
Photo : screenshot from EBC
ቦርከና
መስከረም 7 2011 ዓ.ም
ትላንት ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ቡራዩ ከተማ አክራሪ ኦሮሞ ፖለቲከኞች ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ቡድኖች በተሰወሰደ አሰቃቂ ጥቃት በርካታ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተሰማ።
የማህበራዊ ድረ ገጽ መረጃዎች የሟቾችን ቁጥር እስከ 60 ያደርሱታል። በርካቶች ቆስለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩም ከቡራዮ ተፈናቅለው በአዲስ አበባ በተለያዮ አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ተጠልለዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ እጂጉ ጥቃቱ በተደራጁ ዘራፊዎች የተደረገ እንደሆነ ገልጸው የሟቶች ቁጥር 23 ነው ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የወጡ መረጃዎች እንደሚሉት በዚሁ ጥቃት ባለቤቷ የተገለደለባት ነብሰጡር ሴትም እንደተደፈረች እና ሆስፖታል ከገባች በኋላ ህይወቷ ማለፉንም ዘግበዋል።
ጥቃቱ በተለይ በጋሞ እና ጉራጌ ማህበረሰቦች ላይ ያነጣጠረም እንደነበር ተሰምቷል።
በጉዳዮ ላይ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ፓርቲ ሊቀመንበር እና የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሙፈሪያት ከማል መንግስት እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ፈጽሞ እንደማይታገስ ገልጸው ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ ርምጃ እንደሚውስድ እና የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ዜጎችም በጊዜያዊነትም ይሁን በቋሚነት ስለሚረዱበት ሁኔታ መንግስት እንሰሚሰራ ተናግረዋል።
የፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀማል ዘይኑ እስከ 300 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና ዛሬ በአዲስ አበባ በቡራዮ የተደረገውን ግድያ ለማውገዝ በተለያዮ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል ፤ የፖሊስ ኮሚሽነሩም አምስት ያህል ሰዎች “ዝርፊያ” ሲሉ ከገለጹት ሁኔታ ጋር በተያያዘ በፖሊስ እንደተገደሉ ተናግረዋል።
በቡራዮ የተደረገው እልቂት ኢትዮጵያውያንን በእጂጉ ያስቆጣ ጉዳይ ሆኗል ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ እና ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡም ተጠይቋል።
__
ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ።