spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትዶ/ር ዐብይ አሕመድና የሕዳሴው ጉዞ - (ክፍል ሁለት) (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ዶ/ር ዐብይ አሕመድና የሕዳሴው ጉዞ – (ክፍል ሁለት) (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሃምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም (08/03/2018)

ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በርካታ የተሰሩ በጎ ነገሮች መኖራቸው እንደተጠበቁ ሆነው፤ ለሕዝብ ግልጽ ያልሆኑ ፖሊሲዎች ሲተገበሩም ሆነ አሁን ሃገሪቱ እየተዳደረች ያለበትን ሕገ መንግስትም ያልተከተሉ ስራዎች ሲሰሩ እያዩ በዝምታ መታለፋቸው አደገኛ ጅማሮ ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴሩም በተደጋጋሚ እንደነገሩን፤ የሚሰሩት አሁን ያለውን የሃገሪቱን ሕገ መንግሥቱን ተከትለው፤ ሕገ መንግስቱ በሰጣቸው ስልጣን ነው። ይህ ከሆነ፤ ከሕግ ውጭ ሲሰሩ፤ እንዴት ነው ብለን መጠየቅ እና ስህተቶች እንዲሰተካከሉ አቅጣጫ መጠቆም አለብን። ሕገ መንግስት እየተጣሰ ነው ሲባል፤ “ዛሬ ነው እንዴ ሕገ መንግሥት የተጣሰው?” የሚል መልስ መስጠት፤ ጉዞውን አደገኛ እና ሕግ አልባ ያደርገዋል። ያ ሁሉ ዋጋ የተከፈለው፤ ትላንት የተሰራው ስህተት እንዳይደገም ነው። በተደጋጋሚ እንዳስተዋልኩት፤ ዶ/ር አብይ፤ ስለ አንዳንድ የወስዷቸው እርምጃዎች ትክክለኛነት ጥያቄ ሲቀርብላቸው የሚሰጡት የተከላካይነት መልስ፤ “ከዚህ በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር” እንዲህ አልነበር እንዴ ያደረጉት፤ እኔ ስሠራው ለምን ስህተት ይሆናል ዓይነት የሚል ነው። ለምሳሌ በሃምሌ 2010 ለፓርላማው መግለጫ ሲስጡ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አሰብን ለኤርትራ ሲስጡ ሕዝብን አወያይተው ነበር እንዴ ሲሉ ተደምጠዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ስላጠፉ፤ ዶ/ር ዐብይም ያጥፉ ማለት ስህተት ነው። በቅርቡም፤ የኢትዮ ኤርትራን የድንበር መካለል አስመልክቶ ስለኢሮብ ሕዝብ እና ከኤርትራ ጋር ስላለው ድንበር መካለል የተናገሩት፤ ይህንኑ ዓይነት መስመር የተከተለ ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስቴር፤ ባድሜ ተወረረ ዝመቱ ሲሉን ምንም ጥያቄ ሳናነሳ ከነቤተሰባችን ወደ ጦርነቱ ዘምተናል፤ አሁንም እኔ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለምወስደው እርምጃ፤ የኢሮብ ሕዝብን ማወያየት የለብኝም፤ “ይህ የመንደር ፖለቲካ ነው” ዓይነት መልስ መስጠታቸው፤ ለዚህ ፀሃፍ አስገራሚ የሆነ እና ጥያቄም የጫረበት ነው። እኔ እንደሚገባኝ፤ “ያለመንደር ፖለቲካ”፤ ሃገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ አይኖርም። የኢርትራ እና የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ ከድንበር ባሻገር እንዲሆን ሪፖርተር ጋዜጣ እና ቦርከና ባተሙት ጽሁፌ ላይ በሰፊው ሃሳብ አቅርብያለሁ። በድንበር ላይ ለሚኖረው ሕዝብ ግን ይህ ፍላጎት እና ዓላማ እፎይታ አይሰጠውም። ነገ ሕይወቴ ምን ይሆናል፤ ቤቴ ሊፈርስ ነው ወይ፤ መሬቴ፤ ሃብቴ፤ ንብረቴስ ለሚለው መልስ አይሆነውም። ለዚህም ነው ከድንበሩ አካባቢ ከሚኖረው ሕዝብ ጋር በመነጋገር፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ምን እንደሆነ ማስረዳት የሚያስፈልገው።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከኢርትራ ጋር ያለንን ግንኙንተ በተመለከተ፤ አለኝ በሚሉት ሥልጣን የወሰዱትን እርምጃ ትክክለኛነት ቢገልፁም፤ በተለይም፤ የአልጀርሱን ስምምነት በተግባር ከመተርጎም ባለፈ፤ ከኢርትራ ጋር የተደረገውን ስምምነት በምን ሥልጣናቸው በመተግበር ላይ እንዳሉ ለዚህ ፀሃፍ ግልጽ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 ቁጥር 12፤ አለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲያጸድቅ ሥልጣን የሚሰጠው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ፤ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ እንድትጠቀም፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ስምምነት ከማድረጋቸው በስተቀር፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ሲወያይም ሆነ፤ ስምምነቱን ሲያጸድቅ አልተደመጠም። በተደጋጋሚ እንደተገለፀው፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ሙሉ ሥልጣን አላቸው። ምክንያቱም ይህን ስምምነት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የፈረሙት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም “ተወያይቶ” ያፀደቀው ስምምነት ነው። ከዚህ ሌላ ግን፤ በሌሎች የኢኮኖሚ ትሥሥሮች ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይመክርበት እና ሳይወስንበት ወደ ስራ መገባቱ ሕጉን ተከትሏል ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በነገሬ ላይ፤ አቶ መለስ ዜናዊ የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብያለሁ ባሉ ጊዜ፤ ይህ ስምምነት እንዳይተገበር፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለበርካታ ዓለም አቀፍ መንግሥታት አቤቱታ የፃፉትና የፈረሙት፤ ዶክተር የሚል ማዕረግ ያንጠለጠሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ዛሬ የት እንደገቡ አላውቅም። ዛሬ ድምፃቸውን አንሰማም። በወቅቱ አቶ መለስ ስምምነቱን ሲፈርሙ ስሕተት ከነበረና እንዳይተገበር ከሞገትን፤ ዛሬ፤ ዶ/ር ዐብይ ሲተገብሩት ልክ ነው ብሎ ተቀብሎ ድምጽ ማጥፋት እንዴት ልክ ሊሆን ይችላል? ይህንን ነጥብ ለማንሳት የፈለግኩት፤ ሃሳቦችን የምንቃወምውም ሆነ የምንድግፈው ከዓላማ ጽናት ሊሆን እንደሚገባው ለመጠቆም እና ሃገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ወደ ግልም ሆነ ድርጅት ፍቅር ወይም ጥላቻ ተመንዝረው አመለካከታችንን እንዳይጋርዱ በሚል እሳቤ ነው።

ከዚህ ቀደም ሪፖርተር የተሰኘው ጋዜጣ እና የቦርከና ድኅረ ገጽ ባተሙት “ጥንቃቄ የሚያስፈልገው የኤርትራ ጉዳይ” በሚለው ጽሁፌ እንደገለጽኩት፤ የኤርትራ ጉዳይ፤ ለእኔ ግላዊ እና ሃገራዊም ነው። በኢትዮጵያ እና በኢርትራ መካከል የሚኖረው ማንኛውም ግንኙነት ዘላቂ እንዲሆን ነው ምኞቴም። ዘላቂ ሰላም እና ዘላቂ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ከተፈለገ፤ ከኢርትራም ጋር ሆነ፤ ከማንኛውም ሃገር ጋር የሚደረገው ስምምነት ሁሉ ተቋማዊ እና ሕግን የተከተለ መሆን አለበት። ስምምነቶቹ፤ “በሁለት መሪዎች” በጎ ፍላጎት ብቻ ሲሆን፤ እየቆየ የሚፈነዳ ችግር ይኖርባቸዋል። ይህን ከታሪካችን መማር አለብን። ታማኝ የዜና ምንጮች እንደገለፁት፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት፤ በአሜሪካ፤ በሳውዲ ዓረብያ እና፤ በዪናይትድ አረብ ኢምሪት መንግስታት ለረጅም ጊዜ “በጓዳ” ጥረት ሲደረግበት የነበረ ነው። ዶ/ር ዐብይ ወደ መንበር ሥልጣኑም እንደመጡ፤ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሳውዲ ዓረብያ ውስጥ የሚስጥር ስብሰባ ነበራቸው። ለዚህም ነው፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ “እርቅ” ከጀት በፈጠነ ሁኔታ ሊተገበር የቻለው። እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ሃገራዊ ጉዳይ፤ ተድበስብሶ “በመተቃቀፍ እና በመሳሳም” ብቻ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፤ በተለያየ መድረክ ባደረጓቸው በርካታ ስብሰባዎች፤ ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ ያላት ፖሊሲ ምንድነው? የአሰብንስ ወደብ ኢትዮጵያ የምትጠቅምብት ዝርዝር ስምምነቱ ምንድነው? በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እስረኞች እና ምርኮኞች ጉዳይስ ውይይት ተደርጎበታል ወይ ብሎ የጠየቀ የለም። በኤርትራ ምክንያት፤ የኢትዮጵያ እና የኢርትራ ሕዝብ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የሚደረግው ማንኛውም ስምምነት ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት። የውጭ መንግስታት ሚና ምን እንደነበር እና ምን እንደሆነም ሕዝቡ የማወቅ መብት አለው።

የሕዳሴው ጉዞ፤ እርቅ እና “መደመር” በሚሉ ያማሩ የቃላት ሃረጎች ቢታጀብም፤ እርቁም ሆነ መደመሩ እንዴት እንደሚከናወን ምንም ዓይነት ንድፍ ያለ አይመስልም። በአንድ ወቅት አቶ መለስ “ኪራይ ሰብሳቢ” ሲሉ፤ ምን ማለት እንደሆነ ያልተገነዘበው ሁሉ፤ “ኪራይ ሰብሳቢ” የምትለዋን ሃረግ ይጠቀምበት ነበር። “መደመር” ስንል ምን ማለት እንደሆነ ለምን ያህሎቻችን ግልጽ ነው?መደምር ስንል፤ በስብዓዊ መብት ገፈፋ እና ረገጣ መጠየቅ ያለባቸው ሰዎች አይጠየቁም ማለት ነው? የሕዝብ ገንዘብ የዘረፉ ወንጀለኞችስ በምን ሂሳብ ነው የሚደመሩት? የሃገሪቱ ሕገ መንግስት አንቀጽ 28፤ የስብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉ፤ ከሕግ ውጭ የገደሉ፤ ዘር ያጠፉ፤ ዜጎችን የደበደቡ (የቀጠቀጡ)፤ ሰዎችን አፍነው የወሰዱ፤ የየትኛውም የመንግስት አካል ምህረት የማድረግ ሥልጣን እንደሌለውም ይደነግጋል። በእንደዚህ ዓይነት ወንጀል ለተሳተፉ ሰዎች፤ በየትኛው ሕግ ነው ይቅርታ የሚደረገው? ላለፉት 27 ዓመታት ስለ ብሄራዊ እርቅ ሲስበኩ ከነበሩት አንዱ ነኝ። ለእኔ ግን ብሔራዊ እርቅ ማለት፤ የተሳሳቱትም፤ ያጠፉትም፤ ሃላፊነት ሳይወስዱ፤ ሁሉም ተደባብሶና ተሳስሞ፤ “ፍቅር ያሸንፋል” በሚል መፈክር “መደመር” ብሎ መዘመር አይደለም። በሕዝብ ላይ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች፤ መጠየቅ እና፤ በይፋ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ለዚህ ፀሃፍ አስቂኝ፤ ግን አሳዛኝ የሆነው ድራማ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ከሕግ ውጭ፤ በተጭበረበረ እና በተመሳጠረ “ክስ” እንዲሁም ያለ ክስ እና ፍርድ ለዓመታት በገዠው ፓርቲ ታስረው ሲስቃዩ የነበሩ ብርቅዬ ዜጎችን፤ “ይቅርታ አድርገንላቸዋል” በሚል ስላቅ፤ በቅርቡ ያስተላለፈው ውሳኔ ነው። ለዚህም ብዙዎች አጨብጭበዋል። በሕዝብ ላይ ይህ ሁሉ በደል ሲፈፀም፤ ሲያጨበጭብ እና፤ ጣቱን እየቀሰረ ውሳኔ ሲያሳልፈ የነበረው፤ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ የሚገባው የተከበረው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” በምን ሂሳብ ነው ይቅርታ ሰጪ ሊሆን የቻለው? ወንጀል ሳይሰሩ፤ በተለያዩ የመንግስት አካላት፤ በእስር እና በቅጥቀጣ ወንጀል የተፈፀመባቸው ሰዎችስ፤ በምን እሳቤ ነው፤ ወንጀል እንደሰራ ሰው “ይቅርታ የሚጠይቁት?

የሕዳሴው ጉዞ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም፤ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ፤ ፖለቲካዊ ብልጠት የጎደለው አካሄድ፤ ወደ ያልተጠበቀ መንገድ እንዳይወስደን፤ ሁላችንም ከማጨብጨብ ባሻገር፤ ነገሮችን በጥሞና ማየት እና በሃገራችን ጉዳይ ተሳታፊ መሆን ይገባናል። እንደ እኔ አመለካከት፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ፤ ለሃገር መሪነት ሳይሆን፤ መታጨት የነበረባቸው ለጳጳስነት ወይም ፓትርያርክነት ነበር። በጣም ቅን እና ሁሉን ነገር በበጎ የማየት ዝንባሌ እንዳላቸው፤ በዚህች በአጭር ጊዜ ለመመስከር ችለናል። በአንድ እጅ ግን ማጨብጨብ አይቻልም። የዓለማችን ፖለቲካ፤ በመንጠቅ ወይም በመቀበል የታጀበች ነች፤ ሰጥቶ መቀበልን የሚተገብሩ የፖለቲካ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ዶ/ር ዐብይ ስ-ለሰጥቶ መቀበል ሳይሆን፤ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ የምሰማቸው ስለመስጠት ነው። በመስጠት ብቻ የተገነባች ሃገር፤ ወይም በሥልጣን ላይ የቆየ የሃገር መሪ አላውቅም። የመስጠት ጥሩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የመቀበል ሃላፊነትም እንዳለ ደግሞ መዘንጋት የለበትም።

ከበርካታ ስህተቶቹ ጋር፤ የተጀመረው የሕዳሴ ጉዞ ለብዙዎቻችን ተስፋ ሰጥቶናል። ተስፋውን ሰንቀን ስንጓዝ፤ ከፊታችን የተደቀነው አደጋም ያሳስበናል። ብዙዊቻችን እጅ አጣምረን፤ ሁሉንም ነገር ከዶ/ር ዐብይ እና የትግል ጓዳኞቻቸው ብቻ የምንጠብቅ እንመስላለን። እኛም እንሳተፍ፤ ሃሳብ እናመንጭ፤ ሌሎችን በመኮነን ብቻ ጊዜያችንን አናጥፋ፤ ሌሎችን በመኮነነ መጽደቅ አንችልም፤ ለመጽደቅ የራሳችንን የጽድቅ ስራ መስራት አለብን። ምን እናግዝ እንበል፤ በግል፤ በቡድን፤ ወይም የተለያዩ ኮሚቴዎች በማቋቋም፤ በጥናት የተደገፈ አቅጣጫ የሚያሲዝ ንድፈ ሃሳብ እናቅርብ። ተቃዋሚው/ተፎካክሪው ይንቃ፤ ይስራ፤ ለብሔራዊ እርቅ የራሱን መርሃ ግብር ይዞ ይንቀሳቀስ፤ ገዥውን ፓርቲ ለሰላም እና እርቅ ጉባኤ ይጋብዝ። ጥሩ ነገር ሲሰራ እንደግፍ፤ ስህተት ሲሰራ፤ ስህተትን የሚያቃና ሃሳብ እንሰንዝር፤ የሕዳሴው ጉዞ፤ ለመጨረሻ ግብ አቅጣጫ የሚያሲዝ እንጂ በራሱ ግብ አለመሆኑን እንገንዘብ። የዘር ፖለቲካ ከየትኛውም ክፍል ይምጣ፤ የተሸነፈና የከሰረ፤ ሃሳብ መሆኑን በጭብጥ እንሞግት። ትልቁን ስዕል እንመልከት፤ ዶ/ር ዐብይ እንዳሉት፤ “ከቀበሌኛ” አስተሳሰብ እንውጣ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በስራ እንትጋ። ዛሬም ለብሔራዊ እርቅ ድምፃችንን ክፈ አድርገን እናሰማ፤ ያለብሔራዊ እርቅ፤ እውነተኛ “መደመር” ሊኖር አይችልም። ተቀዋሚው/ተፎካካሪ ፓርቲውም ሆነ ገዥው ፓርቲ፤ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን በመገንባት፤ ለቀጣዩ ትውልድ፤ የተሻለ ስልተ ስርዓት ከማስረከብ ይልቅ፤ የሚጠመደው፤ ለሚቀጥለው ምርጫ በመዘጋጀት ከሆነ፤ የመሪዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት ገና አልገባንም ማለት ነው። “የምርጫ ባሕል ሳይሆን” ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓትን እንገንባ። ለግልሰብ ተክለ ሰውነት፤ ወይም ለድርጅት ፍቅር ሳይሆን፤ በዓላማ ጽናት ለሃገር እና ለሕዝብ እንቁም። ያን ስናደርግ በቻ ነው፤ ለቀጣዩ ትውልድ፤ የተሻለች ሃገር፤ የተሻለ ስልተ ሰርዓት ልናስረክብ የምንችለው። ያን ስናደርግ ብቻም ነው፤ እንደ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ያሉ መሪዎች የዛሬው ሕልም እውን ሊሆን የሚችለውና የጀመርነው የሕዳሴ ጉዞ ከግብ የሚደርሰው።

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።

___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here