መስከረም 25 ፤ 2011 ዓ.ም
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሃዋሳ 11ኛ ድርጂታዊ ጉባዔውን ሲያካሂድ የነበረው ኢህአዴግ ዛሬ ዶ/ር አብይ አህመድን እና አቶ ደመቀ መኮነንን እስከመጪው ጉባዔ ድረስ እንዲያገለግሉ በድጋሚ በሊቀመንበርነት እና በምክትል ሊቀመንበርነት በመምረጥ አጠናቋል ።
ያስመራጭ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ጸጋየ ከተሰጠው 177 ድምጽ 176 ዶ/ር አብይ አህመድ ፤ አቶ ደመቀ መኮንን ደሞ 149 ድምጽ በማግኘት በሊቀመንበረነት እና በምክትል ሊቀመንበርነት መመረጣቸውን ለጉባዔተኛው ሲያበስሩ ጉባዔተኛው በሞቀ ጭብጨባ ደስታውን ገልጿል፤ ሌላኛው ተወዳዳሪ የነበሩት ዶር ደብረጺዎን ገብረሚካዔል ደሞ ከተሰተው ድምጽ 15 አግኝተዋል።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትናንት እንደዘገቡት ጉባዔው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በአወንታዊ መልክ እንደገመገመ እና ለውጡን በትጋት ለማስቀጠል አቋም ይዟል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል አጋር ድርጂቶች በመባል የሚታወቁት ድርጂቶች በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና በስራ አስፈጻሚ ደረጃ እንዲሳተፉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል አንደ ፋና ብሮድጋስቲንግ ዘገባ።
ዛሬ ወደተጠናቀቀው ጉባዔ ከማምራታቸው በፊት አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጂቶች የየራሳቸውን ጉባዔ በማድረግ የተለያዮ ውሳኔዎች በማሳለፍ በአብዛኛው ወጣት አመራሮችን በማከላዊ ኮሚቴ አባልነት መምረጣቸው ይታወሳል።
ሁለት ድርጂቶች ደሞ የስያሜ እና የአርማ ለውጥ ጭምር አድርገዋል፤ በዚህም መሰረት ቀድሞ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጂት (ኦህዴድ) ይባል የነበረው ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፤ ቀድሞ ብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ይባል የነበረው ደሞ አማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ በሚል የስም ለውጥ ማድረጋቸው ይታወቃል።