ቦርከና
መስከረም 21 2011 ዓ.ም.
የቤንሻነጉል ጉምዝ ካማሽ ዞን አራት ባለስልጣናት ግድያን ተከትሎ ከአርብ መስከረም 18፣ 2011ዓ.ም ጀምሮ በቤንሻጉል ጉሙዝ ከማሺ ዞን እና በኦሮሚያ ክልለ አጎራባች ወረዳዎች በተፈጠረ ግጭት ስድስትን ንጹሃን ሰዎች መገደላቸዉንና ሌሎች መቁሰላቸዉ ተገለፀ።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ካማሽ ዞን የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጋር በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ለመሳትፍ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ የካማሽ ዞን ከፍተኛ ባለሰልጣናት ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን ተጉዘዉ በመመለስ ላይ እንዳሉ ባልታወቁ ታጣቂ ሀይሎች በተሰነዘረባቸዉ ጥቃት 4 ሰዎች መገደላቸዉ በአካባቢዉ ከፍተኛ ዉጥረት ፈጥሮ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በምዕራብ ኦሮሚያ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥም ከኦነግ ጋር በተደረገው ስምምነት በስሙ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ካምፕ እንዲገቡ እየተሰራ ነው ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ቅሊጡ ሸንኮሬ ዞን የፀጥታና አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ታከል ቶሎሳ በበኩላቸዉ በአካባቢዉ ተከስቶ በነበረዉ ግጭት ምክኒያት ከሃምሳ በላይ የመኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ፤አራት ሰዎች እንደቆሰሉና በርካቶች ከመኖሪያቸዉ እንደተፈናቀሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡
አክለዉም የፀጥታ ሀይሎች ሁኔታዉን ለማረጋጋት ወደ ሥፍራዉ እንደተሰማራና የተፈጠረዉን ችግር በፍጥነት ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሰይፈዲን ሀሩን አደጋዉን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ጥፋቱን የፈጸሙት ማንነታቸዉ ያልታወቁ ፀረ ሰላም ሀይሎች እንደሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ሥፍራዉ መሰማራቱ ቢገለፅም ከችግሩ አንጻር ቁጥሩ እጅግ አነስተኛ መሆኑን በአካባቢዉ የሚኖሩ ግለሰቦችን በማነጋገር መረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአካባቢዉ ይኖሩ የነበሩ የጉምዝ ተወላጆች ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ ወደ ጫካ መሰደዳቸዉንና የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ በአጎራባች ወደሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች እንደተሰደዱ የቤንሻንጉል ክልል የኮሙኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ዘላለም ጃለታ ተናግረዋል፡፡
ከወር በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዋና ከተማ አሶሳ በተፈፀመ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግጥት የ10 ንፁሃን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች መፈናቀላቸዉ ይታወሳል፡፡
ከስፍራዉ የተፈናቀሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የአማራ ክልል ተወላጆች በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናትና ትምህርት ቤቶች ተጠልለዉ እርዳታ ሲደረግላቸዉ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ በተለያ ክልልሎች ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካቶች የመኖሪያ ቀያቸዉን ጥለዉ እንዲሰደዱ ተገደዋ፡፡
በያዝነዉ ዓመት ብቻ በኦሮሚያ፤ በሶማሊ፤ በደቡብ ክልሎች ተፈጥረዉ በነበሩ ግጭቶች ምክኒያት ከ1.6 ሚሊየን በላይ ዜጎች መሰደዳቸዉን ዩኒሴፍ በነሃሴ ወር ያወጣዉ መረጃ ያመለክታል፡፡