spot_img
Saturday, April 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትሌ/ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ምን እያሉ ነው? (በመስከረም አበራ)

ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ምን እያሉ ነው? (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
ነሃሴ 19 ፤ 2010 ዓ.ም.

የህወሃት ነባር ታጋይ የሆኑት ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ከህወሃት ተለየሁ ካሉ በኋላም መለስ ቀለስ እያሉ ኢቲቪን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡ ህወሃት አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት ዘመን ሁሉ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሃሳብ ልዩነት ተለይተው ከወጡ በኋላ የጦር አማካሪ መሆን፣እየነገዱ መኖር፣ደርሶ የዩኒቨርሲቲ መምህር መሆን፣በሚዲያ ብቅ እያሉ አስተያየት መስጠት የሚቻለው ህወሃት የሆኑ እንደሆን ነው፡፡

ህወሃት ያልሆኑቱ የኢህአዴግ የቀድሞ ባለስልጣናት ከቀናቸው እንደ እነ ኤርሚያስ ለገሰ፣ጁነዲን ሳዶ፣ኡሞድ ኦቦንግ ሃገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡እንደ ታምራት ላይኔ ያሉት ደግሞ ሁለት ዲጅት ቁጥር አመት እስር ቤት እንዲያሳልፉ ይሆናል፣ ሌ/ጄ አሳምነው ፅጌን፣ጄ/ል ተፈራ ማሞን ያገኘ ያገኛቸዋል፡፡ህወሃት ሆነው እስር ቤት የገቡት ስየ አብርሃ እና ወልደስላሴ የተባሉ ሰዎች እስራቸው የሌሎቹን የኢህዴግ አባላት ታሳሪዎች ያህል የልረዘመ ካለመሆኑም ባሻገር ከእስር ሲወጡ የገጠማቸው እድል እንደ ሌሎቹ ጡረታ ተከልክሎ፣ከመኖሪያቤት ተፈናቅሎ በመዋጮ የመኖር እጣ አይደለም፡፡ ትክክለኛው ለህወሃቶቹ የተደረገው ነው፡፡አንድ ወቅት በመንግስተዊ አስተዳደር መሰላ ውስጥ ሆኖ ሲያገለግል የኖረ ሰው በሃሳብ ተለየ ተብሎ ልጆቹን የሚያበላው እህል ውሃ፣ ጎኑን የሚያሳርፍበት ቤት እስከሚያጣ ድረስ መበቀል መንግስትነትን አይመጥንም፡፡

በጎ ባልሆነው ህወሃት ዘመን ሳይቀር በጎ የሆነላቸው ጄ/ል ፃድቃን በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ የሚሰጧቸውን አስተያየቶች እከታተላለሁ፡፡ብዙ ጊዜ በሚሰጧቸው ሃሳቦች ላይ ልዩነቶች አሉኝ፡፡በሃሳቦቻቸው ውስጥ የህይወት ልምዳቸውን የሚመጥን ሚዛናዊነት አጣለሁ፡፡ ሚዛናዊ ለመምሰል የሚወረውሯቸው አንዳንድ ሃሳቦች ቢኖሩም አፍታም ሳይቆዩ ወደ ህወሃት ዘመም ዘመም ሲሉ ይገጥመኛል፡፡የትግራይን ህዝብ ከሰው የተለየ ፍላጎት ያለው፣ከህግ በላይ የመሆን መብት የተሰጠው፣የተለየ እንክብካቤ የሚገባው ልዩ ፍጡር አድርገው የያቀርቡት ነገር አይዋጥልኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ 15/12/2010 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣው ቃለ ምልልሳቸው የተናገሩት ይህንኑ ነው፡፡

በቃለ ምልልሱ ላይ እርስበርስ የሚጋጩ ብዙ ሃሳቦችን አስተውያለሁ፡፡ይህ የሆነው ፃድቃን በእውነት በሚያምኑት እና መስለው መታየት በሚፈልጉት ነገር መሃል ባለ መጋጨት ነው፡፡ አስተውሎ ለተከታተለው ግን ፃድቃንም ሆኑ ባልንጀራቸው ጄ/ል አበበ ተክለሃይማኖት የህወሃትን የበላይነት አይጠሉትም፡፡የትግራይን ህዝብ የተለየ ህዝብ አድርጎ ከማየቱን ዘረኝነት ወለድ እበልጣለሁ ባይነት የተዋጁ ሰዎችም አይደሉም፡፡ ይህን ያስባለኝ ምክንያቴ በብዙ ቦታዎች ካደረጓቸው ቃለምልልሶች፣ ከፃፏቸው ፅሁፎች የታዘብኩ ቢሆንም ለዛሬ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከተናገሩት ብቻ እያነሳሁ ላስረዳ፡፡

አሁን ለመጣው ለውጥ መፅናት መንግስት በሰላማዊ ተፎካካሪዎች እና ህዝብን በሚያናውጡ ታጣቂዎች መሃል ልዩነት አስምሮ በበጥባጮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያስቀመጡትን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ያለውን ስጋት ሲያስቀምጡ “….የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ይገደላሉ…..” ያሉት ነገር ግን በተለይ ለአማራው ህዝብ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ለሌ/ጄ/ል ፃድቃንም አዲስ ነገር አይመስለኝም፡፡

ወላድ፣እርጉዝ፣ህፃን፣አዋቂ ሳይል ሰባ ምናምን ሽህ ህዝብ አማራነቱ ብቻ ጥፋት ሆኖ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሽፈራው ሽጉጤ በተባለ ባለስልጣን ፊርማ ከጉራፈርዳ ሲባረሩ ፃድቃን ያልሰሙት ጉዳይ አይደለም፡፡የፃድቃን የትግል ጓድ አቶ መለስ ስለዚሁ ጉዳይ ፓርላማ ቀርበው ሲጠየቁ “ደግ አደረግን” አይነት መለስ ሲሰጡ የህዝብ በማንነቱ ብቻ መፈናቀል ስጋት ሆኖባቸው ፃድቃንም ወደ አዲስ አድማስም ሆነ ወደ ማንኛውም ሚዲያ ቀርበው ዛሬ የሚናገሩትን አልተናገሩም፡፡ በዚሁ መከረኛ ህዝብ ላይ በበደኖ እና በአርባ ጉጉ የሆነው ሲሆን ፃድቃን አድራጊ ፈጠሪ የመንግስት ባለስልጣን ነበሩ፤ እኔ በወቅቱ ሚዲያ መከታተል የምችል ሰው ባልሆንም ነገሩን ሲያወግዙ ሰማሁ የሚል ገጥኝ አያውቅም፡፡

በአንፃሩ አብይ በሚመሩት መንግስት ውስጥ የሚደረገውን ማንኛውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያወግዛሉ፡፡የድርጊቱን ፈፃሚዎች ያወግዛሉ፡ይህ ነገር ሲደረግ ዝም ብለው ያዩ የመንግስት አካላትንም ራሳቸውን ከስልጣን እንዲያገሉ እያደረጉ ነው፡፡ የጠፋው የሰው ነፍስ የሚያሳዝን ቢሆንም አብይ ለነገሩ እልባት ለመስጠት ያላቸው ዝንሌ እና ቁርጠኝነት ደግሞ የነገሩ ማብቂያ እንደ ደረሰ ተስፋ የሚያጭር እንጅ ፃድቃን ዛሬ የተጀመረ አድርገው እንደሚያወሩት “እግዚኦ” የሚያስብል ነገር አይመስለኝም፡፡

ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ነገሩን አተኩረው እንዲያዩት፣በሚዲያም መጥተው አፅኖት እንዲሰጡት ያደረጋቸውም ምናልባት ህወሃት እሳቸውም አባል በነበሩበት ወቅት ማኒፌስቶ ፅፎ ጠላቴ ነው ላለው የአማራ ህዝብ የደገሰው የማፈናቀል፣የማሳደድ፣መገደል ክፉ ድግስ ዛሬ ህወሃት ጠመንጃውን ታቅፎ ከኖረበት መንበሩ ሲጠፋ “ህዝቤ” ለሚለው የትግራይ ህዝብም የተረፈ ስለመሰላቸው ይሆናል፡፡ለዚህ ማስረጃው ፃድቃን ስጋታቸውን ሲያስረግጡ ጣና በለስ ላይ ስለሞቱ ሁለት ሰዎች (እነዚህ ሰዎች ትግሬዎች ናቸው የሚል ወሬ ሲናፈስ ሰንብቷል) ማንሳታቸው፣በተደጋጋሚ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሚያሳስባቸው መናገራቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን ማዕከል አድርጎ መሞት የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የሰው በማንነቱ መሞት የሚያሳስበው፣በሰው ሁሉ እኩልነት የሚያምን ሰው እሪ የሚለው ድርጊቱ የተጀመረ እለት እንጅ ሄዶ ሄዶ የእሱን ሰፈር ሰዎች ሲያሰጋ መሆን የለበትም፡፡ ጣና በለስ ላይ ሁለት ትግሬዎች ሞቱ ተብሎ ሞት ብርቅ በሆነበት ሃገር የሞቱ ያህል ብዙ ሲባል ሰንብቷል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ነገር አለ፡፡አንደኛ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ምንም አይነት ሰራተኞች እንዳልሞቱበት ለዋዜማ ሬዲዩ ተናግሯል፡፡ሁለተኛ ሰዎቹ ሞቱ በሚባልበት ጊዜ በትግሬነታቸው ብቻ እንደሞቱ ፃድቃንም ሆነ ሌሎቹ አራጋቢ የትግሬ አክቲቪስቶች መረጃቸውን ሲያቀርቡ አልታየም፡፡

