spot_img
Tuesday, March 5, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሲዳማ ፖለቲካ (በመኮንን የሱፍ)

የሲዳማ ፖለቲካ (በመኮንን የሱፍ)

(በመኮንን የሱፍ)
መስከረም 25 2011 ዓ.ም

ኢህአዴግ ያነበረው የጎሳ ፌደራሊዝም ስሁትነት ከሚገለጥባቸው ክልሎች አንዱ ከ50 በላይ የሚሆኑ ብሄሮችን አጭቆ የያዘው፣ሌሎች ክልሎች በዘራቸው ሲሰየሙ በአቅጣጫ የተሰየመው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ነው፡፡በዚህ ክልል ውስጥ ከሚኖሩ በርካታ ብሄረሰቦች አንዱ የሲዳማ ብሄረሰብ በአቅጣጫ ስም ከተሰየመው ክልል ወጥቶ፣በብሄሩ ስም የሚጠራ የራሱን ክልል የመመስረት ጥያቄ ሲያቀርብ ዘለግ ያሉ አመታትን አስቆጥሯል፡፡

የሲዳማ ብሄር ይህን ሲል ከሚያቀርባቸው መከራከሪያዎች ቀዳሚው በህገ-መንግስቱ የተደነገገውን፣ ለብሄረሰቦች የተሰጠውን እስከ መገንጠል የሚዘልቀውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጋው የሲዳማ ህዝብ ቁጥር እና የያዘው ሰፊ የቆዳ ስፋት በደቡብ ክልል ካሉ ብሄረሰቦች ቀዳሚውን አብላጫ ቁጥር የሚይዝ ሲሆን በሃገር ደረጃም ከሶማሌ ህዝብ ቀጥሎ አራተኛው ትልቅ የህዝብ ቁጥር ነው የሚለው መከራከሪያ ነው፡፡

እንደ ሶስተኛ ምክንያት ሊነሳ የሚችለው ዞኑ ቡና አብቃይ ከሆኑት አንዱ በመሆኑ ክልል ለመሆን የተፈጥሮ ሃብትም አያንስም በሚል ነው፡፡የሃዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን መሬት ላይ መከተሟ የሲዳማ ልሂቃን ከተማዋን ለሲዳማ ክልል ዋና ከተማነት አጥብቀው እንዲመኟት ያደረገ ሁነኛ ምክንያት ነው፡፡ይህ ነገር ኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ በግዛቴ ላይ በመንጣለሏ ለእኔ ትገባለች ከሚለው ነገር ጋር ይመሳሰላል፡፡

ይህ ተመሳስሎሽ ጉዳዩን በየፈርጃቸው የሚያሚያቀነቅኑትን ኦነጎችን ከሲአኖቸ መሳ ሳያደርግ አልቀረምና OMN የተባለው በኦሮሞ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ሚዲያ ለሲአን አባላት እና ደጋፊዎች ድምፅ ሊሆን ይሞክራል፡፡ በዚሁ ሚዲያ ዘወትር ብቅ የሚሉት እነ ኦቦ ፀጋየ አራርሳም የሲዳማ ልሂቃንን ጥያቄ አንዳንዴ ከራሳቸው ከሲዳማ ልሂቃ በበለጠ አክራሪነት ሲያራግቡት ያጋጥማል፡፡

የሲዳማ ክልልን ጥያቄ ከፊት ሆኖ የሚመራው በታዋቂው የሲዳማ ልሂቅ አቶ ወ/አማኑአኤል ዱባለ የተመሰረተው እና እስከ ዕለተ ሞታቸው በእሳቸው ሲመራ የነበረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) በመባል የሚታወቀው ፓርቲ ነው፡፡ይህ ፓርቲ እነ ኦነግ፣ህወሃት እና የመሳሰሉት ዘውግ ተኮር ፓርቲዎችን መመስረት ተከትሎ በደርግ ዘመን የተመሰረተ ማርኪሲስት ሌኒኒስት ፓርቲ ነው፡፡መሪው አቶ ወ/አማኑኤል ዱባለም ከሲዳማ ባላባት ወገን የሆኑ፣ የሰፊ መሬት ባለቤት ከሆኑ የሲዳማ ፊውዳል ቤተሰቦች የተገኙ ነበሩ፡፡በዚሁ ምክንያት የሰፊ መሬት ባለቤት ፊውዳሎች ብቻ በሚገቡበት የአፄው ዘመን ፓርላማ ተመራጭ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡

ሲአን እንደ ህወሃት እና ኦነግ ጎላ ያለ ባይሆንም በሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች አምባ ይዞ በደርግ ላይ የትጥቅ ትግልም የሞከረ ፓርቲ ነበር፡፡ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባም ሃገር ለማሸጋገር ከተጠሩት ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች አንዱ ሲአን ነው፡፡ህወሃት ደቡብ ክልልን በአንድ ጨፍልቆ፣ደኢህዴን የሚባለውን ፓርቲ አቋቁሞ “አስተዳዳሪያችሁ እሱ ነው” ከማለቱ በፊት አብዛኞቹ በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሄረሰቦች የራሳቸው ፓርቲዎች ነበሯቸው፡፡ ሲአንም ከነዚህ አንዱ ነበር፡፡

ሆኖም አቶ መለስ የደቡብን ክልል በአንድ ጨፍልቀው ደኢህዴን የሚባለውን እሽ ባይ ፓርቲ በሁለት እግሩ ካቆሙ በኋላ በመጠኑ የራሱ መንገድ የነበረውን ሲአንን ፊት መንሳት ጀመሩ፡፡ኦህዴድ ከተቋቋመ በኋላ ለኦነግ የገጠመውን የሚመስለው እጣ ሲአንንም ገጠመው፡፡ሲአኖች ልክ እንደ ኦነግ ለሁለት ተከፍለው ገማሾቹ ተሰደው ወጥተው ብረት አንግተው ኤርትራ መመሸግም ሞክረው ጎልቶ መውጣቱ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ሌላው ክፋይ በዶ/ር ሚሊዮን ቶማቶ የሚመራው እስከ አሁን በምርጫ የሚሳተፍ ግን ደግሞ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በአንክሮ የሚታይ አቅመቢስ ፓርቲ ነው፡፡

ሲዳማን ራሷን የቻለች ክልል የማድረጉን ጥያቄ አጥብቆ የመጠየቁን ነገር በግልፅ የሚያነሳው ሲኣን ቢሆንም በአፍቃሬ ህወሃት/ኢህአዴግነቱ በሚታወቀው ደኢህዴን ውስጥ የተሰገሰጉ የሲዳማ ልሂቃንም በውስጣቸው ይዘውት የሚወዘወዙለት ጉዳይ ነው፡፡ ሃዋሳን ማዕከሏ ያደረገች የሲዳማ ክልልን እውን የማድረጉን ነገር በተመለከተ በሲአንም ሆነ በደኢህዴን ውስጥ ያሉ፣ከፌደራል እስከ ክልል በተዘረጋ ግዙፍ የመንግስት ስልጣን ላይ የተሰሙ፣የወንበር እድል ያልቀናቸው ማናቸውም የሲዳማ ልሂቃን በጠቅላላ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በወል የሚጋሩት ናፍቆት ነው፡፡

በአንፃሩ ከመለስ እስከ አብይ በዘለቀ ሁኔታ የሃገሪቱ መንግስት የሲዳማ ክልልነትንም ሆነ አዋሳን የሃሳባዊው ክልል ዋና ከተማ አድርጎ የማፅናቱን ሃሳብ እምብዛም አይወዱትም፡፡የዚህ ዋናው ምክንያቱ የሃዋሳ ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሃዋሳ ከተማ የክልሉ ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል ሃያ ሰባት አመት አለፋት፡፡ በዚህ ሃያ ሰባት አመት ውስጥ ከተማዋ በፍጥነት የምታድግ ውብ ከተማ ከመሆኗ የተነሳ የሃገሪቱ ሁለተኛ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ የፌደራሉ መንግስት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች የሚከወኑባት፣ከወዳጅ ሃገር የመጡ የፌደራሉ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ እንግዶች የሚስተናገዱባት፣አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች የሚርመሰመሱባት፣ቱሪስቶች የሚዳረሱባት በፌደራሉ መንግስት በስስት የምትታይ ከተማ ነች፡፡

ከተማዋ እንዲህ አድጋ ላያት የምታማልል እንድትሆን ከፌደራል እስከ ደቡብ ክልል የዘለቀ የወል ንዋይ ፈሶባታል፡፡የደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ ሃዋሳን በማሳደጉ በኩል ከሲዳማ ህዝብ እኩል አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ሃዋሳ የደቡብ ክልል ከተማ ሆና ስትከተም ከተማዋን ያስዋበው በጀት የሚፈሰው በሁሉም የክልሉ ብሄረሰቦች ስም ነው፡፡ዞን ቀርቶ የወረዳ ከተማ የማይመስሉ እጅግ ያላደጉ ዱራሜን፣ተርጫ፣ጅንካ የመሰሉ ከተሞችን የያዙት በክልሉ ያሉ ዞን ህዝቦች የሚፅናኑት በሃዋሳ ነው፡፡

የፌደራሉ መንግስት በበኩሉ መናገሻውን አዲስ አበባን ፈጣን በሚባሉት የትራንስፓርት ዘዴዎች ሁሉ(በአየር መንገድ፣በፈጣን መንገድ፣በባቡር) ከሃዋሳ ጋር ማገናኘትን ይሻል፡፡ የፌደደራሉ መንግስት አይኑን በከተማዋ ላይ በመጣሉ ዝንባሌ ሳቢያ እንደውም በአቶ መለስ ዘመነ-መንግስት ከተማዋን የፌደራል ከተማ ለማድረግ ዝግጅቱን ጨርሷል የሚል ወሬ ሲናፈስ ከርሟል፡፡የፌደራሉ እና የክልሉ ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ አይናቸውን የሚያሳርፉባትን አዋሳ ከተማን የሃሳባዊው የሲዳማ ክልል መናገሻ የማድረግ ከባድ ምኞት ያላቸው የሲዳማ ልሂቃን በበኩላቸው ሃዋሳን ማዕከሏ ያደረገች የሲዳማ ክልል ለመመስረት ከፍተኛ ትግል ሲደርጉ ኖረዋል፡፡

በዚሁ ትግላቸው ሞትን እና እስራትን አስተናግደዋል፡፡በ1995 ይህንኑ የክልል ጥያቄ አንግበው አደባባይ የወጡ ከአዋሳ ዙሪያ የሲዳማ ገጠራማ ቀበሌዎች የመጡ የሲዳማ ተወላጆች በጥይት የተቆሉበት “የየሎቄው ግድያ” በመባል የሚታወቀው እልቂት በሰፊው የሚታወቅ ነው፡፡ከሎቄው ግድያ በኋላ ጋብ ብሎ የነበረው የሲዳማ የክልል ጥያቄ ከምርጫ 1997 ማግስት በኋላ አገርሽቶ አቶ መለስ ራሳቸው አዋሳ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪ እንዲሰጡ ግድ ብሎ ነበር፡፡ አቶ መለስ በ1999 በአዋሳ ከተማ ተገኝተው ከሃገር ሽማግሌ እስከ የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙበት ውይይት ቢየደርጉም ሲዳማዎች የሚፈልጉትን የሲዳማ ክልል እነሆ ማለት አልቻሉም፡፡

በምትኩ ብልጣብልጡ አቶ መለስ ክልል ትጠይቃላችሁ እንጅ በሃዋሳ ከተማ ውስጥ ያለው የሲዳማ ህዝብ ቁጥር የሰባተኛ ደረጃን የያዘ ነው፤አብዛኛው ነዋሪ አማራ፣ወላይታ፣ጉራጌ፣ትግሬ፣ከምባታ፣ስልጤ ሆኖ እናንተ ሰባተኛ ናችሁ፡፡ስለዚህ ክልል ከመጠየቃችሁ በፊት በከተማው ውስጥ ያለውን ህልውናችሁን አሳድጉ፡፡ለዚህም በገጠር የሚኖሩ አምስት ሽህ የሲዳማ አባወራዎች በአስቸኳይ በሃዋሳ ከተማ መሬት ይሰጣቸው ተብሎ አምስት ሽህ ብር ማስያዝ የቻለ ሲዳማ አዋሳ ውስጥ 200 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ሆነ፡፡ከዚህ በተጨማሪ በሲዳማ ክልል ውስጥ ወደ ሃያ የሚደርሱ አዳዲስ ወረዳዎች እንዲዋቀሩ ተደረገ፡፡ጥያቄን በቀጥታ መመለስ የማይሆላቸው “አራዳው” አቶ መለስ እንዲህ ባለ ከጥያቄው ጋር ፈፅሞ በማይገጥም መንገድ የሲዳማን የክልል ጥያቄ አድበስብሰውት አፈር ገቡ፡፡

የልባቸው ያልደረሰው የሲዳማ ተወላጆች ታዲያ አቶ መለስ የቸሯቸውን የመሬት እደላም ሆነ የአዳዲስ ወረዳዎች መዋቅር አመስግነው ተቀብለውም በየአመቱ በሚያከብሩት ጨንበላላ በተባለው የዘመን መለወጫ በዓላቸው ሲዳማ ያልሆነውን የሃዋሳ ነዋሪ ምቾት እንዳይሰማው በማድረግ ቅሬታቸውን ያሳያሉ፡፡በየአመቱ የጨንበላላ በአል በደረሰ ቁጥር ሲዳማ ያልሆነው የከተማው ነዋሪ የቀኑን በሰላም ማለፍ በፀሎት ጭምር ይለማመናል፡፡ የሲዳማ ተወላጅ ንብረቶች ያልሆኑ ንግድ ቤቶች በጊዜ ይዘጋሉ፣የመጠጥ ቤቶች ጠጥቶ በልቶ በማይከፍል፣ይባስ ብሎ የምግብ መጠጥ ማቅረቢያ እቃዎቻቸውን ዱቄት እስከ ማድረግ በሚደርስ የሲዳማ ጎረምሳ ድርጊት ይሰቃያሉ፡፡በአሉ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚከበር መሆኑ ደግሞ ከሲዳማ የማይወለደውን የአዋሳ ከተማ ነዋሪ እንግልት ያከፋዋል፡፡ችግር የመንግስታቸውን ወንበር እስካልነቀነቀ ድረስ ችግር የማያሳስባቸው አቶ መለስ የአዋሳን ህዝብ አመታዊ እንደግልት ነገሬ ብለው ሁነኛ መፍትሄ ሰጥተውት አያውቁም፡፡

የቤት ስራው ግን እየተንከባለለ ዛሬ ላይ ደረሰና ዶ/ር አብይ ተስተካክለው እንኳን ወንበራቸው ላይ ሳይቀመጡ ያጣድፋቸው ገባ፡፡ዶ/ር አብይ ወንበራቸው ላይ ከመቀመጣቸው የመጀመሪያውን ፈተና የደቀነባቸው ይኽው ከወደ አዋሳ የመጣው የክልል ጥያቄ ነው፡፡በዶ/ር አብይ ዘመን የተደረገው የሲዳማ የክልል ጥያቄ እንቅስቃሴ መስመሩን የሳተ፣ ሲዳማ ባልሆነው የአዋሳ ከተማ ነዋሪ በተለይ በወላይታዎች ላይ እጅግ አስደንጋጭ አረመኔያዊ የግድያ ድርጊቶች የተስተዋሉበት ነው፡፡የሰው ልጅን በድንጋይ ቀጥቅጦ ገድሎ ቤንዚን አርከፍክፎ እስከማቃጠል የደረሰ፣በቀን በብርሃን የሰው ቤት ከፍቶ ገብቶ ዝርፊያ የተደረገበት፣የግለሰብ ንብረት የሆኑ መኪኖች የተቃጠሉበት በርካቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናሉበት ለሶስት ቀን የቆየ እጅግ አሰቃቂ እና አስነዋሪ ድርጊት ነበር፡፡

የሲዳማ ክልል ጥያቄን እንደ ሲአኖቹ ጮክ ብለው ባያነሱትም በልባቸው ይዘውት የሚጓዙት የሲዳማ ብሄር ተወላጅ የደኢህዴን ባለስልጣናት ይሄ ሁሉ አሰቃቂ ጥፋት ሲደረግ ሊያስቆሙ ያልፈለጉት ምናልባትም ነገሩን ሲያቀናጁ የነበሩት የክልል ባለቤት የመሆን ፍላጎታቸውን በዚህ መንገድ ለማሳካት የሚቻል መስሏቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሰቃቂውን ግድያ በማቀናበር በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተጠርጥረው ዛሬ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ አሁን በቁጥጥር ስር ያሉት በወቅቱ የከተማው ከንቲባ የነበሩት አቶ ቴድሮስ ገቢባ ኢቲቪ ስለረብሻው አሳሳቢነት ሲጠይቃቸው “ዓመት በዓላቸው ስለሆነ ወጣቶች ደስታቸውን መግለፅ መብታቸው ነው፤ ማንም አይከለክላቸውም” ሲሉ ነበር ፍርደገምድል ንግግር የተናገሩት፡፡

ጥያቄው የክልል ጥያቄ ነው እየተባለ ክልል ለመስጠትም ለመንፈግም ስልጣኑ የሌላቸውን ለፍቶ አዳሪ ወላይቶችን ልጅ አዋቂ ሳይሉ ቀጥቅጦ መግደል ግንኙነት የለውም፡፡ ነገሩ በወላይቶች ተጀመረ እንጅ በቀጣይ ቀናት ደግሞ ሌሎችን ብሄረሰቦች የማጥቃት እቅድ እንደነበረው ነው የሚነገረው፡፡ወላይቶች መጀመሪያ የሆኑበት ምክንያት ምናልባትም አዋሳ ላይ ሌሎች ብሄሮች ያላቸው ብዙ ቁጥር ከተማዋ የሲዳማ ክልል እንዳትሆን እንደከለከ አቶ መለስ ቀደም ብለው ከጠቆሙት ጋር የሚዛመድ ሆኖ በወላይቶች ላይ የበረታው እና የእነሱ ጥቃት ቀዳሚ እንዲሆን ያደረገው ቀደም ሲል ታሪካዊ የሆነ በሁለቱ ብሄሮች መሃከል የኖረ የውድድር ስሜት እንደሆነ ይነገራል፡፡በተጨማሪም በ1995ቱ የሎቄው ግድያ የፌደራል ፖሊስ የሲዳማ ተወላጆችን በገደለበት ወቅት ወላይታው አቶ ኃ/ማርያም የደኢህዴን ሊቀመንበር እና የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩ መሆናቸው ነገሩን ሳያባብሰው አልቀረም፡፡

በስልጣናቸው ማግስት አዋሳ ላይ የተከሰተው አሰቃቂ ግድያ ያበሳጫቸው ዶ/ር አብይ አህመድ በአዋሳ ከተማ ተገኝተው በመልካም አንደበት ረጋ ብላችሁ አስቡ ሲሉ ከመምከር በዘለለ ሊፈይዱ የቻሉት ነገር የለም፡፡የሲዳማ የክልል ጥያቄን ለፌደራ መንግስት ለመመለስ አስቸጋሪ የሚያደርገው ክልል ጠያቂዎቹ ሊመሰርቱት ለሚመኙት ክልል ዋና ከተማው አዋሳ ብቻ እንዲሆን መፈለጋቸው ነው፡፡ከላይ እንደተጠቀሰው አዋሳ በመላው የደቡብ ክልል ህዝቦችም ሆነ በፌደራል መንግስቱ በስስት የምትታይ ከተማ ነች፡፡ ይህችን ከተማ ለሲዳማ ክልል ዋናከተማነት መስጠት የፌደራል መንግስቱ በተቀረው የደቡብ ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲገጥመው ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ የፌደራል መንግስቱ ራሱ በከተማዋ ላይ ጥብቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፍላጎት አለው፡፡ በአቶ መለስ መንግስት እንደ ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ሃዋሳን ሳትሉ የሲዳማ ክልል መስረታችሁ ይርጋለምን ወይም አለታ ወንዶን ዋና ከተማችሁ ማድረግ ትችላላችሁ የሚለው አማራጭ ደግሞ የሲዳማ ልሂቃን ሊሰሙት የማይፈልጉት ነገር ነው፡፡

የሲዳማ ልሂቃን እንደሚፈልጉት የሲዳማን ክልል መፍቀዱ ብዙ ነገሮችን የሚነካካ ነው፡፡ አንደኛው በሃገሪቱ ዘጠኝ ክልሎች እንዳሉ የሚደነግገው የሃገሪቱ የህገመንግስት እንዲሻሻል መጠየቁ ነው፡፡ሁለተኛው ከፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ መጠን የሚያሳድግ ነው፡፡የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችን ጥምረት የሚያናጋ ነው፡፡ በደኢህዴን ተወክሎ ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው ሲዳማ ህዝብ የራሱ ክልል ሲኖረው ክሉን የሚመራ የራሱ መሪ ፓርቲ ይፈልጋል፡፡ይህ አዲስ የሲዳማ ፓርቲ ደግሞ የአውራው ፓርቲ ኢህአዴግ አባልን ነው አጋር ነው ተቃዋሚ የሚለው ትልቅ ፖለቲካዊ ጥያቄ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ኢህአዴግ በተወካዮች ምክርቤት፣በማዕከላዊ ኮሚቴ ፣በስራ አስፈፃሚ አባላቶቹ ላይ ያለውን መስተጋብር የሚቀይር ነው፡፡ይህ ሁሉ ታልፎ የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ቢሰምር እንኳን አርአያነቱ ለሌሎች የክልሉ ዞኖችም ተመሰሳይ የክልል እንሁን ጥያቄ በር የሚከፍት ስለሚሆን ለፌደራል መንግስቱ ከባድ ራስምታት መሆኑ አይቀርም፡፡

እንዲህ እልባት የራቀው የሲዳማ የክልል ጥያቄ ሲዳማ ላልሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ስጋትን እያጫረ ቀጥሏል፡፡ፈልገዋት የሚሄዱባት የፍቅር ከተማ ትባል የነበረችው አዋሳ ዛሬ ጥለዋት ለመሄድ የሚያመነቱባት፣ቱሪስት ቢውልም የማያድርባት የስጋት ቀጠና ሆናለች፡፡በዚሁ ውጥረት ሳቢያ የከተማዋ ኢኮኖሚ፣የመሬት ግብይት ዋጋዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳሽቆለቆለ ነው የሚነገረው፡፡እንዲህም ሆና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የወታደር ጥበቃ የኢህአዴግን 11ኛ ጉባኤ ጉባኤ ለማስተናገድ ሽር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡

እንዲህ ወታደር ከትሞባትም ሲዳማ ባልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት የግቢ በሮች እና ግንብ አጥሮች ላይ ሰማያዊ ቀለም ያለው ምልክት መደረጉ የህዝቡን ስጋት አንሮታል፡፡ይህን ተከትሎ ጉዳን አስመልክት የከተማው ከንቲባ ፅህፈት ቤት የሚሰጠው ቃለ ምልልስም ሆነ መግለጫ ስለቀለም ቅቡ አላማም፣ የቀቢዎች ማንነትም ሆነ ስጋቱንለማርገብ ስለተወሰደው እርምጃ ይህ ነው የሚባል ማረጋጊ ነገር ያለው አይደለም፡፡ ይልቅስ የሲዳማ ብሄር ስም በክፉ እንዳይነሳ ማድበስበስ የበዛበት አደናጋሪ እና የተውሸለሸለ ነው፡፡

የሲዳማ ልሂቃን ክልል የመሆን መብታችንን ተነፈግን ብለው በፌደራል መንግስቱ ላይ የሚያጉረመርሙትን ያህል በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ብሄረሰቦች ደግሞ የደቡብ ክልል ሁለመና ለሲዳማ ያደላ ነው ሲሉ በክልላችን ባይትዋር ተደረግን የሚል ሰፊ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ክልል ከተመሰረተ አንስቶ አንዴ ብቻ ወላይታው አቶ ኃ/ደሳለኝ ክልሉን ከመምራታቸው በቀር ሃያሰባት አመት ሙሉ ክልሉን የሚመሩ ርዕሰ ማስተዳድሮች ሁሉ የሲዳማ ተወላጆች መሆናቸው ክልሉ በከፍተኛ የሲዳማ ልሂቃን ተፅኖ ስር ለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር መዋቅር መሰላሎች ሹመት ላይ ከከንቲባ ጨምሮ ግልፅ የሆነ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሲዳማ ልሂቃን ህልውና ይስተዋላል፡፡በዚህ ምክንያት ሌሎች የክልሉ ብሄረሰብ ልሂቃን ከፍተኛ ቅሬታ አለባቸው፡፡ በሃዋሳ ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬትን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለሲዳማ ተወላጆች የሚሰጡ መሆናቸው”ክልሉ የሲዳማ ነው የደቡብ ህዝቦች?” የሚል ጥያቄ ሲያስነሳ የኖረ ነው፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here