ቦርከና
ጥቅምት 8 ፤ 2011
በቅርቡ የደመወዝ ጭማሬ ለመጠየቅ ወደ ቤተ መንግስት ያመሩት ወታደሮች አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ያለሙ አካትን ተልዕኮ አንግበው እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
በ2011 የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መከፍቻ ላይ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር ላይ ለፓርላማ አባላት መልሽ ለመስጠት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የታጠቀ ወታደር ወደ ቤተ መንግስት የመጣው አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሁሉም የመጡት ወታደሮች ይህን እሳቤ ይዘው ነው የመጡት ለማለት እንደሚያስቸግርና በአንዳንድ ተንኮለኞች ሴራ ተጠንስሶ የተፈፀመ ድርጊት ነው እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ የተወሰደው እርምጃ በጥንቃቄ ባይሆን ኖሮ አገርን ወደቀውስ የሚከት ክስተት እንደነበርም ነው ያብራሩት፡፡አሁን ላይ ራሱ ወታደሩ በሴራው ውስጥ የነበሩትን የድርጊቱን መሪዎች እየለየ አሳልፎ እየሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ የወታደሮቹን አመጣጥ ወታደራዊ ጥበብ በሚጠይቀው መልኩ አረጋግቶ መመለስ መቻሉ አገርን የማትረፍ ወሳኝ እርምጃ አድርጌ ነው የምወስደውም ብለዋል፡፡ “እየተዝናነሁ፣ እየሳቅኩ ቃለ መጠይቅ የሰጠሁት መንግስታችን ተነካ ብለው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ህዝቡ ለመዋጋት እየመጣ ስለነበረ እነሱን ለማረጋጋት ነበርም” ብለዋል፡፡
ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ባለፈው ቅዳሜ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «ግለሰቦች የገፋፉት እና ያርገበገቡት ነው። እነዚህን ግለሰቦች ማን ነው የገፋቸው? የሚለውን አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን።» ብለው ነበር።
ወታደሮቹ ወደ ቤተ-መንግሥት ለመሄድ የወሰኑት «በተበተነ አኳኋን» እንደሆነ የገለጹት ጄኔራል ሰዓረ የተፈጸመው ጥፋት ተራ የዲሲፕሊን ግድፈት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
በሰለሞን ይመር