አየናቸው አሰፋ
ነሃሴ 23 2010 ዓ.ም.
የሰሞኑ “ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ኢትዩጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፈጣን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል” የሚለው የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ በማህበራዊ መገናኛዎች መነጋገሪያ ሆኗል። በተለይ በጤና አገልግሎቶች ላይ የ 25 በመቶ ቅናሽ መደረጉ የድጋፎችን ያህል የትችቶች እና ቀልዶች ምንጭም ሆኗል።
በርግጥ ለማንም ቢሆን የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ምንም ክፋት የለውም። ከዚህ ይልቅ ዋናው ጥያቄ ይህ ለሃገሪቱም ሆነ ለዲያስፖራ አባላት ዋና እና አንገብጋቢው ጉዳይ ነው ወይ የሚለው ነው። የነገሩ አቀራረብ የዲያስፖራ አባላት የአዲስ አመት በአልን ለማክበር ወደሃገር ቤት እንዲመጡ እንደማበረታቻ የታሰበ ይመስላል። ይሁን እንጂ የአንድ ማበረታቻ አስፈላጊነት (እና ውጤታማነት) የሚመዘነው የማበረታቻው መሰጠት የተቀባዩ ውሳኔ ወይም ባህሪ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል በመሆንና ያለመሆኑ ነው። ይህም የጤና አገልግሎት ለዲያስፖራው ወደ ሃገር ቤት መምጣት ወይም ያለመምጣት ወሳኝ ጉዳይ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል።
በጠቅላላውም ባይሆን በአመዛኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ወደ ሃገር ቤት ከመምጣት የሚያግደው ከፖለቲካ ልዩነት የሚመነጭ አለመግባባት፣ ክልከላ፣አፈና እና ከዛ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ስጋቶች እንጂ የፍላጎት እጦት አይደለም። ይህም ባለፉት ጥቂት ወራት በበለጠ በግልፅ ታይቷል። ስለዚህ እነዚህን ከልካይ ሁኔታዎችን ማሻሻልና ማስወገድ የሚያስችሉ ህጋዊና ተቋማዊ እርምጃዎች መውሰድ እንጂ የማበረታቻ ፕሮግራሞችን ማቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው እርምጃ ሆኖ አይታይም።
በመጀመሪያ ዲያስፖራው ለበአል ወደ ሀገር ቤት ምመጣትን ሲያስብ የጤና ጉዳይ እክል ይሆንብኛል የሚለው ፍራቻው በዚህም የተነሳ ሃሳቡን የመቀየር እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። ድንገተኛ ህመም ካልሆነ በስተቀር አንድ የዲያስፖራ አባል የላቀ የህክምና አገልግሎት እና ከሞላ ጎደል የተሻለ የጤና መድህን ካለበት ሃገር ሄዶ ኢትዮጵያ ህክምና ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። ድንገተኛ ህመም የተከሰተ እንደሆነም ወደ መንግስት ጤና ጣቢያ ወይም ሆስፒታል መሄድ ቀዳሚ ምርጫ የሚሆን አይደለም። ወደ ግል ተቋማት ሲኬድም የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና እንጂ በአንፃራዊነት ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም ላለው ዲያስፖራ ዋጋ ወሳኙ ጉዳይ አይሆንም። ስለሆነም ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዲያመጣ የማይጠበቅ ማበረታቻ ማቅረብ ከይስሙላነት አያልፍም። እዚህ ላይ ለዲያስፖራው የሚሰጡ ማበረታቻዎች ሁሉ ዋጋ ቢስ ናቸው ለማለት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በቋሚነት ወይንም ለረጅም ጊዜ ወደሃገር ቤት ለሚመጡ የዲያስፖራ አባላት እንዲህ ያለው ማበረታቻ ቢሰጥ የበለጠ ትርጉም ያለው ይሆናል።
በሌላ በኩል ባለፉት ወራት ዲያስፖራው ከሀገሩ ጋር ያለውን ግንኙንት ለማጠናክር እና ሀገሩን ለማገልገል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የሚያመለክቱ ማሳያዎች በተለያዩ መድረኮች ጎልተው ወጥተዋል። በመሆኑም ይህንን ፍላጎትና አቅም ለመጠቀም የሚያስችል የፖሊሲና ተቋማዊ ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የዲያስፖራ አባላት በሚመጡባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማትን እንዲጎበኙ፣ ያሉትን ክፍተቶች እንዲያዩ፣ ከጤና ባለሙያዎች፣ የጤና ተቋማት አመራሮች ፣ከመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ፣ከነዋሪዎች እና ከጤና ተማሪዎች ጋር እንዲወያዩ ማድርግ ፤ በሙያ አገልግሎት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ፣ በተቋማዊ ትብብር ፣ በኢንቨስትመንትና በመሳሰሉት ረገድ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ምክክር ማድረግ ፤ የፖሊሲ ፣የህግና የተቋማት ማእቀፎችንና የመንግስት እቅዶችን ማስተዋወቅ፤ የዲያስፖራውን ሃሳብና አስተያየት ማሰባስብ፤ በዲያስፖራ ህጉ እና በዲያስፖራ ፖሊሲው ላይ የተቀመጡትን ሃሳቦች ማብላላት፣ ክፍተቶችን መለየት እና ማሻሻያዎችን መሻት፤ ብሎም ቀጣይ እርምጃዎችንና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት የሚያስችሉ እቅዶችን በጋራ መንደፍ። እነዚህንና የመሳሰሉትን ማድረግና ዲያስፖራው በጤና አገልግሎት ዘርፍ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ተግባር መሆን አለበት።
በርግጥ “ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ባላቸው አቅምና ሙያዊ ችሎታ ሀገራቸውን ለማገልገል እንዲችሉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው” በመግለጫው ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ ይህ ሰፊ ስራና አትኩሮት የሚጠይቀው ዋና ጉዳይ በአንድ አርፍተ ነገር ተጠቃሎ ሌሎች የማሻሻጫ የመሰሉ ሀሳቦች ላይ ትኩረት መደረጉ የሚያመለክተው ነገር ካለ ግልፅ የቅደም ተከተል (priority) መዛባት መኖሩን ነው። በዲያስፖራው ተሳትፎ ዘላቂ የጤና አገልግሎት ልማት እንዲመጣ ስር ሰደድ የሆኑ ተቋማዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ።
___
ጸሃፊውን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል :ayenachew@gmail.com
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።