spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየት"ሽግግር... ይቅር፤ሕገ-መንግሥት ይከበር...፤ሕገ-ሕዝብም ይቀበር...፤"ለምን?...? ? ?(አብይ ኢትዮጵያዊ)

“ሽግግር… ይቅር፤ሕገ-መንግሥት ይከበር…፤ሕገ-ሕዝብም ይቀበር…፤”ለምን?…? ? ?(አብይ ኢትዮጵያዊ)

አብይ ኢትዮጵያዊ
abiyethiopiawe@gmail.com]
ነሃሴ 25 2010 ዓ.ም.
በዕውነት እና በሐቅ እንነጋገር ለምን?…?…?…

የለውጥ ባቡሩ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሮጬ፤ባቡሩን መቅደም እችላለሁ የሚል ሰው ማን ነው?ለእኔ ከባቡሩ ውጭ ስለሚሆነው አማራጮችን የሚያስብ ብልህ ብቻ ነው።

ዶክተር አቢይ አህመድን ለመተቸት ዕውቀቱም ሆነ ብቃቱ የለኝም፤ሆኖም በእኔ ፍላጎት በእርሳቸው መልካም ፈቃድ አስተያየቴን ለመስጠት ስለወደድኩ፣ እነሆ እዚያ ስለሚፈጠረው ሁኔታ ጠንቋይ አያስብለኝም፤አሊያም ታምረኛ አያደርገኝም።”ብዬ ነበርንም”አልወደውም፤ችግሩን በጋራ መፍታትን ከሁሉ እመርጣለሁ።

ኢትዮጵያውያን ሙሴን የመሰለ የፍቅር ጠንካራ እና የፃነት መሪ ዶ/ር አብይ አህመድን ከገለባ ውስጥ በተዓምር በግልፅ አግኝታለች።ጠቅላይ ምኒስቴር አብይ አህመድ ተስፋ የሰነቁ፤የፍቅርን ካባ የተካኑ፤ለበጎ ሥራዎች ልባቸው የተከፈተ፤ባጠቃላይ ተክለ-ሰውነትን የተላበሱ፤ልሳነ ርዕቱነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ናቸው፤በዚህም ብዙዎቻችን እንስማማለን።እንዲህ የሚያሳሱን የንብ ተምሳሌት ብርቅዬ የአገር መሪ ሰው ደግሞ፣በቀላሉ የሚገኙ ሳይሆኑ በዘመን ተቆጥሮ የሚመጡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው።በመሆናቸው ነው አጠገባቸው ዘውድ የጫነውን{የሥርዓት አወቃቀሩ ውጥንቅጥ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ባለሙሉ ባለሥልጣን የሆኑትን}ፕሬዘዳንታችንን የሚያስረሱት፤ሁሉም በጊዜው ይፈፀም ዘንድ።
ጊዜን ስናነሳ ሰከንድ እንኳ የእኛ አይደለችም፤አልፎም ነገ የማናችንም እንደሆነ እርግጠኞች አይደለንም፤የእኛ ነው የሚያስብለንም ሞታችን ካልተረጋገጠብን ብቻ ነው።ቁም-ነገሩ ዶ/ር አቢይ አህመድ ነገ የእርሳቸው እንዳይደለ፣ቢያንስ ካለፈው ጠቅላይ ሚኒስቴር”ወቸገል *ናዊ”የመቅሠፍት(በሕዝብ ዕምባ ከእግዚአብሔር የተወረወረ ፍላፃ ነው፤እንደ እኔ ዕምነት።)እሳትን ልብ ሊሉ ይገባል እላለሁ።የዚህን ሐቅ ለማረጋገጥ መስተዋት ፊት ለፍት ቆመን ያዘልነውን የሞት ዕዳ ሸክም ለማየት መሞከር አያስፈገንም።ለምን? ቢባል፣ሕሊናችን በደመነብስ ያውቀዋልና የሌላ ሰው ሬሳያስታውሰናልና።በሌላ በኩል”እግዚአብሔር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንደሚናገር”ስለማምን ነው።ደግሞ’ኮ ቁጣውን በክንዱ አንዴ ብቻ አይደለም ያሳየን፤እግዚአብሔር፣ሁለቴ ነው፤የሞትን ፍላፃ አከታትሎ በአንድ ሳምንት ውስጥ”ሕዝቤን ልቀቁ”ብሎ የወረወረው።በሕዝብ የማይታወቅ መስሏቸው ፍርፋሪ ከሕዝብ አፍ የመነተፈውን ጨምሮ፣ተቀጣሪ አልቃሾችንና ስነሓዘን-ሥርዓት አስጠባቂዎች ድረስ ምን ዓይነት የቀብር አፈጻፀም እንደነበረ አንዘነጋውም።

አንደኛው”የአባ *ያ*ሎስ” ነው።ፓትርያርክ የተባሉት አስበውና ገምተው፣የዓለም ዕውቋ ኮማሪና እርቃነ ብልሹዋን፣አስፈልገውና በወኪሎች አስጠርተው፣ በተቀደሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ስፍራ ላይ በሥጋ ርካቦት ሳይሆን በዐይነ-ሥጋ ዝሙት ፈፀሙ።ይባስ”ምን ታመጣላችሁ?”የወቸገል *ናዊን የሥልጣን ጋሻቸው አድርገው፣ባደባባይ፣በንቀትና በትዕቢት፤ካህናትን አሳፍረው ዣንጥላ አሲይዘው፣እርኩሱን ዝሙት በዓይን ደፍረው፣እንደ”ኦርዮን” ሚስት በዓይነ-ሥጋ ዘሙተው ሸኝተዋታል።እናም ወቸገሉና *ባ **ሎስ አባቴና ልጄ ሲባባሉ የነበሩት ቆይ ነገ እንፈፅመዋለን ብለው፣ገና ይቀረናል እያሉ እቅድ ሲያወጡ የእግዚአብሔር ቍጣ በሁለቱም ላይ ነደደ፥ስለ ድፍረታቸውም ለመልዓከ ሞት ተገልፆ በያሉበት ተቀሠፉ።ብናምንም ባናምንም፣ይህ ቅስፈት ሰማያዊ ነው፤ገና የምድራዊው ቅጣትም ይቀራቸዋል፤የሚሆኑትም ደግሞ ይሄው ነው፣የትውልድ እርግማን ይሻሉና።እነርሱ ለነገ ብለው ሳይጨርሷቸው የቀሩትን ውስብስብ ተንኮሎች የሕዝብ አመፅ ዶግ-አመድ ያደርጋቸዋል፣ለምን ቢባል፣በደም የተጨማለቁ ርኩሳን ተግባሮች እና ቅርሶቻቸው እንደተመዘገቡ መኖራቸውን ስለሚያውቅ ነው።ከነዚህም መካከል ሁለቱ ብቻ ሲጠቀሱ፣እንደፈርዖን በቁማቸው ያሰሩት የአ* ዲ**ሎስ ሓውልት እና የወቸገል *ናዊ መቃብር ሌላው ነው።

ቢያንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተአሕዶ ቤ/ክ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተከትሎ መፍረስ ይኖርበታል።የአ* ዲ**ሎስ ከሃውልታቸው ላይ በእጃቸው ያለው መስቀሉ መነሳት አለበት፤አለበለዚያም የተሰበረ መስቀል ሆኖ በሥነ-ጥበብ አርት በመሠራትና ቤተክርስቲያኗን እንዳረከሰ ለትውልድ መቅረት አለበት።የወቸገል *ናዊ መቃብርም ከቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ግቢ ሊወጣ የሚገባው ዕምነቱ የሌለው ስለሆነ ነው።መቃብሩ ከኢሰፓዎቹ የቀብር ቦታ ማረፍ ይኖርበታል፤ይህም ኃላፊነት በዓለም ሬሳቸው ተጥሎ ለቀረው የኢትዮጵያ ወገኖቻችን ማስታወሻ ሆኖ እየተረገመ ሊታወስ ይገባል።ፓትርያርኩም የኢትዮጳያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ያረከሱ እና ፓትርያርክ ሊያስደርጋቸው የሚያስችል አንዳችም የቀኖናም ሆነ የቤ/ክ ሕግ የለምና ትውልድ እንዲረግማቸው ለመጪው ትውልድ ትምህርት ሊሆን ይገባል።ምክንያቱም ሁለቱም በገዳማት ላይ የፈፀሙት ርኩሰት ታሪካቸው ተነግሮ አላለቀምና ከግለሰብ ያደባባይ ግድያ እስከዝሙተኛን በቅዱስ ቦታ ማርከስ ብልግናቸውን አምጥቀዋልና ያንሳቸዋል።

በተጻራሪው ደግሞ አሁን የመጡት የእነጠ/ሚ ዶክተር አቢይ አህመድ መልካምና በጎ የምንመኝላቸው ባለሥልጣናት ለፍቅር ደፋ ቀና ሲሉ፤የሠይጣን ሠራዊቶች ዝም ብለው አይመለከቱምና ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ጀምሮ በነቃ-ዐይን ካልጠበቅናቸው ለማድረግ የማይሞክሩት ጥፋት አይኖርም።ስለዚህም ከእግዚአብሔር በላይ ምንም እንደሌለ ብናምንም እንደሙሴ አገላለፅ በአምሳሉ የፈጠረን እግዚአብሔር ምልዑ-በኩለሄ አድርጎ ባይፈጥረንም በሰጠን ሕሊናችን ማድረግ የምንችላቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ ልናደርግ ይጠበቅብናል።ከነዚህም አንዱ እና ዋናው አስፈላጊ ነገር”አይመጣምን ተትሽ፣ይመጣልን ያዢ”የሚለው ብሂልን በመከተል ሁልጊዜም ራስን ዝግጁ ማድረግን ነው።

በቁምነገር እናስበውና መቶ በመቶ ፐርሰንት እርግጠኛ ነኝ”ዕለተ-ነገ”አይቀርም ይመጣል፤መምጣቱን የሚመሰክሩት ግን የመጣላቸው ብቻ ናቸው፤በሕይወት ስላሉ።ስለዚህም ወደ”ነገ የሚያሸጋግሩን ጉዳዮች”በአግባቡ መለየት አለባቸው፤የቀልድ አይደለም።ርኩስ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እግዚአብሔርን አያውቁምና ፍቅርን አይፈልጉም፤መልካም ነገርን ሁሉ ማየትም ሆነ መስማት አይሹም፤እናም ሰው ናቸውና እናሳያቸው፣ለምን ሠይጣን ጋርዷቸዋልና።

ስለዚህ መንግስትና ሕዝብ የተለያዩ አካላት ናቸው፣መንግሥት ሕልውናውን የሚያረጋግጠው በመንግሥት ሳይሆን፣በሕዝብ ብቻ ነው።ታዲያም በሕዝብ ላይ የሚነገሩት አባባሎች ሁሉ እንደመንግሥት የሚቀለዱባቸው እና በቀላሉ የሚታለፉ አይሆኑም፤ስለዚህም ነው፣ነገ አይደለም ዛሬውኑ የትኛውን ዓይነት የሽግግር ሁኔታ እንደሆነ ዶ/ር አቢይ አህመድ የኔ ድርሻ ነው ያሉት?እናም ሽግግሩ ለሕዝብ በግልፅ መታወቅ ይኖርበታል፤አመፅን እንዳያረግዝ።

የዓዲሱን አመት ፪፲፻፲፩ን ነው ብዬ አላምንም፤ሁላችንም በየግላችን በየቤታችን ወይም በያለንበት እንደየአቅማችን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አበቃህ እየተባባልን፣የምንሸጋገረው ነው።የሥርዓተ-መንግሥት ሽግግር ከሆነ ደግሞ በቁምነገር እንጂ በቀልድ፣በፈገግታ፣በለበጣ እና በታማኝነት ሊሆን አይችልም፤”ነው!” ተብሎ ከታለፈ ግን አመፅ ይፀንሳል።ምክንያቱም መንግሥት የሕዝብ እንጂ ሕዝብ የመንግሥት አይደለምና የትዕዛዙ የዕዝ ሰንሰለት ይበጠሳል።ይህም ማለት ዶክተር አቢይ አህመድ ቅቡልነቱን እንዲያጣ ለሕዝቡ የአመፅ-ሰበብ ይፀልለታል ማለት ነው፤እሳቸው ልባቸውን ከሕዝቡ ከደበቁ ጥሩ አይደለም፤ነው ብዬ አላምንም።

ሕዝቡን ሕገ-መንግሥት አይገዛውም ሊገዛውም አይገባም፤ምክንያቱም “ሕገ-መንግሥት”ማለት በቀጥታ መንግሥት ሕዝቡን ግዴታ ያስገባበት ስምምነት ሲሆን፤”ሕገ-ሕዝብ” ግን ሕዝብም ሆነ መንግሥት፣”ሁለቱም” በአንድ ላይ የሚገቡበት የሕዝቡ የዜግነት ዋስትና እና ማስታወሻ ስምምነት ነው።እናም ሕገ-መንግሥት ባለበት አሰራር “ሕገ-ህዝብ”ከሌለ ተጠቃሚው ምንጊዜም መንግሥት ብቻ ይሆናል፤እንዲያውም አልፎ ተርፎ ሕዝብን ያሽቆጠቁጥበታል።ሲብስም መንግሥት በራሱ ጊዜ ፖሊሲዎችን እየነደፈ፣መመሪያዎችን እያወጣ ባጀት እየበጀተ እና አዋጅ እያፀደቀ የሕዝቡን ነጻነት እስከዜግነቱ ሕልውና ማሳጣት ድረስ፤በቁም እስከመግፈፍ ይደፍራል።ዶክተር አቢይ አህመድም በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ደጋግመው እንደሚሞክሩትና፤ገና ብዙ መብት እሰጣችኋለው እያሉ የሚያቁለጨልጩን ይሄው ፈተና ተጋርጦባቸው ሳይሆን አይቀርም፤እንፀልይላቸዋለን።አንድ መታወቅ ያለበት አተያየት፣”የለውጥ ባቡሩ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ሮጬ፤ባቡሩን መቅደም እችላለሁ የሚል ሰው ማን ነው?ከባቡሩ ውጭ አማራጮችን የሚያስብ ብልህ ብቻ ነው።”የሚለውን እንዳንዘነጋ።ምክንያቱም ዶክተር አቢይ አህመድ በጠቅላይ ምኒስቴርነት ማዕረግ ለስንድ ዓመት ተኩል ያህል የጊዜ ሠሌዳ ብቻ፣በአምስት ሚሊዮን የኢሃድግ ካድሬዎች ዙሪያ ውስጥ ተከበው የሚገኙ በመሆናቸው፤ብርቱ ተደራጅቶና ጎትቶ በስልት የሚያወጣቸው እገዛ ስለሚያስፈልጋቸው ነው።

ዶክተር አቢይ ሆይ፦የት እንዳሉ እናውቃለን፣ምን አልማዝ ቢነጠፍልን ከዜግነታችን እና ከነፃነታችን እንደማይበልጥ የሦስት ሺህ ዘመናት ታሪካችንን ደጋግመው ይመልከቱ።የኢትዮጵያ ታሪካችን የመቶ ዓመታት ብቻ እንዳልሆነ በትክክል መገንዘብ ይገባዎታል፤በጥቅም አበዱ እንደወቸገሉ ዜናዊ እንዳይደድቡ።እናም አይበልጥም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ የአርባ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ባለ ዕዳ ያደረጉን በሕይወት እያሉ እኛ በባርነት እየማቀቅን የእነርሱ የዓለም ባንኮችን አጣቦ እኛ በትብብር ከመኖር በታች ተቀብረን ዕዳውን ለመክፈል መጀመር በፍፁም አይቻለንም፤ለምን ቢባል ሐቅ መሆኑን ሰበብ እና ምክንያቱን ግልጫለሁና ሕሊናችን አይፈቅድም። ጠ/ሚ ዶክተር አቢይ አህመድ ዕውነቱን ተገንዝበው፤ሐቁን ሊውጡ ይገባል።በዓይነ-ሕሊና ስለምንጓዝበት የለውጥ ባቡር ማወቅ የሐቅ መድሃኒት በመሆኑ ለምናደርገው ሩጫ መፍትሄ ነው፤ብያለሁ።በቁም ነገር፦ነገ አይደለም ዛሬ የትኛውን ሽግግር ነው ዶ/ር አቢይ አህመድ የኔ ድርሻ ነው ያሉት?…በቂ ማብራርያ በመንግሥት ኃላፊነት ስሜት መልስ መስጠት ያስፈልጋቸዋል።

ልብ ያለው ልብ ይበል፣ይህን አቢይ ጉዳይ በልቦናው ውስጥ አስገብቶ ዶ/ር አብይ አህመድ ለምላሻቸው የኢሃድግን ውሳኔ የሚጠብቁ ከሆነ በባለሙያዎች የተዘጋጀውን “ሕገ-ሕዝብ” ርቂቅ ለፓርላማው እንዲያቀርቡ ያደርጉ ዘንድ ከዓዲስ ዓመት በፊትም የምስራቹን እንዲያበስሩን ማድረግ ከብዙ ጥፋት ያድናቸዋልና አንድላይ እናሰማቸው።ምክንያቱም እሳቸው አሁንም ያሉት የኢሃድግ ሳጥን ውስጥ ናቸውና።ልክ ባቡሩ ውስጥ እንደመሮጥ ነው፤ምን የፈለገ ቢፈጥኑ ከባቡሩ አይቀድሙም።የእኛ ዋናው ኃላፊነት መቃወም እና ትግሉን ማደናቀፍ ሳይሆን ከባቡሩ እንዲወጡ ስልቶችን መዘርጋት ነው፤አንዱ አማራጭ ደግሞ ሕገ-ሕዝብን እንዲቀበሉ ማድረግ ሲሆን “—ሽግግር” ደግሞ ለዚህ መፍትሄነትና በጣም አስፈላጊ ዘዴ ነው።

ስለዚህ “ሽግግሩም…አይቅር፤ሕገ-መንግሥቱም አይከበር…፤ሕገ-ሕዝብም አይቀበር…፤ለምን?…? ? ?…ሶስቱም ያስፈልጋሉ፤ሽግግሩ ለነፃነት፤ሕገ-መንግሥቱ ለማስተካከል እና ሕገ-ሕዝቡም ለመቆጣጠር።

አዲሱ ዓመት ፪፻፲፩ ዓ/ም የፍቅር፣የሰላም፣የደስታ፣የፍትሕና የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዓመት ይሁንልን።

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here