ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.
በይዘቱ መርዘኛ የሆነውን ፈሳሽ “ጠበል” ወይም “የወይን ጭማቂ” ቢሉት፣መርዝነቱን አይለቅም። ኮሶን በወርቅ ዋንጫ ውስጥ አሳምረው ቢያቀርቡትና ማር ነው ቢሉት ኮሶነቱን አይለውጥም፣ ያው ኮሶ ነው።በተመሳሳይም በማንኛውም አካል የሚደረግ ውጫዊ አቀራረብና ስያሜ ውስጣዊ ይዘትና ጸባዩን ወይም ማንተቱን አይቀይረውም።ፉንጊትን ቆንጂት ቢሏት፤ ያው ፉንጊት ነች።ስሟ ስለተለወጠ ቆንጆ አትሆንም።
በዚህ እርእስ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የገፋፋኝ በአገራችን በኢትዮጵያ ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት የሰፈነው የፖለቲካ ስርዓትና አንቀሳቃሾች በዬጊዜው ስልጣን ላይ ሲወጡ ወይም ስልጣን ከያዙ በዃላ ስም እየቀያየሩ፣ ሳይለወጡ ስማቸውን እዬለወጡ ሕዝብን ማምታታታቸው የተለመደ ባህል እዬሆነ መምጣቱን በማዬቴ ነው።
በ1966 የተቀሰቀሰውን የለውጥ ማዕበል ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ተገን አድርጎ በሰኔ 1 ቀን 1966 ዓም ከሥልጣን መንበር ላይ የተፈናጠጠው የወታደር መንጋ ፣በመጀመሪያ የሕዝቡን ቀልብ በሚስብ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል መፈክር መሿለኪያ ተብሎ ይጠራ በነበረው አካባቢ በአራተኛ ክፍለጦር ካምፕ ውስጥ ለሁለት ወራት አስተባባሪ ኮሚቴ በሚል መጠሪያ ከቆዬ በዃላ በሦስተኛው ወር ላይ ደርግ የሚል መጠሪያ አንግቦ እስከ መስከረም ሁለት ቀን 1967ዓም ድረስ አዘገመ።በመስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓም ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ነኝ ብሎ አወጀና በአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ዙፋን ላይ ወጣ።
ገና ከውጥኑ ጀምሮ በወታደሩ ክፍልና በሕዝቡ ተቃውሞ ሲነሳበት በጉልበት እዬደፈጠጠ ስልጣኑን በሽብር እርምጃ አጠናከረ።የሕዝቡ አለመደራጀትና የፖለቲካ ንቃት ማነስ ብሎም ነቅተናል የሚሉት ምሁራኖች በከፈቱት የእርስ በርስ ቅራኔና ግጭት ደርግ ካለምንም ችግር በስልጣኑ ላይ ለአስር ዓመት በወታደር መንግሥትነት ቆዬ። የወታደር መንግሥትነት አላዋጣው ሲል ወታደራዊ ልብሱንና መለዮውን አውልቆ ጥሎ ቱታ በመልበስ የሰራተኛው መደብ ተወካይ ነኝ በማለት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ ኢሰፓ ሆኛለሁ ብሎ አወጀ።በነዚህ የተለያዩ ስያሜዎችና የሥልጣን እርከኖች ግን የወታደሮቹን ማንነት፣አምባ ገነንነት፣ገዳይነትና አረመኔነት ከስልጣን ተወግደው እስከተበታተኑበት እለት ድረስ ሊለውጠው አልቻለም።ባደረጉት አራት የስም ለውጥ ሳይለወጡ ያው የመጀመሪያዎቹ ለስልጣን ያበዱ እብዶች እንደሆኑ ታሪካቸው ተደመደመ።የሁሉም ነገር መጀመሪያ እንዳለው ሁሉ መጨረሻም አለውና ፣የደርግም ዕድሜ መጨረሻ ሆነ፤አገሪቱም ለሌላ አምባገነን የጎሳ ስብስብ ተጋለጠች።
አሁን ላለፉት 28 ዓመታት በስልጣን ላይ ተቀምጦ አገራችንን የሚያምሰው የወያኔ መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥትንም ታሪክ ብናይ ከዚሁ የተለዬ አይደለም።ላለፉት 27 ዓመታት በውስጡ ባጠራቀማቸው የጎሳ ድርጅት ድምር ውጤት የሆነው ኢሕአዴግ የትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር፣ብሔረ አማራ ፣የኦሮሞ ሕዝብ፣የደቡብ ሕዝቦች በማለት በክልል ከፋፍሎ፣እየገደለ፣እያሰረ፣እያኮላሸ፣እያፈናቀለ፣እዬዘረፈ ሲገዛ ከቆዬ በዃላ የሕዝቡ የማያቋርጥ ትግል ወጥሮ ሲይዘው ከአምስት ወራት ወዲህ ተፈጥሮውን ሳይሆን ብልሃቱንና ስልቱን በመቀየር ብቅ አለ።የፈረደበት ሕዝብ በሚሰማው ዲስኩርና አንዳንድ የጥገና ለውጥ በደስታ ተስፋ አድርጎ አጨበጨበ።በተግባር ግን አሁንም በየቦታው መፈናቀሉና ግድያው እንደቀጠለ ነው።
አሁን ሰሞኑን ደግሞ እያንዳንዳቸው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የየበኩላቸውን ስብሰባ/ጉባኤ በማካሄድ ከስማቸው ውስጥ ሕዝብና ድርጅት የሚሉትን ሁለት ቃላት አንስተው የዴሞክራሲ ፓርቲዎች ሆነናል ብለው ብቅ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገልና የህይወት መስዋእት ሲከፍል የኖረው ሁለቱን ቃላት ለውጣችሁ በስልጣኑ ላይ ቆዩ ብሎ ሳይሆን ወግዱልኝ ብሎ ነው።የስርዓት ለውጥ እፈልጋለሁ፣እናንተ በቃችሁኝ፤እንደኮሶ መረራችሁኝ ብሎ ነው።የአገሬን አንድነት የሚያፈርስ ሕገመንግሥታችሁን አልፈልግም፣በቋንቋ ተዋረድ ያቆማችሁት የክልል ግምብ ይፍረስ ብሎ ነው። እነሱ ግን አይናቸውን በጨው አጥበው በአዋሳ ከተማ ባካሄዱት የ11ኛው ጉባኤያቸው ላይ ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ይዘን፣ እኛም ተለውጠን መጥተናል፤በስልጣኑም ላይ ለመቆዬት የሚረዳ ብቃት ያለው ተቋምና አመራር መስርተናል፤ በማለት የጉባኤ መደምደሚያ መግለጫ አውጥተዋል።ለቀጣይ የኢሕአዴግ ስርዓት በውስጣቸው ያለውን ልዩነት አሶግደው በአንድነት መነሳታቸውን በዚሁ የ11ኛው ጉባኤ ማጠቃለያ ባወጡት መግለጫቸው አስረግጠዋል።በዚሁ መግለጫ ሕገመንግሥቱና የዘረጉት ጎሰኛ የክልል አስተዳደር እንደሚቀጥል ይፋ አድርገዋል።ይህች ነች ጨዋታ! እውነትም መለወጥ!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ስርዓት ይስፈን ብሎ ታገለ እንጂ እነሱ የዴሞክራሲ ታርጋ ለጥፈው በቀጣይነት ጸረ ዴሞክራሲና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን መመሪያ ሕገ-መንግሥት ተብዬ ተሸክመው በስልጣን ላይ እንዲቆዩ አልጠዬቀም።ዴሞክራሲ የምትለዋን ሁለገብ ቃል ቀርቶ መለኮታዊ ስያሜ ቢይዙ ሕዝቡ አይቀበላቸውም።ኢሕአዴግና ሕዝቡ ሆድና ጀርባ ከሆኑ ቆይቷል።ሕዝቡ የሚፈልገው የስም ለውጥ ሳይሆን የመሪዎች ስነምግባርና የስርዓት ለውጥ ነው።የአንድን አገር ሕዝብ “ሕዝቦች” ፣ለመገንጠል እንዲረዳም ነገድ ወይም ጎሳን “ብሔርና ብሔረሰብ ” እያለ የሚለያይን አጠራር የሚጠቀም ስርዓት ይለወጥ፤ ፖለቲካው በጎሳ ማንነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ማንነት መርሆ ላይ ይነደፍ! ብሎ ነው የሚታገለው።ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ተቀብሎ አግባብ ያለው መልስ ካልሰጠ ኢሕአዴግ ምንም ጊዜ ቢሆን፣የትኛውንም መጠሪያ ሰሌዳ ቢያነግብ ከሕዝቡ ጋር ሊታረቅ አይችልም።
ምናልባት ኢሕአዴግ ከሕዝቡ ጋር ለመቀራረብ የሚችልበትና ለይቅርታ የሚበቃበት መንገድ ቢኖር፣
1 አሁን ያለው ሕገመንግሥት ተሰርዞ ሕዝብ የተካፈለበትና የኢትዮጵያን አንድነትና የሕዝቡን ሙሉ መብት የሚያረጋግጥ፣የክልልን ግምብ የሚያፈራርስ፣በጎሳና በእምነት ዙሪያ የፖለቲካ ድርጅትንና እንቅስቃሴን የሚከለክል ሕግ ለማውጣት ፈቃደኛ ሲሆንና ሲተባበር፣የሚዲያው ዘርፍ ነጻና ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅት እኩል ድርሻ ሲኖረው
2 ላለፉት 27 ዓመታት፣አሁንም በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ የሽብር ተግባር ላይ የዋሉትን ጨምሮ፣ በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ ወንጀል የፈጸሙትን፣የገደሉ፣ያስገደሉ፣ያሰቃዩ፣ያፈናቀሉና የመዘበሩ ሁሉ ለፍርድ ሲያቀርብና የሕግ የበላይነት በተግባር እንዲረጋገጥ ሲያደርግ።ለወደፊቱም የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮና ደህንነት ለማስጠበቅ በተግባር ላይ ሲንቀሳቀስ
3 ለመሚጣው ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሱንም ኢሕአዴግን ጨምሮ የሚዘጋጁበት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ፈቃደኛ ሲሆንና ሥልጣኑን ለዚያ ሁሉንም ላካተተ አካል ለሚመርጠው ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን በተግባር ሲገልጽ።እራሱ ኢሕአዴግ የችግሩ ምንጭ መሆኑ እዬታወቀ የሽግግር መንግሥት ሊሆን አይችልም። በስልጣን ላይ ተቀምጦ የሚካሄድም ምርጫ ታማኝነት የለውም፤በዓለም ከሚካሄዱትም ምርጫዎች የተለዬ ያደርገዋል።
4 በከባቢና በክልል ደረጃ በተደጋጋሚ የታዬውን የፖሊስን ወገንተኛ አሰራር ለመከላከል የክልል ፖሊስ በመባል የተቋቋመውን ጎሳ ተኮር ተቋም አፍርሶ በፌዴራሉ የፖሊስ ተቋም ስር እንዲጠቃለል ማድረግ ለሰላምና ለለውጥ ለመነሳቱ አንዱ ምልክት ይሆናል።
እነዚህን ማሟላት ለተደቀነው አገር አቀፍና መጠነ ብዙ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የሚረዳ ቁልፍ ወይም መንደርደሪያ ይሆናል።አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን እነዚህን ለማሟላት ፈቃደኛ የማይሆን ከሆነ ለለውጥ ሳይሆን ለነውጥ የተዘጋጀ መሆኑን ያረጋግጣል። ስለሆነም የስም መቀያዬሩ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንደሚባለው ይሆንና ደርግን በተለያዬ ስሞች መጠራቱ ከገዳይነቱ እንዳልቀዬረው ሁሉ ኢሕአዴግንም አሁን በሚለጥፈው የተለያዬ መጠሪያ ከወንጀሉና ከተመሰረተበት የጎሰኝነት ዓላማው አያላቅቀውም።አሁንም በኢሕአዴግነቱ የነደፈውን ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ተሸክሞ የሚሄድ ከሆነ ዴሞክራቲክ ሆኛለሁ ብሎ ቢጮህ የሚሰማው አይኖርም።ቢኖርም እያደር ሲገለጥለት አይንህን ላፈር ይለዋል።ጉድና ጅራት ከበስተዃላ ነው!
የጉባኤው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው ኢሕአዴግ በውስጡ ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር አንድነቱን እንዳጠናከረ ገልጿል።ያም ማለት የዓላማ ልዩነት የለም ማለት ነው።ወያኔና ሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሚመሩበትንና የተመሰረቱበትን ዓላማና ሕገ መንግስት ይዘው ይቀጥሉበታል ማለት ነው።እንዲያ ከሆነ ደግሞ ኢሕአዴግ በሌላ ሕዝባዊ ሃይል መለወጥ የሚገባው እንጂ እራሱን ለውጦ ኢትዮጵያን ሊለውጥ የማይችል ጸረ ለውጥ ቡድንነቱን ያረጋግጣል። እያንዳንዱ የኢሕአዴግ አባል” ዴሞክራቲክ ፓርቲ” የምትለዋን ቃል ለጥፎ ቢመጣና በጥምርም” የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ” ሆኖ ቢቀርብ ኢሕአዴግ ዴሞክራት ሆነ ማለት አይደለም፤ደርግን የሰራተኛው ፓርቲ ብሎ መምጣቱ የሰራተኛው ፓርቲ እንዳላደረገው ሁሉ።ግለሰቦችን ከኢሕአዴግ የጎሳ ሳጥን ውስጥ እያወጣ ባለሥልጣን ቢያደርጉ ባረፈ ጉልበት የሚተካኩበት ሂደት እንጂ ስርዓቱ ተለወጠ ማለት አይደለም።ሴቶችን በሥልጣን ላይ ማምጣት የሴቶችን እኩልነት እንደሚያከብር ለማሳዬት ከመሆኑ ባሻገርና ተገቢነቱ ቢታመንበትም ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ የሚከተሉት መመሪያና አቋም የኢሕአዴግ ፍልስፍናና የጎሳ ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ ያው በገሌ ነው።የፖለቲካን እምነት ጎሳና ጾታ አይለውጠውም።
የአንድነት ሃይል ወይም ሕብረ-ብሔራዊ የሚባሉትን በጎሳ ስም ያልተደራጁትን የፖለቲካ ድርጅቶች በሚመለከት
እነዚህም ቢሆኑ የሚጠሩበትን ስም በተግባር የሚተገብሩ አልሆኑም ።ከአንድነትና ጠንክረው ግዙፍ ሃይልና አማራጭ ከመሆን ይልቅ በሆነ ባልሆነው ጥቃቅን ልዩነት ወይም በግል የስልጣን ሽኩቻና አባዜ ተለያይተው ስማቸውን ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውን ለማወቅ አዳጋች ሆነዋል።አንዳንዶቹም ከጎሳ ድርጅቶች ጋር ተጣብቀው ውዥንብር ውስጥ ገብተዋል።መቼም ቢሆን መቼም በዘመናችን ግፋ ቢል ከአራት የበለጠ የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም መስመር የለም።በእኛ አገር ውስጥ ግን ከ80 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ አሁን እንኳን ሰሞኑን በኢሕአዴግ 11ኛ ጉባኤ ላይ ድጋፋቸውን የሰጡት 18 ሕብረ-ብሔራዊ ነን ባዮች ድርጅቶች ናቸው።ታዲያ ኢሕአዴግ አራት ሆኖ እንደ አንድ ቆሞ አገር በሚያምስበት ወቅት 80 ወይም 18 የተለያዬ ስምና ዓላማ ያለው ድርጅት ሆኖ ምን አይነት ተቃውሞና አገራዊ ፖለቲካ ማራመድ ይቻላል? መልሱን ለነሱው እተወዋለሁ።እስከ አሁን ድረስ ባደረጉት መዝረክረክና ቡድናዊ ፍላጎት የተነሳ ሕዝቡ ተስፋ እንዲቆርጥና ለአሕአዴግ የተመቼ ያደረጉት መሆናቸውን ተቀብለው ከጥፋታቸው ተምረውና ታርመው ለእውነተኛ ለውጥና ለአንድነት የተነሱ አማራጭ መሆናቸውን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል።አንድነትን በተግባር ያላሳዬ ስለአንድነት ሊቆምና ሊያወራ አይችልም።