spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትተቃዋሚ ለተቋማት (ባህር ከማል )

ተቃዋሚ ለተቋማት (ባህር ከማል )

ባህር ከማል
ነሃሴ 24 2010 ዓ.ም.

ሀገራችን ውስጥ እየተከናወነ ላለው ለውጥ የምናሳየው ድጋፍ ከማጨብጨብ ባሻገር ተገባራዊ መሆን ይኖርበታል።ይህ ለውጥ በኢህአደግ መሪነት ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ብዙዎች የሚስማሙበት ይመስለኛል። በመሆኑም ነው ሁሉንም ነገር በዶ.ር አብይና በፓርቲያቸው ላይ መጣል የለንብም የምንለው። የዳያስፖራው ህብረተሰብ አገር ውጥ ካለው ህዝብ በቁጠር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም በእውቀቱ፤በገንዘቡና በጉልበቱ በግልም ሆነ በቡድን ሊያበረክታቸው የሚችል አስተዋጾ ከፍተኛ ነው።

እስክዛሬ በተቃውሞ ያሳለፈው ዲያስፖራ ተቋማትን በመገንባት ረገድ በደጋፊነትም ሆነ በተፎካካሪነት ኢትዮጵያን በመታደጉ ረገድ አስተዋጽኦው መቀጠል ይኖርበታል። የጥምር ዜግነት ከተፈቀደ (መፈቀድ አለበት ተብሎ ይታመናልና) ዳያስፖራውን ለትውልድ አገሩ የበለጠ ስለሚያቀርበው ድርሻውን ለማበርከት የበለጠ አመቺ ሆኔታን ይፈጥራል።ዳያስፖራው ያራሱ አገር ተጨባጭ ሁኔታን ከመረዳት አንስቶ በሚኖርበት ዲሞክራሲያዊ ከሆኑት አገራት በሚቀስማቸው ልምድ ከአገሩ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ የማድረግ ከሌላው የውጭ ሰው የበለጠ የበላይነት (upper hand ) ያለው በመሆኑ ተቋማትን በመገባቱ ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህንን ሲል በ100 ሚሊዮን ውስጥ ያለውን እምቅ ሃይል አሳንሼ ከማየት ሳይሆን የዲአስፖራውም ድርሻ በቁጥር ንፅፅር ብቻ ሊሰጥ የሚችለው አገልግሎት እንዳይዘነጋ ነው።

ሲቪክ ማህበራት ይህዝብን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ከመንግስት ውጭ ያለትርፍ ተደራጅተው (none profit (organization) የሚንቀሳቀሱ አካላት ናቸው።እነዚህ ማህበራትና ተቋማት የሞያ ማህበራትን፤ለትርፍ ያልቆሙ ድርጅቶችን NGO ) የሃይማኖት ተቋማትንና ሌሎች ለህብረትሰቡ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ስብስቦችን በአገራችን አንዳሉ እንደ እቁብና እድር የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።የሲቪክ ማህበራት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በመከታተል( watchdog) ፤ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ህዝቡ እንዲያውቅና አስፈላጊ ለውጦች እንዲደረጉ በመወትወት፤ (advocacy ) በትምህርት፤በጤና ለአደጋ ጊዜ ቅደመዝግጅቶን በማድረግና አገልግሎት በመስጠት (service provider)፤ፖሊሲና ስትራቴጂን ለመቅረጽ ልዩ ልምድና እውቀት ያላቸውን በመለየትና በማቅረብ፤በማስተማርና በማሰልጠን አቅምን በመገንባት (capacity building )፤ለተገለሉ፤ ለተረሱና ድምጽ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክሎች ድምጽ በመሆን (reperesentative ) ና ህበረተሰቡ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ በማበረታታትና ማስተማር (citizen champion )ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

ተቋማት ለዲሞክራሲ ግንባታና ለህግ የበላይነት ዋስትናዎችም ናቸው። ዛሬ ባደጉት አገሮች የምናየው የህግ የበላይነት መረጋገጥና የዲሞክርሲ መበልጸግ የመንግስታት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተወዳድረው በምርጫ ስልጣን መያዛቸው ብቻ ሳይሆን የተቋማት የስራ ውጤት ጭምር ነው። ለአገር ዕድገትና ብልጽግና ጠንቆችን ወገንተኝነትን፤ አድሎን፤ ጎበኝነትን፤ምዝበራን፤ አፈናንና የመሳሰሉን በእንጭጩ መቅጨት የሚቻለው ነጻ የሆኑ ተቋማት ሲኖሩ ብቻ ነው።አለመታደል ሆኖ በህዝብ አዎንታ ስልጣን ላይ የውጡ መሪዎች ወይም ቡድኖች ስላልነበሩን ሁሉም የነበረውን በማፍረስ በግላቸው ወይም የሚመሩት ቡድን ባመነበት ከቀደመው ባልተሻለ ሁኔታ ግን ለእነሱ በሚስማማና ለረዥም ጊዜያት ሥልጣን ላይ በሚያቆያቸው መልኩ ተቋማትን ይገነባሉ። እነዚህ ተቋማት ደግሞ የህዝብ አገልጋዮች ሊሆኑ እንዳልቻሉና ሊሆኑም አንደማይችሉ ከቀደምት ታሪካችን መገንዘብ አዳጋች አይሆንም።ፈተናውን ተቋቅመው ለመስራት የሚሞክሩም እንደ ፖለቲካ ተቀናቃኝ ተደርገው ስለሚታዩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከጨወታ ውጭ ይደረጉ ነበር።

ዲሞክራሲ በሚገባ ሊገነባና ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ተጠያቂ የሆነ፤ግልጽነት የተላበሰና በነጻ ሃሳብ መንሸራሸርን የሚያበረታታ ህዝባዊ ተቋም ሲኖር ብቻ ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ እየተቀጣጠለ ያለው ለውጥ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትም ሆነ ውጤቱ ዘላቂ እንዲሆን በተቋማት መደገፍ የግድ ነው። ለዚህም ያሉትን ተቋማት ከማፍረስ ይልቅ አስፈላጊውን ጥገናና ማሰተካከያ ተደርጎባቸው ከማንኛውም ተፅእኖ ነፃ ሆነው በህግና በህግ ብቻ በመተዳደር ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ ነው።ተቋማት በስሩ ለተሰባሰቡት አባላት በእኩልነት አገልግሎት መስጠት ቀዳማዊ ሥራቸው ቢሆንም ከሌሎች ተቋማት ጋርም አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸው በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት መኖር ግድ ይላል።

ተቋማትን በተለይም መንግስታዊ ያልሆኑትን የሃይማኖትን ጨምሮ የማጠናከሩ ተግባር በተቀዳሚነት ሃላፊነቱ የህብረተሰቡ ነው። የተፈጠረውን የለውጥ አጋጣሚ በመጠቀም በመሰባሰብ መንግስትም ተቋማትን በህግ እንዲደግፍና ቀደም ሲል የወጡ ህጎች (የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ) እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሰረዙና በምትካቸው የተሻሉ ህጎች እንዲወጡ ጫናና እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በመንግስት አንሳሽነት የተጀመረው ጥናት ውጤታማነት የተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የምሁራንና ትልቁ ባለደርሻ የሆነው የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።የሚተኩትም ካሉ በበዙሃን የሚደገፉና የሚተገበሩ በተለይም የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማይጋፉ ሆነው እንዲቀረጹ ከወዲሁ ሊታሰብበትና በጥንቃቄ መቀረጽ ይገባቸዋል።ሕግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚው፤ሕግ አስፈጻሚው፤ ፓርቲና መንግስት መለያየት ለህግ የበላይነት መስፈን መሰረትና አስፈላጊዎች ናቸው። ስለሆነም መንግስታዊ የሆኑትንም ተቋማት ነጻ ሆነው እንዲጠናከሩ የተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲ መሪዎች፤የምሁራን፤የአክቲቪስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ ነው።

ነጻ ጠንካራ ተቋማት መገንባት ሂደት ቢሆንም ካሁኑ ካልተጀመረ ለውጡን ወደፊት አራምዶ ለታቀደው ግብ ለመድረስና እስካሁን የተገኙትንም ሆነ ለወደፊት የምንቀዳጃቸውን ድሎች ለመጠበቅና ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ አይቻልም።ግልጽነትን፤ተጠያቂነትንና ውጤታማነት ለማስመዝገብ ነጻ ተቋማት ከመገንባት ሌላ አማራጭ የለም አይኖርምም። በመሆኑም የምርጫ ቦርዱን ከማስተካከል (ገለልተኛ ማድረግ) ጭምር የህግጋትና የተቋማት ሁኒታ መስመር ሳይዙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝቡ ውስጥ ገብተው ሃሳባቸውን ለማንሸራሸር የሚችሉበት ሁኔታ ሳይፈጠር ሀጋራዊ ምርጫ ብቻን ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀሱ ለገዥው ፓርቲ እንዳለፈው ከራስ ጋር መወዳደር እንዳይሆን ያሰጋል። ይህ ደግሞ ውጤቱ ጤናማ ላይሆን ስለሚችል ካሁኑ ሊታሰብበት ይገባል።ትናት የአንድ ፓርቲ አመራር ያውም አምባገነንነት በተላበሰ መልኩ የነበረው ነገም እንዳይደገም ከተፈለገ መፍትሄው በነጻ ተቋማት መደገፍ ነው ያ ደግሞ በበኩሉ ለብዝሃነት ፓርቲ ስርአት (multi party system) ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከነህዝቦቹዋ ይባርካት።አሚን።
bahirk@hotmail.com
ጽሁፉን በፒዲ ኤፍ ለማንበብ ይሄን ይጫኑ
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here