spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትምነዉ ጃኪን የበላዉ ጅብ አልጮህ አለ? (ሃራ አብዲ )

ምነዉ ጃኪን የበላዉ ጅብ አልጮህ አለ? (ሃራ አብዲ )

ሃራ አብዲ
ሃምሌ 14 2010 ዓ.ም.

«ልቤ ይኖራል እንጂ እንደተከፋ፤ ፈጽሞ እኔ አልቆርጥም ባንቺ ተስፋ» (ሃራአብዲ) ምን ጃኪ ብቻ! ወንዲ ማክ የት ነዉ? ስዩም ተሾመ እንዴት በኦሮምኛ ችሎታዉ ብቻ ተመዘነ? እረ እንዴት ነዉ ጎበዝ??

ማንን አንስቼ ማንን ልተዉ??

ፈረንጆች the rat on a treadmills የምትል አባባል አለቻቸዉ። እንግዲህ ትሬድሚሉ (ኤክሰርሳይስ መስሪያ ማሽኑ) ላይ የወጣች አይጥ ትንፋሽ እስኪያጥራት ከመሮጥ በቀር ለመዉረድ ብልሃቱ የላትም።ይህ የጊዜን መፍጠንና የሰዎችን ከወቅቱ ሁኔታ ጋርም ሆነ ከግል ህይወት ጥድፊያ ጋር የሚያደርጉትን ግብግብ ለማሳየት የሚጠቀሙባት አባባልነች።
በሀገራችንም ያለዉ የለዉጥ ሁኔታ እንዲሁ catch up ለማድረግ እያቃተን ይመስላል። በአንዱ ሁኔታ ላይ የተዘገበዉን ሳናጣጥም ሌላ ትኩስ መረጃ ይደርሰናል። ስለዚህ ዛሬ እንደ እድር ወጥ የተለያዩ ነገሮችን ባንድ ማእድ ማቅረብ ግድብሎኛል።

ጃኪ ጎሲ

ትግሪኛ ባደባባይ መናገር የፋራና የ ወያኔነት መገለጫ በነበረባቸዉ በእነዚያ የኢትዮጵያ የጭለማ ዘመናት፤ ጥቂት ባለራእዮች ያንጎራጉሩበት ነበር። ከእነዚህ ባለራእይ የሙዚቃ ባለሙያዎች መካከል ጃኪጎሲ አንዱና ከዋነኞቹም መካከል ነዉ።
«ፊያሜታ ፤ ባይኔ እስከ ማይሽ፣ ሰላም ያቆይሽ»
ባለፈዉ ሳምንት እሁድ ከሜሊኒየም አዳራሽ የተላለፈዉን የቀጥታ ስርጭት ስከታተል የተሰማኝ ደስታ ወደር – አልባነዉ ብል አላጋነንኩም። ሙዚቀኞቻችን በቀደመዉ የወጣትነት ስራዎቻቸዉ በትዝታ ወደ ሁዋላ ሲመልሱን (እነ አረጋኸኝ) የቅርብ ጊዜዎቹ ደግሞ ( እነ ሃጫሉ) ለህሊናመገዛት፣ሰዉ የመሆን አኩሪ ገድል መሆኑን ደጋግመዉ ያሰመሩበት ቀን ነበር።
«ሀቲ ኬኛ ቶኮ ማልቱ አዳንኑባሴ »ብሎ አሊ ቢራ ሲያስገመግም,,, የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አይኖች ዉሃማ ሆነዉ ታይተዉኛል። ተሳስቼ ይሆን? ይህ ብቻ ምሳይሆን »ኢሱ» በእዉነት አማርኛና ኦሮምኛ ሙዚቃ እንደናፈቀዉ ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር። ለምን አይናፍቀዉ? የኤርትራ መሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ እኮ ነዉ!!
እነ ንዋይም እንደ ደርግ ጊዜ የእናቶች ኪነት ከመድረክ ላይ የወረዱት በጠቅላይ ሚኒስትራችን የ« ደህናሁኑ» እጅ ማዉለብለብ ተጠርገዉ ነበር። በዚህ አላማቸዉም። ማን ከእንደዚያ ያለ የሰላም፤ የፍቅርና የናፍቆት መድረክ ላይ በቀላሉ መዉረድ ይፈልጋል?

«ናይ ዘላለም እዩ ፍቕርና፤
ሎሚም ካብ ቀደምና»

ሲል በአንቆረቁረዉ ድምጹ ልባችንን የማረከዉ ጃኪ ባለዉለታችን ነዉ። የትግራይ ነጻ አውጭዎች ወሽመጣችንን በቆረጡበትና «ኢትዮጵያ እንዴት እነዚህን እርጉማን ፈጠረች በማለት ቁዋንቁዋዉን ጭምር እንድንጠየፍ በተገደድንበት ጊዜ እንኩዋን ለጃኪጎሲ «ፊያሜታ» ጆሮ ነበረኝ።

መቼም የሀገራችን ነገር እንደጉዋያ ለቃሚ የፊት የፊቱን ነዉና፤ ጃኪን የበላዉ ጅብ ምነዉ አልጮህ አለ አስብሎኛል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ለእርቅ ሲበቁ ጃኪ ጎሲ (የመድረክ ስሙ ወይም ቁልምጫዉ ሊሆን ይችላል) ወፍራም ቡልኮ የሚያሸልም ስራዉ መወደስ መቻል ነበረበት።

የድል አጥቢያ አርበኞች ጥንት እንደሞሉት ሁሉ ፤ዛሬም ሞልተዉ እየፈሰሱ ነዉ። እግረ-መንገዴን ሃጫሉ ላይ አፋቸዉን ለማላቀቅ ትንሽም ያልከበዳቸዉ ስም-አልቦዎችን ነገር ሳላነሳ ማለፍ አልሆነልኝም። ለመሆኑ እነዚህ ሃሳብ እንደገንዘብ የሚቸግራቸዉ simpletons; ሓጫሉ አርቲስታዊና አክትቪስታዊ ተልእኮዉን በብቃት ለመወጣት የነሱን እርዳታ የሚፈልግ ይመስላቸዋል? ያን ጊዜ የኦሮሞ ወጣት አራት ኪሎ ግባ ብሎ የዘፈነዉ እንዴት በናሺናል ቲቪ ይተላለፋል ብሎ ዘርአይ አስገዶም አጥን እንደያዛት በግ የአግድም ሲንቀጠቀጥ፤ በፍርሀት ሲርድ የነበረ ሁሉ ይሆናል አሁን ከየጎሬዉ ወጥቶ ሃጫሉን የሚተቸዉ። የቴዲምነገር~~~ብዙ ተብሎበታልና ልለፈዉ።

ስዩም ተሾመ ስራዉቹና የኦሮምኛዉ መመዘኛ፤ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ!

ለዚህ ለዉጥ መምጣት እስራትና ድብደባን ጨምሮ ብዙ ዋጋየ ከፈሉ አክቲቪስቶችና የሰብአዊ መብት ተሙዋጋቾች እንደ አሮጌ ቁና ወደ ጎን እየተገፉ ከወያኔ ጋር ተለጥፈዉ ህዝባችንን መከራ ሲያበሉ የነበሩ ሰዎች የለዉጡ አስተናባሪ (Ushers) ሆነዉ መታየት ልብ ያጥወለዉላል። ለዚህ ትልቅ ምሳሌ አድርጌ የማቀርበዉ ስዩም ተሾመን ነዉ።
ስዩም ኦሮምኛ በደንብ አትችልም ተብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሊደርጉት በታሰበዉ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንዳልተጋበዘ ያስነበበዉን አይቼ በአግራሞት ተሞልቻለሁ።ጎበዝ እንዴት ነዉ ነገሩ??

ስዩም ትህትና ገዝቶት፣አስር መምህራን ቢጋበዙ እሱ ላይጋበዝ ቢችል ተገቢ እንደሆነ ሃሳቡን በግልጽ አስቀምጦአል። በእኔ እምነት ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አምስት ምሁራን እንኩዋን ቢሰበስቡ ስዩም ተሾመ አንዱ መሆን አለበት። አለቀ።

ስዩም በተደጋጋሚ በወያኔዎች የታሰረዉ፤ የተገረፈዉና የበዛ ስቃይ የተቀበለዉ ከቁዋንቁዋ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አልነበረዉም።ቢሆን ኖሮ ኦሮምኛ በደንብ ባለመቻሉ ለወያኔ ስጋት መሆኑ ይቀንስ ነበር፤ ድብደባና እንግልቱም በዚያዉ መጠን።በመላእክትም ልሳን ሆነ በወፍቁዋንቁዋ ቢናገር የወያኔን የዘር መድልኦ እስከተቃወመ ድረስ ዋጋ ከመክፈል አይድንም ነበር። እንዴት ነዉ ታዲያ፤ ያሁኑ መስፈርት? ለመሆኑ ስብሰባዉ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት በቁቤ ለመጻፍ ነዉ እንዴ?
ያ ሁሉ ወደ አራት ሺህ የሚጠጋ ምሁር ኦሮምኛ አይችል ምን ሊበጀዉ ነዉ??

ይህ መቼም የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ስራ ጥላሸት ለመቀባት የወያኔ አሽከሮች የሚያደርጉት ነገር ነዉ እንጂ ከአብይ ጋር ምንም ንክኪ እንደሌለዉ አምናለሁ። ይህ ለዉጥ ስር እንዲሰድ ከተፈለገ፤ ሙያና ሞያተኛዉ፤ ትግሉና ታጋዩ ይገናኙ።

በ«እንደመር» ሰበብ እባቦቹ እየተደመሩ እንዳይነድፉን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻል, ይህን እያየን አይደለም። በስዩም ላይ የደረሰዉ መገፋት በሌሎችም ላይ በአስፈሪ ሁኔታ እየደረሰ ነዉና በቅርቡ እመለስበታለሁ። ይህ ለብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሞራ ልከማሰብም ያለፈ ነዉ። የመጣዉን ለዉጥ ዋጋ የከፈሉበት ጀግኖች ተጠንቅቀዉ እንዲገፉበት እድልካልተሰጣቸዉ ምድረ እበላ-ባይ ገብቶ ሲፈተፍት ድሉ ባፍጢሙ እንዳይቆም ለመከላከልም ጭምር ነዉ ።

ሥዩሜ!! ጅግንነትህ በእዉቀትና በምክንያታዊነት የተማገረ ስለሆነ ጽና!! ብዙዎች ብእርህንና ደህንነትህን ይፈልጉታል። እናት ኢትዮጵያም አብዝታ ትፈልግሃለች!!

ወደ አርቲስቶቻችን ስመለስ ፤ ጃኪስ ታዲያ፤ስራዎቹን እንዲያቀርብ ፤ፊያሜታን እንዲጫወት ተጋብዞ ነበር? ወንዲማክ «ወይነይልኝ»ን እንዲያንቆረቁር ጥሪ ደርሶታል? (ስለ አማራና ኦሮሞ ግንኙነት ነዉ የተጫወተዉ የሚሉ አሉ። ወንዲ ስለማንም ይጫወት ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሻሻል አስደናቂ አስተዋጽኦ አድርጎአል።

እስቲ የምታዉቁትን አቀብሉን።ቸር ይግጠመን። እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይባርክ።

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here