ቦርከና
ጥቅምት 7 ፤ 2011 ዓ.ም
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወታደራዊ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር በማስረከብ የብሄራዊ ኢንዱሰትሪያል ምህንድስና ኮርፖሬሽን በሚል አዲስ ስያሜ ሊደራጅ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል፡፡
ከተቋቋመ ጀምሮ በጥቂት ጊዜ በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶችን እንዲይዝ ተደርጎ የነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከብቃት እጦትና ከብክነት ጋር ተያያዘ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል።
እጁ ላይ የነበሩ በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ አቅቶት ፕሮጀክቶቹን ሲቀማ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን ወስዶ መስራት ባለመቻሉም ቢሊየን ብሮች እንደባከነ መሰማቱን ዘገባዉ አስጣታዉሷል።
አሁን በመንግስት በተወሰደው እርምጃ መሰረት በሜቴክ ስር ወታደራዊ ምርቶችን ሲያመርቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር በመስጠት ቀሪዎችን በስሩ የሚያስቀጥል መሆኑንም አቶ አብዱልዓዚዝ መሀመድ የኮርፖሬሽኑ የኮመርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለፋና ተናግረዋል።
ለዚህ አዲስ አደረጃጀት ረቂቅ ደንብ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸቀደ በኋላ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ሜቴክ እስካሁን 14 ኢንዱስትሪዎችን ሲያስተዳድር የቆየ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወታደራዊ ምርቶችን የሚያመርቱ አራት ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር እንዲያስረክብ በመንግስት ተወስኗል።
ሜቴክ ለመከላከያ ሚኒስቴር እንዲያስረክብ የተወሰኑት ተቋማት መካከል ሆሚቾ ኢንዱስትሪ፣ ደጀን አቪየሽን፣ ጋፋት አርማመንት እና ልዩ ትጥቆች አምራች ኢንዱስትሪ የተባሉትን ይገኙበታል።
አዲሱ ኮርፖሬሽንም ሀገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ የሚያንደረድሩ ምርቶች ላይ የሚሰማራ ይሆናል ብለውናል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።
አዲሱ ኮርፖሬሽን ከብቃት ማነስና ከብክነት ጸድቶ ለመሄድም እንደበፊቱ ኮርፖሬሽኑ አቅም ሳይኖር ብዙ ስራን ከመውሰድ ይልቅ፥ የተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የሰው ሀይሉን በአግባቡ ለመጠቀም ታስቧል ብለዋል።