አገሬ አዲስ
ነሐሴ 5ቀን 2010 ዓ.ም.
አገር የሕዝብ የጋራ ንብረት ነው።በዚህ የጋራ ንብረት ላይ የመወሰን መብቱም ባለቤት የሆነው ሕዝብ ነው።ስለሃገሩ የወደፊት እጣፈንታ ቀያሽና ወሳኝ ያው ባለቤቱ ሕዝቡ ነው።ይህንን ተግባር የሚያከናውንበት መሳሪያዎች አሉት፤ እነሱም ሕግ አውጭ፣ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ(ፓርላማ፣አቃቤ-ሕግና ፍርድ ቤት) የተባሉ መዋቅሮች ናቸው።እነዚህ እርከኖች ደግሞ በውቀትና በፍልስፍና ላይ የተመሰረቱ እንጂ በጎሳ ማንነት ዙሪያ የተቋቋሙ አይደሉም፤መሆንም የለባቸውም።የዚህ አይነቱ የሕዝብ ተሳትፎና የመቆጣጠሪያ እርከን ያላቸው አገሮች ለዴሞክራሲ አሰራር ዋስትና አላቸው።የሚሰፍነው ስርዓትም ዴሞክራሲያዊነቱን በጠንካራ ካስማ ላይ የተከለ ይሆናል።በዚህ ዴሞክራሲያዊ መዋቅር የተገነባ አገርና የሚመሰረተው ስርዓት ወይም መንግሥት ከሕዝብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን በጋራ ተባብረው ይሠራሉ።ግልጽነት ስላለ መተማመን እንጂ ጥርጣሬና ስጋት አይኖርም።ሕዝቡና መንግሥት እንደ ሌባና ፖሊስ ሲተናነቁ አይኖሩም።ሁሉም ለሕግ ተገዢ ስለሚሆን ሰላምና መረጋጋት ይሰፍናል፤ የእድገቱ ጉዞ የተፋጠነ ይሆናል።ሁሉም በአገር ፍቅር ሰንሰለት የተሳሰረ ነው።
በዚህ የሕግ የበላይነትና የሕዝብ ልዑላዊነት በተከበረበት መዋቅር(ስርዓት) ስር በሚንቀሳቀስ አገር ሥልጣኑን የተረከበ ቡድን ወይም ድርጅት(ፓርቲ)እንዳሻው የሚፈነጭበትና ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት ዕድሉ የመነመነ ነው።ከሕጉ ውጭ ልንቀሳቀስ ቢል ወይም አላስፈላጊ ውሳኔ ላሳልፍ፣ካሻኝ ጋር ያሻኝን ስምምነት ልፈራረም ቢል የሚቃወመው ብዙ ነው።ፓርላማው ሰንጎ ይይዘዋል።ጥፋቱ ከተረጋገጠበትም በሕጉ ተገቢውን ቅጣት ያገኛል፤ከስልጣኑ መወገድ ብቻም ሳይሆን ባጠፋው ጥፋት አንጻር ቅጣት ይጣልበታል።
እነዚህ የስርዓት ካስማ የሆኑት መዋቅሮች በሌሉበትና ለስሙ ቢኖሩም በተግባር ባሏሉበት አገር የሕዝቡ የዴሞክራሲ መብትና ልዑላዊነት የተጣሰ ነው። በጉልበትም ሆነ በማጭበርበር ስልጣኑ ላይ የሚወጡ ቡድኖች ወይም አምባ ገነን ግለሰቦች እራሳቸው ሕግ አውጪ፣ሕግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚዎች ይሆናሉ።ሕዝብ አድማጭና ታዛዥ እንጂ ጠያቂ አይሆንም።ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት ከማለት ወይም ከማጨብጨብ ሌላ ለምን?እንዴት?ምን?ብሎ የመጠዬቅ መብቱ የተከለከለ ነው።
ወደ አገራችን ስንመለስ የምናዬው ከዚህ የተለዬ አይደለም፣ለስሙ ሕግ አውጪ፣ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ የተባሉት መዋቅሮች ቢኖሩም አገልግሎታቸው ሥልጣን ላይ ላለው አካል ነው።የተመሰረቱትና የሚንቀሳቀሱትም በራሱ ፍላጎትና ትእዛዝ መሰረት ስለሆነ አገልግሎታቸው ለፈጠራቸው አካል ነው።
ይህንን ባለፉትና አሁንም ባለው ስርዓት ያየነውና በማዬትም ላይ ያለ የማይካድ እውነታ ነው።ሥልጣኑን የያዘው በራሱ ፈቃድና ፍላጎት ያሻውን ሲወስን፣ውል ሲፈራረም እንጂ ለስሙ የተቋቋመው ፓርላማ እንኳን ለመወሰን ቀርቶ ለማወቅ መብት የለውም።ሕዝቡማ የሩቅ ተመልካችና ሰሚ እንጂ ለመጠዬቅም ሆነ ለመቃወም መብት የለውም።ሲጀመርስ የማያውቀውን ነገር እንዴት ሊቃወመው ይችላል?
አንድ ባለስልጣን ብቻውን የሚያደርገው ውልና ስምምነት የዃላ ዃላ ዋጋ እንደሚያስከፍል በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል።ሱልጣን ኢብራሂም የተባለው የደንከሉ ባላባት ለጣሊያኖች ሃሰብን ለመስጠት ውል ባይገባ ኖሮ የጣሊያኖች ወረራ ባልተሳካም ነበር፤የሱ ብቸኛ ውሳኔ በአገራችን ላይ ያደረሰው ስብራትና የተከፈለው ዋጋ በታሪካችን አንዱ ትልቁ ጥቁር ነጥብ ነው።ከዚያም ወዲህ በስልጣን ላይ የነበሩት መሪዎች በግል ውሳኔያቸው ከብዙ አገሮች ጋር ውል ተፈራርመዋል፤ሕዝቡ ግን መዋዋላቸውን እንጂ የውሳኔውን ዝርዝር የማወቅ መብት አልነበረውም።በእርግጠኛነት መመስከር የሚቻለው ግን የነበሩት መሪዎች ያገራቸውን ጥቅም፣ክብርና ነጻነት አሳልፈው የሚሰጡና የሚደራደሩ አልነበሩም።ስለሆኑም ነበር የነጮችና የአረቦች የጠላትነት አድማ የተመታባቸው።
ላለፉት 27 ዓመታት የሰፈነው ስርዓት ያንንኑ የብቸኛ ወሳኝነቱን አጠናክሮ መዝለቁ ብቻም ሳይሆን የአገሪቱን ነጻነት፣አንድነትና ልዑላዊነትም ተዳፍሯል።ለባዕዳን ጥቃት አጋልጧታል።ባለቤት የሌላት አገር አድርጓታል።
ከአራት ወራት በፊት ስልጣኑን የያዙት ዶር አብይ አህመድም ያንኑ ተረክበው እየተንቀሳቀሱ ነው። በዚህ አጭር የስልጣን ዘመናቸው ለጆሮ የሚጥሙና የሚያስደስቱ ዲስኩሮችን ከማሰማት አልፈው አንዳንድ የሚደገፉ እርምጃዎችን ውስደዋል። ከብዙ አገሮች ጋር ውል ተፈራርመዋል።በተለይም ከአረቦች ጋር የውጭ ምንዛሬንና የከባቢን ሰላም፣እድገትንና ልማትን አስታኮ የኢንቨስትመንት ሽፋን ያደረገ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።መስማማቱ ቀና ቢመስልም ይዘቱ ግን ምን እንደሆነ፣በየትኛው ዘርፍ ዙሪያ መሆኑ የተሰጠ ዝርዝር የለም።የውጭ ምንዛሬና የቀጠና ሰላም ከሚለው ባሻገር በአገሪቱ ልዑላዊነት፣በሕዝቡ የወደፊት እጣ ፈንታ፣ስነልቦናና አንድነት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን ሊሆን እንደሚችል የተደረገ ጥናትና መግለጫ አልቀረበም። ስምምነቱ ላይ የሚመለከተው አካል ወይም መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ያደረጉት ጥናት የለም።የውሉም ተካፋይ መሆኑ አይታወቅም።ፓርላማው ተወያይቶ ያጸደቀውም አይደለም።የነጻ ባለሙያዎችና የተቃዋሚ ድርጅቶች አስተያዬትም አልተሰጠበትም።ዶር አብይ እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ወይም ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከዚህ አገር መንግሥት ወይም ምኒስትር ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ደረሱ የሚል መግለጫ አይሰማም።
ዶር አብይ የሚፈራረሙት ውል ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታመንበት እንኳን በአሠራሩ ትልቅ ስህተት ተፈጽሟል።እራሳቸው ብቸኛ ወሳኝ በመሆናቸው ሌላው ከጨዋታው ውጭ ሆኗል። አያድርገውና የተደረገው ውልና ስምምነት ይዞት የሚመጣው ጉዳት ቢኖርና ቢከሰት ሕዝቡ ሊጠየቅበት ይሆን?አይቀርም፤ምክንያቱም ዶር አብይ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆነው እንጂ በግላቸው ያደረጉት ውል ተደርጎ አይወሰድም፤ስለሆነም ከሚመጣው ዕዳ ማምለጥ አይቻልም።
በአገር ስም የሚደረግ ውልና ግንኙነት ነጻነትና ሥልጣን ባለው አካል የሚመረመርና የሚወሰን ፣ለሕዝቡም ዝርዝር ይዘቱና የሚሰጠው ጥቅም እንዲሁም ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት በግልጽ መፈተሽና መቅረብ ይኖርበታል።ያንን የሚያደርገው ነጻ ፓርላማ ቢኖር በዛው ሥር የሚነቀሳቀስ የባለሙያዎች ተቋም፣ማለትም በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣በዓለም አቀፍ ሕግ፣በንግድና ኢንቨስትመንት (international relation, law,business and investment,…)ዘርፍ የሰለጠኑ ኤክስፐርቶችን ያካተተ ነጻ አካል ቢቋቋም ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለማወቅና ለመከላከል ይረዳል።ሕዝቡም ለማወቅ ያለውን መብቱን ያረጋግጣል፣መሪዎቹም እንደፈለጉ የሚጋልቡበትን የሥልጣን ፈረስ ይገራል፤ልካቸውን እንዲያውቁ ያደርጋል።
ባለፉት ዓመታት በተደረጉ የውስጥ ለውስጥ ስምምነቶች አገር ለባዕዳን ዘረፋ ተጋልጣለች።ሕዝብ ዓይን ላወጣ ስቃይና የመብት ጥሰት ተጋልጧል።ወጣቱ በተለይም አነስታይ ኢትዮጵያውያን ለኢሰብአዊ ድርጊትና ለባርነት ተጋልጠዋል፤ተደፍረዋል።ሕዝብ እንዳይስማማ የተንኮል ድር ተደርቶበታል።በንግድና ኢንቨስትመንት ስም የገቡ ባዕዳን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሰርገው የሚገቡበት ሕጋዊ በር ሆኖላቸዋል።
የስምምነቱ ሥራ ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአገር በቀል የተገንጣይ ቡድኖችም ጋር ተከናውኗል። ላለፉት አስርታት ዓመታት ኢትዮጵያን ለመገንጠል ሲጥሩና የአገሪቱን አንድነትነትና የሕዝቡን ሰላማዊ ኑሮ ሲያምሱ፣የብዙንጹህ ዜጎችን ህይወት ያጠፉ፣ያቆሰሉ፣ያፈናቀሉትን እንደ ኦነግና የመሳሰሉትን ጎሰኛ ድርጅቶች የጨመረ ነው።ከነዚህ ጋር የተደረገው ውል ይዘቱ ባይታወቅም አገር ውስጥ ገብተው የተነሱበትን ዓላማ በነጻነት ማራመድ እንደሚችሉ ባንዲራቸውን በአደባባይ ሲያውለበልቡ የታዬው ድፍረት ያረጋግጣል።እነዚህ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ከዓላማቸው መለያዬታቸውን፣ኢትዮጵያዊነታቸውንና የኢትዮጵያን አንድነት መቀበላቸውን ይፋ ሳያደርጉ እንዲሁም ተሳስተው ያሳሳቱትን ህብረተሰብና ለፈጸሙት ጥፋት ይቅርታ ሳይጠይቁ፣አሁንም አቋማቸውን በድንጋይ ካርታ ላይ እየቀረጹ ያሻቸውን ሲያደርጉ እያዩ በመደመር አባዜ ለአጥፊ ድርጅታቸው እውቅና መስጠትና በነጻ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ የአንድን አገር አንድነትና ልዑላዊነት አስጠብቃለሁ ከሚል መንግሥት ወይም መሪ የሚጠበቅ አይደለም።የተደረገው ስምምነት ለሕዝቡ በግልጽ መቅረብና ሕዝቡ ውሳኔ እንዲሰጥበት ያስፈልጋል። ነጻ አውጭ ነኝ የሚል ቡድን ነጻ መውጣት አለብኝ በሚለው አገር ውስጥ የፈለገውን እንዲያደርግ የሚፈቅድ ሕግ እንዳለም ቢታወቅ መልካም ነው።ከሌለ ግን የተደረገው ውል ሕገወጥ ነው።የአገርን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነትና ሰላም ለማረጋገጥ ያልቻለ ሕግም ሕግ ነው አይባልም።
ከዚህ ሁሉ ማጥ ለመውጣት በአገራችን ጉዳይ ላይና የለት ተለት ጉዞ የማወቅና የመወሰን መብታችን ይከበር!ያንን የሚያረጋግጥ ነጻ አካል ይቋቋም! መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ መሆኑ ይቁም!ሕዝቡም ለማወቅ ያለውን መብት ከመጠየቅ አይቦዝን!በሚሰማው መልካም ቃላት እያጨበጨበ ገደል ለመግባት አይራኮት! ምሁራንም የነገውን ያገሪቱን እጣ ፈንታ ለማሳዬት ድፍረቱ ይኑራቸው!ተሳስተው አያሳስቱ!
አገሬ አዲስ
agereaddis1974@gmail.com
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።