‹ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር››
መስከረም 13 2011 ዓ. ም.
‹‹ መሸ በሩን ዝጉት ከቀረ ልማዴ፣
ተከፍቶ ማደሩን አይወደውም ሆዴ፡፡››
የኢሣት ጋዜጠኞች መጪውን የሃገሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ በምሁራን ጥናታዊ ስራዎች መረጃ በማስደገፍ ትንበያቸውን ያቅርቡ ዘንድ የጋዜጠኛ ሙያችሁ ነው እንላለን!!! ወያኔ/ኢህአዴግ የሃገሪቱን ህገ መንግሥት፣ የወንጀለኛና የፍህታብሄር ህግ በሙሉ ላለፍት 27 አመታት ዓይኑን አጥፍቶታል፡፡ የህግ አውጭ፣ ህግ ተርጎሚና የህግ አስፈፃሚ ተናበው ይስሩ፣ የህግ ሉዓላዊነት ከሌለ ሠላምና ልማት የለም!!! በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ከሌለ የሃገር ህልውና አጠያያቂ ነው፡፡ ዜጎች የመኖር ዋስትና፣ የስብዓዊ መብት ነፃነት፣ በሃገራቸው ተዘዋውረው የመሥራት ነጻነት፣ የሚከበረው በህግ ነው፡፡ መንግሥት ቅድሚያ ለህግ የበላይነት መከበር መሥራት ይጠበቅበታል፣ ጋዜጠኞች ተግታችሁ ስሩ፡፡ ህወሓት/ኦህዴድ ኢህአዴግ በወንጀሉ ንሰሃ ገብቶ እንዳልነበር ከመቼው ረስቶት‹‹ግመሎቹ ይጎዛሉ ውሻዎቹ ይጮሃሉ››አለን!!!
በዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የአጋዚ ጦር ከካንፑ ወጥቶ በሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ በስናይፐር ተኮሾች አምስት ወጣቶች በአዲስ አበባ ገድለዋል፣ እርምጃው ወጣቶቹ መሣሪያ ለመንጠቅ ሞከሩ ቢባልም፣ እርምጃው ተመጣጣኝና ሚዛናዊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አልሞ ተኮሾቹ ከወገብ በታች ተኩሰው ቢመቶቸው ኖሮ ወጣቶቹ አይሞቱም ነበር፡፡ ከወገብ በላይ ከተተኮሰ ግን ለመግደል ሃራራ ሰላላቸው ነው እንላለን፡፡ ወላጆቻቸው እነዚህን ወጣቶች ለማሳደግ ብዙ አመታት ደክመዋል፣ የሰው ልጅ እንደ ባህር ዛፍ ተተክሎ የሚበቅል ችግኝ አይደለም እንላለን፡፡ ቡራዩ፣ አሸዋ ሜዳ፣ አስኮ ወዘተ የህዝብ ጭፍጨፋና ሰዎች ያረዱ ወንጀለኞች እንኮ ዝንባቸውን እሽ ያላቸው የለም፡፡ ይህን የተቃወሙ ሠልፈኞች ላይ የተፈፀመ ግድያ በአስቸኮይ ተጣርቶ መንግሥት ይቅርታ ይጠይቅ እንላለን፡፡ ለውጡ ከህወሓት/ኢህአዴግ ለኦህዴድ/ኢህአዴግ ከተሸጋገረ የመጀመሪያው የአጋዚ ጦር እርምጃ የወሰደበትና አጋዚ መሣሪያ ጠምዶ አዲስ አበባን መጠበቅ የጀመረበት ዘመን ሆኖል፡፡ በእናንተ ልጆች ላይ ቢሆንስ የደረሰው ምን ይሰማችሁ ነበር!!! መልዕክቱ ገብቶናል አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ፣ መቐሌ የመሸገውን ገዳይ ለመታደግ ሌላ ገሎ ማሳየት ቅጣቱ በህይወት ለሚኖሩት ዜጎች ነው፡፡ ይህን ግድያ ያልተቀወመ የፖለቲካ ድርጅት ነግ ለኔ ይበል እንላለን፡፡
ምሁራን በሚቸሩት ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ፣ በጊዜው መታረም ሲቻል ዝም ማለት ወደፊት ብዙ መሥዋትነት ያስከፍላል እንላለን፡፡ በእርግጥ ለውጥ ካለ የህግ ሉዓላዊነት መከበር ይኖርበታል፣ የወያኔ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ የወያኔ ሹማምንትና የጦር ጀነራሎች ለፍርድ እንዳይቀርብ ስምምነት እንዳለ አንድ ታሪክ ያወጣዋል እንላለን፡፡ ኢሣት ሚዲያ የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊት የት እንዳለ ለምን የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት መሪዎችን አይጠይቁም፣ ወታደራዊ ትርዒት የት ይካሄድ እንደነበርና አሁን ያለውን የሃገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በተመለከተ አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብ የህወሓት /ኢህአዴግን እኩይ ሴራ ከወዲሁ በመረጃ ማጋለጥ የኢሣትን ጋዜጠኞች የወደፊት የሃገሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ወታደራዊ ዘርፍ ትንበያ የበሰለ ያደርገዋል እንላለን፡፡
የህወሃት የጦር አበጋዞች መንግሥት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ኃይል ማለትም የአየር ኃይል ተዋጊ ጀቶችን ከውቅሮ ደብረዘይት አልመለሰም፡፡ የሃገሪቱ ታንኮች ናዝሬት እንዲመለስ፣ የጦር ግምጃ ቤቱ የጦር መሣሪያ በሙሉ በትግራይ ክልል ወደ ነበረበት ሥፍራ ዱኮም አለመመለሳቸው ያሳስበናል፡፡ ህወሓት ከኢትዮቴሌኮም የነበረውን አጠቃላይ የዜጎችን፣ የባንኮች ዲጂታል መረጃዎችን መቐለ መውሰዳቸው እንደዜጋ ያሳስበናል፡፡ የዋልታ፣ ፋናና ዋልፍ (ተኩላ) ብሮድካስት የቴሌቨዝንና ሬዲዬ አገልግሎት በወያኔ ስፖንሰር አድራጊነት ፕሮግራሙን ቀጥሎል፡፡ በተጨማሪ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ የነበረ የስለላ መረጃ መሣሪያ አስቀድሞ ተነቅሎ ወደ ትግራይ ተወስዶል መባሉ ያሳስበናል፡፡ በሙስና ወንጀል የሚጠየቁ የኢፈርትና ሜቴክ ሹማምንቶች የህዝብ ኃብት ዘርፈው በክልሉ ውስጥ ተደብቀዋል፡፡ ኢሣት ያለማሰለስ ይሄን ጉዳይ ማጋለጡን ይቀጥል እንላለን!!! የህወሓት/ኢህአዴግ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ለማስቀጠል አሊያም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሃገሪቱ የምትመራበት አጠቃላይ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ሁሉን አቀፍ ፍኖተ ካርታ እስካሁን አለመነደፉ ያሰጋናል፣ የህዝቡ የመኖር ህልውናና የሃገሪቱ እያንሰራራ የነበረው ኢኮኖሚ ዳግም ውድቀትና የመጪውን አገር አቀፍ ምርጫ እጣ ፈንታ ያሳስበናል፡፡ የህወሓት የ27 ዓመታት የግፍ አገዛዝ ዘመን የተፈፀሙ የዘር ፍጅት ተወናዬች፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስፈፃሚዎች፣ አፋኞች፣ ገዳዬች፣ ገራፉዎች ወንጀለኛ የሆኑ የደህንነት፣ የፖሊስና መከላከያ እንዲሁም የወያኔ አህአዴግ የፖለቲካ ካድሬዎች በፈፀሙት ወንጀል እስካልተጠየቁ ድረስ ሃገራችን ህዝብ በህግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል አይሆንም፡፡ የህግ ልዓላዊነት ሳይከበር ልማትና ሰላም አይኞርም፣ ወንጀለኞችን የሚደብቅ መንግሥት፣ ወንጀለኞችን አሳልፎ የማይሰጥና ከለላ የሚሰጥ መንግስት ተባባሪና ከወንጀለኞች ጋር ቃል ኪዳን የገባ መንግሥት መሆኑ አንድ ቀን በህግ ያስጠይቀዋል፡፡ በወያኔ 27 አመታት አገዛዝ በዘር ማጥፋት የተፈፀሙ የጅምላ ግድያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የአፓርታይድ ሥርዓት ወንጀሎች፣ ተጠያቂዎች ለፍርድ እስካልቀረቡ ድረስ በሃገሪቱ ሠላም አይመጣም፡፡ የገብረ ጉንዶን ሠራዊት በደመነፍሱ እጅ ለእጅ ተያይዞና እግር ለእግር ተቆላልፎ ትልቅ ወራጅ ወንዝ ይሻገራል፡፡ የፍርሃት ፖለቲካ ወንዝ አያሻግርም!!! የህግ ሉዕላዊነት በሌለበት ሃገር ፍትህ አይኖርም እንላለን!!! የወያኔ ፖለቲካ ጥንስስ ዘመን ተሸጋሪ የሸርና ተንኮል የመርዝ ብልቃጥ ነው፡፡ በድፍረት እናስወግደው!!! ህግ በሌለበት ሃገር ፍትህ የለም!!!
ከባህር ማዶ የገቡት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች የፈረደበት ህዝብ ሲገቡ አደግድጎ ዝናብና ፀሃይ ሳይል በሆታ ተቀብሎቸዋል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በመላ ሃገሪቱ እየተዘዋወሩ የድርጅታቸውን ፕሮግራም ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ተጠምደዋል፣ የምርጫ ጊዜ ይመስላል፣ እርስ በእርስም ይሻኮታሉ ህብረ ብሄር ፓርቲ ኬክ ያበላል፣ የጠባብ ብሄር ፓርቲ ቂጣ ነው ያሚያበላው ይባባላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ይሻልሃል፣ ትግራዋይነት፣ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ሶማሌነት ወዘተርፈ ይሻልሃል ይባባላሉ፡፡ አንድ አገር፣ አንድ ህዝብ!!! ይሄ ነው ባንዲራው፣ አንባሻ ያለው የሌለው ባንዲራ ይሻልሃል!!! የኦሮሚያ ባንዲራ፣ የትግራይ፣ ወዘተ የዘጠኝ ክልል ባንዲራ፣ ባንዲራ የተራበ ህዝብ፣ ሠልፍ የተጠማ ህዝብ፣ ዲስኩር የራበው ህዝብ መስሎቸው፡፡ የደርግ ጊዜ የነበረ ዘመቻና አዋጅ በዚህ የተተካ ይመስላል፡፡ ከባህር ማዶ የገቡት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች ሰዎችን ሀገርና ህዝቡን ከዚህ አስከፊ ችግር እንደሚያላቅቁ ከልቡ ያምንባቸዋል የእኛ ልጆች መጡ ብሎ ነው ህዝቡ የሚያምንባችሁ፡፡ በወያኔ ሥርዓተ መንግሥት ሁለት አስርት አድርባይ የነበሩ የወያኔ ካድሬ ምሁራኖች አንደበታቸውን ቅቤ አውጠው፣ ጉሮሮቸውን ማር አልሰው፣ እንጥላቸውን በዘይት ወልውለው፣ አንዴ በቴሌቪዥን መስኮት የዴሞክራሲውን ሥርዓት ለማዋለድ ህወሓት/ኢህአዴግን እያብጠለጠሉና፣ ኦህዴድና ብአዴን /ኢህአዴግ እያሞካሻ፡፡ አንዴ በሬዲዬ አርባ ክንድ አውቶማቲክ ምላስ፣ ላውንቸር የሚተኩስ አንደበት፣ ተርገብጋቢና ታጣፊ የእንስቶች ምላስ አንዴ በቴሌቪዥን፣ ብሎም በሬዲዩ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያ ፌዝቡክ፣ ቱተር፣ አንዴ በህልም አንዴ በእውን ለውጡን ያመጣሁት ባቆራጭ እኔ ነኝ! የለም በቆረጣ እኛ ነን! ይሉናል!!! በህቡዕ ግንኙነት እስከ አናቱ መልምለናቸው ነው እኛ!!!፣ ያደራጀነውን የወጣት ሠራዊት ብናዘው ምድር ቁና ትሆናለች!!! በዘራችሁ አትደራጁ ህብረ ብሄር ፓርቲ ይመጣላችሆል!!! ምርጥ ፓርቲ እንደ ቡና የታጠበና የተቀሸረ የእኛ ነው ይሉናል፡፡ አንዳንዶቹ የእኛ አገር የፖለቲካ ልሂቃን ከአውሮፓና አሜሪካ ለዘመናት ኖረው የዴሞክራሲን ቁንፅል ፅንሰ ሃሳብ በህሊናቸው ሳያሰርፁ ህዝብ ያስፈራራሉ!!! እንደ ባላባት ሽህ ሰው ከፊታቸው፣ ሽህ ሰው ከሆላቸው እንዲያጅባቸው ይሻሉ፣ ስንቶቹ ከፖለቲካ ሠራ ውጪ ለሃገራቸው ምን ሠርተው ያውቃሉ፡፡ በሃገራችን ፖለቲካ ሽሮ መብያ ከሆነ ሠነበተ የህወሓት/ኢህአዴግ የመለስ ካቢኔ ሚኒስትሮች በሙሉ አስራአንደኛ ክፍል ያልጨረሱ ቡችሎች ነበሩ፣ ወርዲያና የጋንታ መሪ የነበሩ ጀነራል ሆኑ፣ ሰላይ ፊርማቶሪ የነበሩ ዲፕሎማትና ጰጳስ ሆኑ፣ የሃገሪቱ ታሪክ ፀሃፊዎች ግራ ስለገባቸው ታሪክ መፃፍ ፈሩ፣ ካድሬዎቹ እራሳቸው ገድላቸውን አንዴ ገድለ ደደቢት! አንዴ ገድለ ሽሬ! አንዴ ገድለ ቢሊሱማ ዉልቂጤማ! አንዴ ዘመቻ ዋለልኝ ዘማርታ እያሉ መፃፍ ጀመሩ፣ በፊልም ቀረፁ፣ እዚህ ሃገር ከጠርሙሱ የወጣው ጂኒ አልተመለሰም፡፡ ወያኔ የዘራው የፖለቲካ ጥላቻ ስር ሰዶ፣ የዘር ግጭት በየቦታው ተከስቶል፣ የክልሎች የድንበር ግጭት የማያባራ ጦርነት እስከትሎል፡፡ ግብር ከፋዩ ደሞዝ የሚቆርጥለት ወታደርና ፖሊስ ቡራዩ፣አሸዋ ሜዳ፣ አስኮ ወዘተ የተካሄደውን የህዝብ ጭፍጨፋ መከላከል ለምን አልቻለም፣ የህዝብን ህይወትና ንብረት ለምን አልጠበቀም!!! የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል የጎረቤት ሱማሌን ሰላም ሲያስከብር በሃገሩ ለምን ተሳነው!!! ወያኔ ላለፉት 40 አመታት በስውሩ ዓለሙ ስፖንሰር በሚያደርገው ገንዘብና የጦር መሣሪያ መሆኑን ግን ሁሉም የፈሪ ልጅ ያውቃል!!! አገር አለኝ ብለው የገቡ ወገኖቻችን ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ አገሩን ሁሉ ከመዞር በቴሌቪዝንና በሬዲዬ፣ በስካይፕ ቀርበው ሃሳባቸውን ለደጋፊዎቻቸው ማሳጨት ይችላሉ እንላለን፡፡
ወያኔ ስለወሰደው የሃገር ሃብትና ንብረት ለማስመለስ የሚሞግት አንዳችም የህግ ሰው የለ!!! ህወሓት/ ኢህአዴግ ስለፈፀመው ወንጀል ለመፋረድ ፍርድ ቤት የሄደና የክስ ቻርጅ የከፈተ አንዳችም ተቃዋሚ ፓርቲ አሊያም ጥቃት የተፈጸመባት የለም!!! ኤርትራ የእኛ ነው፣ አሰብ የእኛ ነው ብለን ስንሞገት እንዳልነበር ወያኔ ስለወሰደው የሚሞግት ቀርቶ የሚናገርና የሚጮህ ከድፍን ሠልፈኛ አንድ ባጣ ያበድኩኝ መስሎኝ፣ ቤቴን ዘግቼ ሱባኤ ገባሁኝ፡፡ እናቴ ጎደኞቼ ከቤት ሲመጡ አባ ዘግተዋል፣ ሰው አያናግሩም እያለች ስንቱን የዴሞክራሲ ባልቴት፣ የለውጡ አዋላጂ ጎደኞቼን መለሰችልኝ፡፡ እኔ ‹‹የህዝቡ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፣ የብሄራዊ ዳቦ ድርሻ ጥያቄ ነው፣ የሥራ አጥ ጥያቄን ለመፍታት በአፋጣኝ ወያኔ የዘረፈውን ይመልስ ነው የምለው፣ የሃገር ሃብት ይመለስ›በማለቴ ሆነ እብደቴ፡፡ ታዲያ ጎደኞቼ ‹የውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን!!!›› ያሉኝን አልሰማ ብዬ ነው፡፡ ጎደኞቼ የሚያውቁት ነገር ያለ ይመስለኛል፣ በመጽሃፍ ገላጭ፣ በኮኮብ ቆጣሪ አሊያም በአባይ ጠንቆይ ይሁን እንጃ እንጂ!!! እሱን ተወዉ! እሱን አታንሳ ብለውኝ ነበር፡፡ ህዝበ አዳምና ሄዋን ለካ ህወሓት/ኢህአዴግ መቐሌ መሽጋ በሠላም እየኖረች፣ በህግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው!!! ብለው ሲሰብኩኝ ከለውጡ በኃላ ነው በፊት ብዬ እጠይቃለሁ፣ ከእስር ቤት የወጡ ዜጎች ላይ የደረሰ ስብአዊ መብታቸው የተደፈረ የተገሰሰ፣ የአካል ግርፋት የተፈጸመባቸው፣ ክስ ሰይቀርብባቸውና ሳይፈረድባቸው የታሰሩ፣ ክብራቸውና ማንነታቸው የተዋረደባቸው፣ የወሲብ ትንኮሳ ግብረሰዶም ወንጀል የተፈጸመባቸው፣ ሁሉ ዝም ብለዋል፡፡ በ1997 ዓ/ም ምርጫ ጊዜ በአጣሪው መርማሪ ኮሚሽን ተረጋግጦ በግፍ የተገደሉ 198 ሰዎች ገዳዬች ለፍርዱ ሳይቀርቡ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ፣ በሱማሌ፣ በወላይታ ፣ በሲዳማ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት ተዋናዬች ፍርድ ሳያገኙ፣ ይቅር በላቸው ይሉኛል!!! አልልም!! ለዚህ ነው ዛሬ የስው ልጅ እንደ ፍየል የሚታረድበት ዘመን የደረስነው፡፡ የ1997 ዓ/ም ሞቾች ደም በከንቱ ፈሶ በመቅረቱ ነው እላለሁ፡፡ በወያኔ ገዳዬች ልጆ አስክሬን ላይ ቁጪ በይ የተባለች እናት፣ ዛሬም የልጆን ገዳዬች እያየች እንድኖር ተገድዳለች፣ ዛሬም እስረኞች ገራፊዎቻቸውን እያየሁ እንዲኖሩ ተገደዋል፡፡ ዛሬም በፍርኃት የኖርንበት ህወሓት/ ወያኔ ለ27 ዓመታት ባደረሰብን የህሊና ጠባሳ፣ የእስራት ትዝታ፣ ለስንቶቻችን ቀኑ ሌት፣ ሌቱ ቀን ሆኖብን እንደቀረንና ያሳለፍነው ያልኖርንበት የልጅነት ትዝታ ውስጥ ተዘፍቀው በጣታቸው ምድር የሚቆረቁሩ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ይቅር በላቸው ይሉኛል፣ ይቅርታ ምንድን ነው፡፡ የኢህአፓ ልጆች ልክ ናቸው፣ የቀይ ሽብር ወንጀለኞችን በሃገር ውስጥና በባህር ማዶ እያሳደዱ ዛሬም ለፍርድ ያቀርባሉ፡፡ ስብዓዊ መብት የጣሰ የሰው ልጅን ያሰቃየና የገረፈ፣ የዘር ፍጅት ለፈፀመ ወንጀለኛ፣ ሴት ለደፈረ ኮርማ፣ ህፃን ለገደለ ወያኔ ይቅር በለው የሚል ምድራዊም የሊቀ ሊቃውንት አሊያም ሃይማኖታዊም መፅሃፍ የለ ይመስል!!! እነዚህ ገዳዬች፣ እነዚህ ገራፊዎች ለፍርድ ቀርበው የሚቀጡት ሌላው ሹም እንዳይደግመው ለማድረግ ነው፡፡ ኢህአፓዎቹ ‹‹መቼም የትም አይደገም!!!›› ብለው ለቀይ ሽብር›› ሠመዓታት ጎዶቻቸው ሃውልትና ሙዚየም ያቆሙላቸው ለዚህ ነበር፡፡ ሆኖም በሙዚየሙ ውስጥ ኢህአፖዎቹም ያለፍርድ የገደሎቸው ሰዎች ሁሉ ቢዘከሩ ሙዚየሙ ሙሉ ይሆን ነበር፡፡ በዚያ ትውልድ ያለቁ የቀ.ኃ.ሥ 60ዎቹ ሹማምንት ጀምሮ የኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኢጭአት፣ ወዝሊግ፣ ሰደድ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ተዋናዬች ጀነራል መኮንኖች ሁሉ፣ የኢትዩጵያ ልጆች በታሪክ ሊዘከሩ ይገባል፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ከዚህ እልቂት ተምሮ ህይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ የደርግ ፋሽታዊ ዘመን መቼም የትም አይደገም!!!›› ብለን ሃውልት ባቆምን በማግስቱ፣ ለምን መግደል፣ ማሰር፣ መግረፍና ማረድ በወያኔ ተደገመ፡፡ በባህር ማዶዎቹ መገናኛ ብዙሃንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢሳት፣ ኦኤምኤን ወዘተ የቴሌቪዝንና ሬዲዮ የተዘገበው በወያኔ የተፈፀመ የጅምላ መቃብሮች በጋምቤላ፣ በሱማሌ፣ በሲዳማ፣ በሐረር፣ በባሌ፣ በአዲስ አበባ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ያሉ የጂምላ መቃብሮች ሳይወጡ፣ የህግ ሉዓላዊነት በሃገራችን ይከበር ይሆን ወይስ ተረሱ!!! ይህ ዓይነት ወንጀል በቀጣይስ ላለመደገሙ ምን ዋስትና አለን!!! ወያኔ አድብቶል እንጂ አልሞተም!!! ወያኔ እንደ እባብ አፈር ልሶ፣ መሬት ምሶ፣ እንደ እበት በስብሶ እንደ እባብ ቆዳውን ለውጦ ብቅ ይላል፣ አንዴ በአብዬታዊ ዴሞክራሲ፣ አንዴ በሊብራል ዲሞክራሲ፣ አንዴ በዴሞክራሲ አንዴ በፀረዴሞክራሲ፣ አንዴ በህብረብሄር ፓርቲ አንዴ በብሄር ፓርቲ ይመላለሳሉ፡፡ የፍርሃት ፖለቲካ ወንዝ አያሻግርም!!! ህግ በሌለበት ሃገር ፍትህ አይኖርም!!!
በደርግ ዘመን የለውጡን አራማጆች ‹‹የለውጥ ሃዋርያት›› ይሎቸው ነበር፡፡ ለህዝቡ ዲስኩር ሲጀምሩ ‹‹በ1966 አብዬት ፈንድቶ፣ የቀ.ኃ.ሥ ስው በላው ስርዓት … ›› ብለው መስበክ ከጀመሩ ቁርስ አፉ ሳያረግ የወጣ ገበሬ ለእራቱ ቤቱ ይገባ ነበር፡፡ ዛሬም ‹‹የዴሞክራሲያዊው ለውጥ አዋላጆች›› ምሁራኖች የዴሞክራሲ ሃዋርያት›ቢባሉ በተሸለ ነበር፣ ባለፈው አትቆዝም፣ ወደፊትህ እይ፣ ይቅር ለእግዜር በል፣ በህግ ፊት ሁሉም እኩል ነው!!! ይሉናል፡፡ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆኑ ምላሳዊ ጋዜጠኞች ትላንት የሚዲያ መንኮራኩር ጠፍር ላይ አምጥቀው በሁለት አሃዘ አደግን፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ገባን እንዳላሉን፣ ዛሬ አንዴ የሜቴክ አንዴ የኢፈርት ሙስና ይገልፁና አድበስብሰው ያልፉታል፣ የእምነት አባቶችን ሥራ እየተሸሙ የፈሪሃ እግዚአብሄርን ይቅርታ ይሰብካሉ፣ አዲሱን ለውጥ ይነውጡታል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዬ ተዋናይ ጋዜጠኞች ‹‹ የአስቸኮይ ጊዜ አዋጅ ናፈቀን!!!