ቦርከና
ጥቅምት 7 ፤ 2011 ዓ.ም
ጣና ሐይቅ እንቦጭን ጨምሮ የተጋረጡበትን አደጋዎች በዘላቂነት መከላከል እንዲቻል በአማራ ክልል ምክር ቤት ዉሳኔ መሰረት በመጋቢት 2010 ዓ.ም በተቋቋመዉ የጣና ትረስት ፈንድ በኩል 32 ሚሊዩን ብር መሰብሰቡን የአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባዉ ከሆነ ማንኛውም ለጣና ያገባኛል የሚል አካል የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ በፈቀዳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ወጋገን እና ዳሸን ባንኮች በተከፈቱ የጣና ትረስት ፈንድ አካውንቶች ብር ገቢ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡
ዶር. በላይነህ አየለ የአማራ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር እንዳስታወቁት ከሆነ እስካሁን በሁሉም ባንኮች 32 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል::ገቢው በዓመቱ ከተያዘው እቅድ በእጅጉ ልቆ መገኘቱንም ነው የተናገሩት::
የጣና ትረስት ፈንድ በቦርድ እየተመራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመረጧቸው አካላት ቁጥጥር የሚደረግበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ገንዘቡ የእንቦጭን ወረራ ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ፈሰስ ይደረጋል ማለታቸዉን ዘገባዉ አካቷል፡፡
ጀልባዎችን እና ሌሎች ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በመግዛትም እንቦጭ በብዛት ባጠቃጨው ጣና ጭርቆስን ለመሰሉ ገዳማት እንዲሁም ወረዳዎች እንደሚሰራጩም አስታውቀዋል፡፡
በጣና ሃይቅ የተከሰተውን እንቦጭ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም የአረሙ ስርጭት እንዳይጨምር ለማስቻል በማሽን ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የስነ ህይወታዊ መከላከያ ዘዴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል::
የሀይቁን ህልውና ለማስጠበቅ ዜጎች እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ የያገባኛል ርብርብ ያደነቁት ዳይሬክተሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስቀዋል፡፡
እስካሁን የተሰበሰበው 32 ሚሊየዮን ብር ከሃገር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ፣ድርጅቶችና መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ በጎ ፈቃደኛ ተቋማት ብቻ የተገኘ መሆኑን የገለፁት ዶር. በላይነህ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለጣና ትረስት ፈንድ ተብለው በተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች በተጠቀሱ ባንኮች ገቢ ማድረግ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጣናን ለመታደግ በሚል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ተግባራትን እንደፈፀሙ ቢታወቅም እስካሁን ግን የክልሉ መንግስት በከፈታቸው የሂሳብ ቁጥሮች ገቢ የተደረገ ገንዘብ አለመኖሩንን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
በሰለሞን ይመር