመራ ጥገናዊ እና/ወይም መሠረታዊ መሆኑ ነው።

በኢትዮጵያ የማንነት ፖለቲካን ከውያኔ “የማእከላዊነት” ቁጥጥር ለማላቀቅ ብቻ የሚሹ አንዳንድ የዘር ብሔርተኛ ምሁራን የጠ/ሚንስትር ዐብይን የአመራር አቅም በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝ መሪ የነበረው ደክለርክ ካሳይው ፖሊሲ የማመንጨት ችሎታ ጋር በማመሳሰል ጠ/ሚንስትሩን በተገቢና ተስማሚ የጥገናዊ ለውጥ መሪነት ፈርጀውታል። ግን ምስስሉ የተምታታ ነው። የደቡብ አፍሪካው መሪ ደክለርክ የፈለገው ነገር የአፓርታይድን አገዛዝ በጥገና ማዳን ነበረ ቢባልም ባይባልም አገዛዙ ታክሞ ሊድን የሚቻል አልነበርም። አብዛኛው፣ በተለይ ነጭ ያልሆነው፣ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ የዘረኛ ፖለቲካ ሥርዓቱን ጥገናዊ መሻሻል ሳይሆን መሠረታዊ ለውጡን ነበር የፈለገው፣ የጠየቀውና ያገኘው። አገራችን ላይ የተጫነውን አፓርታይድ መሰል አገር በዘር ከፋፋይ አገዛዝም (የተፎካካሪ ጎሠኛ ድርጅቶችን ተጽእኖ ጨምሮ) ስንመለከት በመሠረቱ ከዚህ ያልተለየ የሕዝብ ፍላጎትና ጥየቃ ነው የምናየው።

ወደ ኢትይዮጵያ ስንመጣ፣ አንደኛ፥ ከንግግሮቹ እንደምንገነዘበው፣ ጠ/ሚንስትር ዐብይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደከብት በዘር ጉረኖዎች መከለሉ ለአስከፊ ግጭቶች መዳረግ፣ እንዲሁም ከርስትና ጉልቱ ተፈናቅሎ (በተለይ አማራው) በገዛ አገሩ ለስደተኛነት እንደተጋለጠ ያውቃል። በሱ ዘብ ጥበቃ እነዚህ ችግሮች ጋብ ማለታችው ቀርቶ ተባብሰው ቅጥለዋል። የሕዝቡ በጎሣ ባንቱስታኖች መታጎር የማይበጀው ለአገር አንድነትና ለልማት መቀላጠፍ ባቻ ሳይሆን ለዜጎች ግለሰባዊ ነፃነቶችና ለባህላዊ/አካባባዊ ማኅበረሰቦች ራስ ገዝነትም መሆኑን ጠ/ሚንስትሩ ሳይገባው አልቀረም።

ይህን ከተረዳ ደግሞ የተለመደውን ሕዝብ አጋጪና አገር አሰናካይ የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት ጠጋግኖ ቀጣይ ማድረግ ይገባል ወይም ያዋጣል ብሎ ያስባል ማለት አዳጋች ነው፣ ፈጽሞ ታሳቢ የሚያደርገው ነገር አይደለም ማለት ባይቻልም። ሁለተኛ፥ ጠ/ሚንስትሩ የሚጥረው ለጥገና ለውጥ ብቻ ቢሆንም ይህ ውስን ጥረት ከነገደ ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ፍለጋ ጋር የሚጣጣም አይሆንም። ሕዝቡ፣ በተለይ አንድ ነን ያለው አማራውና ኦሮሞው የሥርዓት ቅየራ ጥያቄውን ለጠ/ሚንስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ወሳኝ አስተውጽዎ ባደረገበት ትግሉ ግልጽ አድርጓል። ለዚህ ጥያቄው ከመሪዎቹ በቂ መልስ ካላገኘ ትግሉን ለመቀጠል ይገደዳል።

እርግጥ በኢትዮጵያ እንደ ዛሬ ባለ የአገር ህልውናና ደህንነት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሁናቴዎች ባልተረጋገጡበት ወቅት አገር አዳኝ፣ አዳሽና መልሶ አጠናካሪ የሆነ መሠረታዊ የሥርዓት ቅየራ ማቀድና ተፈጻሚ ማድረግ ለማንም መሪ ቀላል አይደለም። በማንም ሰው የግል አመራር ፈቃደኝነትና ችሎታ ብቻ ሊከናወን አይችልም። ተስፋ በተመላበትም አስጊ በሆነም ያልተቀየሰ አዲስ የለውጥ መንገድ አገር ይዞ መጓዝ የተደራጀ የአስተሳሰብና የተግባር ንቅናቄ ይጠይቃል። የመንገዱ ጠረጋ የሚከናወነው በመስተፋቅር ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ጀግንነትና ስልታዊ ቅየሳ ጭምር ነው። በሥርዓት ለውጥ ትግሉ ከአእምሮ የሚፈልቅ ቆራጥ፣ ምክንያታዊ እሳቤ ከልብ የሚመነጭ የፍቅር ስሜትን አይለይም።

