
ቦርከና
ጥቅምት 7 ፤ 2011
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲሱን ካቢኔያቸውን ትላንት በተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አጸድቀዋል። የፖርቲው ሴት ፖለቲከኞች በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ እኩሌታውን የስልጣን ቦታ እንደያዙም ታውቋል። “የጾታ እኩልነት የተረጋገጠበት ካቢኔ” ነው በሚል ዜናው የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
ከቁጥር በተጨማሪም የኢህአዴግ ሴት ፖለቲካኖች ቁልፍ የሆኑ የካቢኔ ስልጣን ይዘዋል። አዲስ የሚዋቀረው የሰላም ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ ቁልፍ የስልጣን ቦታ እንደሆነ ተንታኞች እየተናገሩ ሲሆን ቀደም ሲል በተወካዮች ምክር ቤት በአፈጉባኤነት ሲያገለግሉ የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከማል በሚኒስትርነት እንዲመሩት ተሾመዋል። በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ሰላምን ማስፈን ተልዕኮ የተሰጠው አዲሱ የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ፤የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ፤ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲን ፤ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን ፤የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን እና የሰራተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲን በበላይነት እንደሚመራ ወይንም የእነዚህ መስሪያቤቶች ተጠሪነት ለሰላም ሚኒስቴር እንደሆነ ታውቋል። በተጨማሪም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሃይማኖት ተቋማት ጋርም እንደሚሰራ ታውቋል።
ሌላ ለኢህአዴግ ሴት ፖለቲከኞች የተሰጠ ቁልፍ ቦታ የመከላከያ ሚኒስቴር ነው። ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የሚኒቴር መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ተሾመዋል።
አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ የጎሳ እና የጾታ ስብጥሩ ላይ ጥያቄ ባያስነሳም ብቃትን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም የሚል ትችት ተሰንዝሮበታል፤ በፖለቲካ ተንታኞች።
የካቢኔው ሙሉ ዝርዝር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባዘጋጀው የኢንፎግራፊክ ላይ እንደሚከተለው ቀርቧል