ቦርከና
ጥቅምት 9 ፤ 2011
የላሊበላ ቅርስ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ እና ታሪካዊ ይዘቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ትውልዱ በሃላፊነት እንዲረባረብ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ ማቅረባቸዉን ፋና ብሮድካስቲንግ በድህረ ገፁ አስነብቧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በዚህ ዘመን የላሊበላ ቅርስ ኪነ-ህንፃዊ ጥበብ ዳግም ለመገንባት የማይታሰብ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ቢያንስ የቅርሱን ደህንነት አስጠብቆ ማስቀጠል ካልተቻለ ለዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኪሳራ መሆኑን የላሊበላ ቅርስ የተጋረጠበት አደጋ በተመለከተ ከላሊበላ አከባቢ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ዉይይት ወቅት ተናግረዋል ።
ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዉ ላሊበላን ሰርቶ ያስረከበን ትውልድ አካል እስከሆንን ድረስ በአሁን ጊዜ ቅርሱ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግና ታሪካዊ ይዘቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ትውልዱ በሃላፊነት መረባረብ እንደሚጠበቅበት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የሰፊውን ማህበረሰብና የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያግዙ ብሄራዊ መድረኮች በአጭር ጊዜ እንደሚመቻቹ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል።
የላሊበላ ቅርስ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ መላው የሃገሪቱ ህዝብና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ ምላሹን በተግባር እንዲያሳይ ተዎካዮቹ ጥሪ ማቅረባቸዉን ዘገባዉ አካቷል።
ከሳምንት በፊት የላሊበላና አካባቢዉ ነዋሪወች በቅርሱ ላይ የተጋረጠዉ አደጋ በፌደራሉና ክልሉ መንግስታት ተገቢን ትኩረት አላገኘም በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸዉ ይታወሳል፡፡
በሰለሞን ይመር