መስከረም 7 ቀን 2011ዓም
(17-09-2018)
ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር አለመቻሉ ከምን የተነሳ ነው?
አንድ መንግሥታዊ ስርዓት በሰፈነበት አገር ውስጥ የሕግ በላይነት መኖሩ የሚጠበቅ ነው።በዚህ የሕግ የበላይነት በተከበረበት አገር የሕዝብ ሰላምና የሕይወት ዋስትና የተረጋገጠ ይሆናል።አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሕገወጥ ግለሰብም ሆነ ቡድን የሚፈጸም ወንጀል ቢኖር ያንን ለመቆጣጠር አቅም ያለው መንግሥት ወንጀለኛውን ለፍርድ አቅርቦ እርምጃ እንደሚወስድና መውሰድም እንዳለበት የሚያስገድደው ሕግ ይኖራል።ይህንን ተግባር ለመፈጸም የማይችል መንግሥት ካለ የመንግሥትነት አቅሙንና ተግባሩን ከጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ ብቻ ሳይሆን አንድን አገር ስርዓተ አልበኞች እንዲፈነጩበትና እንዲቆጣጠሩት ያሻቸውን እንዲያደርጉ ዕድልና በር በመክፈቱ የወንጀሉ ተባባሪ ያደርገዋል።
ባለፉት 28 ዓመታት በአገራችን ውስጥ የታዬው የመንግሥት ስልጣን ሽፋን ባደረጉ የወንበዴ(ማፊያ) ቡድኖች የተከናወነው መጠነ ሰፊ ወንጀል አከተመ ተብሎ ሕዝቡ የመኖር ተስፋ አንግቦ የመዝናናቱና የነጻነት አየር የመተንፈሱ ጅማሬ በሚታይበት ወቅት ከጥቂት ወራት ወዲህ ከየአቅጣጫው የሚፈጸመው ጎሳ ተኮር የሽብርና የስርዓተ አልበኝነት ተግባር ተስፋውን አጨልሞት የጥቁር ደመና ድባብ ጥሎበታል።ይህ የእንደመር አባዜ የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ንብረት እየዘረፈና እያወደመ ለመጣ ቡድን ሕዝቡን እንደዳረገው ለማዬት ችለናል።ይህ በጎሳ ማንነት የሚከናወን የሽብር እርምጃ በሁሉም ኢትዮጵያውያን መወገዝና ብሎም የመከላከል እርምጃ በአስቸኳይ ካልተወገደ በስተቀር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መቀመቅ ውስጥ የሚከት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ይህ ከመሆኑ በፊት በተለይም ሁኔታውን ለማሶገድ በስሙ የሚነገድበትና ወንጀል የሚፈጸምበት ጎሳ ተወላጆችና መሪዎቹ የበለጠ ሚና ለመጫወት ሃላፊነት አለባቸው እንላለን።የቁጥርህን አብዛና የመሬትህን አስፋ ዘመቻ በሌሎቹ ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መምጣቱ የሚካድ አይደለም።በራያ፣በከሚሴ፣በጎንደር ፣በመተከል ያሁኑ ቤንሻጉል፣በደቡብና ምዕራብ፣ ፣በጋምቤላና በቀሩትም ያገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደው ማፈናቀል ለሰላምና ለአገር አንድነት ጸር ከመሆኑም በላይ አገር ጠፍቶ ለጥቃት ፈጻሚው ወገን ጭምር የመጥፊያው ምክንያት ይሆናል።
ባለፉት ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በመፈጸም ላይ ያለው ዃላቀርና የአውሬ ጸባይ ገጽታ ያለው፣ የሽብርተኞች የተቀነባበረ ግድያ፣ዘረፋና ማሳደድ የአገር ህልውና የሚፈታተነው እኩይ ሴራ አካል ስለሆነ በቀላሉ መታዬት አይገባውም፤የማያዳግም መልስ ሊሰጠው ይገባል።የኢትዮጵያ ሃፍረት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብ ማፈሪያ ድርጊት ነው።አንዱ የኦሮሞ ተወላጅ እንደገለጸው” እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከጓደኞቼ ጋር ስከራከር ኦሮሞ እንዲህ አያደርግም ያልኩትን አባባል አፈርኩበት፤ አሁን መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ እመርጣለሁ፣ከሰማሁት በላይ በዓይኔ አይቼ ኦሮሞነቴን ጠላሁት፤ አፈርኩበት” ሲል ድርጊቱን በማውገዝ ገልጾታል።
ከሁሉም በላይ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው የመንግሥትነት ሃላፊነት የተቀበለው ቡድን የአገሪቱን አንድነትና የሕዝቡን ሰላማዊ ኑሮ ማስከበር ይጠበቅበታል።ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሳይውል ሳያድር የሰላም አስከባሪና የመከላከያ ሃይሉን አሰማርቶ ሽብርተኞችን አሳዶ የመያዝና የመቆጣጠር ተግባር ላይ እንዲውል ጥሪያችንን እናቀርባለን።የፖሊስ አባላት ከአሸባሪዎቹ ጋር በመሆን ወንጀል በመፈጸማቸውና ድምጹን ለማሰማት በወጣው ሕዝብ ላይ በመከላከያና በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸመው ተመሳሳይ እርምጃ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርገዋል።ሌሎቹም የኦሮሞ ድርጅት ነን ባዮች ድርጊቱን ከማውገዝም ባሻገር ወንጀለኞቹን አሳልፈው ሊሰጡ ይገባል።
የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ህብረት በሰላምና በፍቅር ለዘመናት ተሳስሮ የኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አጠንክሮ የመጣበትን ችግር ሁሉ እንዳሳለፈው ሁሉ አሁንም በየአቅጣጫው የሚከሰቱትን ችግሮች ተባብሮ እንደሚያሶግዳቸው ይተማመናል።የችግሩ ምንጭና ምክንያት የሆነው ክልልና ዃላ ቀር የጎሳ ፖለቲካ ተወግዶ በዘመናዊ ሕብረብሔራዊ የፖለቲካ ፍልስፍናና አስተዳደሩም በክፍላተ አገራዊ አወቃቀር እንዲተካ የሚያደርገውን ትግል ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ እንደሚቀጥልበት እየገለጸ ለአሁኑ ችግር መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሕዝቡም እራሱን ለመከላከል እንዲደራጅ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ሰላም የማደፈረሱ እርምጃ በሰላም ማስከበር ሽፋን የመንግሥት ግልበጣ ለማካሄድና ወደ ስልጣን ለመመለስ በወያኔና ተባባሪዎቹ የተሸረበ ሴራ ለመሆኑ አመላካቾች በገሃድ እዬታዩ ነው።ምንም እንኳን በዛው በወያኔ ጣራ በኢሕአዴግ ስር የሚካሄድ ቢሆንም ለመሰረታዊ ለውጥ መንደርደሪያ ሊሆን የሚችለው በሕዝቡ ትግል የተገኘው ይህ የጥገና ለውጥ እንዳይሰናከል ሕዝቡ ተባብሮ ሊከላከልለት ይገባዋል።
በተጨማሪም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ጸረ ሰላምና አንድነት ብሎም የሽብር ተግባር በማውገዝ ለዓለም ማህበረሰብ እንዲያሳውቁና በውጭ አገር ሆነው ለሽብር ቅስቀሳ የሚያካሂዱትን ግለሰቦች ባሉበት አገር ሕግ እንዲጠየቁ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ጥሪ ያደርጋል።
የኢትዮጵያውያን ሰላምና የኢትዮጵያ አንድነት ለዘላለም ይኑር!
አሸባሪዎች ለፍርድ ይቅረቡ!!
የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።