በጣም የሚገርመው ፃድቃን በዚሁ በማንነት ምክንያት የመሞትን እና ሌሎች በሃገሪቱ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግርግሮችን በተመለከተ የዶ/ር አብይን መንግስት ሊወቅሱ መነሳታቸው ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ ፃድቃን “በአሁኑ ወቅት ህዝብ ብሶቱን እየገለፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጉዳቱን የሚያመጣው የብሶት አገላለፁ ነው፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ ደግሞ ሁኔታውን ተረድቶ ብሶቱን ከማባባስና ሂደቱን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ከመግፋት ይልቅ ሁኔታውን ማርገብ ይገባው ነበር፡፡….ቀደም ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተሰርቶ ነበር፡፡ የበደሉ፣ የብሶቱ ሁሉ ምንጭ፣ እሱ ነው ተብሎ፣ ውስጥ ለውስጥ በርካታ የፕሮፓጋንዳ ስራ ተሰርቷል። በአንፃሩ፤ ይሄን ፕሮፓጋንዳ የመመከት ስራ አልተሰራም፡፡ ቀደም ሲል የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣንን ይቆጣጠራል ተብሎ የነበረው ኃይል ከቦታው ሲወጣ፣ ለዘመናት የነበሩ ጥላቻዎች ፊት ለፊት እየወጡ ነው ያሉት። ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የጥላቻ ፖለቲካ ደግሞ ለወደፊት በሃገራችን ውስጥ ልንፈጥር የምናስበውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የሚበርዝ ነው፡፡ አንደኛውን ወገን ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ጠባሳም ጥለው የሚያልፉ ናቸው፡፡.” (የአፅኖት መስመር የእኔ)፡፡

በፃድቃን አስተሳሰብ የዶ/ር አብይ መንግስት የህዝብን ብሶት እያባባሰ እና ሁኔታውን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እየመራ ነው፡፡አድማጭ እስኪሰለቻቸው ድረስ በየደረሱበት ሁሉ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሃትን ለዩ” እያሉ የሚወተውቱት ጠ/ሚ/ር አብይ የትግራይ ህዝብ ራሱብሎት የማያውቀውን “የትግራይ ህዝብ በህወሃት እንደ ሁላችሁም የተበደለ ነው፣እኔን ከወደዳችሁኝ በዚህ ህዝብ ላይ አንዳች ክፉ እንዳታስቡ” እስከ ማለት የደረሱ ሰው ናቸው፡፡

ይህ ሰው በጠ/ሚነት የሚመሩት ማዕከላዊ መንግስት የህዝብ ብሶት እያባባሰ ነው ባይ ናቸው ፃድቃን ደግሞ፡፡ ሌላው ሌላው ይቅርና አብይን/መንግስታቸውን እንዲህ ብሎ ለመውቀስ ፃድቃን ማኒፌስቶ ፅፎ በአንድ ህዝብ ላይ የሞት አዋጅ ያወጀው ህወሃት አባል ያልሆኑ፣ ለዚሁ ያልሰሩ ሰው መሆን ነበረባቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት በየደረሱበት ስራየ ብሎ “የትግራይን ህዝብ እባካችሁ አትጥሉት፣ ምስኪን ደሃ ህዝብ ነው፣ ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ አይደለም” እያሉ በሃገር ውስጥ ሆነ በውጭ መድረክ ፣በአደባባይ ሰልፍ ሆነ በቤት ውስጥ ውይይት ሁሉ መወትወት ፃድቃን “በትግራይ ህዝብ ላይ ተነጣጥሮ ተሰራ” የሚሉትን ፕሮፖጋንዳ የመመከት ስራ አይደለም፡፡ዶ/ር አብይንም ሆነ መንግስታቸውን በዚህ መውቀስ አንድም ትልቅ ፍርደ ገምድልነት፤ሁለትም “ዘር ማንዘሬን ሰብስባችሁ በአንቀልባ እዘሉልኝ” አይነት ነገር ነው፡፡

በበኩሌ አንድም ሁለትም ትግሬ ‘እንዲህ በተባለ ሃገር ሞተ’ የሚለው ነገር በማስረጃ ተረጋግጦ ቢያንስ ሞቱ የተባሉት ሰዎች ፎቶ በማህበራዊ ድህረገፅ ሲቀርብ፣ ዘመዳችን ሞተብን የሚሉ ሰዎች በገለልተኛ ሚዲያ ቀርበው ስለ ሁኔታው ሲያወሩ ሰምቼ አላውቅም፡፡በአንፃሩ ህወሃት በማንነታቸው ሲያስር ሲገድል ሲያፈናቅላቸው የነበሩ ሰዎች በየሚዲያው ሲቀርቡ ከራሳቸው አንደበት ብሶታቸውን እንሰማለን፡፡ የትግሬዎቹ ተጎጅዎች ነገር እንዲህ ጥርት ባለ መረጃ ቢቀርብ እኛም ነገሩን የምናወግዘው፣ሃዘኑም የሚሰማን ሰዎች ነን፡፡

ለትግሬ ለማዘን የግድ ትግሬ መሆን አያስፈልግም፡፡ነገር ግን ባልተረጋገጠ ወሬ፣ ሞቱ የተባሉ ሰዎች ይሰሩበት ነበር የተባለው መስሪያቤት ለሚዲያ “የሞተብኝ ሰው የለም” እያለ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ፣ የሞተው ሰው ስም ማን ይባላል? ቢባል እንኳን መጥራት በማይቻልበት ነገር ፃድቃንን የሚያክል የእድሜ ዘመን ፖለቲከኛ የትግራይ ህዝብ ሞት ታወጀበት ብሎ ማውራት በማንነቱ ሲሞት በኖረው ህዝብላይ መቀለድ ነው፡፡

እንደማንኛውም የትግሬ ፖለቲከኛ ፃድቃን የመሃል ሃገር ሰው ትግሬ ወገኖቹን ለማጥፋት ዘመቻ እንደ ጀመረ አፋቸውን ሞልተው ያወራሉ፡፡ይሄ መዓት መጥራት በትግሬ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለመደ፣ይበልጥ የተበደሉ አስመስሎ አስቀድሞ በመጮህ የህወሃትን በደል ለመሸፈን የሚሞከርበት አስቀያሚ አካሄድ ነው፡፡ በተረፈ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በሚያወሩት መጠን በትግራይ ወንድሞቹ ላይ ሴራ አሲሮ አንዳች ክፉ ነገር ለማድረግ የሚያስብ ሆኖ አይደለም፡፡

ፃድቃን ግን ያለምንም የሃላፊነት ስሜት እንዲህ ይላሉ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በመሃል ሀገር የሚደረገው ፀረ-ትግራይ እንቅስቃሴ፣ በነበረው ይቀጥል የሚሉትን ኃይሎች የሚያጠናክርና ድጋፍ የሚያስገኝላቸው ነው የሚሆነው፤ ግን በግልፅ በህወሓት ውስጥ ሁለት ኃይሎች ፍትጊያ እያደረጉ ነው……በኋላ ግን በጅምላ የሚፈርጀውና ትግራይ ላይ ያነጣጠረው እንቅስቃሴ ሲመጣ፣ ህዝቡ ለውጡን በስጋትና በጥርጣሬ ለማየት ተገድዷል፡፡…….በየሄድንበት እየተሸማቀቅን ልንኖር ነው ወይ? በሀገራችን ተዘዋውረን ሃብት አፍርተን፣ እንደ ማንም ሰው መብታችን ተጠብቆ በስርአት መኖር ልንከለከል ነው ወይ? የሚል ስጋት አለው፡፡ ለዚህ ስጋት ደግሞ ዋናው ምክንያት በየአካባቢው የትግራይ ህዝብ ዒላማ እየተደረገ፣ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የመንጋ ፖለቲካ ነው።” መሃል ሃገር የት ቦታ የተጀመረ፣ ምን በሚባል ስም ስለሚጠራ፣በነማን ስለሚመራ ፀረ-ትግራይ እንደቅስቃሴ እንደሆነ የሚያወሩት አልገባኝም፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት ሰለባ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ስንት እንደሆኑ፣የት ቦታ ምን እንደደረሰባቸው በተጨባጭ ያስረዱን ይሆን? ይህ ጥያቄ በቃለ ምልልሱ ወቅት ቢነሳ መልካም ነበር፡፡

እውነት እንዲህ ያለ በመሃል ሃገር ሰዎች የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ ለምን ወደ ህግ አልወሰዱትም? ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? አሁን በተጨባጭ በደልን አቅርቦ ተበደልኩ ማለት የሚቻልበት ዘመን ነው፡፡ መለስ እና ፃድቃን ይመሩት እንደነበረበት ዘመን ሰው በማንነቱ ምክንያት በገደል ተወርውሮ፣ ሆዱ በጦር ተቀዶ፣ወለል በሌለው ጥልቅ ውስጥ ከነነፍሱ ተጥሎ ዝም የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡ በተጨባጭ በደል ካለ ማስረጃ ይዞ መቅረብ ነው፡፡የማይጨበጥ ነገር እያነሱ ማውራት ግን ዘር ማንዘሬ ለምን ከስልጣን ሰገነት ጠፋ የምትል አደባባይ የማትወጣ ምክንያት የምትገፋው ማላዘን ነው የሚሆነው፡፡

በህወሃት መንደር የደረሰ ሰው መቼም እፍረት የለውምና ፃድቃን ወደ አንድ ህዝብ ላይ ያተኮረ ጥላቻ ለወደፊቱ ሃገራዊ አንድነት ችግር እንዳለው ኮራ ብለው ይናገራሉ፡፡በመጀመሪያ ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የሚሉት ጥላቻ የትኛው ነው? ይሄኔ እኔም በዚህ ፅሁፍ እሳቸው የተናገሩትን በመሞገቴ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንደምሰብክ እያሰቡ ይሆናል፤በዚህ የሚስማማ የወንዝ ልጅም አይጠፋም፡፡

“የትግራይ ህዝብ እውነት ህወሃት እንደ በደለው ካሰበ ለምን ተቃውሞውን አይገልፅም፣ለምን በስሙ ሲነገድ ዝም ይላል፣ ለምን እኛን ወገኖቹን አግዞን ሁላችንም ከህወሃት ግፈኛ አገዛዝ ነፃ እንድንወጣ አይሆንም?” ማለት በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ፕሮፖጋንዳ ከሆነ ማኒፌስቶ ፅፎ አንድን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሃያ ሰባት አመት ሲያስገድሉ መኖር ምን ሊባል ነው? ወይስ የትግሬ ነፍስ ልዩ፤ ሞቱም እጥፍ ነው? የትግራይን ህዝብ አትንኩት እያሉ በየደረሱበት በሚማልዱት አብይ ዘመን ቀርቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ያለ አንዳች እፍረት በአንድ ህዝብ ላይ ሞት ሲያውጅ፣ገድሎ ሲያስገድል፣ሰድቦ ሲያሰድብ በነበረው መለስ ዜናዊ ዘመንም ተኑሯል፡፡

ዛሬ ደርሰው የሰብአዊነት ዘበኛ ሊሆኑ የሚቃጣቸው ፃድቃንም ጠመንጃቸውን አንግበው ይህንኑ የሞት አዋጅ ሲያስፈፅሙ የኖሩ ሰው መሆናቸውን ሌላው ቢረሳ የውሻ ሞት ሲሞት ከኖረው የአማራ ህዝብ የወጣን እኛ አንረሳውም! ጅብ እንኳን ቁርበት አንጥፉልኝ የሚለው በማያውቁት ሃገር ሄዶ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በሚታወቅበት ሃገር ቁጭ ብሎ ደርሶ ሩህሩህ፣ብድግ ብሎ የሰብዓዊነት ዘብ ሲሆን የሚስገምተው ራሱን ነው፡፡

አንድን ህዝብ ነጥሎ ማጥቃት ተጎጅውን ህዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ያሉት ፃድቃን ይህ ዛሬ ለምን እንደገባቸው ግልፅ ቢሆንም ሃሳቡ እውነት ነው፡፡በማንነቱ ብቻ እንደውሻ በየሜዳው ሲገድሉት፣በየእስርቤቱ ሰውነቱን ሲተለትሉት፣አእምሮውን በርካሽ አንደበታቸው ሲያደሙት የኖረው አማራ የሚወደውን ኢትዮጵያዊነቱን ድርድር ውስጥ አሰገብቶ በማያውቀው የጎጥ ከረጢት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ፃድቃን ጭምር ታጥቀው የሰሩበት ዘር ተኮር ጥቃት ተስፋ አስቆርጦት ነው፡፡ በዘር ማንነት ምክንያት የመገለል፣ከሰው ተለይቶ የመክፋፋት፣በሃገር ዳርቻ የመሳደድ ጠባሳውም በሁላችንም አእምሮ ውስጥ አለ፡፡አሁን በወንበሩ ላይ ያሉት መለስ ሳይሆኑ አብይ መሆናቸው ነው ተስፋን የሚያሰንቀው መልካሙ ዜና!
ሌ/ጄ ፃድቃን ስለ ትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ስሜት የተናገሩት ካሉት ነገር ሁሉ ይበልጥ ያደናገረኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፃድቃን ስንቱን ትግሬ አናግረው ምን ያለ ጥናት አድርገው እንዲህ የአንድ ክልልን ሰው ሁሉ ስሜት ማውራት እንደቻሉ ጥያቄ ነው፡፡ሲቀጥል ስብሰባ ለማድረግ ስሄድ ካየሁት ትዝብቴ ተነስቼ የተገነዘብኩት እያሉ የሚያወሩት ነገር እውነት የትግራይን ህዝብ ስሜት የሚወክል ከሆነ አሳሳቢ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ቁጣው ነዷል የሚሉት ፃድቃን የቁጣውን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ “ቁጣው ምንድን ነው? ከተባለ፣ መሪዎች አጥፍተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከትግራይ የወጡ መሪዎችን ጥፋት መነሻ በማድረግ፣ የህዝቡን መስዋዕትነት ማራከስ፣ እንደ እላፊ ተጠቃሚ መቆጠር ህዝቡ ውስጥ ቁጣ እየፈጠረ ነው፡፡ የዲሞክራሲ እጦትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል በትግራይ የባሰ ሆኖ ሳለ፣ እላፊ የስርአቱ ተጠቃሚ ተደርገን በጅምላ መፈረጃችንና የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ መሆናችን ተገቢ አይደለም ከሚል የመነጨ ቁጣ ህዝቡ ውስጥ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ለውለታችን ምላሽ ይሄ ነው ወይ የሚል ቁጣ አለ፡፡”

ይህ አባባል እንደተባለው የትግራይ ህዝብ ስሜት ከሆነ የሚያስነሳው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡ ከትግራይ የወጡ ሰዎች ባጠፉት ጥፋት የህዝብን መስዕዋትነት ማራከስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ማን ነው መስዕዋትነታቸውን ያራከሰው? የትግራይን ህዝብ መስዕዋትነት ማክበር ማለት እንደ አቶ ኃ/ማርያም ሶስት ገበያ ህዝብ አስከትሎ፣ኩሽሽ አንገት ላይ ጠምጥሞ ደደቢት በረሃ ወርዶ የጥንቱን የህወሃት የዋሻ ቢሮ መሳለም ነው? የተፈለገው ይህ ከሆነ አብይ አሁን ያሉበት ሃገራዊ ፈተና ይሄን ለማድረግ ጊዜ የሚሰጣቸው አይደለም፡፡በተቀረ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ መቀሌ በሄዱበት ወቅት የሰማዕታት ሃውልት በተባለው ስፍራ ተገኝተው የሚደረገውን አድርገው ነው የተመለሱት፡፡

ከዚህ በላይ ምን መደረግ ነበረበት? እውነት እንነጋገር ከተባለ ልጅ ያልሞተበት ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የትግራይ ህዝብስ ለሞቱት ልጆቹ ሃውልት አቁሞ የመጣው ሁሉ ለቅሶ እደረሰ ነው፡፡ እነዚህ የትግራይ ሰማዕታት የገደሏቸው የሌላው ኢትዮጵያዊ ልጆች ግን መታሰቢያ እንኳን የቆመላቸው አይደሉም፡፡ የሞቱለት አላማ ቢመረመር ደግሞ የማናቸውም ሞት ለኢትዮጵያ የተሻለ ቀን አላመጣም፡፡ስንሞትም ስንቆምም እንበልጣለን ካልተባለ በቀር!

የዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጦቱ በትግራይ ይብሳል ለሚለው የባሰው ሰው ተነስቶ ታግሎ ቀንበሩን ያሽቀነጥራል፡፡የትግራይ ህዝብ ደግሞ ለዚህ የታወቀ ነው፡፡ደርግን ለመታገል አንድ አመት አልጠበቀም፡፡ደርግ ተስተካክሎ ወንበሩ ላይ ሳይቀመጥ ነው ህወሃት ወደ ጫካ የገባው፣የትግራይ ህዝብም ትግሉን የተቀላቀለው፡፡አሁን ህወሃት በደለኛ ነው ከተባለም ተመሳሳዩን ለማድረግ አፈናው ከለከለ የሚለው ለኔ በግሌ አይዋጥልኝም፡፡ ኦሮሞ የመታገያው ሜዳ እነሆ ተብሎ ተሰጥቶት አይደለም “ሆ!” ብሎ ወጥቶ የሞተው ሞቶ የተረፈው የተሻለ ስርዓት ለማየት የበቃው፡፡ አማራ የልጁ ደም ጣናን ሲያቀላ እያየ ነው ሲታገል የነበረው፣ኮንሶው፣ጉራጌው፣አፋሩ ወዘተ መንግስት እየደጎመው አይደለም በቻለው ሁሉ ሲታገል የነበረው፡፡

ሰው ተበድያለሁ ብሎ ያሰበውን ያህል ይታገላል፡፡እውነቱ ያ ነው! መበደል ብቻውን ቁምነገር አይደለም፤ለትግል እኩል አስፈላጊው ነገር ተበዳዩ በደልን የመቁጠር ጭካኔ ላይ ደርሷል ወይ የሚለው ነው፡፡ ህወሃት የትግይራን ህዝብ እንደሚበድል ይታወቃል፡፡ ጥያቄው የትግራይ ህዝብ የደርግን በደል ይቆጥር በነበረበት መንገድ የህወሃትን በደል ይቆጥራል ወይ? የሚለው ነው፡፡ይህን በተመለከተ ፃድቃን ራሳቸው በዚሁ ቃለመጠይቃቸው”የትግራይ ህዝብ ከፈለገ ህወሓትን ያጎለብታል፤ ካስፈለገው ደግሞ ይገድለዋል” ሲሉ ጨርሰውታል፡፡
የትግራይ ህዝብ ለሌላው ህዝብ ውለታ ውያለሁ፤የውለታየ ምላሽስ ይህ ነው ወይ እያለ ያዝናል ይቆጣል የተባለው ነገር ግራ አጋቢ ነው፡፡ውለታ የተባለው እነዚሁ ዘወትር የሚነሱት ስልሳ ምናምን የትግራይ ሰዎች ህወሃትን ወግነው ደርግን ሲታገሉ መሞታቸው መሰለኝ፡፡ ህወሃት ትግራይን እገነጥላለሁ እያለ በነበረበት ዘመን ትግራይን ለመገንጠል የሞቱት ሰዎች ውለታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሆነበት መንገድ አልገባኝም፡፡ህወሃት ብድግ ብሎ “ትግራይን መገንጠሉን ትቼዋለሁ” ሲል ደግሞ “ታዲያ ለምን እንዋጋለን?” እስከማለት ተደርሶ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፤ አቶ መለስም በዚህ ጉዳይ ተቸግረው እንደሆነ በራሳቸው በአንደበት ተናግረዋል፡፡መለስ እንደምንም ብለው አሳምነዋቸው ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የሞቱት ደግሞ የሞቱለት ስርዓት ሲዘርፈን፣ሲገድለን፣ሲያሰድደን ኖረ እንጅ ውለታቸውን እንቆጥር ዘንድ ዲሞክራሲን አላመጣልንም፡፡በአጭሩ የማንም ውለታ የለብንም!

“[ኢትዮ-ሶማሌ ክልል] ሶማሌ ውስጥ የተደረገው ነገር ትግራይ ውስጥ ሊመጣ እንደሚችል ወጣቱ ይነገረዋል፤ በዚህም ይሰጋል።የትግራይ ህዝብ በትግሉና በመስዋዕትነቱ ያገኘውን መብት ማንም ሰው መጥቶ እንዲድጠው አይፈልግም።ከውስጡ የወጡት አጥፊ ኃይሎችንም ቢሆን ራሱ ሊቀጣቸው ይፈልጋል እንጂ በሌላ ኃይል ተድጠው፣ አንተ የትም አትደርስም የሚል መልዕክት እንዲተላለፍለት አይፈልግም፡፡ጥፋት ያጠፉ ካሉ በህገ መንግሥቱ መሰረት ይስተካከል እንጂ ኃይል ያለው ሁሉ በዘፈቀደ ከህግ ውጪ፣ እኛን ወደ ጎን ትቶ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ከሆነ፣ የኛን ክብርና ማንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” የሚል ነገር ይፈጠራል፡፡” ይላሉ ፃድቃን በሌላ ንግግራቸው፡፡

ኢትዮ-ሶማሌ ክልል ውስጥ ምን ሆነ? ህወሃት ቀብቶ በህዝብ ላይ የጫነው፣አንድ ሚሊዮን ህዝብ ሲያፈናቅል ቅር የማይለው፣የራሱን ህዝብ እስርቤት ከቶ መከራ የሚያሳይ፣ሃገር ያስመረረ አብዲ ኢሌ የሚባል ወንበዴ የኢትዮ-ሱማሌ ህዝብ አዲስ አበባ ድረስ ተጉዞ አቤት በማለቱ ሳቢያ ከስልጣን እንዲነሳ ህጋዊ መንገድ እንዲጀመር ሲጠየቅ አሻፈረኝ ብሎ ህዝብ አስጨረሰ፣ የእምነት ቦታዎችን በተላላኪዎቹ አወደመ በስተመጨረሻው ተያዘ፡፡ይሄ እንዴት ነው በትግራይ የሚደገመው? በማዕከላዊ መንግስቱ የሚፈለጉ የትግራይ ተወላጅ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ባለስልጣናት ትግራይ መሽገው የክልሉ መንግስት ደግሞ ለወንጀለኛ ከለላ የሰጠ እንደሆን ነው፡፡

ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ማድረግ የሚችለው የትግራይ ህዝብ እና የክልሉ መንግስት ነው፡፡ቀላሉ መንገድ ትግራይ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ የቀድሞ ባለስልጣናት የፍርድቤት ጥሪ አክብረው በህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸውን የሚመረምረው የወጡበት ጎሳ የቤተ-ዘመድ ጉባኤ አይደለምና ፃድቃን እንደሚሉት የትግራይ ህዝብ “ተጠርጣሪዎቹ ካጠፉም እኔ ልቅጣቸው” የማለት መብት ፈፅሞ የለውም! ፍርድቤት ችሎት ላይ ተቀምጦ የጎሳውን ሰው የክስ መዝገብ የመረመረ ህዝብ በዓለም ላይ ታይቶ ስለማይታወቅ የትግራይን ህዝብ ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡

ትግሬ የሆነ የቀድሞ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ፍርድቤት ቀርቦ በመጠየቁ የሚጎድል የትግራይ ህዝብ ክብር የለም፡፡እንዲህ መታሰቡ ራሱ ስህተት ነው፡፡ ‘እኛን ወደጎን ትቶ ለውጥ ማምጣት አይቻለም’ ማለትስ ምን ማለት ነው? የትኛው ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ስልጣን ላይ እንደወጣ ነው የትግራይ ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ወንበር ላይ የሚወጣው? ወይስ የትግራይ ህዝብ አልተገለለም እንዲባል የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላለሙን በህወሃት ጊንጥ ሲገረፍ መኖር አለበት? ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት እኛን ያልጨመረ፣ግልፅ ያልሆነ ነው ማለትስ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሁለት ሃገሮች በሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ድርድር የትኛው ጎሳ ነው መሃላቸው ቁጭ ብሎ የድርድር አካል የሆነው? መለስ ዜናዊ “ይባኝ ሳልል የምትሉትን እቀበላለሁ” ብሎ መሬቱን ሲያስረክብ “እኛን አላማከርክም” ተብሎ ነበር?

የህወሃት ማኒፌስቶ ግልባጭ የሆነው ህገ-መንግስትም በትግራይ ህዝብ ዘንድ አለው ስለተባለው ትልቅ ቦታ እንዲህ ብለዋል ፃድቃን “የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ህገ-መንግስት እንደ ዋስትና ያየዋል፡፡አንቀፅ 39ን እንደ ዋስትና ነው የሚመለከተው፡፡ ይህ ሲባል በኢትዮጵያዊነት ይደራደራል ማለት አይደለም። ራሱን ከኢትዮጵያዊነት ነው የሚያስተሳስረው። ኢትዮጵያዊነት ከደሙና ከአጥንቱ ጋር የተዋሃደ፣ ታሪኩም ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን አንቀፁ ዋስትና ይሰጣል፣ መብትን ለማስከበር ይረዳል ብሎ ያምናል፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር ሲል ከዚህ አንፃር ነው፡፡”

ህወሃት ጠላቴ የሚለውን የአማራ ህዝብ አግልሎ፣በአመዛኙ እንደ እሱው የአማራን ህዝብ በመጥላት በሽታ የታወሩ የጎሳ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ያወጣው ህገ-መንግስት ለትግራይ ህዝብ እንደክታብ አንገት ላይ የሚታሰር በስስት የሚታይ ክቡር ነገር ነው- እንደ ፃድቃን ገለፃ፡፡ህወሃት በሌሎች ላይ ላይ ያልተገበረው ምናልባት ስልጣኑን ያጣ እለት ኤርትራ ፊት ከሰጠቸው ትግራይን ገንጥሎ በሚወደው የገዥነት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ሲል ያስቀመጠው አንቀፅ 39 ለትግራይ ህዝብ ዋስትና መሆኑ እውነት ከሆነ፤ ስለትግራይ ህዝብ እና ህወሃት ልዩነት ፃድቃን ሲያወሩ የዋሉት ሁሉ ማሞ ቂሎ ብቻ የሚያምነው ተረት ነው የሚሆነው፡፡ ለማንኛውም የትግራይ ህዝብ የሚሰስትለት ህገ-መንግስት የአማራ ህዝብን እንደ ዘውግ ያገለለ፣ ከሁለት ዘውግ ለተወለዱ ኢትዮጵያዊያን ቦታ የሌለው እና ራሳቸውን እንደ ኢትጵያዊ ዜጋ ብቻ የሚገልፁ ሰዎችን የማያውቅ በመሆኑ ሌላው ህዝብ እንደ ትግራይ ህዝብ በእንስፍሳፌ ሊወደው እንደማይችል ሌላው ሌላው ቢጠፋው ፖለቲካ አዋቂ ነኝ የሚሉት ፃድቃን አይጠፋቸውምና ለወገኖቻቸው ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here