ስለዚህ ጠ/ሚንስትር ዐብይ ለግል አመራሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰፊ ቅቡልነትና ድጋፍ ከመሳብ ባሻገር ከኢሕአዴግ አገዛዝ ውስጥም ውጭም ያሉ ለዉጥ ደጋፊ ወገኖችንና ሃይሎችን በአዲስ የአብሮነት መንፈስ አሰባስቦ መምራት የሚያስችለው አዲስ አስተሳሰብ፣ድርጅታዊ ሥነ ሥርዓትና ዘዴኛነት ያስፈልገዋል። የስቪልና የጦር ሃይሎች ባለስልጣናትን ሹም ሽር ተፈጻሚ ከማድረግ በተረፈ የመንግሥትና የፖለቲካ ተቋማትን ባህልና ገቢሮች ቅየራ አስፈላጊነት ተገንዝቦ ሳይውል ሳያድር በዚህ ረድፍ ተነሳሽነትና ተንቀሳቃሽነት ማስየት አለበት።

ጠ/ሚንስትሩ ይህን የተቋማዊ ለውጥ ንቅናቄ አመራር ከራሱ ፖለቲካ ቤት፣ ማለትም በሊቀ መንበርነት ከሚመራው የኢሕአዴግ፣ በተልይ ደግሞ ከሚወክለው ከኦነግ ግርፉ ኦሕዴድ፣ ውስጥ ጀምሮ በስልታዊ አኪያሄድ ወደ ሌሎች ጎሠኛ ድርጅቶች ሊያዛምተውና ሊያስፋፍው ይችል ይሆናል። በዚህ አይነት ሂደት ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልክና መጠን በአንጻር ነፃ የሆነ አካባባዊ ማንነትንና ራስ ገዝነትን ከሙሉ ኢትዮጵያዊነት ጋር ተወራራሽ፣ ተናባቢና ተደጋጋፊ የማድረግ ተቻይነት አለ ብዬ አምናለሁ። ተቻይነቱ ግን በተለመድው ስታሊናዊ የፖለቲካ ሰዋሰውና ቃላት የተቀረጸ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” የሚል ግዑዝ ዲስኩር እውን ወይም ተፈጻሚ መሆኑ ይቅርና ለአጥጋቢ ውይይት፣ ትችትና ትንተና እንኳን ክፍት ሊሆን የማይችል መሆኑን ከተገነዘብን አስርተ አመታት አልፈዋል። ይህ የፖለቲካ ኮድ ወይም ቋንቋ ራሱ ከናካተተው ግትር ቀኖና መፈንቅለ ርዕዮት ሊኪያሄድበት የሚገባ ነው።

ጠ/ሚንስትር ዐብይ በኢትዮጵያ የዘር ወገንተኝነትንና አገዛዝን ፓራዳይም ቅየራ አስፈላጊነት ከልቡ የተቀበለ ከሆነ በፖለቲካ ርዕዮት መስክ ተንቀሳቅሶ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ አመራር መስጠት መቻሉ ወሳኝ ነው። ጠ/ሚንስትሩ ነገሮችን በጽንሰሃሳብም በገቢርም የማወቅና የማሳወቅ ወይም የማስተማር ፍላጎት ያለው ይመስላል። ግን በምሁራዊው መስክ ከአመራር ጓዶቹ ጋር ሆኖ ለሥርዓት ለውጥ ሲንቀሳቀስ ራዕዩ ወይም ዋናው ተልዕኮው ምን እንድሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብና የፖለቲካ መደብ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ተልዕኮው በተራማጅነት ልምዳችን በአነጋገር ዘይቤነት ብቻ ተወስነው የቀሩ ‘ጽንሰሃሳቦችን’ (ለምሳሌ “ዲሞክራሲ” እና “ሕገ መንግሥታዊነት”) እንዳሉ ማስተጋባት አይደለም። ወይም የጽንሰሃሳብ ፈርጆቹን እንደገና መፍጠር ሊሆን አይችልም። ከጋራ አገራዊ ባህላችን ተነስቶ የስከዛሬውን ዘመናዊ ሃሳቦች አያያዛችን ጠለቅ ብለን መፈተሽ፣ መተንተንና መገምገም፣ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚጠቅም መልክ መርሃዊ ፍሬ ነገሮቻቸውን የሚለቁባቸውን ሁኔታዎች መፍጠር ወይም ትርጉማቸው በአግባብ ተለውጦ፣ ተሻሽሎና ተሟልቶ ሕያው የሚሆኑባቸውን ተቋማዊና ተግባራዊ መንገዶች መጥረግ ነው።

እዚህ ላይ የርዕዮታዊ ለውጥ ንቅናቄ የሚነሳበትን የጽንሰሃስቦች ግንዛቤ ባጭሩ ግልጽ ማድረግ ይጠቅማል። ጽንሰሃሳቦች ከተውሰኑ ፎርሙላዊ የወገንተኛ አጠቃቀሞች ውይም የጎሣ ማንነት ፖለቲካ ሕንፀቶች ውጪ በአገርና ዓለም አቀፍ ደርጃዎች እውን ሊሆኑ የሚችሉ እምቅ ትርጉሞች አሏቸው። ይህ ምንነታቸው ነው በተለያዩ፣ አንዳንዴም በተጻረሩ፣ የአገዛዝ ወይም የርዕዮት ጎራዎችና በተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታዎች የሆኑ ያልሆኑ ፍችዎች ይዘው መዘዋወርና ለአማራጭ የፖለቲካ እቅዶች ክፍት መሆን የሚያስችላቸው።

በመጨረሻ፣ በኔ ግምት ለጠ/ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የለውጥ አመራር ሁለት የተዛመዱ መሠረታዊ የግጥሚያ ጥሪዎች (challenges) አሉ። መጀመሪያ በነባሩ የድርግ እና የሕወሓት/ኢሕአዴግ አብዮተኛነት ልምድ ሃሳቦች፣ አገራዊ እሴቶች፣ የመንግሥት ተቋማትና ገቢሮች፣ መገናኛ ባዙሃን፣ እንዲሁም የባህላዊና አካባባዊ ማኅበረሰቦች ማንነቶች የተረጋገጠ አንጻራዊ ነፃነት፣ ሃቀኝነትና ራስ ገዝነት ኖሯቸው የማያውቅ መሆኑን ማሳየት ነው። እነዚህ ሁሉ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ቅጥያዎችና ማያያዣዎች የነበሩ መሆናቸውንና ቦታቸውም ሥራቸውም በአመዛኙ በአገዛዙ መዋቅር ራሱ በቀጥታ የተወሰነ እንደነበረ ለኢትዮጵይ ሕዝብ ማስገንዘብም የመጀመሪያው የግጥሚያ ጥሪ አካል ነው። በደርግና ውያኔ አገዛዞች ምንም ነገር – ምንም ጽንሰሃሳብ፣ ምንም መርህ፣ ምንም ተቋምና ገቢር – የሚመስለውን እንዳልነበር ጠንቅቆ ማወቅ ለዛሬው መሠረታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ንቅናቄ ወሳኝ እውቂያ ነው።

የጠ/ሚንስትር ዐብይ አመራር ይቀበለውም አይቀበለውም ሁለተኛውና ተያያዡ የግጥሚያ ጥሪ ሰፋና ጠለቅ ያለ ሃሳብ ላይ የተመሠረተ ፖሊቲካን በኅብረተሰብ የበላይ ገዢነት ሳይሆን በአዲስ ሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በጥሞና መገንዘብና መቅረጽ፣ እንዲሁም ለዘለቄታው ተቋማዊና ተፈጻሚ ማድረግ ነው። ይህ አማራጭ የፖሊቲካ ሥርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ ቅርብ የአብዮትና ድህረ አብዮት ታሪክ ወደር በሌለው መልክና መጠን የአስተሳሰብ ሃቀኝነት፣ ሥነ ሥርዓት፣ ብስለትና ተጨባጭነት ይጠይቃል።

የዚህ ሥርዓት ግንባታ አካል የሆነ ሌላ ተግዳሮት አለ። ይኸውም የኢትዮጵያ ነገድ ዘለል ኅብረተሰብ አገዛዞች ወይም የሆኑ ያልሆኑ ፓርቲዎች በተወሰነ ርዕዩተ ዓለማዊ ፎርሙላ በድፍኑ ከላይ ቀርጸውና ስይመው የሚጠመዝዟቸው “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” የተያዘ ዘርፍ ሳይሆን ነፃ ዜጎች፣ ሲቪክ ስብስቦችና የክፍለ ሃገራዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች አባላት ያለ ሰርጎ ገብ ወይም ተሽሎክላኪ ፖለቲካ ጥምዘዛ ራስቸውን በራሳቸው በመላ አገራቸው ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉበት ምሕዳር ለመሆን እንዲበቃ ማድረግ ነው። ባጭሩ የግጥሚያው ጥሪ በዘመናዊ ድህረ አብዮት ኢትዮጵይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአምባገነናዊ አገዛዝና ከወገንተኛ ጎሠኝነት ተጽእኖ የተላቀቀ ነፃ ኅብረተሰብ የሚያዳብሩ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መፍጠር ነው።

tesfayedemmellash@gmail.com
___
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,866FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here