መጀመሪያ በውስጣቸው ያለውን ጥቃቅን ልዩነት አሶግደው በአንድ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት የሚጠራ ድርጅት ሊፈጥሩ ይገባል።በስመ አንድነት ሃይል የጎሳ ድርጅቶችን ተሸክሞ መሄድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።ያሉት የጎሳ ድርጅቶች በሙሉ የኢሕአዴግን ሕገመንግሥት የሚቀበሉ ናቸው።ቅድሚያ ለጎሳቸው እንጂ ለኢትዮጵያ አንድነት አይደለም።
አንድ ድርጅት መፍጠር ካልተቻለና የመስመር ልዩነትም ሊኖር ስለሚችል ግፋ ቢል ወደ ሶስት ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ሊጠጋጉ ይገባቸዋል።ከዚያ በላይ ሕዝቡን ከማደናገር ያለፈ ጥቅም የለውም።”ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል” እንደሚባለው ሕዝብ ጠብቆ ጠብቆ ለውጥ ካላዬ እንኳንስ ሊመርጣቸውና ሊከተላቸው ቀርቶ መኖራቸውንም ይረሳል።ተባብረው አንድ ከሆኑ ግን ከነሱ ጎን ይሰለፋል፤የፈለጉትን ያደርጋል።መርተውም ለድል ያበቁታል።ለዚያም የመጀመሪያው እርምጃ መሆን የሚገባው፣-
ኢሕአዴግ የራሱን መንገድ ቀይሷል፤ያልቀየሰው አማራጭ ነኝ የሚለው ሕብረ-ብሔራዊው ጎራ ነው።የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ የሚመልስና የአገሪቱን አንድነትና ነጻነት የሚያረጋግጥ ራዕይ ያለው መርሃ ግብር ነድፎ የመታገልና የማታገሉ ሥራ ገና አልተነካም።ከፊቱ ተደቅኖ ይጠብቀዋል።
በኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ እዬተገኙ አድማቂ ከመሆን በተረፈ የራሳችሁን ስብሰባ /ጉባኤ ለማካሄድ ተዘጋጁ።ኢሕአዴግ በየቦታው ለሚያካሂደው ስብሰባ ከአገር ካዝና በመጠቀም ከሆነ፣ እናንተም ለመጠቀም መብታችሁ መሆኑን አትዘንጉት። ያም ባይሳካ በገንዘብ ምክንያት ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ መጓተት የለበትም።ለስብሰባ የግዴታ ትልቅና ያማረ ውድ አዳራሽ መያዝም አያስፈልግም።ወሳኙ የቦታ መስፋትና ማማር ሳይሆን የአስተሳሰብ መስፋት ነው።የየድርጅቱ ተወካዮች ጠቅላላ ቁጥር ግፋ ቢል ከመቶ አይበልጡም፤ ከታዛቢ እንግዶች ጋር 150 ቢሆኑ ነው።በዚህ ቅጥ አምባሩ በጠፋበትና አማራጭ አልባ በሆነበት ወቅት ጊዜ ሳትፈጁ የራሳችሁን ጉባኤ አካሂዳችሁ ዓላማ ነድፋችሁ ለሕዝቡ አማራጭ ሆናችሁ ቅረቡለት።አለበለዚያ ያው እንደ መግቢያው ትንታኔ ስም ብቻ ተሸክማችሁ፣ያልሆናችሁትን ሆናችሁ ትቀራላችሁ። ከጥቅማችሁ ጉዳታችሁ ያመዝናል።አማራጭ ሳትሆኑ ሕዝብ ለጠላው ስርዓት አጫፋሪና የባዶ ዴሞክራሲ ጭንብል /ተምሳሌት/ ሆናችሁ ትኖራላችሁ።
አሁን ያላችሁበትንም ሁኔታ ማጤንና ማሰላሰል ተገቢ ነው።ያላችሁት በቁም እስረኛነት ነው።በሆነ ባልሆነው ሰበብ ወይም ተራ በተራ በሚስጢር ልትጠፉ እንደምትችሉ ወይም በውስጣችሁ ለጥቅም ያደሩ ሰላዮችን በማሰማራት ልትዳከሙ እንደምትችሉ አስቡት።ለደህንነታችሁ ዋስትና የሚሆን ጠንካራ የኢንተሊጀንሲ /መረጃ ተቋም ሊኖራችሁ ይገባል።ከሁሉም በላይ ዋስትናችሁ ሕዝቡ ነውና ከሕዝቡ ጋር አንድ የሚያደርጋችሁን ዓላማ ይዛችሁ ሥራ ለመሥራት በአንድነት ቁሙ።
አገሬ አዲስ
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን ።