ቦርከና
ጥቅምት 9 ፤ 2011
“የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት መስኮት ሰብረው ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል” ሲል ፖሊስን ጠቅሶ የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት ዛሬ ዘግቧል።
አቶ አብዲ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው አቶ አብዲ መሐመድ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ሲባል የፖሊስ ቢሮ ውስጥ ታስረው የነበረ ሲሆን የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ብሏል ዘገባዉ።
ይሁን አንጅ አቶ አብዲ መሐመድ ድርጊቱ ሆን ብሎ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት የተደረገ ሴራ በማለት ድርጊቱን ፈጽመዋል መባሉ ውሸት መሆኑንና በእርሳቸው ላይም ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ መናገራቸዉን የኢዜዓ ዘገባ ያመለክታል።
ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታሳሪ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም በደህንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
የታሰሩበት እስር ቤት የማይመችና በጤናቸው ላይም እክል እንደፈጠረባቸውም የተናገሩት አቶ አብዲ በአንድ አጋጣሚም አንድ አስረኛ የሽንት ቤት በር ገንጥሎ እሳቸው ላይ በመጣል ጉዳት ሊያደርስ መሞከሩንም ተናግረዋል።
እንደ ኢዚዓ ዘገባ ከሆነ ፖሊስ ከእርሳቸው ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ መሆናቸውንና በዚህም ተጸጽተው ይቅርታ መጠያቃቸውን ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ አብዲ መሐመድ ከሐምሌ 26-30 ቀን 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።
በሰለሞን ይመር