›› አለ ህዝቡ የሚል ዜና ያስደምጣሉ፡፡ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር ‹ሞንጆሪኖ› ቃለመጠይቅ ‹‹አብዬታዊ ዴሞክራሲ፣ የብሄር ፌዴራሊዝም›› የኢህአዴግ አዲሱ ለውጥ አራማጆች ዶክተር አብይ አህመድ ትክክለኛ መስመሩን እንደሚከተል በኢቲቪ ገልፃለች፡፡ የወያኔ ፀረዴሞክራሲ ኃይል ማሞካሸት ተጀምሮል፡፡ የወያኔ/ኢህአዴግ የፖለቲካ መረብ መልኩን ቀይሮ ከመቀሌ በመተወን ላይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከህግ ፊት እኩል ከሆነ መቀሌ የመሸገው የወያኔ ፋሽስቶች ለ27 ዓመታት የፈፀሙት ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የወያኔ ወንጀለኞች ለህዝብ ሳይቀርብ በኢትዮጵያ ሠላም አይመጣም፡፡ በሃገሪቱ ውስጥ የሚከናወነው አለመረጋጋት ምንጩ ወያኔ በገንዘብና ጦር መሣሪያ ስፖንስር የሚያደርገው የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመጀመሪያ የህወሓት የጦር መሣሪያ ክምችትና የተዘረፈ ኃብት ጠይቀው በማስመስልና በእውን የምናየውን በመንግሥት ውስጥ መንግሥት› የአዲስ አበባው መንግሥትና የመቐሌው መንግሥት እንዳለ እያያችሁ የተጨፈናችሁ ሁሉ አንድ ቀን ፍንትው ብሎ ሴራው ይገለፅላችሆል እንላለን፡፡ ይህን ሃሳብ ቁምነገር ዘጠና ከመቶው የፖለቲካ ምሁራን ሳይገባው ቀርቶ ሳይሆን በአድርባይነት ካልሆነ በስተቀር ወያኔ በሪሞት ኮንትሮል ሃገሪቱን እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ አጥተውት አይደለም!!! ወያኔ ሃገር ዘርፎ መቐሌ መሽጎል አዲስ አበባ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብና የብር ዝውውር እጥረት ተከስቶል፣ የሃገሪቱ የተዘረፈ ኃብት እስካልተመለሰ ድረስ የኢኮኖሚ ቀውሱ ይባባሳል፡፡ የህግ የበላይነት ይከበር!!! የህግ አውጭ፣ ህግ ተርጎሚና የህግ አስፈፃሚ ተናበው ይስሩ፣ የህግ ሉዓላዊነት ከሌለ ሠላምና ልማት የለም!!!
ቡራዩ፣አሸዋ ሜዳ፣ አስኮ ወዘተ ዜጎች ለተሠው ሰማእታት መታሰቢ ለቤተሰቦቻቸው መፅናኛ ትሁን!! ከገዳዬቻችን፣ ከአራጆቻችን፣ ከገራፊዎቻችን፣ ከወንጀለኛች ጋር እየፈራን አብረን እንድኖር ተገደናል፡፡ ይህ የወንጀለኞች ድርጊት እንደማይደገም ምን ዋስትና አለ!!! እያሉ ነው ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ዜጎቸች ሹሞችን የጠየቁት!!! መንግሥት ኃላፊነቱን ይውሰድ ድርጊቱ ከተደገመ መንግሥት ለፍርድ ይቅረብ እንላለን፡፡ የህግ ትርጉሙ ይሄ አይደለም! ፍትህ እንሻለን፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ቆሰለ እንጂ አልሞተም!
ወንጀለኞች በህግ ካልተቀጡ ወንጀለኞች ይፈለፈላሉ!!! ወያኔ ወንጀለኞችን የሚደብቅ የማፍያ መንግሥት ነው!!!
አበው ለፈሪ ሲተርቱ ‹‹ ፈሪ ፈራና እጉድባ ቢኛ፣ ጆሮውን በላው ያይጥ ቀበኛ፣ ቂጡን ደገመው የእባብ ሸረኛ፡፡››
ረብዕ መስከረም ዘጠኝ ከሌሊቱ 9 ስዓት ተፃፈ!!!
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።